Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጣት ቀሳሪ ፖለቲከኞች

0 363

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጣት ቀሳሪ ፖለቲከኞች

                                                      ዘአማን በላይ

ሀገራችን ውስጥ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን ለሚገኙበት የተዳከመ ሁኔታ ተጠያቂው ገዥው ፓርቲ መሆኑን ሲገልፁ ይሰማል። በተለይም ቅንጅት፣ ሰማያዊና ኢዴፓን የመሳሰሉ ፓርቲዎች ለመዳከማቸው ምክንያት ኢህአዴግ መሆኑን ይናገራሉ። ርግጥ ይህን ጉዳይ በስፋት ለማተት የፓርቲዎቹን ባህሪ፣ የጥምረታቸውን ምክንያትና ያላቸውን የፖለቲካ መስመር ጠንቅቆ ማወቅ ይገባል። በእኔ እምነት በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ተዳክመናል የሚሉ ከሆነ ለመዳከማቸው ምክንያት ገዥው ፓርቲ የሚሆን አይመስለኝም።

እንደ እውነቱ ከሆነ የአንድ ፓርቲ ጥንካሬም ይሁን ድክመት የሚለካው በመስመሩ ጥራት፣ በአባላቱ ጥንካሬና ዲሲፕሊን እንዲሁም የዓላማ ቁርጠኝነት ሆኖ ሳለ፤ ጉዳዩን ወደ ገዥው ፓርቲና መንግስት ለማላከክ መሞከር ተገቢም ትክክልም አይመስለኝም። እነዚህ ፓርቲዎች በተለያዩ ወቅቶች በ“እሳትና ጭድ” ተምሳሌትነት የሚቀርቡ፣ የሚቧደኑበት ዓላማ በደፈናዊ ጥላቻ የሚመራ፣ በ“ጠላቴ ጠላት…” ቁርኝት የታጀለ፣ ትክክል ያልሆነና ይህ ነው የሚባል የጠራ የፖለቲካ መስመር የሌላቸው ናቸው።

የፓርቲዎቹ ድርሳነ ታሪክ እንደሚያወሳው፤ ተጣማሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካም ይሁን በአመለካከት ምንም ዓይነት ግንኙነት ከሌላቸው ፓርቲዎች ጋር የመዋሃድና አፍታም ሳይቆዩ ደግሞ “እየተቦጫጨቁ” የመለያየት ባህል ያላቸው ናቸው።

ርግጥ ይህን ማንነታቸውን ባለፉት አምስት ሀገራዊ ምርጫዎች ተግባሮቻቸው እንድንገነዘብ ማድረጋቸውን ራሳቸው ባይክዱትም ቅሉ፤ ድክመታቸውን በገዥው ፓርቲና በመንግስት ላይ ለማላከክ መሞከራቸው ግን “የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ” በማለት የራስን ችግር ለመሸፋፈን የሚደረግ አስገራሚ ዲስኩር ይመስለኛል።

“የአብዬን ወደ እምዬ” በማላከክ ጣት የመቀሰር ፖለቲካን ሲያራምዱ እንደነበር ያለፈው ታሪካቸው አፍ አውጥቶ ይናገራል። ፓርቲዎቹ ወትሮም ቢሆን የአቤቱታን ሙግት እያጨዱ መከመር ስራቸው ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት “አኛ ተፎካካሪ ነን” በማለት ስለ ፖለቲካ ምህዳርና ስለ ምርጫ እንዳላወሩ፤ ዛሬ ደግሞ ለመዳከማችን ምክንያተቱ ገዥው ፓርቲና ኢህአዴግ ነው እያሉን ነው።

በእኔ እምነት ሀገሬ እንደ አለመታደል ሆኖ የፖለቲካ ጨዋነት ያለው፣ የተሟላ ስነ ምግባርና ፕሮግራምን የተላበሰ፣ የጠራ ድርጅታዊ መስመር ኖረሮት ሀዝብን በአጀንዳው ሊያሳምን የሚችል ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ አልታደለችም። ሃቁን እንነጋገር ከተባለ የተቃዋሚ ፓርቲዎቻችን ቁመና፣ ታሪክና የስነ ምግባር ስስ ነው።

ለተወዳዳሪነትም በአቅመ እንደራሴነቱም ያልባቱ ምናልባትም በዚህ ጣት ቅሰራ ፖለቲከኝነታቸው ወደፊትም ለመብቃትና ተመራጭ ሆኖ ለመገኘት ዝግጁነትም ያላቸው አይመስለኝም። ጊዜያቸውን ‘ለእኔ መዳከም ተጠያቂው እገሌ ነው’ ከማለት በስተቀር ራሳቸውን ወደ ውስጥ የመመልከት ባህል የላቸውም። ነገ የተሻለ ተቀናቃኝ ሆነን ለመገኘት ራሳችንን በምን መልኩ ማጠናከር ይኖርብናል ብለው ሲጠይቁና ሲመካካከሩ ሰምቼ አላውቅም። ከዚህ ይልቅ በሌላው ላይ ጣት መቀሰር የሚቀናቸው ናቸው።

አሁንም በእኔ እምነት ኢህአዴግ ነፍስ ያወቀ፣ የደረጀና ባለ ራዕይ ድርጅት ነው። እናም ከኢህአዴግ ጋር ራስን አወዳድሮ ሽንፈትን አምኖ መቀበል አግባብነት ያለው አንድ ነገር ነው። አግባብነት የሌለውና የሚያስገምተው ግን አቅምን ባለመገንዘብ ‘የችግራችን ሁሉ ምንጭ ኢህአዴግ ነው’ የሚል ጣት ቅሰራ ነው።

ኢህአዴግን ጨምሮ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የተውሸለሸለ የፖለቲካ ፕሮግራም ይዞ ሚዛናዊው ህዝብ ፊት መቅረብ አይችልም። የጠራ፣ የህዝብን ቀልብና ፍላጎት የሚማርክ እንዲሁም ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መስመር ሊኖረው ግድ ይላል። አሊያ ግን ህዝቡ እንኳንስ በካርዱ ውክልና ሊሰጠው ቀርቶ የምራጮች ሁሉ ምራጭ እንደሚያደርግ ባለፉት ምርጫዎች በገሃድ አሳይቷል።

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰበብ አስባቡ ጣታቸውን ወደ ገዥው ፓርቲና ወደ መንግስት የሚቀስሩት ዜጎችን መማረክ የሚችልና የኢህአዴግ ፕሮግራሞች የሚያስንቁ የፖለቲካ ማኒፌስቶዎች ስለሌሏቸው ይህን እውነታ ለመሸፋፈን ካላቸው ፍላጎት በመነሳት መሆኑን ማንም የሚስተው እውነታ አይደለም። በእኔ እምነት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አውርቶ አደሮች እንጂ ባለፉት ዓመታት ህዝብ ዓይን ውስጥ የሚገባ መስመርን አልተከተሉም።

መድረክን የመሳሰሉ ፓርቲዎች በውጭ ሃይሎች የሚመራ ፖለቲካን እዚህ ሀገር ውስጥ የሚያልሙ ናቸው። እንዲያውም በተለያዩ ወቅቶች የአክራሪ ኒዮ ሊበራል ሃይሎች “ዓይንና ጆሮ” ሆነው ሲሰሩ ታዝቤያቸዋለሁ። ይህ ግን ሁሉንም ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚመለከት አይደለም። እዚህ ላይ በሀገራዊ መንፈስና በሀገር ተጠቃሚነት እሳቤ የሚንቀሳቀሱ በስነ ምግባር የታነፁ ጨዋ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሃቅ ለመደፍጠጥ አልሻም።

እነ መድረክና ሰማያዊ ግን ለእኔ “እነ አያ ጉዶ” ናቸው። ትናንት ለእነ “ሂዮማን ራይትስ ዎች” ተላላኪ ሆነው የቀለም አብዮት አቀጣጣይ፣ የእነ ቢቢሲ ናይት የውሸት መስክሮች፣ በውጭ ሃይሎች ግፊት ቤተ መንግስት ገቢዎች ሆነው ራሳቸውን የሾሙ ነበሩ።

የህዝቡን ፍትሐዊ ድምፅ ከመጤፍ ባለመቁጠር ስልጣንን ከምርጫ ኮሮጆ ሳይሆን ከቀለም አብዮት አንጋሾች ለማግኘት ደፋ ቀና ይሉ እንደነበር አስታውሳለሁ። ይህ አሳፋሪ ማንነት የታሪካቸው አካል ሆኖም እንደ ጥላ እንደሚከተላቸው የተገነዘቡት አይመስሉም።

እናም “እነ አያ ጉዶ” ዛሬ ‘እኛ ያልባረክነው ወይም የሌለንበት ድርድር ዋጋ የለውም’ ብለው አሊያም እንዲሉ “በአንጋሾቻቸው” ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው በሰጥቶ መቀበልና በፍፁም ሀገራዊ ጥቅም እየተካሄደ ያለው ድርድር ቁብ አልሰጣቸውም። ይህም ምን ያህል ለሀገራቸው ፖለቲካ ምህዳር መስፋት ደንታ ቢሶች እንደሆኑ የሚያሳይ ነው።

እናም ጠቧል የሚሉት የፖለቲካ ምህዳር ካለ፣ ራሳቸው ውስጥ ገብተው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ታግለው ሃሳባቸውን ማቅረብ ሲችሉ ውጭ ሆነው ለመዳከማችን ምክንያቱ ገዥው ፓርቲና መንግስት ናቸው ቢሉ የሚያገኙት አንዳች ትርፍ ሊኖር አይችልም። ሰላማዊ ድርድርን ረግጦ በመውጣት የሚገኝ ዴሞክራሲን የማጎልበት ሂደት ምን ዓይነት እንደሆነ የሚያውቁት እነርሱ ብቻ ይመስሉኛል።

ስለ ተቃዋሚዎቹ ድክመትና ጣት ቀሳሪነት ሳወሳ ገዥው ፓርቲ ምንም ዓይነት ችግር የለበትም እያልኩ አይደለም። ሌላው ቀርቶ ሰሞኑን በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ደረጃ ለ17 ቀናት ባካሄደው ግምገማ ራሱን በሚገባ አይቷል። ችግሮቼ ብሎ ያነሳቸውን ጉዳዩች ከ‘ሀ’ እስከ ‘ፐ’ ድረስ ዘርዝሮ ህዝቡን ይቅርታ ጠይቋል። የችግሮቹ አልፋና ኦሜጋ ራሱን አደርጎ ኮንኗል። በእኔ እምነት ይህ ራስን መሄስ ትልቅነት ነው። የችግሮች ምንጭ እኔ እንጂ ሌላ አካል አይደለም ብሎ ማመን ብስለት ነው። ጣትን በሌላ ላይ ከመቀሰር የሚመጣ ውጤት አለመኖሩን መገንዘብ አዋቂነት ነው። እናም ከዚህ የኢህአዴግ መንገድ መማር ተገቢ ይመሰለኛል። ራስን ወደ ውስጥ አይቶ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት መሞከር እንጂ የጣት ቅሰራ ፖለቲካ ለማንም የማይጠቅም የሽሽት መንገድ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ስለሆነም ተቃዋሚ ፓርቲዎች “ኢህአዴግ አዳከመን” ከማለት ለምን ተዳከምን ብለው ራሳቸውን ቢፈትሹ ምላሹ ራሱ እጁን አውጥቶ “እዚህ ነኝ” የሚላቸው መሆኑን ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል።

ያም ሆኖ ግን በእኔ እምነት እነርሱ እንደሚሉት ተቃዋሚዎቹን ኢህአዴግ አዳክሟቸው ከሆነ፤ ይህ ክስተት የእነርሱን ተሸናፊነትና የኢህአዴግን ጥንካሬ የሚያሳይ ይመስለኛል። ይህ ማለት ተቃዋሚዎቹ ሲጀመር ለመዳከም የተዘጋጁ ናቸው መሆናቸውን ያመላክታል። ለመዳከም ዝግጁ የሆነ አካል ደግሞ ውስጣዊ ጥንካሬ የሌለው፣ ለውሸት የተሰባሰበ፣ አባላቱ የጋራ ግብና ራዕይ የሌላቸው ከመሆን የሚዘሉ አይደሉም። እናም ርግጥም እነርሱ እንደሚሉት ተቃዋሚዎቹን ኢህአዴግ አዳክሟቸው ከሆነ ማፈር ያለባቸው በራሳቸው ውስጠ ፓርቲ ጥንካሬና አንድነት እጦት እንጂ፣ ችግራቸውን ለመሸፋፈን በሌላው ላይ ጣት መቀሰርን አይመስለኝም።

ዳሩ ግን እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ገዥው ፓርቲም ይሁን መንግስት ዴሞክራሲን እንደ ህልውና የያዙ ናቸው። የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን ለማጠናከርና በጣት የሚቆጠር ደጋፊ ያላቸውን ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሀገራቸው ጉዳይ ቢሳተፉ አነስተኛም ቢሆን የህዝቡን   ድምፅ ለማክበር ያስችላል ብለው የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እስከ ድርድር የዘለቀ ስራዎችን እያከናወኑ ነው። ይህን የሚያደርጉት ድርጅትና መንግስት የረባ የፖለቲካ መስመር የሌላቸውን ተቃዋሚዎችን ያዳክማሉ ብሎ ለማሰብ እጅግ ይከብዳል። ውሃ የማይቋጥርና ሚዛን የማይደፋ አስተሳሰብም ነው።

እናም ጣት ቀሳሪ ፖለቲከኞች “አመልካች ጣትን ወደ ሌላው ስተቀስር ቀሪዎቹ ወዳንተ ያመለክታሉ” የሚለውን ብሂል ሊዘነጉት አይገባም ባይ ነኝ። የተቃውሞ ፖለቲካ ግብ መነሻውን ማደረግ ያለበት ራስን ብቁ ከማድረግ እንጂ፤ ገና ከወዲሁ በፈጠራ ድርሰት ‘እገሌ አዳከመኝ’ እያሉ በመልፈስፈስ አይደለም።

የፖለቲካ ስራ እንደ ሽሮ ፈሰስ አሁን ተዘጋጅቶ አሁን የሚደርስ አይደለም። ጊዜን ይጠይቃል። የትግሉም ሂደት አልጋ በአልጋ አይደለም። አባጣ ጎባጣ የበዛበት፣ ረጅም አቀበትን መውጣትና ቁልቁለትን መውረድ እንዲሁም ሰው ወሳጅ ፈረሰኛ ውሃን የያዘ ወንዝ በድፍረት መሻገር የግድ ይላል። የተቃውሞው ጎራ እነዚህን ሂደቶች ሃሞተ ኮስታራ ሆኖ ማለፍ አለበት። የፖለቲካ ስራ ዳር ቆሞ የጣት ቅሰራ ፖለቲካ ሐሜት አራማጅነት የሚመራ አይደለም። ስንክሳሮችንና አሜኬላዎችን እየተጋፈጡ ራስን በማብቃትና ህዝብን የሚያማልል ፕሮግራም ቀርፆ ወደሚፈለገው ግብ መድረስ ይቻላል።

የተቃውሞ ጎራው ይህን ማድረግ ከቻለ ሁለት ነገር ሊያተርፍ ይችላል ብዬ አስባለሁ። አንደኛው፤ ከተራ ውንጀላ ወጥቶ ራሱን በመፈተሽ የጠራ መስመር ኖሮት የህዝቡን ቀልብ ሊያሸፍት መቻል ነው። ሁለተኛው ደግሞ፤ ሀገሪቱ እያከናወነች ባለችው የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በሚደረገው ጥረት ላይ የራሱን አሻራ ሊያሳርፍ ይችላል። ይህን ማድረግ ከተሳነው ግን ነገም ሆነ ከነገ በስቲያ ከፈጠራ ውንጀላ ፖለቲካና ከጣት ቀሳሪ ፖለቲከኞች የሚላቀቅ አይመስለኝም።      

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy