Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እውን የትግራይ የበላይነት አለን?(ክፍል አንድ)

0 358

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እውን የትግራይ የበላይነት አለን?

                                                  ቶሎሳ ኡርጌሳ

(ክፍል አንድ)

“እንዴት?” አሉኝ፤ አዛውንቱ አቶ ይመር መሸሻ፤ ድምፃቸውን ጎላ አድርገው በቁጣ መንፈስ። አልደነገጥኩኝም። ለዓመታት አሳምሬ አውቃቸዋለሁ። ወትሮም ወጋቸውን የሚጀምሩት ከመሃል ነው። ‘ነገርን ከመሰረቱ መጀመር ወጌን አያጣፍጥልኝም’ የሚሉት፣ ለእኔ ግን ሁሌም የማይገባኝ ፈሊጥ አላቸው። አዛውንቱ ዕድሜያቸው ወደ 80ዎቹ አጋማሽ አካባቢ ይገመታል። ግና እሳቤያቸው እንደ ዕድሜያቸው አይደለም—የአንድን ጉዳይ ስረ መሰረት አይስቱም። ደግመው ፊታቸውን ቅጭም አድርገው ተመለከቱኝ። ግራ እጃቸውን ወደ ጭንቅላታቸው ሰደድ አድርገውም እንደ ጥጥ ባዘቶ የነጣ ፀጉራቸውን ቆፈር…ቆፈር አደረጉት። ወዛሙ ብስል ቀይ ፊታቸው እንደ በርበሬ ቀላ። ፍም መሰለ። አሁንም አልፈራኋቸውም።…

ይልቁንም ወጋቸውን እንዲቀጥሉ በማሰብ “አባባ ይመር፤ ምኑን ነው ‘እንዴት’ ያሉት?” ስል ጠየቅኳቸው። ለአፍታ ቀዩ፣ ወዛምና ገራገር ፊታቸው የፈገግታ ፀዳልን ተላበሰ። ፈገግታቸውን እየመገቡኝም ትክ ብለው ተመለከቱኝ። አስተዋይነት የደረጀበትና የሚነበብበት አባታዊ ምልከታ ነበር። በእውነቱ ሲቆጡም ሆነ ፈገግ ሲሉ አንጀት የሚያርሱ አዛውንት ናቸው።…‘ቁጣውም ይሁን ሳቁ ይማርካል’ ሲባል ሰምታችሁ ታውቁ ይሆን?—አዎ! ርሳቸው እንዲያ ዓይነት ሰው ናቸው።….

አባባ ይመርን ከስምንት ዓመታት በላይ አውቃቸዋለሁ። ማልጄ ጧት በመነሳት በአንድ ጎኑ አቦል እንጂ በረካና ቶና ከሌለው፣ በሌላ ዘውጉ ደግሞ፤ ኢትዮጵያዊ ባህልን ከሚያስተዋውቀው “ዘመን አመጣሹ” የጀበና ቡና ከምጠጣባት መሸጫ ደጃፍ አጥቼያቸው አላውቅም። ቡና ነፍሳቸው ነው። አንድ ሲኒ ሱና ከመቼው እንደ ቀዝቃዛ ውሃ ጅው አድርገው እንደሚጠጡ ይገርመኛል። ጠጥተው ከጨረሱ በኋላም ፍንጃሉን እየተመለከቱ “የቡና ስባቱ መፋጀቱ!” ይላሉ። ባገኘኋቸው ቁጥር ሰላምታ ሳቀርብላቸው “ድሮ በጉ ላይ ዶሮ አስሬ እየነዳሁ በምሄድበት ገንዘብ ይኸው አንድ ፍንጃል ቡና እጠጣበታለሁ። ክብሩ ይስፋ፣ ይሄንስ ማን አየው በል?!” የሚል ምላሽ ከመስጠት ቦዝነው አያውቁም። ትንሽ ፋታ ወስደውም “አንተስ እንዴት ነህ ልጄ?” በማለት ስለ እኔና ስለ ቤተሰቦቼ መጠየቅ የዘወትር ልምዳቸው ነው።

እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ከእኚህ ዕድሜ ጠገብ አዛውንት ብዙ ነገር ተምሬያለው። ባለኝ ነገር ተመስገን ብዬ መኖርን፣ ለእውነት ሟች መሆንን፣ በሰከነ አስተሳሰብ መመራትንና ከመፈረጅ ይልቅ የነገሩን ስረ መሰረት እስከ መጨረሻው ድረስ መፈተሽ እንዳለብኝ ያስተማሩኝ እኚሁ ከኦሮሞና ከአማራ ብሔረሰቦች የተገኙት አባባ ይመር ናቸው። ስለ እርሳቸው ብዙ አስብኩኝ።…ሃሳቤን ግን “እንዴት? ያልኩህማ ነገሩ ወዲህ ነው።…” የሚለው የአዛውንቱ ጎርናና ድምፅ አናጠበኝ። ከመሃል የጎረዱትን ጉዳይ ከእኚህ ዕውቀት ጠገብና ሚዛናዊ አባት ለመስማት ጆሮዬን ቀሰርኩ። ወጉ የእርሳቸው አይደለም። ሁለት ወጣቶች የጀበና ቡና መሸጫ በረንዳው ላይ ከእኔ ከመምጣቴ በፊት አጠገባቸው ቁጭ ብለው ይጨዋወቱ ኖሯል። የርሳቸውን አንደበት ተውሼ የወጣቶቹን ጨዋታ እንዲህ ባስነብባችሁስ?…

ወጣት አንድ፦ ‘ቅድም ፌስ ቡክ ላይ ምን እንዳነበብኩ ታውቃለህ?…የትግራይ ህዝብ

             ሊገነጠል ነው አሉ።’

ወጣት ሁለት፦ ‘ይህን ሀገር በበላይነት ሲያስተዳድሩ ኖረው እንገነጠላለን ቢሉ ማን

              እሺ ይላቸዋል።’

ወጣት አንድ፦ ‘ታዲያስ! ማንም አይሰማቸውም።’

ወጣት ሁለት፦ ‘የትግራይ ህዝብ የበላይነት መቆም እንዳለበት ኢሳትም ሲናገር

             ሰምቻለሁ።’…

በዚህ ጨዋታ መሃል ላይ አዛውንቱ አባባ ይመር ጣልቃ ይገባሉ—“ልጆቼ የተወራው ሁሉ እውነት አይደለም። ይሄ የምትሉት ነገር ደግም አይመስለኝም። ያን ህዝብም የሚመለከተውም አይዶለም” በማለት። ሁለቱ ወጣቶች ግን አዛውንቱን አያውቋቸው ኖሮ፤ “ሼባው ወያኔ ነሽ እንዴ?!” ብለዋቸው እብስ ይላሉ።…ለካስ አባባ ይመር ነገሩ ከንክኗቸውና ከራሳቸው ጋር ሲነጋገሩ ቆይተው ነው—እኔ የጀበና ቡና መሸጫው ጋ ስደርስ ጉዳዩን ሊያጫውቱኝ ፈልገው “እንዴት?” ማለታቸው።

በተለይ ‘የትግራይ ህዝብ ሊገነጠል ነው። የትግራይ ህዝብ የበላይ ነው” የሚሉት ወጣቶቹ ከፌስ ቡክ የቃረሟቸው ሃሳቦች አግራሞትን ጭረውባቸዋል። የትግራይ ህዝብን ማንነት ጠንቅቀው ለሚያውቁትና ዕድሜያቸውን ሁሉ በትግራይና በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ውስጥ ከዚህ ህዝብ አብረውት ለኖሩት ለእኚህ አዛውንት ጉዳዩ የፌዝ ያህል የሚቆጠር ነው። ርግጥ እንደ አዛውንቱ ዓይነት ዕድሜ ጠገብ ሰው ትናንትን ከዛሬ ጋር በማንሰላሰል አሁን ያለውን ትክክለኛ እውነታ ብያኔ ለመስጠት አይከብደውም።

እንደ ርሳቸው ዓይነት ዕውቀትንና ተሞክሮን ከዕድሜ ጋር አስተሳስሮ ሃሳብ የሚሰጥ ሰው፤ እንደ ፈላስፋው ዲዩጋን በጠራራ ፀሐይ በፋኖስ መብራት ሰው ፈልጎ የማግኘት ያህል ከባድ ይመስለኛል። እናም በጉዳዩ ዙሪያ ብዙ ተጨዋወትን። የአንዳንድ የሀገራችን ወጣቶችን ስሜታዊነትንና ችኩልነትን እንዲሁም የግንዛቤ እጥረትን ብሎም ስለ ትግራይ ህዝብን ማንነት አለማወቅ ተጨዋወትን። የጫወታችን ማጠንጠኛም ቀልቤን ሳበው። ይህን አጭር ትንታኔ እንዳሰናዳም ምክንያት ሆነኝ። እነሆ ‘እውን የትግራይ የበላይነት አለን?’ የሚል ርዕስን በወረቀቴ ራስጌ ላይ እንድከትብ ሰበብ ሆነኝ። ‘ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም’ እንዲል የሀገራችን አርሶ አደር፤ ሃሳቤን “እነሆኝ!” አልኩኝ።…

የፅሑፌ ራስ ወይም ርዕስ ጥያቄያዊ ነው። ግና የጥያቄው መነሻ ምንም ይሁን ምን፣ እዚህ ሀገር ውስጥ የትግራይ ብሔር የበላይነት “አለ” ወይስ “የለም” የሚለው ጥያቄ የግድ መመለስ ይኖርበታል። ካለ፤ መገለጫው ምንድነው?፣ መዳረሻውስ ወደ የት ነው?፣ ከሌለ ደግሞ፤ “አለ” የሚሉ ወገኖች መነሻቸው ምን እንደሆነና መድረሻቸው እምን ድረስ ሊዘልቅ እንደሚችል አፍታትቶ መመልከት ይገባል። ምክንያቱም ሃሳቡ ፈረንጆች እንደሚሉት “The end Justifies the means” ዓይነት በሚሉት ልኬታ መቃኘት ስለሚኖርበት ነው። የመጨረሻው ውጤት፣ ለውጤቱ መገኘት ምክንያት የሆነን እውነታ ያረጋግጣል እንደሚባለው ማለቴ ነው።

እናም አንድን እውነታ መኖሩን አሊያም አለመኖሩን ካረጋገጥን በኋላ በቀጥታ “መነሻው ምንድነው?” ብለን ስንጠይቅ፤ መነሻውና መድረሻው ነሲባዊና ሃሳባዊ ሊሆን አይችልም—በመስፈሪያ የሚታወቅ ልኬታ ያለው እንጂ። ልኬታው ሲሰፈር ደግሞ፤ “ባዶ” ወይም “ዜሮ” የመሆን ዕድል ሊኖረው ይችላል—“ደፈናዊ ጥላቻ”  እንደ ወለደው ተረክ ዓይነት። አሊያም መስፈሪያ መለኪያ ቁጥሩ እጅግ በዝቶ ‘ከዚህ እስከዚህ ድረስ’ ተብሎ የሚቆጠርና መገለጫ ያለው ወይም “መድረሻ የሌለው” (infinity) ሆኖ የትክከለኛነቱ ቀመር ንፋስ አመጣሽና አድማሳዊ ሆኖ መጨበጫና መቋጫ የሌለው ሊሆን ይችላል። እናም “የትግራይ የበላይነት” መኖርና አለመኖር ጉዳይም ከእነዚህ መለኪያዎች ውስጥ በአንዱ ስር የሚወድቅ ይመስለኛል።

ለማንኛውም እስቲ ወደ እውነታው ጓዳ ለመግባት አብረን እንዝለቅ።…ሆኖም የትግራይ ህዝብ የበላይነት “አለ” ወይስ “የለም” የሚል ብያኔ ለመስጠት እውነታዎችን ከማንሳቴ በፊት፤ በቅድሚያ ስለ ትግራይ ህዝብ ማንነት በጥቂቱም ቢሆን ማውሳት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ምክንያቱም እኔ እንደ አባባ ይመር አንድን ጉዳይ ከመሃል የመጀመር ልምድ ስለሌለኝ ነው። ‘ነገርን ከመሰረቱ’ ከሚሉት ሰዎች ውስጥ ነኝ።

የትግራይ ህዝብ የሀገራችን ስልጣኔ መነሻ ነው። የስልጣኔ ዘውጋችን ነው። ለኢትዮጵያ አንድነት ከጥንት የሳባዊያን ዘመን እስከ ዋስና ጠበቃ ሆኖ በመስራት የሚታወቅ፣ እንደ ሌላው የሀገራችን ህዝብ ለፍቶና ጥሮ ግሮ የሚያድር ታታሪ ህዝብ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ፤ የትግራይ ህዝብ ከጎረቤት ክልሎችም ይሁን ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል ጋር በደም፣ በባህልና በቋንቋ የተሳሰረ ነው። የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያዊነት ቀንዲልና መቅረዝ ነው ብል ከእውነታው መራቅ አይሆንብኝም። ርግጥ ይህ ህዝብ ዛሬ ለተፈጠረችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ሲል የሞተ፣ የቆሰለ፣ ንብረቱን ያጣ ነው። በተለያዩ ወቅቶች ኢትዮጵያን ሊወሩ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የመጡ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ቅሌታቸውን ተከናንበው እንዲመለሱ ያደረገ ነው።

ከሁለት የቅርብ ጊዜያችን ትውስታዎች እንነሳ—ከደርግ ጋር የተደረገውን እልህ አስጨራሽና መራር ትግል እንዲሁም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ከሻዕቢያ ጋር በተደረገው ትንቅንቅ ከሌሎች የሀገራችን ህዝቦች ጋር በመሆን ያደረገው ተጋድሎ።

በትጥቅ ትግሉ ወቅት የትግራይ ህዝብ ያላየው የፍዳ ዓይነት የለም። ሞቷል፣ ቆስሏል፣ ደምቷል፣ ንብረቱን አጥቷል። በእውነቱ በትግሉ ወቅት እንደ ትግራይና አካባቢው አበሳውን የበላ ህዝብና አካባቢ ተፈልጎ የሚገኝ አይመስለኝም። ምክንያቱም ይህ ህዝብ ከሚኖርበት አካባቢ ባሻገር በመላ ሀገሪቱ እንደ ጠላት ተቆጥሮ ሲታደን የነበረ በመሆኑ ነው። ርግጥ አምባገነኑ የደርግ ስርዓት ጉጠት ባላቸው ሹል ጥፍሮቹ ያልቧጠጠው፣ ስለት ባለው ቢላዋው ያልሸረካከተው፣ በብረት ለበስ ታንኮቹ ያልደፈጠጠው የህብረተሰብ ክፍል የለም። ያም ሆኖ፤ እንደ ትግራይ ህዝብ የደርግ የአፈና አገዛዝ እንደ መርግ የተጫነበት የህብረተሰብ ክፍል ያለ አይመስለኝም። ሁሉም የብሔረ ትግራይ ተወላጅ ሊባል በሚችል መልኩ በደርግ ጥቁር መዝገብ (black list) ውስጥ የነበረ ነው ማለት ይቻላል። መቼ ታፍኖ እንደሚወሰድ አያውቅም። እስር ቤት የታጎረውም ቢሆን በየትኛው ለሊት ስሙ ተጠርቶ የጥይት አረር እንደሚበላው የሚያውቅበት አንዳችም መንገድ አልነበረውም። ጉዞው የሰቀቀን መንገዱም አሜኬላ እሾህ የበዛበት ነበር።

እናም ይህ ፈታኝ የጭቆናን አገዛዝ መቋቋም ስላቃተው ዱር ቤቴ ብሎ ከ70 ሺህ የሚልቁ ልጆቹ ደደቢት በረሃ ላይ በተለኮሰው የትግል ችቦ አማካኝነት ህይወታቸውን አጡ። ለዛሬዋ ኢትዮጵያም መሰረት ሆኑ። ይህ ሁሉ የሆነው የትግራይ ህዝብ በራሱና በሌላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ላይ የተጫነው አምባገነናዊ ስርዓት እንዲወገድ ካለው ፍላጎት በመነሳት ነው።

በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅትም ቢሆን፤ ጦረኛው የአስመራ መንግስት በእብሪት ባድመንና አካባቢውን በወረረበት ወቅት፣ ሁለተኛው የትግራይ ህዝብ ከአካባቢው ሚሊሻ ጎን በመሆን በሜካናይዝድ የተደራጀውን የሻዕቢያ ጦር የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ተጠናክሮ ወደ አካባቢው እስኪደርስ ድረስ እንዴት አድርጎ መክቶና ገትቶ ባለበት ቦታ እንዳቆመው ማንም የሚዘነጋው አይመስለኝም። በወቅቱ በርካታ የትግራይ ሚሊሻዎች ህይወታቸውንና አካላቸውን አጥተዋል። ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል፤ ከሚኖሩበት ቀዬና መንደር ተፈናቅለዋል። በወቅቱ በሻዕቢያ የተወረሩት አካባቢዎች ጥቂት ቢሆኑም ቅሉ፤ በወቅቱ ሁሉም የክልሉ ተማሪዎች ከ10ኛ ክፍል በላይ ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ተደርጎ ወደ ማሰልጠኛ ማዕከሎች ከትተዋል።

በህዝብ የሚደገፈው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን ተጠናክሮ ወደ አካባቢው ከዘለቀ በኋላም፤ ሁሉም የክልሉ ህዝብ ዳር ድንበራቸው ከተነካባቸውና ከተቆጡት ከሌሎቹ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በአንድነት በመሆን ወራሪውን ጦር አከርካሪውን ሰብሮ ወደ መጣበት እንዲፈረጥጥ ሲያደርገውም የትግራይ ህዝብ ያለውን ጥሪት አሟጦ ተረባርቧል። አዋቂ፣ ህፃንና ሴት እንዲሁም በትጥቅ ትግሉ ወቅት አካላቸው የጎደለ ታጋዩች ሳይቀር በየፊናው ያሰለፈና ያኔም እንደ ትናንቱ ጠላትን ያሳፈረ ህዝብ ነው። እንግዲህ ይህን ህዝብ በሌለ ማንነቱ በመፈረጅ ‘ሊገነጠል ነው፣…ምንትስ’ እያሉ ማውራት የቀልዶች ሁሉ ቀልድ ነው። ልክ እንደ ኮሜዲ ድራማ አስቂኝም ጭምር።

ውድ አንባቢያን ከላይ በፅሑፌ እንደገለፅኩት ‘የትግራይ የበላይነት አለ ወይስ የለም?’ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ፤ አስቀድመን የትግራይን ህዝብ ማንነት ማወቅ ይኖርብናል። ታዲያ ማንነቱ በዚህ አጭር ትንታኔ የሚቋጭ አይደለም። ቀሪውን እንዲሁም የሚባለው የበላይነት ስለመኖሩ አሊያም ስላለመኖሩ በቀጣዩ ክፍል ይዤ ቀርባለሁ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy