Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መጎልበት ያለበት ባህል

0 261

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መጎልበት ያለበት ባህል

ዳዊት ምትኩ

በአገራችን የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ውስጥ የተጀመረው የመነጋገር ባህል ይበልጥ መጎልበት ይኖርበታል። በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እየተካሄደ ያለው የመወያየትና የመደራደር ባህል በራሱ የአገራችን የፖለቲካ ምህዳር እየሰፋ መሄዱን አንዱ ማሳያ ነው። ፓርቲዎች አገራዊ ጥቅምን ብቻ መሰረት አድርገው የሚወያዩ ከሆነ፤ የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋ፣ አሳታፊነት እየጎለበተና ዴሞክራሲው እያበበ እንዲሄድ የሚያደርግ ነው። በፓርቲዎች ንግግር ላይ ስሜታዊነት ከስሞ ቀዳሚ ቦታውን የአገርና የህዝብ ጥቅም ከያዙ፤ የዴሞክራሲያዊ አሰራራችን መገለጫ ይሆናሉ።

ዴሞክራሲያዊ ባህል መጎልበት አለበት። ባለፉት ጊዜያት የፖለቲካ ፖርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ይህን ዕውነታ ተረድተው የዴሞክራሲን ምንነት በውል ተረድተው በምርጫ በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ የነበራቸው ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

ዳሩ ግን እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ዋነኛ ጉዳይ፤ የሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ 26 ዓመት ብቻ የስቆጠረ ለጋ በመሆኑ፣ የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ሂደቱ ስር እንዲሰድ እንከን አልባ ርብርብ ተደርጓል ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም መሰረታዊ የዴሞክራሲ ተግባራትን በማከናወንና ዴሞክራሲው እንዲጎለብት ረጅም ርቀት መጓዝ ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፋት ዓመታት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ስርዓትን በሂደት በመገንባት ድህነትን ለማሸነፍ ባደረግነው ርብርብ አንፀባራቂ ሊባል የሚችል ውጤት ተገኝቷል፡፡ ሆኖም ልዩነታችን አንድነታችን ሆኖ ካልቀጠለ፤ በመነቋቆርና በመነካከስ ከቀጠልን እንደዚህ ቀደሙ ለዘመናት ወደ መጣንበት የድህነት አረንቋላ መዘፈቃችን አይቀርም፡፡ እናም ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ወሳኝ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡

እርግጥ የሀገራችን የህዳሴ ጉዞ ሊረጋገጥ የሚችለው በመጎልበት ላይ የሚገኘው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታችን ያለ አንዳች እንቅፋት ሳይሸራረፍ ሲቀጥል ነው፡፡ እናም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታችን መጠናከርና ማበብ ጤናማ እና ገንቢ ሚና የሚጫወቱ የፖለቲካ ፖርቲዎች መኖር አለባቸው፡፡

መንግስት በአገሪቱ ዴሞክራሲን የሚያጠናክሩ ፖርቲዎች መኖር እንዳለባቸው ያምናል፡፡ ተደጋግሞ እንደሚነገረውም የመንግስት ፍላጐት የሀገራችን የመድብለ ፖርቲ ስርዓት ዳብሮ እና ጐልብቶ ማየት የዘወትር ፍላጐቱ መሆኑ ነው፡፡ ሁሉንም የሀገራችንን ህዝቦች የሚወክሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምፃቸው እንዲሰማ ጥረት እያደረገ ነው፡፡

የሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ጤናማነቱ ተጠብቆ ሊጓዝ የሚችለው ጤናማ እና ገንቢ ሚና የሚጫወቱ የፖለቲካ ፖርቲዎች ተሳትፎ እየጐለበተ ሲመጣ ነው፡፡ በመሆኑም በተለይም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን በማብቃትና ከጅምላዊ አካሄድ በመታቀብ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ማበብ ሀገራዊ ግዴታ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡

አገራችን ለዴሞክራሲ ገና ጀማሪ በመሆኗ ስለ ዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳቦች የሚነሱ ጉዳዩች በሁሉም ወኖች በኩል ህፀፆችን መፍጠራቸው አይቀርም። በዚህም ግልፅነትና ተጠያቂነት ብሎም መቻቻልን የመሳሰሉ የዴሞክራሲ እሴቶችን በተገቢውና በፈጠነ ሁኔታ ገቢራዊ ማድረግ ያስቸግር ይሆናል። ፅንሰ ሃሳቦች አዲስ በመሆናቸውም በአስተማማኝ ሁኔታ ይተገበሩ ዘንድ ጊዜን ይጠይቃሉ። ብዥታምን ሊፈጥሩ ይችላሉ። ሆኖም ለተግባራዊነታቸው ከሂደት መማር ይቻላል።

በሌላ በኩልም ያለፉት ስርዓቶች በሀገራችን ህዝቦች መካከል ፈጥረውት ያለፉት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች በቀላሉ የሚሽሩ አይደሉም። ፀረ-ዴሞክራሲያዊ እሳቤዎችን በዴሞክራሲያዊነት ለመቀየርም አስተሳሰብንና ስለ ዴሞክራሲ ያለንን አመለካከት መለወጥ ይገባል። በህዝቦች ውስጥ ለዘመናት ሲፈጠሩ የነበሩትን የተዛቡ ግንኙነቶች በጥቂት ዓመታት ውስጥ መቀየርም አይቻልም።

እርግጥ ገዥው ፓርቲ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርጋቸው አበረታች ድርድሮች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ የተያዘው ቁርጠኝነት በሚፈለገው ፍጥነት መጎልበት ያለበት ይመስለኛል። ዴሞክራሲውን ለማስፋት በመንግስት በኩል የተያዘው ቁርጠኝነት ተጨባጭ መገለጫዎች ሊኖሩት ይገባል። ተቃዋሚዎችም ይህን ተስፋ በተሳሳተ መንገድ ተረድተው ወዳልተፈለገ እሰጥ አገባ ውስጥ እንዳይከታቸው ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ይመስለኛል።

እናም ከተቃዋሚዎቹ ጋር የሚካሄዱ ውይይቶችና ድርድሮች መነሻቸውና መድረሻቸው በግልፅ ተለይተው ሊገለፁና የጋራ ድምዳሜ ሊያዝባቸው ይገባል። ይህ ሲሆንም መንግስትና ገዥው ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማጎልበት ያላቸውን ቁርጠኝነት ይበልጥ በመግለፅ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ የሚችሉ ይመስለኛል።

በእኔ እምነት ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረገው ውይይትና ድርድር፤ ፓርቲዎቹ ከመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታው ጋር ተያይዞ መንግስት ያለበትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ህፀፆቹን በግልፅ እንዲያይ ያደርጉታል። መንግስትም አግባብና ትክክለኛነት ያላቸውን አስተያየቶች በመቀበል ለስራው እንደ አንድ ድጋፍ እንዲጠቀምባቸው የመነሻ ሃሳቦች ሊሆኑት ይችላሉ።

ይህ ሁኔታም በአንድ በኩል ዴሞክራሲውን ለማስፋትና የህዝቦችን ተደማጭነት ከፍ የሚያደርግ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሰሚነት ድምፅ እንዲጨምር ዕድል ይሰጣል። በፓርላማ ደረጃ የሚኖረው የአሳታፊነት ዴሞክራሲም ይጎለብታል።

ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረግ ውይይት ከላይ እንደጠቀስኩት ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ እንጂ፣ ስልጣንን ከመጋራት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም። ሊኖረውም አይገባም እላለሁ።

የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጊዜንና በእውቀት ላይ የተገነባ አስተሳሰብን ይጠይቃል። ይህ ሁኔታም ምናምባትም ችግሮችን በዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ ውስጥ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን ሊያሰናክል ይችላል።

እናም ዴሞክራሲው እንዲሰፋ እነዚህን ሁለት ተግዳሮቶች መፍታት ይገባል። ይህን ዕውን ለማድረግም የህዝቡ ወኪሎች የሆኑት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይገባል። የህዝብ ወኪል የሆነ ፓርቲ ምንግዜም ማሰብ ያለበት ህዝቡን ነው። ህዝቡን ወክሎ ሲወያይም ዴሞክራሲው እንዲጎለብት የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ነው።

በአሁኑ ወቅት አልፎ አልፎ ከግንዛቤ ማነስ የተነሳ ጥቃቅን ችግሮች ቢኖሩም ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች እያደረጉት ያለው ድርድር እንደ ዜጋ የሚያስመካ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ልዩነት ቢኖርም፣ የውይይቱ አውድ መፈጠሩ በራሱ ትልቅ ርምጃ ነው። ያም ሆኖ እንዲህ ዓይነቱ ዴሞክራሲን የማጎልበት የውይይት ባህል ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy