Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰላማችንን ከሚያናጋ ድርጊት እንቆጥብ!

0 301

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰላማችንን ከሚያናጋ ድርጊት እንቆጥብ!

ሰለሞን ሽፈራው

ይህ ፀሐፊ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙና ሰላም ለሀገራችንን ህዝቦች  ምን ማለት እንደሆነ የመረዳት ፈቃደኝነት ላላቸው ወጣት ዜጎች ሊጠቅም የሚችል የህይወት ልምድ እንዳለው ያምናል፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ፀሐፊው ‹‹የ1960ዎቹ ትውልድ›› በመባል ከሚታወቀው ኢትዮጵያዊ የህብረተሰብ ክፍል ለጥቆ የመጣው ሌላ አሳረኛ ትውልድ አባል እንደመሆኑ መጠን፤ በተለይም ደግሞ ደርግ ስልጣን ላይ የቆየባቸው 17 ዓመታት ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ምንኛ የጭንቅና የመከራ ዘመናት እንደነበሩ ያስታውሳልና ነው፡፡ ይልቁንም  በሰሜናዊው የሀገራችን ክፍል ተወልደን ላደግን ለዚያን ክፉ ዘመን ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በዚህ ዓለም ላይ ከአስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት የሚቀድም ለሰው ልጅ የሚያስፈልግ ነገር ሊኖር እንደማይችል አሳምረን እንገነዘብ ዘንድ የታሪክ አጋጣሚው አስገድዶናል፡፡ ስለዚህ እኔና የኔ ዘመን ትውልድ አባላት ያሳለፍነው የወጣትነት ዕድሜ ሰላምና መረጋጋት እጅጉን ብርቅ ነገር ተደርጎ የሚቆጠርበት ስለነበረም ነው የዕርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እየተማገድን ጎራ ለይተን የተገዳደልንበትን አሳዛኝ እውነታ ለመጋፈጥ ግድ የሆነብን፡፡

ከዚህ የተነሳም ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም ያለ ምንም ደም›› የሚል ሸጋ መፈክር እያሰማ ቀዳማዊ ሃ/ስላሴን ከዙፋናቸው አስወግዶ እራሱን በዘውዳዊው አገዛዝ ምትክ ወደ መንበረ ስልጣኑ ያመጣው የደርግ ወታደራዊ ስርዓት፤ ‹‹ህዝባዊ መንግስት ይመስረት›› የሚል ጥያቄ አንስተው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለማካሄድ የሞከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፤ በቀይ ሽብር የነፃ እርምጃው ጭፍጨፋ አማካኝነት እያሳደደ ድራሻቸውን ያጠፋበት ዘግናኝ ክስተት በዚህ ሀገር ከተሞች ውስጥ ያስከተለው እልቂት መላውን ኢትዮጵያውያን ህዝቦች የሰላም ያለህ ያሰኘ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ እንግዲያውስ እቺን መከረኛ ሀገር ወደለየለት የእርስ በርስ ጦርነት ዓውድማነት እንድታመራ ያደረጋት የያኔው የደርግ ምህረት የለሽ ጅምላ ግድያ እንደነበር ነው የታሪክ መዛግብት የሚያመለክቱት፡፡ እናም ዛሬ ላይ ‹‹የቀይ ሽብሩ ዘመን›› እየተባለ ከሚወሳው አስከፊ የሀገራችን ፖለቲካዊ ታሪክ ጀምሮ ከወታደራዊው መንግስት የነፃ እርምጃ ጭፍጨፋ በተዓምር የመትረፍ ዕድል የገጠማቸው ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን ቀለም ቀመስ ወጣቶች፤ እንደ ምንም ብለው ከየሚኖሩበት ከተማ እየመጡ ለትጥቅ ትግል ወደ ገጠራማው የሀገራችን ክፍል እንዲሸሹ መገደዳቸውን ተከትሎ ነው፤ የዕርስ በርሱ ጦርነት የተራዘመ አዙሪት የተጀመረውም፡፡ ምንም እንኳን ገና ከንጉሱ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ለኤርትራ ክፍለ ሀገር ህዝብ ነፃነት ነፍጥ አንግበው በመታገል ላይ የነበሩትን አስገንጣይ ቡድኖችን ጨምሮ፤ እንደ ኦ.ነ.ግ. ዓይነቶቹ (ተመሳሳይ የማስገነንጠል ዓላማ የነበራቸው) የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ከቀይ ሽብሩ ዕልቂት ቀደም ብሎ ሳይመሰረቱ እንዳልቀሩ ቢታመንም ቅሉ፤ የትጥቅ ትግል ማካሔድ ብቸኛው አማራጭ ተደርጎ የተወሰደው ግን ደርግ የቀይ ሽብር ነፃ እርምጃን በተቃዋሚዎቹ ላይ ማወጁን ተከትሎ ነው ማለት ያቻላል፡፡

ይህን ስንልም ደግሞ፤ ለዚያን ዘመኖቹ ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ናፋቂ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ወደ አንዱ ገጠራማ የሀገራችን ክፍል ሸሽቶ ፀረ ጭቆና የትጥቅ ትግል ላይ መሰማራት ምርጫ ሳይሆን፤ ራስን በህይወት ለማቆየት ሲባልም ጭምር የሚደረግ የህልውና ጉዳይ ነበር ማለታችን ነው፡፡ ስለሆነም አስተማማኝ የሰላምና መረጋጋት አየር የመተንፈስ ጥያቄ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የዕለት ተዕለት ጭንቀት እስከ መሆን እየደረሰ መጥቶ ጉዳዩ መላውን የዚህች ሀገር ህዝቦች የሚያታግል እጅግ በጣም አንገብጋቢ የጋራ አጀንዳ ተደርጎ ተወሰደና ጦረኛው የደርግ አገዛዝ ለመንኮታኮት በቃ፡፡ በግልፅ አነጋገር ለማስቀመጥ፤ መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፈርጀ ብዙ መስዋዕትነት ያስከፈላቸውን የዘመናት ፀረ ጭቆና ትግል ለማካሔድ ከተገደዱባቸው መሠረታዊ የጋራ ጥያቄዎች መካከል አንዱና ምናልባትም ቀዳሚ ስፍራ የሚሰጠው አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለማየት መፈለግ እንደነበር ይታመናል፡፡

ምክንያቱም ደግሞ ያለፈው የሃገራችን ታሪክ የሚገለፅበት አጠቃላይ እውነታ እኛ ኢትጵያውያን የብሔር ብሔረሰብ ህዝቦች፤ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ከደም አፋሳሽ የጦርነት አዙሪት የወጣንበት አጋጣሚ እንብዛም አለመኖሩን ያመለክታልና ነው፡፡ ስለሆነም እንደ ሀገር ስር ወደ ሰደደ የድህነትና የጉስቁልና ታሪካዊ ውድቀት እንድንወርድ ያደረገን ዋነኛው ምክንያት ይሄው በደም አፋሳሽ የጦርነት አዙሪት ከመጠመዳችን የሚመነጭ የአስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት እጦት ነው የሚል የጋራ ግንዛቤ መፈጠር በመቻሉ ምክንያት፤ ኢትዮጵያውያን የብሔር ብሔረሰብ ህዝቦች እንደ አንድ ህብረተሰብ ሰላም የሰፈነባት ሀገር ልትኖረን ይገባል የሚል አቋም ላይ ደርሰን በተለያየ አግባብ መታገላችን የሚካድ ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሌሎች የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥያቄዎቻችንን ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ የሚቻለው በቅድሚያ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ሲቻል እንደሆነ ለመረዳት ፖለቲካዊ ሳይንስ መማር አይጠበቅብንም፡፡ እናም በድህረ ደርግ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከፈተውን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ስናስብ አብሮ መታሰብ ያለበት ቁልፍ ቁም ነገር ቢኖር፤ መላው የሀገራችን ህዝቦች ስለ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት መስፈን ሲሉ፤ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ታግለዋል፤ ትግሉ የጠየቀውን ፈርጀ ብዙ ዋጋም ከፍለዋል የሚለው ነጥብ ይመስለኛል፡፡

ይህን ካልን ዘንዳም፤ ህብረ ብሔራዊው የፌደራል ስርዓታችን ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ አንስቶ፤ ካለፈው የጋራ ታሪካችን ጋር በተያያዘ መልኩ ተፈጥረው የቆዩ የዕርስ በርስ አለመተማመኖችን (የመሰጋጋት ስሜቶችን) የሚያስቀሩ የስር ነቀል ለውጡ ትሩፋቶችን ደረጃ በደረጃ የማረጋገጥ ጥረት ያሳየባቸው ተጨባጭ እርምጃዎች የሃገራችንን ውስጣዊ ሰላምና መረጋጋት አስተማማኝ እንዲሆን አድርጎት እንደነበር፤ የቅርብም የሩቅም ታዛቢ እማኝነቱን የሰጠበት ጥሬ ሃቅ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ መላው ኢትዮጵያውያን የብሔር ብሔረሰብ ህዝቦች በተባበረ የዘመናት ፀረ ጭቆና ትግላቸው አማካኝነት የተቀዳጁትን ሀገር አቀፋዊ ድል ተከትሎ በእነርሱው የጋራ መግባባት ላይ ተመስርቶ የፀደቀው ፌደራላዊ ሕገ መንግስታችን የደነገጋቸውን የሰብዓዊና ዴሚክራሲያዊ መብቶች ወደ ተግባር በመቀየር ረገድ፤ የሚጠበቀውን ያህል ርቀት መጓዝ ካለመቻላችን የተነሳ ይሄው አሁንም ወደ ቅድመ ደርጉ ደም አፋሳሽ የዕርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ሊመልሱን የሚሹ ፀረ ሰላም ሃይሎች እዚያም እዚህም ይስተዋሉ ጀምረዋል፡፡ ለዚህም ደግሞ በተለይ ከታህሳስ 2008ዓ/ም ጀምሮ የኦሮሚያንና የአማራን ክልላዊ መስተዳደሮች ባማከለ መልኩ እየተስተዋለ ያለውን ተደጋጋሚ የሰላምና መረጋጋት መደፍረስ አሳሳቢ ችግር ማስታወስ ብቻ ይበቃል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክስተቱን ወደ ሌሎቹም ክልላዊ መስተዳደሮች ለማዛመትና የጋራ ህልውናችን የተመሰረተበትን ሀገራዊ ሰላማችንን ጨርሶ ለማናጋት ያለመ የሚመስል ሰው ሰራሽ ቅንብር እየተስተዋለ ስለመሆኑም መረዳት አይከብድም፡፡ ለአብነት ያህልም ይህ የምንገኝበት የ2010ዓ/ም መግባቱን ተከትሎ (በመስከረም ወር ውስጥ) ምስራቃዊውን የኦሮሚያ ክልል ከኢትዮጵያ ሶማሌ ጋር በሚያዋስኑት አንዳንድ አከባቢዎች የተከሰተው ችግር ነዋሪውን  ህብረተሰብ ምንኛ በቀላሉ ለማይሽር ሁለንተናዊ ቀውስ ዳርጎት እንዳለፈ ማንሳት እውነታውን በተሻለ መልኩ ይገልፀዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንዲሁም ከዚያ ቀደም ብሎ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ‹‹የወልቃይት ህዝብ የማንነት ጥያቄ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል›› የሚል ሰበብ ፈጥረው ተቃውሞ ያነሱ ወገኖች ትግርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ወንድምና እህቶቻቸው ላይ እጅግ አስነዋሪ የዘረኝነት ተግባር ሲፈፅሙ የተስተዋሉትን ድርጊት ጨምሮ፤ ሰሞኑን የሰሜን ወሎ ዞን ከደቡብ ትግራይ ጋር በሚዋሰንባቸው ከተሞች ውስጥ የታየው ተመሳሳይ እንቅስቃሴ፤ አደገኛውን የፀረ ሰላም ሃይሎች ሰው ሰራሽ ቅንብር ወደ መላው የሀገራችን ክፍሎች የማዛመት ሙከራ እንደሆነ ይታመናል፡፡

እናም እንዲህ ዓይነቱ ጥሮ ግሮ ነዋሪውን ሰላም ወዳድ ህብረተሰባችንን ላላስፈላጊና ፈርጀ ብዙ ኪሳራ እየዳረገ ያለው መሰል ሀገር አውዳሚ የሁከትና የብጥብጥ ተግባር ተደጋግሞ የሚስተዋልበት አሉታዊ ክስተት፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ፈርጀ ብዙ መስዋዕትነትን ባስከፈላቸው የዘመናት ፀረ ጭቆና ትግል የተቀዳጁትን ታሪካዊ ድል ተከትሎ፤ ሀገራችን ውስጥ የሰፈነውን አስተማማኝ የሰላምና መረጋጋት አየር ቀስ በቀስ እያደፈረሰው ሆኖ ስለሚሰማኝም ጭምር ነው እኔ እንደ አንድ ዜጋ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ አዘውትሬ የምፅፈው፡፡ ደግሞስ መላውን ኢትዮጵያውያን የብሔር ብሔረሰብ ህዝቦች በዓለም ማህበረሰብ ታሪክ ፊት የአስከፊ ድህነት፤ እንዲሁም የድርቅ አመጣሽ ረኀብና ሰቆቃ ተምሳሌት ተደርገን እስክንቆጠር ድረስ ለአሰቃቂ የጋራ ውድቀት እንድንዳረግ አድርጎን የኖረው ምክንያት ምን ሆነና ነው የሀገራችን ሰላም እንደዋዛ ሲናጋ በቸልታ የምናየው ወገኖቼ ሆይ!? ስለዚህም እንደኔ እንደኔ፤ እቺ የጋራ ህልውናችን የተመሰረተባት ሀገር ከአሳፋሪው የድህነትና የኋላቀርነት ታሪኳ ተላቃ ማየት የማይሹ መሠረታዊ ጠላቶቿ ከመጋረጃው በስተጀርባ ሆነው የሚደግሱልንን የጥፋት ድግስ ለማስፈፀም ያለመ የሚመስል ቅኝት ባለው የነውጠኝነት እንቅስቃሴ ምክንያት ሰላምና መረጋታችን እንዲናጋ መፍቀድ እንደ ህብረተሰብ ለእርምት እንኳን የማያመች ታሪካዊ ስህተት መፈፀም ተደርጎ ሊወሰድ ይችላልና እጅጉን መጠንቀቅ ይኖርብናል እላለሁ፡፡

ይህ ዓይነቱ ከጭፍን ስሜታዊነት የመነጨ በጥላቻ ፖለቲካ የመነዳት አዝማሚያ ከወዲሁ ሊታረም ካልቻለ የኋላ ኋላ እንደ ሀገር ተያይዞ የመጥፋትን ድምር ውጤት ማስከተሉ እንደማይቀር ለመገመት የነብይነትን ፀጋ አይጠይቅም ማለቴ እንደሆነም ልብ ይባልልኝ፡፡ ይልቁንም ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን ህዝቦች ከድህነትና ከኋላቀርነት የከፋ የጋራ ጠላት እንደሌለን አምነን፤ የጀመርነውን የሀገራዊ ህዳሴ ጉዞ አጠናክረን እንደመቀጠል፤ በየጥቃቅኑ ምክንያት የጎሪጥ እየተያየን ዕርስ በርሳችን እንድንናቆርና የፈጣን ልማት ንቅናቄያችንን በጅምር እንዲቀር ወደሚያደርግ አደገኛ አዝማሚያ እንድናመራ ለሚፈልጉ ፀረ ሰላም ሃይሎች የአጥፍቶ መጥፋት ዕኩይ ተልዕኮ ተባባሪ ሆኖ መገኘት ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት እንደመፈፀም ሊቆጠር ይችላል የሚል ፅኑ እምነት ነው ያለኝ፡፡ በሌላ አነጋገር፤ ኢትዮጵያ የምታካሂደውን ፈርጀ ብዙ ልማትና የህዳሴ ጉዞ የመቀልበስ ዓላማ ያለውን የትርምስ ስትራቴጂ ነድፈው ለሚንቀሳቀሱ የጥፋት ቡድኖች ማንኛውንም ዓይነት ድጋፍ ስንሰጥ፤ በዚያው ልክ የሀገራችን ህዝቦች የድህነትና የጉስቁልና ኑሮ እንዲራዘም የሚያደርግ ታሪካዊ ስህተት እየፈፀምን እንደሆነ ልብ ማለት ይገባል ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ መሰል ስህተት ፈፅሞ ላለመገኘት የተሻለው አማራጭ መፍትሔ፤ ቀና አስተሳሰብን ገድሎ እየቀበረ ካለው የጥላቻ ፖለቲካና የእርሱው መገለጫ ከሆነው ጭፍን ስሜታዊነት ለመራቅ መሞከር ነው ብየ እንደማምንም ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡

አለበለዚያ ግን በፅንፈኖቹ ዲያስፖራ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች ፊትአውራሪነት የሚቀነቀነው የብሔር ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፍን የጥላቻ ስሜትና እንዲሁም ደግሞ እርሱን እንደጠቃሚ ፖለቲካዊ አመለካከት ቆጥረው የሚያዛምቱበት መርዘኛ ፕሮፖጋንዳ እቺን ሀገር የት ሊያደርሳት እንደሚችል ብንገምት ሟርተኝነት ተደርጎ ሊወሰድብን አይገባም፡፡ አሁን አሁን እንደተራ ነገር መታየት የጀመረ የሚመስለው ሀገር አውዳሚ የሁከትና ብጥብጥ ተግባር የጋራ ሰላማችንን ሊያናጋው እንደማይችልም ዋስትና የለንም፡፡ ስለሆነም፤ የአስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት አስፈላጊነት፤ ለዚያኛው አሊያም ለዚህኛው ብሔር ብሔረሰብ ተወላጆች ብቻ የሚተው ጉዳይ እንዳይደለ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ የጋራ ግንዛቤ ሊወሰድበት እንደሚገባ ይሰማኛል፡፡ በተረፈ የትርምስ ስትራቴጂውን በማቀነባበር ድርጊት ላይ የተጠመዱትን ወገኖች ልቦና እንዲሰጣቸው እመኛለሁ፡፡ እንግዲያው ለከት የለሽ ስልጣን የመጨበጥ ምኞት የማስተዋል አቅማቸውን ሰልቦት ይሆናል እንጂ፤ አሁን ላይ እንደ ‹‹አዋጭ የትግል ስልት›› እየወሰዱት ያለው እቺን ሀገር በብሔር ተኮር ግጭት የማተራመስ ፖለቲካዊ ጨዋታ፤ ለእነርሱም ጭምር አይበጅምና ወደ አእምሯቸው ይመለሱ ዘንድ የኢትዮጵያ አምላክ ቀና ቀናውን ያሳስባቸው ማለቴ እንደሆነ ልብ ይባልልኝ፡፡ ለማጠቃለል ያህል፤ ይህ ዛሬ ዓለማችን የምትገኝበት ዘመን፤ መላው ሰብዓዊ ፍጡር ከመቸውም ጊዜ ይልቅ ለጋራ ሰላምና አስተማማኝ ዋስትና ላለው በህይወት የመኖር ደህንነት ጮክ ብሎ የሚዘምርበት እጅግ አሳሳቢ ወቅት ተደርጎ የሚወሰድ እንደመሆኑ መጠን፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ህዝቦችም የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት ሊያናጋ ከሚችል ድርጊት ሁሉ መቆጠብ ይጠበቅብናል የሚለው ነጥብ ሊሰመርበት ያገባል፡፡ለማንኛውም ግን እኔ እዚህ ላይ አብቅቻለሁ፡፡ መዓ ሰላማት!

               

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy