Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በፖለቲካ አመለካከቱ ማንም…

0 240

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በፖለቲካ አመለካከቱ ማንም…

                                                        ታዬ ከበደ

አንዳንድ ወገኖች በተለይም ፅንፈኛው ሃይል የሀገራችንን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማጣጣል ሲል አገራችን ውስጥ ፖለቲከኛ አሊያም ጋዜጠኛ በመሆኑ ምክንያት የታሰረ ሰው ያለ በማስመሰል እየገለፀባቸው ያሉት መንገዶች ስህተት ናቸው። ፖለቲከኛ፣ ጋዜጠኛ አሊያም የሌላ ሙያ ባለቤት የሆነ ሰው በአመለካከቱ ብቻ ሊታሰር አይችልም።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ያረጋገጠና መብቶቹም እየተተገበሩ ናቸው። እነዚህን መብቶች በህግ ካልተደነገገ በስተቀር መግፈፍ አይቻልም። ዜጎች ህግና ሥርዓትን ተላልፈው ወንጀል እስካልሰሩ ድረስ ባላቸው ፖለቲካዊ አመለካከት ለእስር ሊዳረጉ አይችሉም። ይህ የሚደረገው መንግሥት የዜጎችን መብትና ግዴታዎች ለማስከበር ካለው ቁርጠኛ አቋም የተነሳ ነው።

በህገ መንግስታችን ላይ በግልፅ እንደተደነገገው፤ ማንኛውም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው። በመሆኑም ማንኛውም አዋጅ ሲወጣ ሁሉንም ዜጋ ይመለከታል እንጂ ለተለየ የህብረተሰብ ክፍል ተለይቶ አይደለም። እናም ፖለቲከኛውም፣ ጋዜጠኛውም፣ ሙዚቀኛውም፣ መሃንዲሱም፣ ሀኪሙም፣ ቀዳሹም ሆነ ተኳሹ…ሀገሪቱ ያወጣችውን ህግ የማክበርና በእርሱም የመመራት ግዴታ አለበት። በመሆኑም አንድ ግለሰብ ባለሙያ አሊያም የተቃዋሚ ፓርቲ ስለሆነ ሙያውን ወይም የተቃዋሚ ፓርቲ አባልነቱን እንደ መከላከያ ምሽግ በመጠቀም ህገ ወጥ ተግባርን መፈፀም የህግ የበላይነት ገቢራዊ እንዳይሆን የሚያግድ አለመሆኑን መገንዘብ ያሻል።

እንደሚታወቀው በህግ ካለተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ስርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ የሚንቀሳቀሰው ህግ ባለበት ሀገር ውስጥ ነውና ህገ-ወጥ ተግባርን ከከወነ የህግ የበላይነት ተፈፃሚ እንደሚሆንበት ማወቁ ተገቢ ይመስለኛል። ይህ አሰራር ለፖለቲከኛም ይሁን ለጋዜጠኛ አሊያም ለሌላ ባለሙያ እኩል የሚሰራ ነው። ተለይቶ አይታይም።

አንድ ፖለቲከኛ በሰራው የወንጀል ጉዳይ ሊታሰር ይችላል። በህግ ጥላና ከለላ ስር ያሉት ግለሰቦችም ቢሆኑ የሀገሪቱን ህግና ስርዓት ተላልፈው የተገኙ ወንጀለኞች እንጂ ፖለቲከኛ ስለሆኑ የታሰሩ አይደሉም። አንድ ግለሰብ ፖለቲከኛ ስለሆነ ብቻ የሚታሰር ከሆነ፤ በህገ-መንግስቱ ላይ የሰፈሩት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አስፈላጊ ባልሆኑ ነበር።

ሆኖም በሰለማዊ ፖለቲከኝነት ሽፋን አንድ ፖለቲከኛ ወንጀል ከፈፀመና የሀገሪቱን ሰላም ለማወክ ከተንቀሳቀሰ አሊያም በሀገሪቱ ውስጥ በአሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶችን ተልዕኮ ለማስፈፀም ከተንቀሳቀሰ እንደ ማንኛውም ግለሰብ በህግ አግባብ መጠየቁ የሚቀር አይመስለኝም። በየትኛውም ሀገር ውስጥ ማንም ሰው ቢሆን ከህግ የበላይ ሊሆን አይችልምና።

እርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲከኝነቱ ብቻ የታሰረ ግለሰብ ለመኖሩ ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም። ይሁንና ‘አንድ ሰው ፖለቲከኛ ስለሆነ ወንጀል ቢፈፅምም መታሰር የለበትም’ የሚል ከሆነ እሳቤው የትኛውንም ወገን አያስማማም። ምክንያቱም በየትኛውም ሀገር ውስጥ በዴሞክራሲያዊ አግባብ የተመረጠ መንግስት ከህዝብ በተሰጠው አደራ መሰረት የህግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ ሰላለበት ነው። እናም በተቃዋሚነት የተሰለፈም ይሁን የመንግስት ባለስልጣን በወንጀል እስከ ተጠረጠረ ድረስ በህግ ጥላ ስር ውሎ ጉዳዩ መጣራቱ አይቀርም።

በዚህ ዙሪያ መንግስት ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነ በቅርቡ በተለያዩ ክልሎችና ከተማዎች የህዝብን አደራ ወደ ጎን በማለት በኪራይ ሰብሳቢነት በተዘፈቁ አመራሮችና በየደረጃው በሚገኙ አስፈፃሚዎች ላይ የወሰደውን አስተማሪ እርምጃ መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል።

የኢፌዴሪ ህገ -መንግስት ለዜጎች ካጎናፀፋቸው ዴሞክራሲያዊ መብቶች መካከል የቡድንና የግለሰብ መብቶችን ይገኙበታል። መብቶቹ በዋነኛነት የአመለካከትና ሃሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነት እንዲሁም አቤቱታን ማቅረብን የሚያጠቃልሉ ናቸው።

እነዚህ መብቶች ሀገራችን ውስጥ ጥበቃ እየተካሄደላቸው ያሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ በፖለቲካው ምህዳር ውስጥ በተጨባጭ ገቢራዊ እየሆኑ የመጡም ጭምር ናቸው። አንድ ግለሰብ ወንጀል እስካልሰራ ድረስ መብቶቹ በህገ መንግስቱ ዋስትና ያላቸው ናቸው።

መንግስት በህገ-መንግስቱ ላይ በግልፅ የተደነገጉት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶች እውን እንዲሆኑ ከመታገሉም በላይ፣ እንዳይሸራረፉም በፅናት ታግሎላቸዋል፤ እየታገለላቸውም ነው። በተለይም ሚዲያ በሀገሪቱ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ እመርታዎች ላይ የራሱን እሴት የሚጨምር መሳሪያ አድርጎ ነው የሚመለከተው፡፡

ሆኖም ሚዲያ ህግና ስርዓትን አክብሮ ካልተንቀሳቀሰ ከጠቀሜታው ባሻገር፤ በሁለንተናዊ የዕድገትና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዓላማዎች ላይ ጉዳት ሊያደረስ እንደሚችልም እስካሁን ከታዩት ዝንባሌዎች መረዳት ይቻላል።

እርግጥ በእኔ ዕይታ መንግስት የሚዲያን ጉዳት ለማስቀረት ሲል ጥቅሙን የመገደብ አካሄድ አይከተልም። እንደ ሌሎቹ የዴሞክራሲ ግንባታ ስራዎች ሁሉ፤ ሚዲያው ነፃና ጤነኛ ሆኖ እንዲያድግ ፈርጀ ብዙ ተግባራትን ማከናወኑንም ማጤን ያስፈልጋል።

በመሆኑም ጋዜጠኛ እንደ ማንኛውም የሙያ ዘርፍ የሥራ ነፃነት ስላለው ብቻ የሀገሪቱን ህግና አሰራርን እንዲሁም የራሱን የስነ-ምግባር ደንብ እየደፈጠጠ እንዳሻው ሲሆን ዝም ተብሎ ሊታይ አይችልም።

እናም አንዳንድ የግል ፕሬሶች ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ከጀርባ በጦር ለመውጋት ሲፈልጉ፣ የሚዲያ ነፃነትን ጭንብል ተሸፋፍነው ወንጀል ለመስራት ሲሞክሩ እንዲሁም ህግና ስርዓትን ደፍቀው ተጠያቂነትንና ሃላፊነትን አንከተልም ሲሉ ከፍ ብሎም የፀረ ሰላም ሃይሎችንና የአሸባሪዎችን አጀንዳ ሲያራግቡ የሚዲያውን ጤናማነት በሚቆጣጠሩት የሀገሪቱ ህጎች መጠየቃቸው የሚቀር አይመስለኝም። ምክንያቱም በማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ የህግ የበላይነት ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ ባለመሆኑ፣ በሚዲያ ውስጥም የሚሰራ ሆነም ማንኛውም አካል ህጋዊ አሰራሮችን ተላልፎ ሲገኝ በህግ አግባብ የሚጠየቅ በመሆኑ ነው።

በመሆኑም አንድን ጉዳይ በስሜታዊነትና በደፈናው ከመፈረጅ በፊት፤ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዛሬ ላይ የማይገሰሱ ኢትዮጵያዊ ሐብቶች መሆናቸውን መገንዘብ አለባቸው። ከዚህ ጎን ለጎንም በየትኛውም መንግስታዊ ተግባራት ውስጥ እንደሚታዩት ችግሮች ሁሉ፤ በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አከባበር ውስጥ የሚከሰቱ ጉድለቶች ካሉ እነርሱንም ከዚሁ አግባብ መመዘን ይገባል። ከነባራዊ ሃቁ ባለመሸሽ አገራችን ውስጥ በመያራምደው ፖለቲካዊ አመለካከት አሊያም በጋዜጠኝነቱ ወይም በሌላ ሙያ የሚታሰር ዜ አለመኖቱን መገንዘብ ያስፈልጋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy