Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጉባዔውና የኮንፈረንስ ቱሪዝም

0 898

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጉባዔውና የኮንፈረንስ ቱሪዝም

                                                     ቶሎሳ ኡርጌሳ

30ኛው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ ጉባዔ እዚህ ሀገራችን ውስጥ መካሄዱ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ዕድገታችን ከፍተኛ ፋይዳ አለው። በአሁኑ ወቅት ሀገራችንን በቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ እያደረጋት ያለው በዋነኛነት የኮንፍረንስ ቱሪዝም ነው። የቱሪዝም ዘርፍ ከ80 በመቶ በላይ የሚገኘው ገቢ በሀገራችን በሚካሄዱ ኮንፈረንሶች አማካኝነት መሆኑ ግልፅ ነው።

እንደሚታወቀው አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ መናኸሪያ ናት። በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫቸው መዲናችን ውስጥ ነው። ቀጣናዊ፣ አፍሪካዊና ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎች የመዲናችን መገለጫዎች ናቸው። በተለይ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫው በሆነችው ሀገራችን ውስጥ በዓመት አንዴ (አንዳንዴም ሁለቴ) ጉባዔውን ያካሂዳል። የህብረቱ ሌሎች ክፍሎችም በመዲናችን ውስጥ የሚያካሂዱት ስብሰባዎች በርካታ ናቸው። ይህም ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው።

በጉባዔው ላይ የተወሰነው በአፍሪካዊያን ዘንድ ነፃ የአየር ትራንስፖርት ገበያ እንዲኖር የተደረገው ስምምነት የቱሪዝም ኮንፈረንስን የሚያነቃቃው ይመስለኛል። በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርና የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ መሃመት ፋቂና የቶጎው ፕሬዚዳንት ፋውሬ ግናሲንግቤ ይፋ የተደረገው የህ ስምምነት፤ የአፍሪካ ሀገራት ወደ ሌሎች ሀገራት ቀላል እና ቀልጣፋ በሆነ ሁኔታ እርስ በእርስ በአየር ትራንስፖርት መገናኘት እንዲችሉ የሚያስችል ነው። ይህም ከ300 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች በቀጥታ የስራ እድል የሚፈጥር ሲሆን፤ ከሁለት ሚልየን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በተዘዋዋሪ መልኩ የስራ እድል ያስገኛል።

እንዲሁም የአፍሪካ መንገደኞችን ቁጥር በ5 ሚሊየን እንዲጨምር ያደርጋል። የነፃ የአየር ትራንስፖርት የንግድ ቀጣና መተግበር የአፍሪካ ሀገራት ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ያስችላቸዋል። በአሁኑ ወቅት 23 ሀገራት ስምምነቱን የፈረሙ ሲሆን፤ ቀስ በቀስም ሀገራቱ የውስጥ ጉዳዮቻቸውን አስተካክለው ሁሉም ሀገራት ተግባራዊ ያደርጉታል ተብሎ ይጠበቃል።

ርግጥ የሰዎች ፈጣንና ገደብ የሌለበት ህጋዊ ዝውውር እስካለ ድረስ ቱሪዝም ማደጉና መጎልበቱ አይቀርም። ስምምነቱ ለየሀገራቱ አየር መንገድ ከሚያስገኘው ፋይዳ ባሻገር፤ ሀገሮች ለተጓዦች ባህላቸውን፣ ወጋቸውንና እሴቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። እናም አጋጣሚውን በተሻለ መንገድ መጠቀም የሚገባ ይመስለኛል። በተለይ በሀገራችን ውስጥ እያደገ የመጣውን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በዚህ አጋጣሚ ይበልጥ ማሳደግ እንደሚቻል ግልፅ ነው።

ዓለም አቀፍ የአየር በረራና ሌሎች የትራንስፖርት አውታሮችና አገልግሎቶች በፍጥነት መሻሻላቸውና የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎቶች እየተስፋፉ በመምጣታቸው ሣቢያ የመረጃ ልውውጥን የተቀላጠፈ እንዲሆን አስችለዋል። እንዲሁም ዓለም አቀፍ የንግድና የኢንቨስትመንት ልውውጥ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መልኩ እየተስፋፋና ድንበር ሳይገድበው እየተሸጋገረ በመምጣቱ የተነሳ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውም እንዲሁ ይህንኑ ዓለም አቀፋዊ ባህሪ መላበሱ ዛሬ ቱሪዝም ለደረሰበት ደረጃ አበይት ምክንያቶች ሆነዋል።

የቱሪዝም ዘርፍ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ያላቸውን የምርትና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን በማስፋፋት፣ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ዘላቂ ልማትን በማስገኘት እና ድህነትን በማስወገድ ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታል።

ቱሪዝም ከሌሎች ዋና ዋና የኢኮኖሚና ማህበራዊ ሴክተሮች ፋይዳዎች ባልተናነሰ ሁኔታ በመልማት ላይ ለሚገኙትም አገሮች ዋና ጠላት የሆነውን ድህነት በማጥፋትና ልማትን በማፋጠን ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አለው።

እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት የቱሪዝም ኢንዱስትሪያችን የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መገኛ የሆነችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ባህልን፣ ቅርስንና የተፈጥሮ መስህቦችን ቀጣይነት ባለው መልኩ በመጠበቅና በማልማት እንዲሁም የህዝቦችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማጎልበት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ብሎም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መጎልበት ተገቢውን አስተዋፅኦ እንዲያበርክት እየተደረገ ነው። የሁሉም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህላዊ እሴቶች፣ ተፈጥሯዊ መስህቦቻችንንና ቅርሶቻችንን በመመዝገብና በመጠበቅ እንዲሁም እንዲታወቁና እንዲለሙ በማድረግ ለህዝቦች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲውሉ መደረጉ ይታወቃል።

የሀገሪቱ ባህላዊ እሴቶች ጎልብተው በህዝቦች መካከል መተማመንና መከባበርን እንዲጠናከርና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲያግዙ የማድረግ ግብን ያነገበው ይህ ዘርፍ፤  ባህላዊና ተፈጥሯዊ መስህቦቻችንና ቅርሶቻችንን እንዲለሙ ብሎም ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሚና እንዲኖራቸው በማድረግ መካከለኛ ገቢ ያለው ህብረተሰብ የመፍጠርን ብሔራዊ ራዕይ ለማሳካት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ግብ ተጥሏል። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ይህን ግብ ለማሳካት የኮንፈረንስ ቱሪዝም ዓይነተኛ ሚና አለው። ዜጎችም የደርሻቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል።

ሆኖም በመዲናችን ውስጥ በአንዳንድ ዜጎች አማካኝነት ይህን መስክ ለማጎልበት የሚደረገው ጥረት ተግዳሮቶች የሚስተዋሉበት እየሆነ ነው። በተለይ በዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ጉባኤዎች ወቅት በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ የሚታየው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የሀገርን ገፅታ የሚያበላሽ መሆኑን አንዳንድ በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ዜጎች የተገነዘቡት አይመስለኝም።

 

በሆቴል ኪራይ፣ በመኪና ኪራይ፣ በአስጎብኚዎች፣ በስጦታ ዕቃ መሸጫዎች…ወዘተ አካባቢዎች የሚታዩ ዋጋን የማናር የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባራት ለግለሰብም ይሁን ለሀገር ዘለቄታዊ ጠቀሜታ የሚያስገኝ አይደለም። በግለሰብ ደረጃ ተግባሩ ከአንድ ክብሩን ከሚጠብቅ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የማይጠበቅና አሳፋሪ ሲሆን፤ በዚህ የዜጎች ተግባርም ሀገራችን ቀጣይ ታላላቅ ስብሰባዎችን እንዳታስተናግድ የሚያደርጋት መሆኑ መታወቅ ያለበት ይመስለኛል።

 

ለአህጉራዊ ጉባዔዎች ወደ ሀገራችን የሚመጡት ተሳታፊዎች ሁሉም በሚባል መልኩ ከኢትዮጵያ ከማይሻሉ ድሃ ሀገራት እንደመሆኑ መጠን ከእነሱ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት የሚደረግ ሙከራ ዘለቄታዊ ጥቅምን የሚዘጋ ነው። አፍሪካዊያን ሀገራችንን የሚመርጧት የህዝቡን ጨዋነትና ሰላማዊነት ስለሚረዱ እንጂ አንዳንድ አላግባብ መጠቀም የሚፈልጉ ዜጎችን ለማበረታታት አይደለም።

 

አፍሪካዊያን ሙስናን ከአህጉሪቱ ለመቀነስ ብሎም ለማጥፋት እየተሰበሱ እዚህ ሀገር ውስጥ በላያቸው ላይ ያልተገባ ጥቅም የሚፈልጉ አንዳንድ ኢትዮጵያዊያንን ሲመለከቱ ማዘናቸው የሚቀር አይመስለኝም። ይህም ‘ጉባዔው ለምን እኛ ሀገር ውስጥ አይካሄድም’ የሚል ስሜት የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ፤ በእነርሱ መምጣት ይጠቀም የነበረ ባለሆቴል፣ መኪና አከራይና የስጦታ ዕቃዎች ሻጭ ወይም ሌላ ማገኘት የሚገባውን ገቢ ለዘለቄታው እንዳያገኝ ያደርጋል። በጥቂቶች በሚፈፀም ያልተገባ ነገር የማግኘት ፍላጎት ነባር የሀገራችንና የህዝቦቿ ተቀባይነት ብሎም አፍሪካዊ አጋርነት ሊደበዝዝ ይችላል። እናም በዚህ ዓይነት አሳፋሪ ተግባር ላይ የሚገኙ ጥቂት ዜጎች ራሳቸውን መለስ ብለው ቢመለከቱ ተገቢ ይመስለኛል።

 

ርግጥ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ በተካሄደ ቁጥር ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ጥቂት የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ግለሰቦች በሚያደርጉት ያልተገባ ተግባር ሁኔታው በዚሁ የሚቀጥልበት ዕድል ሊኖር የሚችል አይመስለኝም። በአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ላይ በሁሉም የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ያልተገባና አስደንጋጭ ጭማሪ ሲደረግ መንግስትም ዝም ብሎ የሚመለከት አይመስለኝም። ምናልባትም ችግሩን ለመቅረፍ ጉባዔውን ወደ ሌሎች የሀገራችን ከተሞች ለማዛወር ሊገደድ አሊያም የራሱን የጉባዔ መስተንግዶ ማዕከላትን በመገንባት ብዝበዛውን ለማስቀረት ሊሰራ ይችላል። ይህም የግለሰቦችን ዘላቂ ጥቅም የሚያሳጣ ስለሆነ በዚህ ረገድ የተሳሳተ ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች መታረም ያለባቸው ይመስለኛል።

 

የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ሲካሄድ ሾፌሮችን ጨምሮ አገልግሎት የሚሰጡ ግለሰቦች ሁሉ ስጦታ እየለመዱ መጥተዋል። ርግጥ ስጦታ በሰጪው ግለሰብ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ‘ስጦታን መቀበል ክልክል ነው’ እያልኩ አይደለም። ሆኖም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንደ ባህላዊ ማስታወሻ ዓይነት ስጦታ ሲበረከትለት ‘የለም። እኔ የምፈልገው ገንዘብ ነው። ገንዘብ ስጠኝ’ የሚል ከሆነ ሰጪውንም ግራ የሚያጋባ ነው።  እንዲህ ዓይነቱ ዜጋ “የስጦታ ፈረስ ጥርሱ አይታይም” ከሚል ማህበረሰብ የወጣ መሆኑም ያጠራጥራል። አስነዋሪና አሳፋሪም ነው።

 

አመለካከቱ ከእኛ ሀገር ህዝብ እንግዳ ተቀባይነትና የሌሎችን ፍላጎት ከማክበር ባህል ጋር ፈፅሞ የሚሄድ አይደለም። እንዲህ ዓይነት ስጦታ ሰጪውን የሚያስገድዱ አካላት በቸልታ የሚታዩ ይመስለኝም። ምክንያቱም እያጎደፉ ያሉት የህዝቡን ጨዋነትና ክብር እንዲሁም በሀገር ተጠቃሚነት ላይ አሸዋ እየበተኑ በመሆናቸው ነው።

ይህ ተግባር በጥቅል ሲታይም ከቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ ከ80 በመቶ ገቢ የሚያስገኘውን የኮንፈረንስ ቱሪዝማችንን የሚጎዳ ነው። ለአፍሪካዊያን አለኝታ የሆነችውን ሀገራችንን ገፅታ ያጠለሻል። እናም ዜጎች እንደ ዜጋነታቸው በትክክለኛው የንግድ ስርዓት መጠቀም እየቻሉ እንዳይጠቀሙ፣ ሀገርም ከቱሪዝም ስራው የምታገኘውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን የሚያስተጓጉል በመሆኑ በፍጥነት ሊታረም ይገባል እላለሁ።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy