Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስራ ፈጣሪዎቹ መስኮች

0 299

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስራ ፈጣሪዎቹ መስኮች

                                                        ታዬ ከበደ

በአገራችን እየተከናወኑ ያሉት የደንና የተፋሰስ ልማቶች ውጤት እያመጡ ነው። ቀደም ሲል የተጎዱ አካባቢዎች በአሁኑ ሰዓት እያገገሙና መሻሻልም እየታየባቸው ነው። በተፋሰስ ስራዎች አማካኝነትም ምርትና ምርታማነት እየጨመረ ነው። በዘንድሮው የመኸር ምርት የሚገኘው 345 ሚሊዮን ኩንታል የዚህ ውጤት ነው። የደንና የተፋሰስ ልማቶች በአሁኑ ሰዓት ለወጣቶች ስራ የሚፈጥሩ ሌላኛዎቹ መስኮች ሆነዋል።

በአሁኑ ሰዓት በየክልሉ በርካታ ሞዴል አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች እየተፈጠሩ ነው። አብዛኛዎቹ ወጣቶች ሲሆኑ ወደ ኢንቨስትመንትም በመግባት ላይ ይገኛሉ። ለዚህ አብነት ይሆን ዘንድ የአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች እያንዳንዳቸው ከሚሊዮን በላይ ሞዴሎችን ማፍራታቸውን መጥቀስ ይቻላል። በሌሎች ክልሎችም የማይናቅ ውጤት ተገኝቷል። ይህም የአገራችንን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው።

ግብርና አሁኑ ሰዓት የአገራችን ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ነው። ቀኝ እጃችን ነው። መንግሥት ግብርናውን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ተገንዝቦ ሲሰራ ቆይቷል። በያዝነው ሁለተኛው የልማት ዕቅድ ላይም ቀደም ባሉት የልማት ዓመታት የተገኘውን አመርቂ ውጤት ይበልጥ አጎልብቶ ለመቀጠል እየተሰራ መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ።

መንግሥት ለዘመናዊ ግብርና ያልተደፈረውን የአገሪቱን አርሶ አደር የአስተራረስ ዘይቤ የመለወጥን አስፈላጊነት ተገንዝቦ በቀየሰው መስመር እነሆ የሚታየ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው። አርሶ አደሩ በድርቅ በቀላሉ መጠቃት ምክንያቱም ደግሞ የዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ አለመኖር እንደሆነ ተረጋግጧል።

በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ኑሮው እንዲሻሻል ተገቢ ትኩረት አግኝቷል። ለዚህም በቂ ማሳያዎችንም ማቅረብ ይቻላል። መንግሥት የዘመናት ቁጭቱን አገራዊ መሠረት ባላቸው አቅጣጫዎች የመፍታት ትግሉን እያካሄደ ነው። አርሶ አደሩ ከራሱ ተርፎ ለገበያ በማምረት ተጠቃሚ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ ሀገሪቱም ከግብርናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን አረጋግጧል።

አርሶ አደሩ የለውጥ መስመሩን ተረድቶ በእምነት ወደ ሥራው በመግባቱ በዓመት ሁለቴና ከዚያም በላይ ለማምረት ችሏል። እንዲሁም በከርሰ ምድርና በገጸ -ምድር ያለውን የውኃ ሃብት የመጠቀም ሰፊ ተግባር አከናውኗል።

በውኃ ማሰባሰብና ማቆር፣ የጉድጓድ ውኃን በመጠቀም የወንዝ ውኃን ጠልፎ ጥቅም ላይ በማዋል ብዙ ርቀት ተጉዟል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለከተማው ነዋሪዎች ከፍተኛ ፍላጎት የሆኑትን ምርቶች ማቅረብ ችሏል። ከነዚህ ውስጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ናቸው።

ከዝናብ ጥገኝነት በተላቀቁ አመራረት የተገኙትን ምርቶች መጠቀምም እየተቻለ ነው። የመስኖ ልማት ሥራው በበጋ የበቆሎ እሸት ተመጋቢዎች እንዲሆን አስችሎናል። ባለፉት ዓመታት ደግሞ ሥራው በእጅጉ ማደግ ችሏል።

ኢትዮጵያ በግርናው መስክ በአጭር ጊዜ ውስጥ አያሌ ለውጦችንም አስመዝግባለች። ምንም እንኳን ባለፈው ዓመት ሀገራችን ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው ሁከት በኢኮኖሚው መስክ ሊፈጥረው የሚችለው እጅግ አነስተኛ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ባይካድም፤ የግብርናው ልማት ግን ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በዚህ ረገድ በተለይም ከምርት አኳያ የተፈጠረ ችግር አለመኖሩ በተደጋጋሚ ተገልጿል። ይህም የሆነው መንግስት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ምሶሶ ለሆነው የግብርናው ልማት የሰጠው ትኩረት መሆኑ አይካድም።

የግብርና ልማት መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ይችል ዘንድ በበሁለተኛው አምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትኩረት ተሰጥቶታል። እንደሚታወቀው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለእርሻ ሊውል የሚችል ሰፊና ለም መሬት እንዲሁም የአርሶ አደሩ ጉልበት አለ። በሀገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ታዲያ ይህ ግብርናው ውጭ ከፍተኛ እምቅ ሃብት ነው። ይህ ሃብት ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ሲሆን፤ ገና ምንም ያልተነካ እምቅ በመሆኑም ውጤት ሊያመጣ የሚችል ነው። ሀገሪቱን ለመለወጥ ወሳኙ ሃብት ተደርጎ መወሰዱም እንዲሁ።

ይህን መነሻ ታሳቢ ባደረገ ሁኔታም በያዝነው አምስት ዓመታት የግብርና ዘርፍ በየዓመቱ ቢያንስ በአማካይ የስምንት በመቶ ዕድገት የሚያስመዘግብ ይሆናል። ምርጥ ተሞክሮ ያላቸውን አርሶ አደሮች ውጤት ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች በማስፋፋት የዋና ዋና ሰብሎችን ምርት በእጥፍ ለማሳደግ እንደሚቻል ዕቅድ ተይዟል።

በዚህም መሠረት የግብርናን ዘርፍ አማካይ ዓመታዊ ዕድገት በመሠረታዊ አማራጭ ከነበረው ስምንት በመቶ ወደ 11 በመቶ ከፍ ከፍ እንዲያደርገው ዕቅድ ተይዟል። ይህ ዕቅድ ይሳካ ዘንድም በዋናነት አስተዋፅኦ የሚያደርጉት ዋነኛ የሰብል ምርቶች በ16 በመቶ ያድጋሉ ተብለው ይጠበቃሉ።

የዋነኛ የሰብል ምርቶች ከጠቅላላው የግብርና ምርት ተጨማሪ እሴት ያላቸው ድርሻ በአማካይ 40 በመቶ ይሆናል። በዚህ ምክንያት ይህ የዕድገት ጭማሬ በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ዕድገት ላይ ሊኖረው የሚችለው ግብረ መልስ ሳይካተት በግብርና ዕድገት ምክንያት ብቻ በዕቅዱ ዘመን አማካይ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት በከፍተኛ የዕድገት አማራጭ 12 ነጥብ ሁለት በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። ያም ሆኖ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመንም ግብርና በጥቅሉ ዋነኛው የዕድገት ምንጭ ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ነው።

የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች በትክክል ውጤትማ እየሆኑ ነው። በአፈጻጸሙ ከተጠበቀው በላይ መጓዙን መረጃዎች ያመለክታሉ። በሁለተኛው የልማት ዕቅድ ዘመንም ይህን የምርትና ምርታማነት ዕድገት መጠን ለማሳደግ ዕቅድ ተይዟል።

ከዚህ ጎን ለጎንም የግሉ ዘርፍ በግብርናው ውስጥ መሳተፍ የጀመረው በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ውስጥ ነው። ከእነዚህ ዘርፎች ውጪ ባለሃብቱ የግብርና ልማት ውስጥ መሳተፍ የጀመረው በመንግስት በኩል በመስኩ በተደረገው የማበረታቻ ጥረት መሆኑ ይታወሳል። እነዚህን ባለሃብቶች ከአነስተኛ አርሶ አደሮች ጋር በማስተሳሰር ውጤታማ ተግባራትን ለመከወን እየተሰራ ነው።

ከሁሉም በላይ ደግሞ መንግስት እየተከተለ ባለው የግብርና ልማት ስትራቴጂ ትርፍ አምራች ዜጋዎችን ምፍጠር ተችሏል። እነዚህ አባቢዎች በድርቅ የተጎዱት አካባቢዎችን እየሸፈኑ ነው። ይህም የድርቅ አደጋ ተጋላጭነት ቢኖርም ችግሩን በራስ አቅም ለመቋቋም ያስቻለ ነው። በተለይ የተፋሰስና የመስኖ ልማት ስራዎች ስራ እየፈጠሩ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን በመቋቋ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ስራ ፈጣሪ መስኮች ይበልጥ በመጠናከር ችግር ፈቺነታቸውን ማረጋገጥ ይገባል።  

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy