Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ማሞ ሌላ፣ መታወቂያው ሌላ”

0 2,106

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ማሞ ሌላ፣ መታወቂያው ሌላ”

                                                     ዘአማን በላይ

የኢህአዴግ አራቱ አባል የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ከመሰንበቻው መግለጫ ሰጥተው ነበር። በተለይም የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት ጋር ተያይዞ የሚነሳውን የፖለቲካ እስረኞችን የመፍታት ጉዳይ በአንዳንድ ግለሰቦች የተሳሳተ ትርጓሜ ሰሰጠው ይስተዋላል። ይሁንና ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካም ይሁን የህሊና እስረኛ የሌለ መሆኑ ሊታወቅ የሚገባ ይመስለኛል። ጉዳዩ ከወንጀል ጋር የተያያዘ እንጂ ግለሰቡ ከሚከተለው ፖለቲካ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም።

ርግጥ አንድ ግለሰብ በሙያው ፖለቲከኛ፣ ጋዜጠኛ ወይም ዳኛ ሊሆን ይችላል። ይሁንና በተለያዩ ጉዳዩች ዙሪያ የሀገሪቱን ህጎች ተላልፎ ሲገኝ በህግ መጠየቁ የሚቀር አይደለም። ምክንያቱም የህግ የበላይነትን የማስከበር ጉዳይ በሁሉም ዜጎች ላይ በእኩል ሁኔታ ተግባራዊ መደረግ ስላለበት ነው። ጉዳዩ ግለሰቡ ከፈፀመው የወንጀል ስራና ከህግ የበላይነት አኳያ የሚታይ እንጂ ከሚከተለው ፖለቲካዊ እምነት ጋር ምንም ዓይነት ቁርኝት ሊኖረው አይችልም።

በእኔ እምነት ወንጀል ሰርተው በህግ ጥላ ስር የዋሉና የተፈረደባቸው ግለሰቦችን ከፖለቲካ እምነታቸው ጋር ለማስተሳሰር ማሰብ “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” ዓይነት ብሂል ተቃራኒ እውነታዎችን ለማገጣጠም ከመሞከር የዘለለ ፋይዳ የለውም። ርግጥ እስረኞችን መፍታት አንድ ነገር ሊሆን ይችላል፤ ክንዋኔው ግን የሀገሪቱን ህግ በጠበቀና የፍርድ ቤቶችን አሰራር በተከተለ ሁኔታ ተፈፃሚ መሆን ይኖርበታል። አንድ ሰው ፖለቲከኛ ስለሆነ በፈፀመው ወንጀል የህግ የበላይነት ችላ የሚባልበት፤ ስላልሆነ ደግሞ የህግ የበላይነት የሚተገበርበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ የምንገኝ ህዘቦች አይደለንም። ይህም የፖለቲካ እስረኛ የሚባል ጉዳይ እዚህ ሀገር ውስጥ ሊኖር እንደማይችል ማረጋገጫ ይመስለኛል።

እኔ እስከማውቀው ድረስ ሀገራችን ውስጥ በፖለቲካ እምነቱ የታሰረ ሰው የለም። ለምን ይህን አቋም አንጸባረቅክ ተብሎ የታገደ ፓርቲም ይሁን የታሰረ ግለሰብ የለም። ይህ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ የመደራጀት መብት እንዳይኖር መከልከል ነው። ይህን ፀረ ዴሞክራሲያዊና ኢ ህገ መንግስታዊ ተግባርን ገዥው ፓርቲም ይሁን መንግስት የሚፈቅዱት አይደለም—የታገሉለት ጉዳይ ነውና።

ኢትዮጵያ ውስጥ ህገ መንግስቱ ባጎናፀፋቸው የመደራጀት መብት መሰረት በርካታ የመንግስት ተቃዋሚዎች ይገኛሉ። እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዓላማቸውን ለማሳካት በሚያካሄዱት ማናቸውም እንቅስቃሴ ጣልቃ የሚገባ አንድም የመንግስት አካል ያለ አይመስለኝም። ምክንያቱም ህገ መንገስቱን መጻረር ስለሚሆን ነው። ይልቁንም ፓርቲዎቹ  በተለያዩ ጊዜያት በሀገራዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ይሰጣሉ፤ አቋማቸውንም ያንጸባርቃሉ። ከመንግስት ጋርም ይደራደራሉ። በዴሞክራሲያዊ ሰጥቶ መቀበል መርህ ይወያያሉ። ይህ ነባራዊ ሁኔታ ነው።

ከዚህ ውጭ ግን የፓርቲዎቹ አባላት አሊያም አመራሮች ሀገሪቱ የምትመራባቸውን ህጎች ተላልፈውና በወጅጀል ውስጥ ተሳታፊ ሆነው ከተገኙ ‘ለምን ተጠየቁ?’ ማለት አይቻልም። ለአንዱ የሚሰራ፣ ለሌላው ደግሞ የማይሰራ ህግ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም። እንዲህ ዓይነት ፍርደ ገምድልነት ኢትዮጵያ ውስጥ መተግበር ካቆመ ከ26 ዓመታት በላይ ሆኗል። አክትሞለታል።

ርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲከኝነቱ ብቻ የታሰረ ግለሰብ ለመኖሩ ማስረጃ ማቅረብ የሚቻል አይመስለኝም። ግና ክርክሩ ‘አንድ ሰው ፖለቲከኛ ስለሆነ ወንጀል ቢፈፅምም መታሰር የለበትም’ የሚል ክርክር የትኛውንም ወገን የሚያስማማ አይመስለኝም። ምክንያቱም በየትኛውም ሀገር ውስጥ በዴሞክራሲያዊ አግባብ የተመረጠ መንግስት ከህዝብ በተሰጠው አደራ መሰረት የህግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ ሰላለበት ነው።

እናም በተቃዋሚነት የተሰለፈም ይሁን ማንኛውም የመንግስት ባለስልጣን በወንጀል እስከ ተጠረጠረ ድረስ በህግ ጥላ ስር ውሎ ጉዳዩ መጣራቱ የሚቀር አይመስለኝም። በነፃው ፍርድ ቤት ተፈርዶበት በማረሚያ ቤት ሊቆይ ይችላል።

በዚህ ረገድ መንግስት ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነ በቅርቡ በተለያዩ ክልሎችና ከተማዎች የህዝብን አደራ ወደ ጎን በማለት በሙስና እና በኪራይ ሰብሳቢነት በተዘፈቁ አመራሮችና በየደረጃው በሚገኙ አስፈፃሚዎች ላይ የወሰደውን አስተማሪ ርምጃ መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል።

እዚህ ላይ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ለዜጎች ካጎናፀፋቸው ዴሞክራሲያዊ መብቶች መካከል የቡድንና የግለሰብ መብቶችን መጥቀስ ማንም ሰው በሚከተለው ፖለቲካዊ እምነት ሳቢያ በህግ ጥላ ስር ሊውል እንደማይችል ማረጋገጫ ይመስለኛል። መብቶቹ በዋነኛነት የአመለካከትና ሃሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነት እንዲሁም አቤቱታን ማቅረብን የሚያጠቃልሉ ናቸው።

እነዚህ መብቶች ሀገራችን ውስጥ ጥበቃ እየተካሄደላቸው ያሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ በፖለቲካው ምህዳር ውስጥ በተጨባጭ ገቢራዊ እየሆኑ የመጡም ጭምር ናቸው። ለዚህም ጥቂት የታዘብኳቸውን ምሳሌዎች ማንሳት እችላለሁ። በተለያዩ ወቅቶች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚያካሂዱት ሰላማዊ ሰልፎች፤ “መንግስት የታሰሩ ሰዎችን እንዲፈታ፣ ስራ አጥነትን እንዲቀንስ፣ በሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ…ወዘተ.” ጥሪዎችን ሲያካሂዱ ተመልክቻለሁ።

በተለያዩ ወቅቶች በተደጋጋሚ ይካሄዱ የነበሩት ሰላማዊ ሰልፈኞችና ባለቤቶቹ ህግን እስካልጣሱ ድረስ ከፖሊስ አሊያም ከሌላ ህግ አስከባሪ ምንም ዓይነት ተግዳሮት ሲገጥማቸው አልተመለከትኩም። እናም ለእኔ ይህ ተጨባጭ ሁኔታ በሀገራችን ውስጥ የሚታየው ተደራጅቶ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን የሚያመላክትና ለፖለቲካ ሂደቱ አዲስ መንገድ በሂደት እየታየ መሆኑን የሚያንፀባርቅ መሆኑን ነው—አሁንም ቢሆን ብዙ ርቀት መጓዝ የሚያስፈልግ ቢሆንም።

ግና ከተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎች በፓርቲዎች የዕውቀትና የግንዛቤ ችግር ሳቢያ ሁከትን የሚቀሰቅሱ ቃላቶች ሊሰነዘሩ፣ የሌሎችን መብት የሚነኩ አጸያፊ ሰድቦች ሊሰሙ እንዲሁም ‘አትነሳም ወይ!’ የሚሉ ጠብ-ጫሪ ዝማሬዎችም ሊደመጡ አሊያም የዜጎች ህይወት እንዲጠፋ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ጉዳዩች ሲገጥሙ በህግ  ሊያስጠይቁ ይችላል። ህግና ስርዓትን ተላልፎ ‘ለምን እጠየቃለሁ?’ ብሎ መጠየቅ አይቻልም። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ይህ ማለት ‘የፈለግነውን ያህል ብናጠፋ ማንም ሊጠይቀን አይገባም’ ብሎ ማሰብ ነው። እናም “የማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” ህግን ተፃርሮ የሚቆም የፖለቲካ ጨዋታ ቦታ እንደማይኖረው ማወቅ ተገቢ ይመስለኛል።

“የማሞ ሌላ መታወቂው ሌላ” የፖለቲካ ጨዋታ ከፀረ ሽብርተኝነት ህጉ ጋር ተያይዞ ሲነሳ ይደመጣል።የዚህ ጨዋታ አራማጆች ኢትዮጵያ ውስጥ በህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት አማካኝነት የሚወጡት ህጎች ሁሉ፤ በሰላማዊ መንገድ የሚቃወሙትን አፍ ለማዘጋት ተብለው የሚዘጋጁ ይመስላቸዋል። በተለይም የሀገራችንን ሰላም በማስጠበቅ ልማትን ያለ ስጋት ለማፋጠን እንዲያግዝ የወጣውን የፀረ-ሽብርተኝነት ህግን ሲሰሙ በሪፖርት ቅብብሎሽ ጋጋታ “ሰብዓዊ መብት ተጣሰ፣ አዋጁ ተቃዋሚዎችን ለማፈን ነው…ወዘተ” በማለት ከጎሬያቸው ወጥተው ለዚሁ ተግባር የተቋቋሙትን የራሳቸውን ሚዲያ፣ የፅንፈኛና የአሸባሪዎች ልሳኖችን ያጥለቀልቃሉ።  

ዳሩ ግን የፀረ ሽብርተኝነት ህግ ማውጣትና ወንጀለኞችን ለህግ ማቅረብ የዜጎችን መብት ከማፈን ጋር የሚያስተሳስረው አንዳችም ነገር የለም። የኢፌዴሪ መንግስት እንደ ማንኛውም አገር ከራሱ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ልዩ ልዩ አዋጆችንና ህጎችን የማርቀቅና ወደ ስራ የመተርጎም መብትም ሆነ ግዴታ አለበት።

መንግስት የነባራዊው ዓለም ተጋሪ በመሆኑ አዳዲስ የህግ ማዕቀፎችን ማውጣቱና በስራ ላይ ማዋሉ ማንንም ሊደንቅ አይገባም። ከዚህ ጋር ተያይዞ የወጣው የፀረ ሽብር ህጉ ዜጎችን ከማንኛውም የፕሬስ እንቅስቃሴ የሚገታና ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን የሚያፍን ነው የሚለው ጩኸት በፍጹም ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። አይኖረውምም። ምክንያቱም በህግ ገደብ እስካልተጣለባቸው ድረስ አሁንም እንዳሻቸው የሚፅፉና የሚናገሩ እንዲሁም ህግና ስርዓትን ተከትለው ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርጉ አያሌ ፖለቲከኞች በመኖራቸው ነው። እናም ‘እንዳሻችን ከህግና ስርዓት ውጭ እንሁን’ በሚል ስሜት ወንጀል ሰርተው እንዳይጠየቁ የሚሹ “የማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” አቀንቃኞች ይህን ሃቅ እየመረራቸውም ቢሆን ቢውጡት ከእውነታው እንዳይርቁ ያደርጋቸዋል ብዬ አስባለሁ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy