Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህዝባዊነትን የሰነቁ ተልዕኮዎች

0 298

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህዝባዊነትን የሰነቁ ተልዕኮዎች

                                                           ደስታ ኃይሉ

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ህዝባዊ ተልዕኮዎችን ያሉት ሃይል ነው። ሰራዊታችን በአገር ውስጥ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ፕሮጀክቶችን ከጠላት በመጠበቅ፣ ዜጎች ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲደርስባቸው ህይወቱን ጭምር መስዋዕት እያደረገ የሚታደግ፣ ከተሰጠው አገራዊና ህዝባዊ ግዳጅ ባሻገር በልማቱ መስክም እንደ ማንኛውም ዜጋ ከደመወዙ በማዋጣትና አቅመ ደካማዎችን በመደገፍ በርካታ ተግባሮችን በመወጣት ላይ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪ አገርን በሚጠቅሙ የቴክኖሎጂ ልማት ሽግግሮች ውስጥ ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ የሚገኝ ነው። ሰራዊታችን ከራሱ አልፎ በሌሎች አገሮች ውስጥ በህዝባዊ ወገንተኝነት ባህሪው ሰላምና መረጋጋትን ተልዕኮዎች ላይ በመሳተፍ አኩሪ ግዳጅ የፈፀመና በመፈፀም ላይ የሚገኝም ነው። ተልዕኮዎቹ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ህዝባዊነትን የሰነቁ ናቸው።

የአንድ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚቋቋመው ሀገሪቱን ሉዓላዊ አንድነት ከወራሪዎች ለመከላከል እንዲሁም የተቋቋመበትን ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ከማንኛውም አደጋ ለመጠበቅ ነው። ከዚህ አጠቃላይ ድምዳሜ በመነሳት የአፌዴሪ መከላከያ ሠራዊትን ተልዕኮ ስንመለከተው፤ ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን ከማንኛውም የውስጥና የውጭ ፀረ-ሰላም ኃይሎችና አሸባሪዎች የመከላከል ተልዕኮን ያነገበ ሆኖ እናገኘዋለን። በሀገሮች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በሠላማዊና በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ እገዛ  ማድረግም የተልዕኮው አካል ነው።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት እንደ አንድ ሀገር ሰራዊት በተሰጠው ተልዕኮ መሰረት የሚያከናውናቸው ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው፤ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሰላምና ለልማት መሆኑ ግንዘቤ ሊያዝ የሚገባ ይመስለኛል። ምክንያቱም ሰራዊቱ የተደራጀው ሀገሪቱ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ በመሆኑ ነው። የየትኛውም ሀገር መከላከያ ሰራዊት የተደራጀበት ሥርዓት ነፀብራቅ እንደመሆኑ መጠን፤ ሰራዊታችንም በሀገራችን የተመሰረተው ፌዴራላዊ ሥርዓት ፍላጎቶች ነፀብራቅ መሆኑ አያጠያይቅም። በዚህ መሰረትም በህዝቦች መፈቃቀድ እውን የሆነው ፌዴራላዊ ስርዓት ድህነትን በጠላትነት ፈርጆ በመንቀሳቀስ የፀረ-ድህነት ትግሉን እያጧጧፈ ነው። ሰራዊቱም በዚህ ጥረት ውስጥ ለሀገርና ለከባቢው ሀገሮች የሰላምና የልማት ትሩፋቶች ዕውን መሆን እንዲተጋ ተደርጓል።

እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በአዲስ መልክ ከተደራጀበት 1988 ዓ.ም ጀምሮ የሀገሪቱን ሰላም ለማረጋገጥና አሁን የሚገኝበት አስተማማኝ ቁመና ላይ ለመድረስ በርካታ መሰናክሎችን በፅናት፣ ህዝባዊነትን ምርኩዝ በማድረግና በጀግንነት ተወጥቷቸዋል።

መሠረቱን የሀገርን ሰላም በማስከበር ስራ ላይ ያፀናው መከላከያ ሰራዊታችን ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ  ስርዓቱን የመጠበቅ ተልዕኮን ያነገበ በመሆኑ፤ የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት በአስተማማኝ ሁኔታ የማረጋገጥ ታላቅ ሀገራዊ ግዳጅን ያማከለና ብሔራዊ ተዋፅኦ ያለው ስለሆነ ሰላምን ማረጋገጥ ችሏል።

ሠራዊቱ በሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛል።ለአብነት ያህል የመከላከያ መሠረተ- ልማት ዘርፍ የተቋሙን የልማት ስራዎች ከመስራት በዘለለ፤ እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ቦታዎች ላይ ለህዝቡ ወሣኝ የሆኑ የመንገድ ፣የድልድይ፣የመስኖ ልማት …ወዘተ ቁልፍ ስራዎችን እያከናወነ ነው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝም በብረታ ብረትና ኢንዱስትሪ ኮርፖርሬሽን ውስጥ የሚገኙ የሠራዊቱ አባላት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ኮርፖሬሽኑ የወሰዳቸውን የሜካኒካል ስራዎች ከውጭ እንዳይገቡና ሀገር ውስጥ እንዲመረቱ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ወጪን የማዳን ተግባራትን ገባራዊ እያደረጉ ነው፡፡

የኮርፕሬሽኑ ሠራዊት አባላት የትራንስፖርት እጥረትን ለመቅረፍ የከተማ አውቶብሶችንና ሌሎች ተሽከርካሪዎችን ሀገር ውስጥ በመገጣጠም እንዲሁም የሀገሪቱ ልማት ወሣኝ የሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳይቆራረጥ ከፍተኛ ሃይል መሸከም የሚችሉ ትሪንስፎርመሮችን በመስራት..ወዘተ ተግባራትን በማከናወን የልማት አጋርነታቸውን በማረጋገጥ ላይ ይገኛሉ፡፡

እነዚህ አብነታዊ ሃቆች የሚያመላክቱት ሠራዊታችን በመንግስት የተመደበለትን በጀት አብቃቅቶ ከመጠቀም ባሻገር በሀገራዊ ልማት ውስጥ እጁን በማስገባት የውጭ ምንዛሪን በማዳን በኢኮኖሚያዊ እመርታችን ላይ ጉልህ አሻራውን እያሳረፈ መሆኑን ነው፡፡

የሠራዊታችን ልማታዊ ኃይልነት በዚህ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ቀደም ሲል ከተጠቀሱት አብነቶች ባሻገር በየተሰማራበት ቦታ በጉልበቱ፣ በገንዘቡ፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና በሌሎች ዘረፎች የልማት አጋርነቱን በተግባር በማረጋገጥ ላይ ይገኛል፡፡ ሠራዊቱ ለተለያዩ የልማት ስራዎች ከደመወዙ በማዋጣት ከሚያደርገው እገዛ ባሻገር፣ በተሰማራባቸው አካባቢዎች ጊዜውንና ጉልበቱን መስዋዕት በማድረግ የህብረተሰቡን ችግሮች በሚፈቱ ተግባራት ላይ በንቃት እየተሳተፈ ነው፡፡

በሀገሪቱ ውስጥ ተሰማርቶ በሚገኝባቸው የግዳጅ ቀጠናዎች ሁሉ ለአቅም ደካማ አባወራዎችና አማወራዎች ድጋፍ የመስጠት ስራዎችንም አከናውኗል፤ በማከናወን ላይም ይገኛል፡፡ ማሳቸው ላይ ሰብሎችን በመዝራት በማረም በማጨድና በመሰብሰብ ህዝባዊነቱንና የልማት አጋርነቱን እያረጋገጠ ነው፡፡

የአርሶ አደሩ ምርት በፍጥነት ለገበያ እንዲደርስ ለማስቻልም የትራንስፖርት መንገድ በሌላቸው ቦታዎች ከየአካባቢው ህብረተሰብ ጋር እየተቀናጀ በመንገድ ስራ ላይ በንቃት ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በአንድ እጁ ህገ-መንግስታዊ ተልዕኮውን የሚወጣበት በሌላኛው እጁ ደግሞ ልማትን የሚያከናውንባቸውን ድርብ መሣሪያዎች ይዞ ምንጊዜም ከራሱ በፊት ለህዝብና ለሀገር የቆመው ሠራዊታችን ህዝባዊ ልማታዊነቱ ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም። ሠራዊቱ ከህብረተሰቡ ጋር አብሮ ስለሚኖርና ችግሩንም ስለሚገነዘብ የሚመደብለትን በጀት በማብቃቃት ከደመወዙ እያዋጣ ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ኬላዎችን፣ መንገዶችን…ወዘተ በመገንባት እንዲሁም የውስጥ ቁሳቁሶቻቸው እንዲሟላ በማድረግ ለየአካባቢው ህዝብ አስረክቧል፡፡

የአካባቢን ስነ ምህዳር በመጠበቅ ረገድም ከህብረተሰቡ ጋር በመሰለፍ ችግኞችን ተክሏል፣ እንዲፀድቁም በመንከባከብ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም መከላከያ ሠራዊታችን ተልዕኮውን በሚወጣባቸው አካባቢዎች በራሱ የውስጥ አቅም፣ ጥረትና ተነሳሽነት ከሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች በተጓዳኝ ምግባረ ሰናይ ተግባራትንም ያከናውናል፡፡

በመሆኑም በተለያዩ የሠራዊቱ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ የሠራዊት አባላት ከደመወዛቸው ተቆራጭ እያደረጉ በኤች-አይ-ቪ/ኤድስ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን እንደ ወላጅ አባት ሆነው ያስተምራሉ፤ ይደግፋሉ፡፡ በሀገራችን ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱት ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በህዝብ በእንስሳትና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱም ሠራዊታችን ጉልህ አስዋፅአ አበርክቷል፡፡

ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በደረሰባቸው አካባቢዎች ሠራዊታችን በእግረኛ፣ በኮማንዶና በአየርሃይል ቀድሞ በመድረስ የከፋ ጥፋት እንዳይከሰት በማድረግ የህዝቡን ህይወትና ንብረት በመታደግ ህዝባዊነቱንና የልማት ደጋፊነቱን በማያሻማ መልኩ አረጋግጧል፡፡

ከልማቱ በመለስም በተፈጥሮ የአየር ንብረት መዛባት ምክንያት በተከሰቱት የድርቅ አደጋዎች ሠራዊቱ ከደመወዙ ተቆራጭ በማድረግ ወገኑን ከመደገፉ ባሻገር ለተጐጂው የህብረተሰብ ክፍል ዕርዳታው እንዲደርስለት በተሽከርካሪዎቹ በማጓጓዝ ብሎም ዕርዳታው የሚፈለገው ቦታ እንዲደርስ እጀባ በማድረግ አኩሪ ተግባራትን ፈፅሟል፡፡

የአገራችን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አንድ አካል የሆነውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለመገንባት መላው የሠራዊታችን አባላትና ሲቪል ሰራተኞች የወር ደመወዘቸውን በዓመት ክፍያ በመፈፀም ቦንድ ገዝተዋል፤ እየገዙም ነው። ይህም ሰራዊቱ የልማቱ ጠባቂ ብቻ ሣይሆን አልሚ ጭምር መሆኑን የሚያመላክት ነው። በአጠቃላይ የሰራዊቱ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ተልዕኮዎች ህዝባዊነትን የሰነቁ መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy