Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አረንጓዴ ልማት

0 1,669

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አረንጓዴ ልማት

ወንድይራድ ኃብተየስ

ባለንበት ዘመን አለማችንን ስጋት ውስጥ ከከተቷት ቀውሶች አንዱ የአየር ንብረት ለውጥ ነው ፡፡ታድያ  ኢትዮጵያም የዚህ ቀውስ ሰለባ እንዳትሆን ከወዲሁ ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ትገኛለች፡፡ አገራችን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂዎችን ለመተግበር አራት ዋና ዋና መሰረታዊ ግቦችን ይዛ ተነስታለች፡፡እነዚህም የግብርና ልማትና የመሬት አጠቃቀም ፣ የደን ልማትና ጥበቃ ፣ የተሻሻሉና ተመራጭ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለአንዱስትሪ ልማት፣ ለትራንስፖርት አገልግሎትና ለግንባታ ስራ ማዋል፡ እንዲሁም ታዳሽ ሃይልን የማመንጨት ሥራ ናቸው፡፡

ስለሆነም የደን አና የአፈር መራቆትን የሚከላከሉ፣ አካባቢውን ለልማት የሚያውሉና   ቀጣይ አቅምን የሚያጎለብቱ፣ በጎ ተሞክሮዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በማሰስ ጥቅም ለይ ማዋል ተችሏል፡፡እነዚህን ተሞክሮዎችና ቴክኖሎጂዎች  በተለያዩ የገአሪቱ ክፍሎች በማስፋፋት ሙከራ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ አረንጓዴ ልማቱ በኢኮኖሚው ላይ ከሚኖረው አዎንታዊ አስተዋጽኦ ባሻገር በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚያደርሰውን ጫና ከመቀነስ አንፃርም ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡

የግብርናልማትና የመሬት አጠቃቀምን በተመለከ ቴክኖሎጂው ተራራማና ደጋማ በሆኑ አካባቢዎች የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የዕፅዋትና የፍራፍሬ ልማት እንዲሁም የአፈርና ውኃ ዕቀባ ሥራዎችን በማቀናጀት እየሰራ ነው፡፡ የተጎዱ መሬቶችን ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ አፅድቶ እንዲያገግሙ በማድረግ የዕፅዋት እና እንሰሳት አይነቶች እንዲበራከቱ አድርጓል፡፡የጓሮ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን አልምቶ ራሱንና ቤተሰቡን በመመገብ  ጤናው የተጠበቀ ትውልድ እንዲፈጠር ከማድረግ አንፃርም የማይናቅ ሚና ተጫወቷል፡፡ ይህም የህብረተሰቡን ገቢ በማሻሻል የተገነባው ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪው የሚደረገውን ሽግግር የሚያግዝ ሆኖ ተገኝቷል፡፡   

  

የተጎዱ መሬቶችን እንዲያገግሙ ለማድረግ የተለያዩ ገር በቀል ዛፎችን መትከል ዋነኛው አማራጭ ሆኖ እየተሰራበት ይገኛል፡፡ ለዚህም በርካታ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎችን አዘጋጅቶ ችግኞችን በማፍላትና ገበያ ላይ በማቅረብ በአነስተኛ እና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ ግለሰቦች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል፡፡

ለአካባቢ ጥበቃ አጋዥ ናቸው ተብሎ  ትኩረት ከተሰጣቸው መካከል የቀርከሃ ልማት አንዱ ነው፡፡ የቀርከሃ ምርት በቶሎ የሚያድግ ፤ብዛት ያላቸውና የሚጠላለፉ ረዣዥም ሥሮች ያሉትና አፈርን አቅፎ መያዝ የሚችል ነው፡፡ ቀርቀሃ ለማገዶ ፣ ለቤት ውስጥ ቁሳቁሶች እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ግልጋሎት መዋል መቻሉም ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ በአየር ውስጥ ያለውን ሙቀት አምጪ ጋዝ በመምጠጥ  ረገድም ለአረንጓዴው ልማት አስተዋጽኦው ከፍ ያለ በመሆኑ መንግስት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶት እየሰራበት ይገኛል፡፡

አረንጓዴ ልማቱን ለመደገፍ አገራችን ከፍተኛ የሆነ የጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ከፀሃይ ኃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ ቴክኖሎጂን በአማራጭነት እየተጠቀመች ትገኛለች፡፡ በየትኛውም መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና በቂ የፀሃይ ጨረር በሚገኝባቸው ቦታዎች ሁሉ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ቴክኖሎጂ ስለሆነ በአገራችን ተመራጭ ሆኗል፡፡ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን አዎንታዊ አስተዋፅኦ ከዚህ ጋር አያይዞ ማየት ቢያስፈልግ  የሃይል አማራጭ በመሆን ብክለትን ለመከላከል የሚያስችልና  በደን ሀብት ሽፋን ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጫናም የሚታደግ መሆኑ ነው፡፡

የአገልግሎት ጊዜን ማራዘሚያ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም  ሌላኛው የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ ከሚያስችሉ ዘዴዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የውሃና የአፈር መጠበቂያ ስትራክቸሮችን በመስራት የሃይል ማመንጫ እና የመስኖ ግድቦችን ከደለል ብሎም መንገዶችን ከመንሸራተት ለመከላከል የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ በመላው አገሪቱ የሚገኙ አርሶ አደሮች  ወንዞችን እየተንከባከቡ የተለያዩ እርከኖችን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በተካሄዱ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎችም ቀደም ሲል የተራቆቱ አካባቢዎች በዕፅዋት እየተሸፈኑ ይገኛሉ፡፡ የደረቁ ምንጮች መፍለቅ ጀምረዋል፤ የአፈር መሸርሸር በእጅጉ ቀንሷል፤የወንዞች የውሃ መጠን ጨምሯል፤ የዛፍና የደን ሽፋን ዕድገት አሳይቷል፤ መስኖን የመጠቀም ዕድልም ተፈጥሯል፡፡

በአገራችን የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ከግብርና መርህ ወደ ኢንዱስትሪው መርህ ለመሸጋገር የሚደረገው ግስጋሴ ነው ፡፡ ይህን ትልም ለማሳካትም በስኳር ምርት ከፍተኛ የሆነ ምርታማነትን እንደሚያስገኙ በሚታመኑ የአገሪቱ ስድስት ክልሎች ሰፊ የእርሻ መሬቶችን በመጠቀም የስኳር አገዳ ምርት እየተመረተ ነው፡፡ ከዚህ መጠነ ሰፊ የሆነ ምርት የሚወጣውን ተረፈ ምርት ለሃይል ፍጆታ ማዋል ተጀምሯል፡፡ ቴክኖሎጂው ጭስ አልባ በመሆኑ የጤና መታወክ እና ተዛማጅ አደጋዎችን አያስከትልም። ይህም ተወዳጅነቱን ይበልጥ ከፍ አድርጎታል፡፡

በሌላ በኩልም በአካባቢ ጥበቃ በሁለት በኩል ጥቅም ሊያመጡ የሚችሉ ተክሎችን ወደ ሀገሪቱ አምጥቶ በማስተዋወቅ ሰፊ ስራ ተከናውኗል፡፡ ለአብነት ያህልም የጃትፎ ተክል ፍሬን በመጭመቅ በታዳሽ ሃይል አማራጭነት ባዮ- ዲዝልን ለህብረተሰቡ የኢነርጂ ምንጭ እንዲሆን እንዲሆን ማድረግ ተችሏል፡፡ ተረፈ ምርቱንም ለሳሙና፣ ለማዳበሪያና ለመድኃኒት መስሪያ ለማዋል የሚያስችል ቴክኖሎጂን በመጠቀም አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል፡፡እናም አረንጓዴ ልማቱን  ከመደገፉም በዘለለ  ማህበራዊ ጠቀሜታዎችን በመስጠትም የላቀ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡

እንደ አውሮፓውያንኑ ዘመን አቆጣጠር በ2025 ኢትዮጵያ ትርፍ ካርቦንዳይኦክሳይድ የማትለቅበት ደረጃ ላይ የመድረስ ግብ ሰንቃ ሰፊ ለውጥ እያመጣች ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ሃይልን ከታዳሽ ምንጮች በሰፊው በማምረት ለሀገሪቱ ከሚያስፈልገው ሃይል ውጭ ያለውን ለጎረቤት አገሮች የመሸጥ እቅድ የዛ እየሰራች ነው፡፡

የኤሌክትሪክ ሃይልን ለትራንስፖርት (ለባቡር) የምንጠቀምበት ቴክኖሎጂም ሥራ ላይ ውሏል፡፡ በዚህ ሂደትም የካርቦንዳይአክሳይድ ልቀት ሳይኖር የኤሌክትሪክ ሃይልን መጠቀም እንደሚቻልና በከፍተኛ ምንዛሬ ከውጭ የሚገባውን  ነዳጅ ለመቀነስ የሚያስችል ጅምር ታይቷል፡፡

የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን በማምረት እና ወደ ህብረተሰቡ እንዲደርሱ በማድረግ የማገዶ አጠቃቀምን ከ50 በመቶ በላይ በመቀነስ የደን መጨፍጨፍን ለመከላከል የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምም ተችሏል፡፡

አገራችን የኢንዱስትሪ ፍሳሽን በሥነ – ህይወታዊ ዘዴ በማከም ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህም በሰዎች እና እንስሳት ላይ ሊደርስ የሚችለውን የጤና ቀውስ ለመፍታት ተችሏል፡፡ ይህ ክንዋኔ የወራጅ፣ የከርሰ ምድር ውሃንና አፈርን ከብክለት መታደግ እንደሚቻል አሳየቷል ፡፡  

ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት የግብርና ምርትንና የኢንዱስትሪ መሰረትን ማጠናከር እና የውጭ ገበያን ማሳደግ ትኩረት አድርጋ እየሰራች ትገኛለች፡፡ በመልማት ላይ ያሉ ሀገሮች የአየር ንብረት ለውጥን የመመከት ወሳኝ ሚና እንዳላቸውም ተገነዘባ የድርሻዋን በመወጣት ላይ ናት፡፡ ይህም የሀገሪቱን ገጽታ በመገንባት ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ እስካሁን በሀገሪቱ የተካሄዱት የተፈጥሮ እንክብካቤዎችና የደን ልማት ስራዎችም ያስገኙት  ውጤት በህዝቡና በመንግሥት ዘንድ ላቅ ያለ ተቀባይነትን ያስገኘና ቀጣይነቱን የተረጋገጠ ነው፡፡  

ቀጥላልይ…

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy