Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ይህስ፣ የፍትሃዊነት ማሣያ

0 295

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ይህስ፣ የፍትሃዊነት ማሣያ

አይደለምን?

ወንድይራድ ኃብተየስ

ለውጡ እጅግ ፈጣን ሆኗል። በአገራችን የከፍተኛ ትምህርት  ተቋማት ቁጥር አሁን ላይ ወደ 47 ከፍ ብሏል።  በዕትዕ ሁለት ማብቂያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥር ሃምሳ ይደርሳል።  ቀድሞ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  ያልነበራቸው  አካባቢዎች  ዛሬ ላይ  ዩኒቨርሲቲዎች ተገንብቶላቸዋል። በዕትዕ ሁለት ለመገንባት ከታቀዱ  ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በርካቶቹ  ሰሞኑን በመመረቅ  ላይ ናቸው። ለአብነት ሰሞኑን በቴሌቭዥን ጥሪ ሲያስተላልፉ  ከሰማኋቸው  ዩኒቨርሲቲዎች መካከል  ደንቢ ዶሎ፣ ሰላሌ፣ እንጂባራ፣ መቅደላ አምባ፣ ደባርቅ፣ ራያ፣ ወራቤ ሲሆኑ ትላንት ደግሞ  በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የቀብሪዳሃር  ዩኒቨርሲቲ  መመረቁን  ሰማሁ።

የቀብሪ ደሃርን  ዩኒቨርሲቲ  የምርቃት ዜና ሳደምጥ ውስጤን  እንግዳ  ነገረ ፈጠረብኝ።  ምክንያቱም ቀብሪዳሃርንና አካባቢውን ጠንቅቄ አውቀው ስለነበር ያቺ ከአስር ዓመት በፊት አውቃት የነበረች  ከተማ  ዛሬ  ለአቅመ ዩኒቨርሲቲ  መድረሷን  ስሰማ  ለእኔ  እጅግ ትልቅ ነገር ነው።  አዎ ያ አካባቢ አርብቶ አደር የሚበዛበት በመሆኑ  በቀድሞ ስርዓቶች እጅግ የተረሳና በአንጻራዊነት ብንመለከተው  እንኳን በአገራችን  ካሉ  ከተሞች  ቀብሪ ዳሃር እጅግ ኋላቀር የምትባል  ምንም መሰረተ ልማት የሌላት ከተማ ነበረች።   

በአገራችን ባለፉት  ሃያ ሰባት ዓመታት በፖለቲካው፣ ኢኮኖሚው እና ማህበራዊ መስኮች ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል። በመመዝገብም ላይ ናቸው። በፖለቲካው መስክ አገራችን ህገ-መንግስታዊ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት መስርታ ሁላችንንም እኩል አድርጋናለች። የህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችም  ተረጋግጠዋል። በኢትዮጵያ የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ  አስተዳደር  በመተግበሩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር  በመቻላቸው  በማንነታቸው እንዲኮሩ ባህላቸው እንዲያጎለብቱ መልካም ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።  

ዛሬ ኢትዮጵያዊነት በፍላጎት እንጂ በሃይል በህዝቦች ላይ በሃይል  የሚጫን  ዜግነት  አይደለም።  ኢትዮጵያዊነት  በምርጫ ነው፤ እንደእኔ እንደኔ  ኢትዮጵያዊነቱን  ለማይፈልግ ወይም ለማይወድ ግለሰብ ወይም ቡድን በሃይል ኢትዮጵያዊ ለማድረግ መታገል እርባና ያለው አይመስለኝም። ከኤርትራ ልንማር ይገባናል።  ትግራይ ሆኖ ኢትዮጵያዊ፣ አማራ ሆኖ ኢትዮጵያዊ፣  ኦሮሞ ሆኖ ኢትዮጵያዊ፣  ሶማሌ ሆኖ ኢትዮጵያዊ፣ ወዘተ   መሆን ከቻለ  የቡድን ማንነት የሚባል ነገር  አልስማ ማለት ተገቢ አይመስለኝም። የቡድን ማንነትና ኢትዮጵያዊነት  ማንነት እንዲቆራኙለት  የህዝቡ ፍላጎት እስከሆነ ድረስ ክፋት ያለው አካሄድ አይደለም። ቀድሞም ቢሆን ኢትዮጵያን የሰሯት እነዚሁ ህዝቦች ናቸው።

አገራችን አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ በመቻሏ በኢኮኖሚው መስክ ባለፉት 15 ዓመታት  ተከታታይና ባለሁለት አሃዝ ፈጣን እድገት በሁሉም መስክ  በማስመዝገብ  ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ካለችው  የኢኮኖሚ ዕድገት  ሁሉም ፍተሃዊ ተጠቃሚ መሆኑን  ዜጎች ከራሳቸው  ምስክርነት ባሻገር  ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ያወጧቸው ሪፖርቶች ያረጋግጣሉ። አገራችን አሁን ላይ  አቅም መፍጠር  በመጀመሯ፤   በሁሉም አካባቢዎች መሰረተ ልማት በስፋት በመገንባት  በዜጎች መካከል  ፍትሃዊ  የሃብት ክፍፍል  እንዲኖር በማድረግ ላይ ነች።   

መረጃዎች  እንደሚያመላክቱት እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር  በ2016 ማብቂያ ላይ የአገራችን አጠቃላይ አገራዊ ምርት (GDP) ከ72 ቢሊዮን የአሜርካ ዶላር እንደደረሰና  ይህም  የምስራቅ አፍሪካ ግዙፉ  ኢኮኖሚ  ለመሆን በቅቷል። አሁን ላይ ኢትዮጵያ የቀጠናውን የኢኮኖሚ  መሪነት ከኬንያ ተረክባለች።  ከ20 ዓመታት በፊት የአንድ ኢትየጵያዊ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ 250 ዶላር አካባቢ የነበረ ሲሆን  አሁን ላይ  ይህ  አሃዝ  ወደ 800 ዶላር አካባቢ ከፍ ብሏል። በዕትዕ ሁለት ማብቂያ ላይ የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ዝቅተኛውን የመካከለኛ ገቢ ማለትም አንድ ሺህ ዶላር ለማድረስ በመሰራት ላይ ነው። አሁን ባለው ነባራዊ  ሁኔታ  ይህ ዕቅድ በዕርግጠኝነት ማሳካት ይቻላል።  

በተመሳሳይ በዚያን ወቅት  በአገራችን በከፋ የድህነት ወለል  ይኖር የነበረው ዜጋ ከአጠቃላይ የህዝብ ብዛት  44 በመቶ አካባቢ  የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ይህን አሃዝ በግማሽ መቀነስ ተችሏል። በዕትዕ ሁለት ማብቂያ የድህነት መጠኑንም  ከሃያ በመቶ ለማውረድ  ግብ ተጥሎ በመሰራት ላይ ነው።  እነዚህን እውነታዎች ማንም ሊያስተባበላቸው የማይቻለው ሃቅ ናቸው። እውነቱን እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ይነስም ይብዛም  ዕድገቱ በእያንዳንዳችን ቤት ለውጥ አምጥቶል።  

አሁን ላይ በትምህርት ማስፋፋት ረገድ ኢትዮጵያ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር  በጥቅሉ ስንመለከተው ከ30 ሚሊዮን  በልጧል። ይህ ቁጥር የበርካታ አፍሪካ አገሮችን የህዝብ ቁጥር ይበልጣል። ይህን ቁጥር ዛሬ ላይ በአገራችን በመንግስት ወጪ በትምህርት ላይ የሚገኝ መሆኑ ሲታይ መንግስት ለትምህርት ዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ምን ያህል እንደሆነ ያሳያል። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት በአገራችን ሙሉ ለሙሉ በሚያሰኝ ደረጃ ማዳረስ ተችሏል።  መረጃዎች እንደሚያሳዩት በድርግ  መንግስት ማብቂያ ላይ  በአገራችን 4 ሺህ የሚሆኑ የመጀመሪያ ደረጃና 278 የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣16 የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች እንዲሁም ሁለት ዩኒቨርሲቲዎች  ብቻ ነበሩ።  አጠቃላይ የተማሪዎች ቁጥርም ከ2 ሚሊዮን ያልበለጡ ነበሩ። ይህ አሃዝ ከወቅቱ የአገሪቱ የህዝብ ቁጥር ጋር ሲሰላ በዓለም ላይ ዝቅተኛ የትምህርት ተሳትፎ አላቸው ከሚባሉ አገሮች ተርታ የሚያስመድብ  ነበር። በስርጭት ረገድም በከተሞችና ዙሪያ ከመገደቡ ባሻገር ከፆታም አኳያ ሚዛናዊነት የጎደለው ነበር። በተለይ  በአርሶና አርብቶ አደሮች አካባቢ ተሳትፎው ከሌሎች አካባቢዎች እጅግ ይከፋ ነበር።

መንግስት ለማህበራዊ ልማት ዘርፍ መስፋፋት በሰጠው ትኩረት  በአሁኑ ወቅት የአንደኛ ደረጃ የትምህርት ተቋማት ቁጥር ከ39 ሺህ በላይ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተቋማት 3,350 ፣ የቴክኒክና  የሙያ ማስልጠኛዎች  ደግሞ 1,350 የደረሱ ሲሆን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በፌዴራል  መንግስት ብቻ (የግል ዩኒቨርሲቲና ኮሌጆችን ሳይጨምር)   ሃምሳ  እየደረሱ  ናቸው።  መንግስት ሕጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር መብታቸው እንዲከበር በማድረጉ በአገር አቀፍ ደረጃ በ51 ቋንቋዎች ትምህርት እየተሰጠባቸው ይገኛሉ። በጾታ አኳያም በአንደኛ ደረጃ መሳ ማድረግ የተቻለ ሲሆን በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃና በዩኒቨርሲቲዎች ረገድ  አሁን ባለው  ሁኔታ  መቀጠል  ከተቻለ  በቅርብ ዓመታት  ውስጥ  የጾታ ጥምረትን ማሳካት ይቻለል።

የተማሪዎችም ቁጥርንም  ወደ ከ30 ሚሊዮን  አሸቅቧል። ይህ ቁጥር ከሶስት ኢትዮጵያዊ አንዱ ተማሪ እንደሆነ  ያሳያል። ይህን ሃይል በአግባቡ ማስተናገድ ከተቻለ ለነገዋ ኢትዮጵያ ትልቅ አቅም መፍጠር ይቻላል። በአሁኑ ወቅት አገራችን ኢኮኖዋን ከግብርና  ወደ ኢንደስትሪ መር  ለማሸጋገር  በምታደርገው ጥረት በተለያየ ዘርፍ የሚመረቁ   ተማሪዎች  ያላቸው  አስተዋጽዖ እጅግ ከፍተኛ እንደሚሆን መረዳት የሚከብድ አይሆንም። ከዚህ ባሻገር በቀጣይ የትምህርት ጥራትን በማሻሻል አገራችን  እንደህንድና ቻይና ለዓለም የሰለጠነ የሰው ሃይል ምንጭ በመሆን ተጠቃሚ እንደምትሆን በዕርግጠኝነት መናገር ይቻላል።   

በትምህርት ማስፋፋት ረገድ ስኬታማ መሆን  የተቻለው  ግልጽ የሆኑና አሳታፊ ፖላሲዎችና ስትራቴዎቻችን  ማዘጋጀትና ህብረተሰቡን በቀጥታ ማሳተፍ  በመቻሉ ነው።  ትምህርት በማስፋፋት ረገድ  የተመዘገበውን ስኬት  የትምህርት ጥራን በማረጋገጥ ለመድገም  ሁሉም ባለድርሻ አካላት ማለትም መምህራን፣ ተማሪዎች፣ ቤተሰብ፣ የአካባቢ ማህበረሰብ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም መንግስት በቅርበት መስራት  ይኖርባቸዋል። ተማሪዎች፣ ወላጆችና መምህራን እንዲሁም የየአካባቢው ማህበረሰብ  የትምህት ጊዜያት በተለይ ከቅርብ ጊዜያት  ወዲህ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚስተዋለውን  የትምህርት ቀናት  ብክነት  ታግለው ማስተካከል ይኖርባቸዋል።  እንዲህ ያሉ ነገሮች  በትምህርት ጥራት ላይ ቀጥተኛ  ጫና  ከመፍጠራቸው  ባሻገር  ውለው አድረው ደግሞ በአገራችን ልማት ላይ  የሚያሳድሩት አሉታዊ ተጽዕኖ በቀላሉ  የሚታይ  ባለመሆኑ  ሁሉም ባለድርሻ አካል የትምህርት ጊዜ እንዳይባክን የበኩሉን ድርሻ ሊያበረክት ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy