Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አሁንም እየፈተነን ያለ ችግር

0 330

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አሁንም እየፈተነን ያለ ችግር

                                                         ደስታ ኃይሉ

ህገ ወጥ ስደት በአገራችን ላይ እያስከተለ ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጫና ቀላል አይደለም። ይሁን እንጂ መንግሥት ይህን የዜጎችን ህይወት የሚቀጥፍ አደገኛ ተግባር በቁጥጥር ስር ለማዋል ከህግ የበላይነት አኳያ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት ህገ መንግሥታዊ በመሆኑ በቅርቡ ሁኔታዎች እስኪስተካከሉ ድረስ ታግዶ የነበረው የውጭ አገር የስራ ስምሪት በቅርቡ መፈቀዱ ችግሩን የመቅረፍ አንድ አካል መሆኑ ግልፅ ነው።

በዚህ ፅሁፍ መንግስት ለመቅረፍ ችግሩን እስካሁን ድረስ ያከወናቸውን ተግባራት ለመመልከት እንሞክራለን።

ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ መንግስት በሀገራችን የተንሰራፋውን ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ መንቀሳቀስ ሲጀምር፤ ስራ አጥነት መቅረፍ አንደኛው ተግባሩ በማድረግ ነበር፡፡

በዚህም በከተማና በገጠር የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትን በማደራጀት እንዲሁም የብድር አገልግሎት በመስጠት ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ዜጎችም በየሙያቸው በመሰማራት ለሀገራዊ ልማት ከፍተኛ ጉልበትና አቅም መሆን መቻላቸውን አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወትት መንግስት ለስራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድልን በመፍጠር መንግስትነት ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል፤ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋን ለመከላከልም ከግንዛቤ ማስጨበጥ እስከ ተጨባጭ ርምጃዎችን መውሰድ ደረጃም ደርሷል።

እንደሚታወቀው ሁሉ በመላ ሀገሪቱ በተዋረድ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ምክር ቤት ተቀቁሟል። በዚህም ህበረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ሰፋፊ መድረኮች ተፈጥረው እንዲወያይበትና የመፍትሔው አካል እንዲሆን በየክልሉ በርካታ ተግባራት ዕውን ሆነዋል።

በአሁኑ ወቅት በመንግስት በኩል ያለው ቁርጠኝነት በመዋቅሩ ውስጥ የሚገኙ ኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ እየተደረገ ባለው አጠቃላይ ክትትልና ርምጃ ሁኔታው ወደ መሻሻል ያዘነበለ ነው።

የግለሰቦቹን ተግባር በተገቢ ሁኔታ ለማረም ህብረተሰቡና መንግስት ተቀናጀተው መስራት እንደሚገባቸው እነዚህ ጥቆማ የሰጡኝ ወገኖች ያስረዳሉ። በመንግስት በኩል ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ችግሩን ለመፍታት የፖሊሲ፣ የፕሮግራምና የህግ ማዕቀፎች ተበጅተው ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ነው።

ጉዳዩን የሚከታተል ግብረ ኃይል ከማቋቋም አንስቶ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን እስከመስጠት ድረስ ያሉት ጥረቶች “ይበል” የሚያሰኙ ናቸው። ይሁንና ጥረቶቹ ህዝብን ባማከሉና ወደ መሬት ወርደው ገቢራዊ በሚሆኑ አሰራሮች ይበልጥ ሊደገፉና የችግሩን አስኳል ለይተው ሊያወጡ በሚችሉበት ሁኔታ መቃኘት ይገባቸዋል።

ጥረቶቹ የሚያስገኟቸው ውጤቶችም የጉዳዩ ዋነኛ ተዋናይ ከሆኑት ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች አኳያ እየተመዘኑ፣ ተመልሰው ህዝቡን የሚያስተምሩበት መንገድም እየተመቻቹ ናቸው። የስደቱ መንስኤና መፍትሔ ቢቀመጥም አሁንም ችግሩን ልንላቀቀው አልቻልንም።

ዛሬ በተለያዩ መንገዶች ወደ ሌሎች ሀገራት ውስጥ የሚገቡ ዜጎች በመንገድ ላይ ህይወታቸው ካላለለፈና ወደ መዳረሻ ሀገሮች በሰላም ከገቡ ዕጣ ፈንታቸው ብዝበዛ ወይም ለህልፈተ-ህይወት ከሚዳርግ አደገኛ ሁኔታ ጋር መላተም ነው።

መንግስት ብቻውን ምንም ሊያደርግ አይችለም። እናም እውነታውን ቤተሰብ ለልጆቹ ማስረዳት አለበት። እዚህ ሀገር ውስጥ ያለውን እውነታ መግለፅ ይኖርበታል። “ከመሞት መሰንበት” እንዲሉ ችግሩ የወገንን ህይወት የሚቀጥፍ በመሆኑ ቤተሰብ ቁርጠኛ አቋም መያዝ አለበት።

የሚብለጨለጩ ነገሮችን አድርገው አሊያም ተጫምተው የወጣቱን ቀልብ ሊስቡ የሚችሉ ከስደት ተመላሾች ገንዘቡን በስንት ዓመት ውስጥና እንዴት ሊያገኙት እንደቻሉ፣ ገንዘብ አገኛለሁ ብሎ በባሪያ ፍንገላ ንግድ ሰለባ መሆንም ሊከሰት እንደሚችል ማስረዳት የቤተሰብ ተግባር መሆን አለበት።

የስደት ዓለም ኑሮ እንከን አልባና ምንም ውጣ ውረድ የሌለበት አለመሆኑንም ማስገንዘብ ያስፈልጋል። የስደት ዓለም እጅግ አሰቃቂና ህይወትን ቀጣፊ ብሎም የሰው ልጅ እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ፍየልና በግ የባሪያ ንግድ የሚካሄድበት መድረክ መሆኑንም መግለፅ ተገቢ ነው።

ከስደት ህይወት ውርደት እንጂ ክብር እንደማይገኝ፣ በህይወት የመቆየት ጉዳይ በነጠላ ክር ላይ እንደተንጠለጠለ ዳቦ ያህል እንኳ ተስፋ የሌለው ለልጆች ማስረዳት ተገቢ ነው። በሌላ በኩልም እዚህ ሀገር ውስጥ ሁሉም ነገር ተሟልቷል ሊባል የሚችል ባይሆንም፤ በመንግስት በኩል የተፈጠሩ ወጣቶችን የመደገፍ ሂደቶችን ማስረዳት ያስፈልጋል። የግንዛቤ መስጫው ስራ ሁሉንም ያካተተ መሆን አለበት።

ያም ሆነ ይህ ግን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከሀገር ወጥቶ ለመስራት እስከፈለገ ድረስ ህጋዊ ሆኖ በመንግስት ዕውቅና መብቱና ክብሩ ተጠብቆለት የሚሰራበት ምቹ ምህዳር ተፈጥሯል። እዚህ ሀገር በመከናወን ላይ ካለው ተምሳሌታዊ ልማታዊ ተግባር ባሻገር፤ ዜጎች ወደ ውጭ ሄደው እንዲሰሩ በመንግስት የወጣው የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 ይህን ህጋዊነት እያረጋገጠ ነው።

እንደሚታወቀው ህገ ወጥ ስደት የሀገርንና የወገንን ክብር የሚነካ ባርነት ነው። እናም ዜጎች ሰብዓዊ መብታቸውና ክብራቸው ሳይነካ መንገስት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ መጠቀም ይኖርባቸዋል።

ማንኛውም ዜጋ በሀገሩ ለመስራት ካልፈለገና ‘በውጭ ሀገር ሰርቼ ሃብት አፈራለሁ’ ብሎ ካሰበ የሚከለክለው አካል አይኖርም። ምክንያቱም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት ህገ መንግስታዊ እውቅና እና ጥበቃ ያለው ነው። ማንኛውም ዜጋ በፈለገው ጊዜና ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራትና ሃብት የማፍራት የማይገሰስ ህገ መንግስታዊ መብት አለው። ይህን ማንም ሊቀለብሰው አይችልም። ይህን መብት መቃወም ህገ መንግስቱን መፃረር ነው።

ታዲያ ይህን ህገ መንግስታዊ መብት በአግባቡና ህጋዊ በሆነ ሁኔታ መጠቀም ይገባል። አንድ ዜጋ ባሻው ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ስላለው ብቻ ራሱን ለአደጋ ቤተሰቡን ደግሞ ለችግርና ለስጋት አጋልጦ ህገ ወጥ መንገድን መጠቀም ያለበት አይመስለኝም።

የኢፌዴሪ መንግስት ይህን የዜጎችን እንግልትና ችግር በመመልከት ዜጎች ለስራ ወደ ውጭ ሲጓዙ ከሞት፣ ከእንግልትና ከስቃይ ይላቀቁ ዘንድ ህጋዊ የአሰራር ማዕቀፍን አበጅቷል። በተለይም ከላይ የጠቀስኩት አዋጅ ቁጥር 923/2008 የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ተፈቅዷል።

በዚህ አዋጅ ተመርቶ በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ የስራ ስምሪት ማድረግ ራስን ከአደጋ ቤተሰብን ደግሞ ከሃሳብና ከሰቀቀን የሚታደግ ይሆናል። ይህን አዋጅ ተጠቅሞ በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ መጓዝ የህገ ወጥ ደላላዎችን መንገድ ይዘጋል። እናም መንግስት በፈቀደው የውጭ አገር የስራ ስምሪት አዋጅ መሰረት መስራት የፈለገ ሊጓዝ እንደሚችል ማወቅ ይኖርበታል።

በአጠቃላይ ህጋዊነትን ተቀብሎ በህግ አግባብ ማንኛውንም ነገር ማከናወን ራስን ከአደጋና ከውርደት በመጠበቅ የሀገርን ክብርም ማስጠበቅ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ከአዋጁ ጎን ለጎንም በክልሎች ውስጥ ህገ ወጥ ስደትን ለመግታት ብርቱ ጥረት መደረግ ይኖርበታል። ይህን ማድረግ ከተቻለ እየፈተነን ያለውን የህገ ወጥ ችግር መቅረፍ ይቻላል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy