Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ነጋሪ አያሻንም!

0 384

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ነጋሪ አያሻንም!

ወንድይራድ ኃብተየስ

አባይን በተመለከተ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት  የግብጽ መንግስታት የሄዱበትን መንገድ ከመከተል ይልቅ ሁሉም አሸናፊ፣ ሁሉም ፍትሃዊ ተጠቃሚ፣ የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚችል መንገድን  መርጠዋል። ኢትዮጵያ እንደአፍሪካ ህብረት ቀደምት መስራችነቷና  የህብረቱ  መቀመጫነቷ እንዲሁም የአህጉሩ ፖለቲካልና ኢኮኖሚያዊ መዕከላዊነቷን  የሚመጥን ተግባራትን በማከናወን ላይ ነች።  

አገራችን ዛሬ በፈጣን የለውጥ ጎዳና ላይ ነች። በህዝቡ ውስጥም የመልማትና የማደግ ፍላጎት አድሯል። አገራችንም  አቅም ፈጥራለች። በመሆኑም ዛሬ ላይ እንደቀድሞው አገራችንን  ይህን አድርጊ፣ ይህ ደግሞ አይበጅሽም አታድርጊ የምትባል  አይደለችም። ለሁሉም ጊዜ አለው እንደሚባለው ዛሬ ላይ ለአገራችን የሚበጃትንና የማይበጃትን ዜጎቿ የሚወስኑበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ነጋሪ አያሻንም። ኢትዮጵያችን አሁን ላይ ከራሷ አልፋ ለአካባቢው አገራት  ከዚያም ባሻገር ለመላው አፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለመረጋገጥ የምትተጋ አገር ለመሆን በቅታለች።  ለዚህ ጥሩ  ማሳያው የኢትዮጵያ ሜጋ ፕሮጀክቶች ሁሉ ከአገራችን አልፈው ጎረቤት አገራትን የሚጠቅሙ፣ መልካም ጉርብትናን  የሚያጠናክሩ፣  የአካባቢውን ዘላቂ ሰላም የሚያረጋግጡ በመሆን ላይ ናቸው።   

አንዳንድ የፖሊሲ ተመራማሪዎች እንደሚሉት የአገራችን ዕድገት የፖሊሲና ስትራቴጂ ውጤት እንደሆነ ይገልጻሉ። ይህ ዕውነታ ነው። ኢትዮጵያ እስካሁን ባለው ሁኔታ የተፈጥሮ ሃብት አላቸው ከሚባሉ አገሮች ተርታ የምትመደብ አገር አይደለችም። በተከታታይ ለ15 ዓመታት በዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጭምር ይሁንታ ያገኘው የአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት በተፈጥሮ ሃብት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን ህዝብና መንግስት በግብርናውን  ዘርፍ ላይ በቅንጅት መስራት በመቻላቸው  የተመዘገበ  ስኬት ነው።

በውጭና የአገር ድህንነት ፖሊሲ መጸሃፍ ላይ ኢትዮጵያ ፈጣን ልማት ማረጋገጥ ካለባት ያላትን የተፈጥሮ ሐብቷን በአግባቡ መጠቀምና መንከባከብ መቻል እንዳለባት ያስገነዝባል። ይህን መሰረት  በማድረግም መንግስት አገራችን ያላትን ሊለማ የሚችል መሬትና በቀላሉ ሊሰለጥን የሚችል ወጣት ሃይል እንዲሁም አነስተኛ ካፒታል  በማቀናጀት ህብረተሰቡን  በማስተባበር መስራት በመቻሏ ውጤታማ መሆን ችላለች። በዚህም ሳቢያ የሚሊዮኖች ህይወት ተለውጧል። አሁንም ሚሊዮኖች ከድህነት ጠለል በታች እንደሆኑ ግን መዘንጋት አይገባም።

ኢትዮጵያ በፖለቲካው ረገድ በአፍሪካ መሪነት ሚና እየተጫወተች እንደሆነች ሁሉ በኢኮኖሚውም የቀጠናውን አገሮች ጥቅም ለማስተሳሰር የሚያስችሉ በርካታ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን  በመገንባት ላይ ነች።  ለአብነት ትላልቅ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ  ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠቃሾች ናቸው። ከዛሬ 27 ዓመታት በፊት ከ350 ሜጋ ዋት እጅግም ያልዘለለ የነበረው የአገራችን  የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት አሁን ላይ ከአራት ሺህ ሶስት መቶ ሜጋ ዋት  በላይ ደርሷል። በቅርቡም ይህ አሃዝ ከ11 ሺህ ሜጋ ዋት  እንደሚበልጥ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻልባቸው ፕሮጀክቶች ግንባታ አፈጻጸም በመፋጠን ላይ ነው።

ኢትዮጵያ የአካባቢውን አገሮች በኢኮኖሚ እንዲተሳሰሩ ከምታደርጋቸው ጥረቶች መካከል የኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶችን ለአብነት አነሳሁ እንጂ በባቡር ሃዲድ ዝርጋታ፣ በትላልቅ የአስፋልት መንገድ ግንባታ፣ በአየር ትራንፖርት ማስፋፋት እያከናወነቻቸው ያሉ ፕሮጀክቶችም የአካባቢውን  አገሮች ህዝቦች  ተጠቃሚ  እየሆኑ ናቸው። ቀጠናውንም ሆነ አህጉሩን በኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስተሳሰርም ሆነ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ  እንደኢትዮጵያ ያለ ጥረት ያደረገ አንድም አገር የለም።

በተለያየ ጊዜ ወደ ሃላፊነት የመጡ የግብጽ መንግስታት ዓባይን የውስጥ ትኩሳት ማብረጃ  አድርገውት ነበር። የግብጽ ህዝብ  ውስጣዊ ችግሮቹን እንዳይመለከት የአባይ ጉዳይ ዋንኛ የማስፈራሪያ፤ በአጠቃላይ የአጀንዳ ማስቀየሻ በማድረግ  አርፈህ ካልተቀመጥክ  ኢትዮጵያ ዓባይን ልታስቀርብህ ትችላለች፤  በጥም ትሞታለህ  በማለት አባይን የፖለቲካ ትኩሳት ማብረጃ አድርገውት ነበር። በዚህም ሳቢያ  ግብጽ ህዝብ  የኢትዮጵያን ህዝብ ልማትና ዕድገት ለህልውናቸው አደገኛ እንደሆነ አድርገው እንዲረዱትና በመልካም እንዳይመለከቱት አድርገዋቸው ኖረዋል።

አሁን ላይ  እውነታው ገሃድ ወጥቷል። ማንም ኢትዮጵያን ማስቆም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሳለች። የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት አብሮ የመልማትና አብሮ የማደግ ዕቅድ የበርካታ ግብጻዊያንን ቀልብ ጭምር  መግዛት ችሏል።   የኢፌዴሪ መንግስት  ዕቅዶች  የአካባቢውን አገሮች  ዘላቂ ሰላም የሚያረጋግጡ ፍትሃዊ  ተጠቃሚነትና የሚያሰፍኑ  በመሆናቸው  ማንም ምክንያታዊና  ቅን ልቦና ያለውን ሰው ሊያሳምኑ የሚችሉ ናቸው።

አባይን በተመለከተ የኢትዮጵያ አቋም ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በሁሉም የተፋሰሱ አገራት መካከል ማረጋገጥ የሚል እንጂ  ብቻዬን ልጠቀም የሚል አይደለም።  ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት  ወጪው ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያዊያኖች የሚሸፈን ይሁን እንጂ ለአፍሪካ ቀንድ በተለይ ለታችኛው የተፋሰስ አገራት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች የሚያስገኝ ፕሮጀክት  ነው። ይህ አገራችን  ተጠቅሞ የመጠቀም መርህ በሁሉም መስፈርት ተመራጭነት ያለው ፍትሃዊ መርህ ነው። የአባይ ተፋሰስ 10 አገራትን የሚያካልል ቢሆንም  እስካሁን ባለው ሁኔታ አንድም አገር በተፋሰሱ አገራት መካከል የጋራ  ተጠቃሚነትን የሚያሰፍን  ፕሮጀክት ለመገንባት የሞከረ የለም።

የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች  ሁሉ የጎረቤት አገራት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያራግጡ እንጂ ኢትዮጵያን ጠቅመው ሌላውን የሚጎዱ አይደሉም። በአካባቢው አገሮች ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚቻለው  የአንዱ ዕድገት በሌላው ጉዳት ወይም ኪሳራ ላይ የተመሰረተ  ካልሆነ ብቻ ነው። ለዚህም ነው፣ የኢትዮጵያ መንግስት የሚከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ዋንኛ መሰረቱ የህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሆን የተደረገው። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሁሉም የጎረቤት አገራት ከኢትዮጵያ ዕድገት ተጠቃሚ ሆነዋል። ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የጎረቤት አገራት ዜጎች በአገራችን በስደት ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለእነዚህ ስደተኞች ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ ያላቸውን በማካፈል  ላይ ናቸው።

አሁን ላይ የአገራችን ኢኮኖሚ በፍጥነት በማደግ ላይ ነው።  ይህን ዕድገት ለማስቀጠል  ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ይፈልጋል። በመሆኑም መንግስት ከፍተኛ የሃይል ማመንጫዎችን  በመገንባት የሃይል ፍላጎታችንን  በማሟላት እንዲሁም ለአካባቢው አገሮች በተመጣጣኝ ዋጋ በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ  ለማግኘት  የሚያስችሉ  ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ነው። መንግስት በመጀመሪያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድን የያዘውን የአገሪቱን የሃይል አቅርቦት ወደ የ10ሺህ ሜጋ ዋት ለማሳደግ  የያዘው እቅድ የጊዜ መጓተት ቢታይበትም ማሳካት ግን ተችሏል።  ይህ እጅግ የተለጠጠ ዕቅድ በታዳጊ አገር ይቅርና በስልጣኔ ገፍተዋል በሚሉ አገሮች  በአምስት ዓመት መተግበር ከባድ ቢሆንም አገራችን ግን እውን አድርጋዋለች።

በተመሳሳይ በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድም የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም ማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ ነው። በዚህም መሰረት በ2012 ላይ የአገሪቱን  የሃይል አቅርቦቱን ወደ 17 ሺህ ሜጋ ዋት ለማድረስ መንግስት ጠንክሮ በመሰራት ላይ ይገኛል። ይህን ዕቅድ እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ  እንደቀድሞው ሁሉ ያላሰለሰ ጥረቱን ማድረግ ይጠበቅበታል። የአገራችንን ህዳሴ እውን የሚሆነው በሁላችንም ጥረት በመሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ  በተቻለው  አቅም ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል። የአገራችን ህዳሴ  በአንድ ወገን ጥረት ብቻ ሊሳካ አይችልም።    

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy