Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምክንያታዊ ህብረተሰብን ለመፍጠር…

0 269

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምክንያታዊ ህብረተሰብን ለመፍጠር…

                                                     ደስታ ኃይሉ

ውሰጣዊ ችግርን በተገቢው መንገድ መፍታት ከተቻለ፤ ውጫዊው ብዙም ጫና ሊያመጣ አይችልም። ውስጣዊ ችግርን ለመፍታት በመጀመሪያ በሁሉም ቦታዎች የህግ የበላይነት መረጋገጥ አለበት። የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጉዳይ የመንግስት ብቻ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። ዴሞክራሲን በምትከተል አገር ውስጥ ህግና ስርዓትን ማጠናከር የሁሉም ዜጋ ድርሻ ጭምር ነው።

በመሆኑም የእያንዳንዱን ዜጋ ለህግ የበላይነት የላቀ ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል። የህግ የበላይነት በየትኛውም ጊዜና ቦታ የበላይ መሆን አለበት። ለዚህም ህብረተሰቡ አጥፊዎችን ለህግ አጋልጦ መስጠት ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ህግና ስርዓትን ማስከበር አይቻልም።

ህብረተሰቡ ለዘመናት የቆዩ የአብሮነት እሴቶቹን ማስጠበቅ ይኖርበታል። ይህም ምክንያታዊ ህብረተሰብ ለመገንባት የሚያስችል ይሆናል። በአሁኑ ወቅት እንደሚታየው ልማትን እያወደሙ ልማትን መጠበቅ ተገቢና ትክክለኛ አሰራር ሊሆን አይችልም። ልማትን እየሻቱ መልሶ የለማን ነገር ማውደም የህግ የበላይነትን መፃረር ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ በህግ ካለተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም። የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ሥርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። የመኖር ዋስትና በሌለበት ሀገር ውስጥ ደግሞ ሰላምና መረጋጋት ይጠፋና እንደ ሰው ለመንቀሳቀስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ የሚደረስ ይደረሳል።

መንግስት ባለበት ሀገር ውስጥ ማንም ሰው ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየደረጋቸው ከመጣው መንገድ መውጣት የለበትም።

መንግስት መብትም፣ ኃላፊነትም ሆነ ግዴታ ያለበት አካል በመሆኑ በህጉ አግባብ መሰረት ተጠርጣሪዎችን ህግ ፊት በማቅረብ ተገቢውን ትምህርት የሚያገኙበትን ሁኔታ በመፍጠር የተጎጂዎችን እምባ ማበስ ይኖርበታል። ይህን ካላደረገ ህዝቡንም ይሁን በህዝቡ የተመሰረተውን ስርዓት በአግባቡ ሊጠብቅ አይችልም።

ይህ የመንግስት የህግን ልዕልና የማረጋገጥ እርምጃ በህዝቦች ደም ስልጣን ላይ ለመውጣት ለሚሹ አሸባሪዎች፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎችና ፅንፈኞች፤ እዚህ ሀገር ውስጥ እነርሱ የሚመኙት ዓይነት ምህዳርና ህዝብ አለመኖሩን እንዲገነዘቡ ያስችላል።

ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችም የዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዘቦች መቻቻልን መፍጠር የቻሉ እንዲሁም ዴሞክራሲያቸውን ስር እንዲሰድ ለማድረግ የህግ የበላይነትን የሚያፀና ሥርዓትን ዕውን በማድረግ ላይ የሚገኙ እንጂ፤ በደማቸው ፍላፃነትና በአጥንታቸው ወጋግራነት የገነቧት ሀገራቸው እነርሱ እንደሚመኙት ዓይነት በጩኸት፣ በህገ-ወጥነትና በሴራ የምትናጋ አለመሆኗን እንዲያውቁ ያደርጋል።

ከሁሉም በላይ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዝቦች ህገ-ወጦችን፣ አሸባሪዎችንና ሴረኞችን ሊፈጥሩ የሚችሉትን ችግሮች በሰከነና ብልሃት በተሞላበት ሁኔታ ፍትሐዊነትንና የህግ የበላይነትን እያረጋገጡ እንዲሁም ለሚፈፀምባቸው ማናቸውም የትንኮሳ ተግባራት ተገቢውን ምላሽ እየሰጡ ከተያያዙት ድህነትን ድል የመንሳት ትግል አንድም ስንዝር ቢሆን ፈቀቅ ሊሉ የሚያደርጋቸው አይደለም።

ኢትዮጵያ የጀመረችው የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አስተማማኝ ሠላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር የግድ ነው። ምክንያቱም አገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት የሞት ሽረት ያህል የህልውና ጉዳይ አድርጋ ስለያዘችው ነው።

ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት አኳያም መንግስት ረጅም ርቀት ተጉዞ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል። ዜጐች ለልማት መሠረት የሆኑ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች፣ የምግብ ዋስትና፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የመኖሪያና የማህበራዊ ዋስትና የማግኘት መብት እንዲኖራቸው ደንግጓል።

በደርግ ሥርዓት ወቅት ማንኛውም ዜጋ ተገፍፎ የነበረውን የግል ሃብት ባለቤት የመሆን መብት በመሠረቱ ተንዷል። ዛሬ ሁሉም ዜጋ የግል ንብረት ባለቤትነት መብቱ በህገ መንግሥቱ ተረጋግጦለታል።

የአገራችን ህገ መንግሥት የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት የማይሸጥ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ንብረት እንደሆነ በግልፅ አስፍሯል። ይህም በመሬት ስሪት ጉዳይ የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት በፅኑ መሠረት ላይ ለመጣል አስችሏል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ እንደሆነ ተደንግጓል። የኢትዮጵያ አርሶና አርብቶ አደሮች መሬትን በነፃ የማግኘት፣ በመሬቱ የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብታቸው ህገ መንግሥታዊ ዋስትና አለው። እነዚህ የተጠቃሚነት ሁኔታዎች ባሉበት አገር ውስጥ ልማትን መልሶ ማጥፋት የህግ የበላይነትን አለመቀበል ነው።

የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሁ ለይስሙላ የተደነገጉ አይደሉም። ዜጎች ሰዎች በመሆናቸው ሳቢያ የተጎናፀፏቸው መብቶች ናቸው። እናም ማንኛውም አካል የህግ የበላይነት እንዳይሸረሸር መፍቀድ ያለበት አይኖርበትም። እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ በሌላኛው እሳቤ የህግ የበላይነት ዕውን እንዳይሆን መፍቀድ በመሆኑ ነው።

የህግ የበላይነትን መፃረር ስርዓት አልበኝነትን የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር፤ ህጎች ለሁሉም ዜጎች እኩል እንዳይሰሩ ያደርጋል። ይህም ‘ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው’ የሚለውን ህገ መንግስታዊ መርህ ይጥሳል። እናም በየዩኒቨርስቲዎቹ ለሚፈጠሩት ሁከቶች የህግ የበላይነትን ማስከበር ቁልፍ ተግባር ሊሆን ይገባል።

የህግ የበላይነት ከሌለ ሰላም የሚባልን ነገር ማሰብ አይቻልም። ሰላም ከጠፋ ደግሞ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ ማሰብ አይቻልም። ፀረ-ልማትዊነትና ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ቦታውን ይረከባሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ እንደ እኛ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን የህልውናው ጉዳይ ላደረገ ሀገር አሜኬላ እሾህ መሆኑ አያጠያይቅም። እናም በቅርቡ አንድን ወገን በመለየት ልማትን የማቃጠል አካሄድ ፈፅሞ ተቀባየነት ሊኖረው አይገባም።

ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት የህግ የበላይነትን በሚገባ የሚያስከብር ነው። የህግ የበላይነትን ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውም ዜጋ ተጠያቂ ይሆናል። ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል እንደመሆኑ መጠን፤ በመረጃና በማስረጃ በተረጋገጠበት ጥፋት ልክ ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም። ይህ አሰራር በማንኛውም ዜጋ ወይም አካል ላይ ገቢራዊ የሚሆን ነው። በመሆኑም ከሰሞኑ የዜጎችን ንብረት ያወደሙ አካላት የህግ የበላይነት ሊፈፀምባቸው ይገባል። ይህ ካልሆነ ነገም አንዱ ተነስቶ በማን አለብኝነት ልማትን አለማውደሙን እርግጠኛ ለመሆን አይቻልም። እናም ከስሜት የነፃና ምክንያታዊ ህብረተሰብን ለመፍጠር በቅድሚያ በሁሉም ማዕቀፎች ውስጥ የህግ የበላይነት ሊከበር ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy