Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስራ ፈጣሪዎቹ እጆች

0 289

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስራ ፈጣሪዎቹ እጆች

                                                          ታዬ ከበደ

ወጣቱ መንግስት ባዘጋጀው ተዘዋዋሪ ፈንድና በሌሎች ማበረታታቻዎች በመታገዝ እየፈጠረ ያሉትን ሀገር በቀል ስራዎች የሚበረታቱ ናቸው። ስራ ፈጣሪዎቹ የወጣቱ እጆች በአንድነት ተቀናጅተው በአነስተኛና ጥቃቅንና በመካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ባተሌ ሆነዋል። ወጣቱ የተለያዩ ልማታዊ ተግባራትን በማከናወን እያከናወነ ያለው አቅርቦት ድጋፍን የሚሻ ነው። ድጋፉ በግለሰብ፣ በቤተሰብና በአገር እድገት ላይ የራሱን ሚና ይጫወታል።

ወጣቱ እንደሚታወቀው ሁሉ አገራችን ለስራ ዝግጁ የሆነውን የወጣት ጉልበት በሚገባ ሁኔታ መጠቀም ይኖርባታል። ይህን ጉልበት አጣጥሞ በተገቢው መንገድ መጠቀምም ለአገራዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ወጣቶች በተፈጥሯቸው ሁሉንም ነገር የመስራት ስሜት የታደሉ ናቸው። እነርሱን በማናቸውም ሀገራዊ የልማት ትልሞች ውስጥ በማስገባት ማሳተፍ ስራዎችን በአፍላ ጉልበት እንዲሁም በፈቃደኝነትና በፍላጎት ስሜት ሊተገብሩት ይችላሉ።

ይህ ደግሞ የተያዙ ዕቅዶችን ለመፈፀምና የሚፈለገውን ሀገራዊ ዕድገት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ስለሆነም በወጣቶች ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ውጤቱ መልሶ የሚከፍለው ሀገርን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

እርግጥ የኢፌዴሪ መንግስት ለወጣቶች የሰጠው ትኩረት የህብረቱን ፍላጎት አስቀድሞ የተገነዘበ ነው ማለት ይቻላል። ግና እዚህ ላይ ‘ወጣቶች ሀገራችን የሰጠቻቸውን ትኩረት እንደምን ሊጠቀሙበት ይገባል?’ የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። ምንም እንኳን የጥያቄው ምላሽ ሊኖር የሚችለው በወጣቱ ትጋት ውስጥ ቢሆንም፤ እኔም ለመነሻ ይሆኑ ዘንድ ጥቂት ግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ማንሳት ይገባል።

ወጣቱ የመንግስትን ትኩረትና የተመደበለትን ተንቀሳቃሽ ፈንድ በአግባቡ ለመጠቀም ራሱን ለስራ ዝግጁ ማድረግ ይኖርበታል። በእኔ እምነት ራስን ለስራ ማዘጋጀት አንድን ችግር ለመፍታት ግማሽ መንገድ እንደመሄድ ያህል ይቆጠራል። እናም ወጣቱ አስቀድሞ ራሱን ለማንኛውም ስራ ማዘጋጀት አለበት።

ማንኛውም ስራ ከችግር መውጫ ቀዳዳ መሆኑን ማመን ይኖርበታል። በአጭሩ ወጣቱ ስራን ሳይንቅና ምናልባትም በስደት ቢሄድ ለባዕድ ሀገራት ሊያበረክተው የሚችለውን የጉልበት ስራ ዓይነት ጭምር ስራዎችን አክብሮ በመስራት የመንግስትን ትኩረት አሟጦ ሊጠቀምበት ይገባል። ስራ ክቡር ነው የሚለውን አርማ ከፍ አድርጎ ማውለብለብ ይጠበቅበታል። ያኔ ራሱን፣ ቤተሰቡንና ከምንም በላይ እያሰበችለት ያለችውን አገሩን መጥቀሙ አጠያያቂ አይሆንም።

ከዚህ በተጨማሪም ወጣቱ ስራ ፈጣሪ እንጂ ስራ ጠባቂ ሊሆን አይገባም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የፌዴራል መንግስትና ክልሎች ወጣቱ በስራ ውስጥ እንዲያልፍ ተንቀሳቃሽ ፈንድ አዘጋጅተዋል።

ወጣቱ በዚህ ፈንድ እንደምን ራሱን ለስራ ዝግጁ ማድረግ እንደሚችል ማሰብ ይኖርበታል። በዚህ ሰዓት አገራችን ውስጥ የተመቻቸ የስራ ምህዳር አለ። ዋናው ነገር ይህን ምቹ የስራ ድባብ በፈጠራ ክህሎት አጅቦ እንዴት ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል ማወቁ ላይ ነው።

እርግጥ ዛሬ ወጣቱ ስራ ፈጣሪ እየሆነ ነው። ሥራ ፈጣሪ የሆነውም በዚህ ሥርዓት ነው። ወጣቱ ሥርዓቱ የእርሱ እንደ መሆኑ መጠን ሊጠብቀው ይገባል። በተለያዩ ጊዜያት እያሰለሱ በየአካባቢው የሚታዩ ግጭቶች መነሻቸውና መድረሻቸው ሥርዓቱን በውል ካለመገንዘብ አሊያም ጥቅማቸውን ለማሳደድ የሚሹ ኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች የሚነሱ መሆናቸው ግልፅ ነው። እነዚህን ሃይሎች አደብ ለማስገዛት መንግስት ማናቸውንም ተግባሮች እንደሚከውን ቃል ገብቷል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የማናቸውም ችግሮች መፍትሔ የሚመነጨው በአገሪቱ በህዝብ አመኔታ ከተመረጠው መንግስት እንጂ የራሳቸውን አጀንዳ ለማራመድ ብሎም የሌሎች ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ተላላኪ በመሆን በህዝቦች ስቃይ ትርፍ ለማጋበስ በሚፈልጉ ሃይሎች አለመሆኑን ወጣቶች ያውቃሉ።

በመሆኑም መንግሥት የአዳዲስ ልማታዊ ሃሳቦችና አሰራሮች አመንጪ ብሎም ለወጣቶች ችግር የሚደርስ ህዝባዊ አካል መሆኑን በመገንዘብ ከእነዚህ ሃይሎች አሉባልታ በመራቅ የእነርሱ እኩይ ዓላማ መጠቀሚያ ላለመሆን መትጋት አለባቸው።

ምንም እንኳን ወጣቱ በአሁኑ ወቅት ስልጣንን ለግል ጥቅማቸውና ለኑሮ ማደላደያነት ለማዋል በሚሹ የተለያዩ ሃይሎች አማካኝነት የተፈጠረ ጊዜያዊ ችግር ቢኖርበትም፤ ችግሩ በአገሪቱ በመመዝገብ ላይ የሚገኘው ልማታዊ ድል ጊዜያዊ እንቅፋት መሆኑን መረዳት ያለበት ይመስለኛል። ወጣቶች የመንግሥትን የለውጥ ሃይልነት ስለሚያውቁ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ እንደማይወጣና እንደሚለወጥም ማመን የሚኖርባቸው ይመስለኛል።

ይህን ሥርዓት ታግለውና መስዋዕት በመክፈል ጭምር ያመጡት የትናንትናዎቹ ወጣቶች ለዛሬው ወጣት አስረክበውታል። የዚህ ትውልድ ወጣት ደግሞ እነዚያ ውድ የህዝብ ልጆች በደማቸውና በአጥንታቸው የሰጡንን ሥርዓት የማስቀጠል ሃላፈነት የዚህ ትውልድ አደራ ነው።

ይህ ትውልድ ሃላፊነቱን በተገቢው መንገድ መወጣት ይኖርበታል፤ ድህነትን በመዋጋት። የትውልዱ ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው። በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ “የድህነትን ተራራ በዕውቀት ጥይት መናድ ይቻላል” እንዳሉት፤ ድህነትን ለመቅረፍ ዋነኛው መሳሪያ ትምህርት መሆኑን ወጣቶች ሊዘነጉ አይገባም።

እናም የዕውቀት መገብያቸው የሆነውን ትምህርት ቤቶችን ከማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ አመለካከትና ሽኩቻ እንዲሁም ከዘረኝነት አስተሳሰብ እንዲፀዱ ማድረግ ይኖርበታል። ነተለይም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከዘረኝነት አስተሳሰብ ርቀው የአንድ ሀገራዊ ዕድገት ማሳያ መሆን ይኖርባቸዋል።

ዛሬ ስራ ላይ ያሉት ስራ ፈጣሪ እጆቻቸው ሊሳለጡ ይገባል። የሚያመርቱት ምርት የሚከፋፈለው በሰላማዊ ምህዳር ውስጠ በመሆኑ እነዚህ አምራች እጆች ሰላምንም መጠበቅ ይኖርባቸዋል።

መንግስት ለሁለተኛ ጊዜ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነድፏል። የዕቅዱ ዋነኛ ተዋናይ የሆነው የአገራችን ህዝብ፤ በተለይም ወጣቶች ለስኬታማነቱ እያደረጉ ያሉትን ተሳትፎ ማጎልበት አለባቸው።

በዕቅዱ ቀሪ ዓመታት ወጣቶች በእነዚህ የስራ ባህላቸውንና ተነሳሽነታቸውን እንዲሁም የቁጠባ ባህላቸውን በበለጠ በማጎልበት ስራ ፈጣሪ እጆቻቸውን ይበልጥ ማሰራት እንደሚኖርባቸው ማስገንዘብ ያስፈልጋል። አሁን ያለው የስራ ፈጠራ የሚያኮራ ነው። የወጣቱ ተነሳሽነትም ከፍተኛ ነው። ይህን ሁኔታ ከአገሪቱ ፍላጎት ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል። ምክንያቱም እጅግ በርካታ ቁጥር ያለውን ወጣት የያዘችው አገራችን ከወጣቱ መጠቀም ብቻ ሳይሆን ራሱን በመጠቀም ጭምር ችግሩን እንዲፈታ ማድረግ ስለሚቻል ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy