Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መብት ተጋፊ መብት ጠያቂዎች

0 260

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መብት ተጋፊ መብት ጠያቂዎች

አለማየሁ አሰጋ

ኢትዮጵያ ውስጥ የሃይል የአደባባይ ተቃውሞና አድማ የዘውትር ክስተት መሆን ከጀመረ ሁለት ዓመት ከመንፈቅ እድሜ አስቆጥሯል በ2008 ዓ/ም ህዳር ወር ነበር የተጀመረው። ይህ የሃይል የአደባባይ ተቃውሞና አድማ የጀመረው በኦሮሚያ ምዕራብ ሸዋ ዞን ጊንጪ ከተማ ነበር። የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት የትምህርት ቤት መሬት ለኢንቨስትመንት በሚል ሰበብ ለባለ ሃብት ለመስጠት መለካት ሲጀምር ይህን በመቃወም አደባባይ በወጡ ወጣቶች ነበር ተቃውሞው የተለኮሰው። “ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው” እንዲሉ በመልካም አስተዳደርና በፍትህ እጦት የተንገላታ፣ በመሬት ዘረፋ የተንገበገበ፣ ለልማት በሚል ሽፋን መሬቱ ተቀምቶ ከነቤተሰቡ የደሃ ደሃ እንዲሆን የተደረገ ወዘተ በመላ ኦሮሚያ ከተሞች የሚኖረው ህዝብ የተለኮሰውን የአደባባይ ተቃውሞ እየተቀባበለ አቀጣጠለው።

በ2006 ዓ/ም የአዲስ አበባና በኦሮሚያ የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ረቂቅ ሰነድን በመቃወም ተነስቶ የነበረው ተቃውሞም አገርሸቶ የኦሮሚያ ተቃውሞ ተስፋፋ። “የተቀናጀ ማስተር ፕላን” የተሰኘውን ሰነድ መነሻ በማድረግ ተነስቶ የነበረው ተቃውሞ በአጋጣሚ ከበረደ በኋላ፣ የክልሉ መንግስት በጉዳዩ ላይ ምንም ሳይሰራ ተኝቶ በመቆየቱ ነበር አንዱ የተቃውሞው ምክንያት እንዲሆን ያደረገው። በአዲስ አበባ የኦሮሞ አርሶ አደሮች መኖሪያ በነበሩ አካባቢዎች እንዲሁም በአጎራባች የኦሮሚያ ከተሞች የተካሄደው ብዙዎችን የደሃ ደሃ ያደረገ ምህረት የለሽ የመሬት ወረራና ዘረፋ፣ ህዝቡ የተቀናጀ ማስተር ፕላኑን የመሬት ዘረፋ ሰነድ አድርጎ እንዲወስድ አድርጎታል። ከዚህ አኳያ ሲታይ ስጋቱን ተገቢ ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል።

በክልሉ የተካሄደው የመሬት ዘረፋ አደህይቷቸው እንጀራ ፍለጋ ከነልጆቻቸው የከተማ ተንከራታች የሆኑ አርሶ አደሮች፣ ከሌሎች ወደከተማ የሚፈልሱ ወጣቶችና ነባር የከተሞች ስራ አጦች ጋር ተዳምሮ የኦሮሚያ ከተሞች የብሶተኞች መኖሪያ እንዲሆን ያደረገበት ሁኔታ ነበር። እርግጥ ይህ የኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች ከተሞች መሰረታዊ ችግር ነው።

በአማራ ክልልም በተለይ በሰሜን ጎንደር አካባቢ የቅማንት የማንነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን ተከትሎ እንዲሁም “የማንነት ጥያቄ አለን” በሚሉ ወገኖች ገፊነት ሁከት ተለኩሶ ነበር። እነዚህ ጉዳዮች ህገመንግስታዊ ምላሽ ማግኘት ይችሉ የነበረ ቢሆንም፣ በአመራር ድክመት በወቅቱ ተገቢውን ምላሽ ሳያገኙ በመቅረታቸው የሁከት ሰበብ እንዲሆኑ አድርጓል። ይህ ሰበብ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት፣ የኪራይ ሰብሳቢነት መግነን፣ ከአስከፊ የከተሞች ስራ አጥነት ጋር ተያይዞ ሁከት ለኳሽ ምክንያት ለመሆን በቅቷል።

በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልልም የነበረው ሁኔታ ተመሳሳይ ነበር። በተለይ በኮንሶ የማንነት ጥያቄን የተላበሱ ተደጋጋሚ ሁከቶች ሲያጋጥሙ ቆይተዋል። በዲላም የፍርድ ቤት ውሳኔን መነሻ በማድረግ ማንነትን መሰረት ያደረገ ግጭት ተቀስቅሶ እንደነበረ ይታወሳል።

በእነዚህ የሃይል ተቃውሞዎች በተፈጠረ ግጭት የበርካታ ዜጎች ህይወት ጠፍቷል፤ በተቃውሞ ተሳታፊዎችም በጸጥታ አስከባሪዎችም ወገን። ንብረት ወድሟል። ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። በ2008 ዓ/ም ማገባደጃ ላይ በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞን በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵየውያን በሃይል ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ መደረጉ ይታወሳል።

እነዚህ የሃይል ተቃውሞዎች በተለይ በኦሮሚያ ክልል እየተባባሱና አጋጣሚዎችን እየጠበቁ በአዲስ መልክ እየፈነዱ ሁኔታው መጨበጫ አጣ። በተለይ በ2009 ዓ/ም መግቢያ ላይ በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዲ ይከበር የነበረው የኢሬቻ በአል ላይ የተፈጠረው ሁኔታ በድንገት በመላ ኦሮሚያ የሃይል ተቃውሞ እንዲቀጣጠል አድርጓል። ይህን ተከትሉ ችግሩን በተለመደው ህግ የማስከበር ርምጃ መቆጣጠር የማይቻልበት ሁኔታ በመፈጠሩ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ታውጆ ለወራት ሁከቶች ጋብ ብለው ቆይተዋል።

ይሁን እንጂ በ2009 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጁ ስራ ላይ እያለ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት ተቀስቅሶ ነበር። የተቀረው የሃገሪቱ አካባቢ በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ መረጋጋት ቢታይም፣ የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግን የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጁን አሸንፈው ለበርካታ ዜጎች ህይወት መጥፋት፣ አካል መጉደል፣ መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ግጭቶች ሲካሄድባቸው ነበር። ይህ ግጭት እየተባባሰ መጥቶ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ ከወራት በኋላ በያዝነው ዓመት መግቢያ ላይ በሃገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

ይህ ሁኔታ በተለይ በኦሮሚያ በኩል ከፍተኛ የህዝብ ቅሬታ ፈጥሯል። “መንግስት በቂ ጥበቃ ባለማድረጉ የተፈጠረ ችግር ነው” በሚል ኦሮሚያ ውስጥ በተለይ በፌደራል መንግስቱ ላይ መረር ያለ የተቃውሞና እምነት የማጣት ስሜት ተፈጥሯል። ይህ ስሜት አሁንም አልበረደም። በአጠቃላይ በክልሉ ህዝቡ በፌደራል መንግስቱ ላይ ያለው የህዝብ እምነት እጅግ ሳስቷል ማለት ይቻላል።

በኦሮሚያ የተሃድሶው አመራር የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ባደረገው ጥረትና የህዝቡን ቅሬታ ማዳመጥ በመጀመሩ በክልሉ መንግስትና በህዝቡ መሃከል ቀደም ሲል ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የመግባባት መነፈስ ቢፈጠርም፣ የሃይል ተቃውምዎችና አድማዎች ግን መቆም አልቻሉም። የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው እንደተነሳ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች እለታዊ የገቢ ግምት ይፋ መደረጉን ተከትሎ አድማዎች ተካሂደዋል። አድማውን ጣሱ በተባሉና በአድማው መሪዎች መሃከል ግጭት ተፈጥሯል፤ ንብረት ወድሟል።

በአማራ ክልልም የእግር ኳስ ጫወታን መነሻ በማድረግ በወልዲያ በተፈጠረ ግጭት የሰው ህይወት መጥፋቱን መነሻ በማድረግ በወልዲያ፣ በቆቦና መርሳ ከተሞች ብሄራዊ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ተፈጽሟል።

ላለፉት ሁለት ተኩል ዓመታት ያጋጠሙ የሃይል ተቃውሞዎችና አድማዎች ተገቢ መነሻ ምክንያት (የመልካም አስተዳደርና የፍትህ መጓደል፣ የኪራይ ሰብሳቢነት በተለይ የመሬት ዘረፋ መስፋፋት፣ የወጣቶች ስራ አጥነት . . .) የነበራቸው መሆኑ ቢታመንም፣ ተቃውሞውን ለራሳቸው ዓላማ ለመጠቀም የጠለፉ ቡድኖች መኖራቸውንም የሚያሳዩ አስረጂዎች አሉ።

ለምሳሌ የ2009 የኢሬቻ በአል ላይ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በዓሉን ለመታደም በስፍራው የተገኙ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች ፍላጎት አልነበረም። በኦሮሞ ባህል መሰረት የሰላምና የእርቅ ሁነት ተደርጎ የሚሰደውን የኢሬቻ  በአል የተቃውሞ መግለጫ ለማደረግ ተልእኮ ይዘው የተቀላቀሉና ተቃውሞውን ለማባባስ እንደ ሰበብ ሊያግዝ የሚችል የሰው ህይወት መጥፋት አደጋ እንዲፈጠር ያሰቡ ቡድኖች የነበሩ መሆኑን የሚጠቁሙ ሁኔታዎች አሉ። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በማያሳይ አኳኋን ሰዎች ላይ በሂሊኮብተር ጥቃት የተፈጸመ አስመስለው በአሉን ለማድመቅ ያንዣበቡ የነበሩ ሄሊኮፕተሮችን ምስል በማህበራዊ ሚዲያ በማሰራጨት፣ የሟቾቹን ቁጥር በአስር እጥፍ በማጋነን በመገናኛ ብዙሃን በማስነገር የተካሄደው ቅስቀሳ ለዚህ አስረጂ ነው።

የነጋዴዎች የዕለት ገቢ ግምትን መነሻ በማድረግ የተጠራው አድማም የህዝቡን ፍላጎት ያገናዘበና ከህዝቡ የመነጨ አልነበረም። ህዝቡ በተለይ ወጣቶች የሚያነሱት የልማትና የስራ እድል ፈጠራ ጥያቄዎች ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉት መንግስት ተገቢ ግብር ሲሰበስብ መሆኑ እየታወቀ፣ ግብር በሃገሪቱ የተፈጠረውን ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ሚዛን ማስተካከያ መሳሪያ መሆኑ እየታወቀ፣ የግብር ትመና መነሻ የሆነው የገቢ ግምት መሰራቱን ህዝብ ሊቃወም አይችልም። ነጋዴው በዚህ ጉዳይ ላይ ቅሬታ ቢኖረው እንኳን ይህ የሚፈታበት ህጋዊ ስርአት ስለነበረ፣ ወጣቱ ቅሬታ ያላቸውን ነጋዴዎች መብት ለማስከበር መንገድ የመዝጋትና ሱቆች እንዳይከፈቱ የመከለከል አድማ እንዲካሄድ ማደረግ አይጠበቅበትም ነበር።

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የእግር ኳስ ጫወታን መነሻ አድርጎ ቂም በመያዝ በወልዲያ፣ በቆቦና መርሳ ከተሞች ማንነት ላይ የተመሰረተ ጥቃት መፈጸሙም የህዝቡ ፍላጎት አልነበረም።

ሰሞኑን በኦሮሚያ የተጠራው መንገድ የመዝጋትና የንግድ እንቅስቃሴን የማቋረጥ አድማ ድርጊትም የህዝብ ፍላጎት መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ ነገር የለውም። አድማው እስረኞች እንዲፈቱ ለመጠየቅ መሆኑ ነው የተነገረው። ይሁን እንጂ እስረኞች እየተፈቱ ባለበት ወቅት የተካሄደ በመሆኑ ይህን የሚያውቀው የኦሮሞ ህዝብና ወጣት በተለይ ደሃው የህብረተሰብ ክፍል ላይ ጉዳት የሚያስከትለውን አድማ ለማካሄድ የሚያስስገድድው አንዳችም ምድራዊ ምክንያት አልነበረም።

አድማዎቹ ሱቃቸውን በዘጉ ሁሉም ነጋዴዎችና የትራንስፖርት አገልግሎት ባቋረጡ ተሽከረካሪዎች ባለቤቶችና አሽከርካሪዎች ፍላጎት የተካሄዱም አይደሉም። አድማውን የሚደግፉ ነጋዴዎችና ባለአሽከርካሪዎች መኖራቸው ባይካድም፣ እጅግ አብዛኞቹ የአድማው ተሳታፊ የሆኑት አድማውን በሚመሩ መደበኛ ባልሆነ ሁኔታ ወይም በህቡዕ የተደራጁ ወጣቶች ተገደው ነው። አድማውን የሚመሩ ወጣቶች ተባባሪ ለመሆን ያልፈቀዱት ላይ የሃይል እርምጃ ስለሚወስዱ በመፍራት ነው አድማውን የተቀላቀሉት። ይህ የዜጎችን መብት ያፈነና ድሆችን ጾም ያሳደረ አድማ የህዝብ ጥያቄም አይደለም።

አነዚህ ከላይ ለማሳያነት ያነሳኋቸው እውነታዎች በሃገሪቱ እየተቀሰቀሱ ያሉ የሃይል ተቃውሞዎቸ ውስጥ የራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸውና ሃገሪቱን ማተራመስ የሚፈልጉ ቡድኖች እጅ ያለበት መሆኑንም ያመለክታሉ። እናም በማህበራዊ ሚዲያ በሚተላለፍ መልዕክት አድማ የሚመሩና ሁከት የሚቀሰቅሱ ወጣቶች  ወደእርምጃ ከመግባታቸው በፊት የቀረበላቸው ትእዛዝ የህዝቡ ፍላጎት መሆኑን አለመሆኑን ሊያረጋግጡ ይገባል። ጥያቄዎች አድማ ማደረግ ሳያሰፈልግ ጫና ማሳደር በሚያስችሉ ሌሎች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገዶች ሊቀርቡ እንደሚችሉም ማስታወስ ይገባቸዋል። አድማ ማደረግ ቢያስፈልጋቸው እንኳን የአድማው ተሳታፊ ለመሆን የፈቀዱትን እንጂ ከዚህ ውጭ መሆን የሚፈልጉትን ማስገደድ አይኖርባቸውም። ይህ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው። መብትን ለማስከበር የሚወሰድ እርምጃ በምንም መልኩ የሌሎችን መብት ማፈን እንደሌለበት መታወቅ አለበት። የራስ ፍላጎትን ለማስጠበቅ የሌሎችን መብት መጋፋት የአምባገነኖች ባህሪ ነው። እናም መብት ተጋፊ መብት ጠያቂዎች አትሁኑ።     

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy