Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በታሪካዊ አስገዳጅ ሁኔታ የመጣ ሥርዓት

0 328

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በታሪካዊ አስገዳጅ ሁኔታ የመጣ ሥርዓት

ኢብሳ ነመራ

ኢትዮጵያ ከፌደራላዊ የመንግስት ስርአት ጋር ከተዋወቀች 23 ዓመታት ተቆጥረዋል። ኢትዮጵያ በደርግ ውድቀት ማግስት በተቋቋመው የሽግግር መንግስት ወቅት ነበር ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበትን ፌደራላዊ ስርአት የፀነሰችው።  የደርግን መንግስት ለውድቀት ያበቁት የተለያዩ የብሄራዊ ነጻነት ንቅናቄዎች የሽግግር መንግስቱን ሲመሰርቱ ነበር ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንዲከበር የወሰኑት። የሽግግር መንግስቱ እንደ ህገ-መንግስት ይጠቀምበት የነበረው ቻርተር የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ያረጋገጠም ነበር። በዚህ መሰረት በሽግግር መንግስቱ ወቅት ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስታት ቅርጽ መያዝ ጀመሩ።

ኢትዮጵያ የብዝሃ ብሄር ሃገር ነች። በወሰኗ ውስጥ የየራሳቸው ቋንቋ፣ ባህልና ወግ፣ ታሪክ ያላቸው በራሳቸው መልከዓምድራዊ ወሰን ውስጥ የሚኖሩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ያሉባት ሃገር ነች። እነዚህን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰው አይደለም የፈጠራቸው፤ ፈጣሪ እንጂ። ይሁን እንጂ 19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ላይ ወሰን በማስፋት በደቡብ፣ በምስራቅና በምዕራብ አካባቢዎች የሚኖሩ ብሄሮችን፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን ያስገበረው ፊውዳላዊ ዘውዳዊ ስርአት እንዳፈጣጠራቸው እውቅና ሊሰጣቸው አልፈቀደም። ዘውዳዊው ስርአት አንድ ማንነት ያላት ሃገር የመፍጠር ስትራቴጂ ነድፎ ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ። ይህን ስትራቴጂ ተመራማሪዎች ኢትዮጵያናይዜሽን ይሉታል። ፖለቲካዊ ዝንባሌ ያላቸው ወገኖች ደግሞ አማሃራይዜሽን ይሉታል።

ያም ሆነ ይህ፣ የስትራቴጂው ዓላማ አንድ ቋንቋ፣ ባህል፣ . . . ያለው ማለትም አንድ ብሄራዊ ማንነት ያለው ህዝብ መፍጠር ነበር። ይህን ስትራቴጂ አንድ ጠንካራ ሃገር የመፍጠር ስልት አድርገው በበጎ የሚያዩ ሊኖሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ አንድ ብሄራዊ ማንነት ያላት አሃዳዊ ሃገር የመፍጠሩ ጉዳይ የተካሄደው  በብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ፍቃድ ወይም በላቀ የኢኮኖሚ እደገት ገፊነት የህብረተሰብ እድገት ሂደትን ተከትሎ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በአስገዳጅ ህግና ስነልቦናዊ ጫና የተለያዩ ብሄራዊ ማንነቶችን በመጨፍለቅ ነበር።

በዚህ ስትራቴጂ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በቋንቋቸው የመንግስት አገልግሎት እንዳያገኙ ተደርገዋል። ከንጉሰ ነገስቱ ቤተመንግስት እስከ ንኡስ ወረዳ ያሉ መንግስታዊ ተቋማት አገልግሎት የሚሰጡት በአንድ ቋንቋ እንዲሆን ተደርጓል። ከንጉስ ችሎት እስከ ወረዳ ያሉ ፍርድ ቤቶች የሚያስችሉት በአንድ ቋንቋ ነበር። የየራሳቸው ቋንቋ ያላቸውና ከራሳቸው ቋንቋ ውጭ መግባባት የማይችሉ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የመንግስት መስሪያ ቤት ቀርበው ጉዳያቸውን በማያውቁት ቋንቋ እንዲያስረዱና እንዲረዱ ይገደዱ ነበር። የፍርድ ቤት ጉዳያቸው ላይ ምንም በማያውቁት ቋንቋ እንዲዳኙ ይገደዱ ነበር። የዚህን ሁኔታ አስከፊነት ለመረዳት በድንገት የጎጃም ወይም ጎንደር ፍርድ ቤቶች የስራ ቋንቋቸውን ሱማሌኛ አድርገው ሃገሬውን በጉዳዩ ላይ በዚህ የማያውቀው ቋንቋ እንዲሟገት ቢገደድ የሚገጥመውን ፈተና አስቡ። ከ80 በላይ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከመቶ ዓመታት በላይ በዚህ ፈተና ውስጥ አልፈዋል።

ህጻናት አፍ በፈቱበትና አካባቢያቸውን በሚረዱበት ቋንቋ የመጀመሪያ ደረጃ ወይም መሰረተ ትምህርት ማግኘት አይችሉም ነበር። ህጻናቱ 1ኛ ክፍል ሲገቡ ፈጽሞ ሰምተውት የማያውት ቋንቋ ነበር የሚገጥማቸው። ይህ ሁኔታ መሰረታዊ እውቀት ማስጨበጥ እንዳይቻል ከማድረግ በተጨማሪ፣ ተማሪዎቹ ግራ በመጋባትና የደካማነት ስሜት በሚፈጥርባቸው የሞራል ጫና ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ የሚገደዱበትን ሁኔታ ይፈጥር ነበር። የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በዚህ ውስጥ ካለፉት አንዱ ነው።

ይህ ብቻ አይደለም። ከሃገሪቱ ሚዲያዎች የተሻለ ተደራሽነት የነበረውና ከ90 በመቶ በላይ ለሚሆነው ማንበብና መጻፍ የማይችለው ህዝብ አመቺ የነበረው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ስርጭት በአንድ ቋንቋ ብቻ የተገደበ ነበር። የተቀሩት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋዎች የብሮድካስትም ሆነ የህትመት ሚዲያ ቋንቋ መሆን አይችሉም ነበር። በእነዚህ ቋንቋዎች መጽሃፍ ማሳተምም አይቻልም ነበር። እርግጥ ከንጉሰ ነገስቱ መወገድ በኋላ ጠንከር ያለ የብሄራዊ ነጻነት ጥያቄዎች ያነሱ የነበሩት የኦሮሞ ብሔር ቋንቋ (ኦሮሚፋ) እንዲሁም የኤርትራ/ትግርይ ብሄሮች ህዝቦች የሚጠቀሙበት የትግርኛ  ቋንቋ በቀን ለአንድ ሰአት ያህል የሬዲዮ ስርጭት እንዲያገኙ ተደርጎ ነበር። በኦሮሚኛ የሚታተም በሬሳ የተሰኘ ጋዜጣም በዚህ ወቅት የተጀመረ ቢሆንም አጥጋቢ አልነበረም።

በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ላይ ይደርስ የነበረው ጫና በህግ ማዕቅቦች የተገደበ ብቻ አልነበረም። መደበኛና መደበኛ ባልሆነም ሁኔታ የሞራል ጫና ይፈጸም ነበር። በአማርኛ ቋንቋ አጠቃቀም ላይ የሚታይ የራስ ንቋ ተፅእኖ ለስላቅ ያጋልጥ ነበር። በራስ ቋንቋ የወጡ መጠሪያ ስሞች በተመሳሳይ ሁኔታ ለስላቅና ለፌዝ የሚያጋልጡበት ሁኔታ ነበር። ይህ አሸማቃቂ ሁኔታም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን በራሳቸው ሃገር ላይ አንገታቸውን እንዲደፉና ማንነታቸውን እንዲደብቁ አድርጓል።

ይህን ጭቆና መሸከም ያልቻለው ህዝብም በኢትዮጵያ የብሄራዊ ነጻነት ትግልን ወለደ።  በመሆኑም የመጨረሻውን አፋኝ አሃዳዊ ወታደራዊ የደርግ ስርአትን በየአቅጣጫው የተከፈተው የብሄራዊ ነጻነት ትግል አስወገደ።

ከደርግ ውድቀት በኋላ ሃገሪቱ መንታ መንገድ ላይ ቆመች። አንደኛው የነጻነት ጥያቄ  የትጥቅ ትግል ያካሄዱ ብሄሮች ተገንጥለው የየራሳቸውን ነጻ መንግስት የሚመሰርቱበት የመበታተን አቅጣጫ ነበር። ሌላኛው ደግሞ ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል የቆየው አንድነት ሊቀጥል የሚችልበት ሁኔታን መፍጠር። በዚህ የሃገሪቱ እጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን ሁሉም በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ፣ እንዲሁም በውጭ ሃገራት በተለያየ መንገድ ስርአቱን ሲታገሉ የነበሩ ቡደኖች፣ የደርግ መንግስት በወደቀ ማግስት የተደራጁና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ ለመሆን የበቁት ጭምር የተሳተፉበት ሸንጎ ሰኔ 1983 ዓ.ም ተካሄደ።

በዚህ ካለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነትና አደራዳሪነት በተካሄደ የሰኔው ህዝባዊ ኮንፈረንስ በመባል የሚታወቅ ሸንጎ ላይ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብሄራዊ መበቶቻቸውና ነጻነቶቻቸው ተከብረውላቸው በአንድ ላይ ሊኖሩ የሚችሉበት እድል ለመፍጠር ተስማሙ። በጽሁፉ መግቢያ ላይ የጠቀስኩት የሽግግር መንግስት ይህን አብረው ሊኖሩ የሚችሉበትን ሁኔታ የሚያሟላ ስርአት የመገንባት ተልዕኮ ተሰጥቶት የተመሰረተ ነበር። እርግጥ የሽግግር መንግስቱ ራሱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ‘ሀ’ ብለው የጀመሩበት ነበር።

የሽግግር መንግስቱ የሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ እንዲሁም ሌሎች የፖለቲካ ሃይሎች የተሳተፉበት ህገ-መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን በማቋቋም በባለሞያዎች  የህገ-መንግስት ረቂቅ ተዘጋጀ። ይህ ረቂቅ ህገ-መንግስት ወደመጽደቅ ከመሄዱ አስቀድሞ ለሁለት ጊዜ ያህል ወደህዝብ ተመርቶ ለአካለ መጠን የደረሱ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተወያይተውበት እንዲዳብር ተደርጓል። በመጨረሻም ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምስጢራዊ የድምጽ አሰጣጥ በህዝብ የተመረጡ አባላትን በያዘ የህገ-መንግስት አጽዳቂ ምክር ቤት አማካኝነት እንዲጸድቅ ተደርጓል። ይህ ምክር ቤት የረቂቅ ህገ-መንግስቱ እያንዳንዱ አንቀጽ ላይ እየተወያየ በአብላጫ ድምጽ እያሳለፈ ነበር ያጸደቀው። ይህ ህገመንግስት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ-መንግስት (የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት) ነው።

ህገ-መንግስቱም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር እስከመገንጠል የዘለቀ መብታቸውን ያረጋገጠ ፌደራላዊ ስርአትን ይደነግጋል። ህገ-መንግስቱ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሚኖሩበት ክልል ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ (በተወካዮቻቸው አማካኝነት እየተዳደሩ፣ በቋንቋቸው የመንግስት አገልግሎት እያገኙ፣ ቋንቋቸውን ለትምህርት መስጫነት እየተጠቀሙ፣ ባህላቸውን እያጎለበቱ፣ ታሪካቸውን እየተንከባከቡ) ቀደም ሲል በመሃከላቸው የነበረውን የተዛባ ግንኙነት አድሰው በመከባበር፣ በመቻቻልና በእኩልነት ላይ በተመሰረተ አንድነት አብረው ለመኖር የተስማሙበት የቃል ኪዳን ሰነድ ነው። ይህ በህገ-መንግስት የተረጋገጠ ፌደራላዊ ስርአት ሃገሪቱን ከመበታተን አደጋ ታድጓታል። በሃገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ ሲካሄድ የነበረው የነጻነት የትጥቅ ትግል የፈጠረውን አጠቃላይ ጦርነት አስቀርቶ ሰላም አስፍኗል። ፌደራላዊ ስርአቱ በሃገሪቱ የነበረው ጭቆና በፈጠረው የብሄር ቅራኔ ታሪካዊ ሁኔታ አስገዳጅነት የመጣ ሊታለፍ የማይችል ነው።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ያረጋገጠው ፌደራላዊ ስርአት ስራ ላይ ከዋለ በኋላም የማንነት ጥያቄዎች ተንስተዋል። በተለያዩ ክልሎች ከነባር ብሄረሰቡ ውጭ የሆኑ ዜጎች ከአካባቢው እንዲወጡ የሃይል ጫና የተደረገበት ሁኔታም አለ። ራሳቸውን በራሳቸው በሚያስተዳድሩ ክልሎች መሃከል በወሰን ይገባኛል ጥያቄ ግጭቶች መፈጠራቸውም ይታወቃል።

አንዳንድ ወገኖች እነዚህን ችግሮች ሃገሪቱ ፌደራላዊ ስርአት በመከተሏ ምክንያት የተፈጠረ አድርገው ሲያቀርቡ ይሰማል። ይሁን እንጂ የችግሩ ምንጭ ፌደራላዊ ስርአቱ ሳይሆን የህግ የበላይነት አለመከበርና ከህዝብ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ህገ-መንግስታዊ ምላሽ መስጠት ላይ የታየ ዳተኝነት ነው። የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት፤ የክልል መንግስታት ህገ-መንግስቶችም ዜጎች በሃገሪቱ ውስጥ የመዘዋወር፣ በማንኛውም ክልልና አካባቢ የመኖር፣ የመስራት፣ ሃብት የማፍራት ወዘተ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። ሆኖም አንዳንድ ቡድኖች ይህን ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ጥሰው ሰዎችን ከኑሮ ያፈናቀሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህ የፌደራልና የክልል መንግስታትን ህገ-መንግስት ማስከበር ካለመቻል ወይም ለማስከበር ካለመፍቀድ የመነጨ የአመራሮች ችግር እንጂ ፌደራላዊ ስርአቱ ራሱ የፈጠረው አይደለም።

በሌላ በኩል፤ የማንነት ጥያቄዎች ያነሱ ብሄረሰቦችና ህዝቦችም አሉ። በክልሎችና ሌሎች ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በሚያስተዳድሩባቸው መዋቅሮች መሃከል የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎችም ሲነሱ ቆይተዋል። እነዚህ የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ግጭቶችም አስከትለዋል። የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት በማንኛውም ጊዜ በተለያየ ታሪካዊ ሁኔታ የተደፈቁ ብሄረሰቦች ወይም ህዝቦች የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳድረ ጥያቄ ሊያነሱ የሚችሉ መሆኑን ታሳቢ አድርጓል። እናም እነዚህ ጥያቄዎች ሲነሱ ምላሽ የሚያገኙበትንም ስርአት አስቀምጧል። ከወሰን ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎችም በተመሳሳይ ምላሽ የሚያገኙበት ስርአት በህገመንግስቱ ተደንግጓል። ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ እስካሁን ችግሮች ያጋጠሙት ሃገሪቱ በዋናነት ብሄራዊ ማንነትን መሰረት ያደረገ ፌደራላዊ ስርአት ስለምትከተል አይደለም። ከዚህ ይልቅ የህገ-መንግስቱ ድንጋጌዎች ጥያቄዎች ሲነሱ ተገቢና ፈጣን ምላሽ ባለመኖሩ ነው።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ስርአት የብሄሮችንና ብሄረሰቦችን ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብቶችን እንዲሁም ነጻነቶች በማረጋገጥ የሃገሪቱን አንድነት ማስጠበቅ አስችሏል። ከፌደራላዊ ስረአት ውጭ ያሉ አማራጮች ሁሉ የብሄራዊ ነጻነት ጥያቄዎችን በመቀሰቀስ ሃገሪቱን ወደ ጦርነት ውስጥ በማስገባት ለመበታተን አደጋ የሚያጋልጡ ናቸው። ቅድመ 1993 ዓ.ም የነበረው ሁኔታም ይህ ነበር። አናም ፌደራላዊ ስርአቱ በታሪካዊ ሁኔታዎች አስገዳጅነት የመጣና የሀገሪቱን አንድነት ጠብቆ ማቆየት የሚያስችል ብቸኛው አማራጭ ነው።      

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy