Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እውን የትግራይ የበላይነት አለን?(ክፍል ሁለትና የመጨረሻው)

0 464

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እውን የትግራይ የበላይነት አለን?

                                                  ቶሎሳ ኡርጌሳ

(ክፍል ሁለትና የመጨረሻው)

በክፍል አንድ ፅሑፌ ላይ ስለ ትግራይ ብሔር ማንነት በጥቂቱ ጠቃቅሻለሁ። ቀሪው የማንነቱ አካል በዚህ ክፍል የሚቀርብ ነው። በርዕስነት ያነሳሁት የበላይነት ጉዳይንም እንዲሁ አብረን እንመለከታለን።…

የትግራይ ህዝብ የአኗኗር ዘይቤ እጅግ አሳዛኝ ነው። ምንም እንኳን አካባቢው ለእርሻ የሚመች ባይሆንም፤ አርሶ አደሩ በላቡ ጥሮ ግሮ የሚኖር ነው። እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ አርሶ አደር አፈር ምሶ ጥሮ ግሮ የሚኖር ህዝብ ነው። እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ክልል በዚያ ክልልም ዛሬም ድህነት አለ። ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ነው። ሆኖም ህዝቡ ታታሪና ከተፈጥሮ ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጦ የሚኖር በመሆኑ በተለያዩ ስራዎች አካባቢውን እየለወጠ ነው።

ያም ሆኖ ክልሉን የሚመራው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የክልሉን ህዝብ ከደርግ የአፈና እና አምባገነናዊ አገዛዝ ቢያላቅቀውም፤ የህዝቡን ኑሮ በመሰረታዊነት የለወጠለት አይመስለኝም። እንዲያውም ባለፉት ዓመታት የመልካም አስተዳደር ችግርና ‘የኔት ወርክ ትስስር’ በከፋ ሁኔታ ከሚታይባቸው የሀገራችን ክፍሎች ውስጥ አንዱ የትግራይ ክልል መሆኑን አንድ ጥናት ማረጋገጡን በመገናኛ ብዙሃን ላይ ቀርቦ እንደነበር አስታውሳለሁ።

ሌላው ቀርቶ የህወሓት የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ እንደሚያመለክተው፤ በክልሉ ውስጥ የከፋ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር፣ የቡድንተኝነት ስሜት እንዲሁም ቀደም ሲል የነበሩ የህዝባዊነት መንፈስ መቀዛቀዝና የአደርባይነት መገንገን መፈጠራቸውን በግልፅ አመልክቷል። ይህም በትግራይ ውስጥ ምን ያህል የከፋ የአስተዳደር በደል እንዳለ የሚያሳይ ይመስለኛል። ለዚህ ችግር ተጠያቂው የክልሉ መሪ ድርጅት መሆኑም ግልፅ ነው።   

ለበርካታ ጊዜያት ለስራ ጉዳይ ወደ ትግራይ ስመላለስ ከታዘብኳቸው ጉዳዩች ውስጥ ህዝቡ ከሌላ አካባቢ ለመጣ ኢትዮጵያዊ የሚሰጠው ወደር የማይገኝለት ፍቅር ነው። ያ ህዝብ በርሱ አጠራር “ጋሻ” (እንግዳ ማለት ነው) እጅግ የተከበረ ነው። ያለውን ነገር ያካፍላል። ማጀቱን ከፍቶ፣ ድስቱን ገልብጦ፣ ጮጮውን አንጠፍጥፎ የሚያበላና የሚያጠጣ ህዝብ ነው። በማናቸውም ጉዳዩች ላይ ከሀገሬው ህዝብ ይልቅ “ጋሻ” ቅድሚያ ይሰጠዋል።

ትግራይ ውስጥ ለስራ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የክብር ካባን ደርቦ ደራርቦ ይጎናፀፋል። ያ ህዝብ ድህነት ይዞት ነው እንጂ፣ ምንም ነገር ከመስጠት አይቆጠብም። እኔ በበኩሌ በኢትዮጵያዊነቴ የምኮራው ወደ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሳቀና ነው። ያኔም የትግራይ ህዝብ ትዝ ይለኛል። የፍቅሩና ሌላውን ኢትዮጵያዊ የመውደዱ ምስጢር ሁሌም ከፊቴ ድቅን ይልብኛል። የኢትዮጵያዊነት ምንጭ መሆኑንም ያስታውሰኛል። እናም በዚያ ታታሪና ኢትዮጵያዊ ህዝብ መሃል ሁሌም ብገኝ ደስታዬ ወደር አይኖረውም። ይህ ህዝብ እንደምን ከኢትዮጵያ ሊገነጠል እንደሚችል እንዲሁም የበላይ ሊሆን እንደሚችል ሁሌም ግርም ይለኛል።

በእኔ እምነት የትግራይ ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የበላይ ሆኗል ከተባለ፤ ምናልባትም በዚያ ክልል በሚታየው የከፋ ድህነትና ለሌሎች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባለው ወደር የለሽ ፍቅር ብቻ ነው። በተረፈ ከሌላው ኢትዮጵያዊ በልጦ ከፌዴራል መንግስት የሚመደብለት ሰባራ ሳንቲም የለም። እንደሚታወቀው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለክልሎች የሚሰጠውና ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ገቢራዊ የሚሆነው የበጀት ቀመር ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ይፋ ሆኖ ነበር። በወቅቱ ምክር ቤቱ እንደገለፀው፤ ክልሎች የሚያገኙት ድጎማ የተለያዩ ጉዳዩችን ታሳቢ ያደረገ ነው። እነርሱም ለሥራ አመራርና ጠቅላላ አገልግሎት፣ ለጤና፣ ለውሃ፣ ለከተማ ልማት፣ ለትምህርት፣ ለገጠር ልማትና ለመሳሰሉት የወጪ ፍላጎቶች ናቸው። እንዲሁም የክልሎች ገቢ የማመንጨት አቅም ሌላው የበጀት ቀመሩ መመዘኛ መሆኑ ተገልጿል።

በድጎማ ቀመሩ መሰረት፤ መንግስት ለክልሎች ከያዘው ድጎማ ውስጥ በ2010 ዓ.ም፤ ኦሮሚያ ክልል 34.46 በመቶ፣ አማራ ክልል 21.6 በመቶ፣ ደቡብ ክልል 20.11 በመቶ በማግኘት ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል 9.98 በመቶ፣ ትግራይ ክልል 6.03 በመቶ፣ አፋር ክልል 3.02 በመቶ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል 1.8 በመቶ፣ ጋምቤላ ክልል 1.33 በመቶ፣ ድሬዳዋ አስተዳደር 0.88 በመቶ፣ ሐረሪ ክልል 0.76 በመቶ አግኝተዋል። ይህ የቀመር ድልድል የሚያሳየን የትግራይ ክልል የቀመሩ ዋነኛ ጉዳይ የሆነው የህዝብ ብዛትና ከላይ የጠቀስኳቸው ሌሎች ፍላጎቶች አኳያ የሚያገኘው ድጎማ በአምስተኛ ደረጃ የሚገኝ ነው። ክልሎች የራሳቸውን በጀት በአግባቡ ህዝቡን ባማከለ መንገድ አብቃቅተው መጠቀም ይኖርባቸዋል። ዳሩ ግን ይህን ሳያደርጉ ቀርተውና በጀቱም በኪራይ ሰብሳቢዎች ተዘርፎ ሲያበቃ፤ ህዝቡ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጉዳይን ካነሳ ችግሩ የሚኖረው በራሳቸው በክልሎቹ ጫንቃ ላይ ብቻ ነው። ሌላው ክልል ጣት መቀሰሪያ ሊሆን የሚገባው አይመስለኝም። ከዚህ ጋር አያይዞም የትግራይ ህዝብን ስም ማንሳት አስነዋሪና ፀያፍ ተግባር ነው።

ርግጥ ከአንዳንድ ፅንፈኞ በስተቀር ኢትዮጵያ ውስጥ የትግራይን ህዝብ የሚጠላ ኢትዮጵያዊ አለ ብዬ አላስብም። ያ ህዝብ ከአማራው፣ ከኦሮሞው፣ ከአፋሩ፣ ከቤኒሻንጉሉ፣ ከደቡቡ…ወዘተ. ጋር በደምና በአጥንት የተሳሰረ ነው። የትግራይ ህዝብ ወግና ባህል በሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ አለ። እንግዳ አክባሪነትና ተቻችሎ መኖር የትግራይም ይሁን የሌላው ኢትዮጵያዊ መለያ ነው። ይህ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምንና እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሀገሩን የሚወድ ነው። ይህን ከጥንት ከጠዋቱ ይዞት የመጣውን ኢትዮጵያዊ ማንነት ማንም ሊፍቀው አይቻለውም። ይህ ህዝብ ‘ሀገሪቱ ሲያልፍላት እኔም ያልፍልኛል’ በማለት በመንግስት ዕቅድ እየተመራ የዕድገት ባበቡር ላይ ተሳፍሮ ህዳሴውን አውን ለማድረግ በመትጋት ላይ የሚገኝ ነው። ይህ ህዝብ የርሱ ማደግ በአጠቃላይ ሀገራዊ ዕድገት ላይ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚያሳርፍ የሚገነዘብና ከዚህ አኳያ ተግባሩን እየተወጣ የሚገኝ ነው።

እናም ይሀን ታታሪና ከተፈጥሮ ጋር የሚታገል ህዝብ ማንም ሊጠላው አይችልም። ይህን የኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት የሆነን ህዝብ ሊጠሉ የሚችሉት ፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ብቻ ናቸው። ከጥንት ከጠዋቱ ጀምሮ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስከበር ሲማስን የነበረን ህዝብ ሊጠሉት የሚችሉት በፌስ ቡክና በሌሎች የትስስር መረቦች ላይ በአላዋቂ ሳሚነት የሚዘላብዱ ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ናቸው። እውነቱን ለመናገር የኤርትራ መንግስት እያሰረገ የሚያስገባቸውን ሰርጎ ገቦች ሌት ተቀን በመጠበቁ ሳቢያ ለልማት ማዋል የሚገባውን ጊዜ የሚያባክን ይመስለኛል። በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት፤ ከኤርትራ ጋር መጎራበት አጋም ስር ተጠግታ እንደበቀለች ቁልቋል ሁሌም ማልቀስ ነው። እናም ያ ህዝብ ይህንን ችግር ችሎ በመኖር ጭምር በኢትዮጰያዊነቱ ላይ መደራደር የሚፈልግ አይደለም። እናም ይህን ፍፁም ኢትዮጵያዊነት የነገሰበትን ህዝብ ‘ቢገነጠል ይሻለዋል’ እያሉ የሚያወሩት አንዳንድ የፌስ ቡክ ፅንፈኛ አርበኞች እና ኢትዮጵያ ተዳክማ ማየት የሚሹ የሀገራችን ጠላቶች ብቻ መሆናቸውን መገንዘብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። “ለምን?” ካሉ፤ ቅርንጫፍ ከግንዱ እንጂ፤ ግንድ ከቅርንጫፉ ሊዘነጠፍ ስለማይችል ነው።  

ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው የትግራይ ህዝብ ማንነቶች፤ በርዕሴ ላይ ያነሳሁትንና ‘እውን የትግራይ የበላይነት አለን?’ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በቂ መለኪያዎች ይመስለኛል። አንድ እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራሱን ቋንቋ፣ ባህልና ወግ እያሳደገ የሚገኝ፣ በኢትዮጵያዊነቱ ላይ ፈፅሞ የማይደራደር፣ እኩልነትንና ፍትሐዊ የሃብት ተጠቃሚነትን ለማምጣት የታገለና ያታገለ፣ የሀገሪቱ ዕድገት በሚፈቅደው መሰረት እንደ ሌሎቹ ክልሎች በመስፈርት ድጎማ የሚሰጠው ህዝብ በምንም ዓይነት የሂሳብ ስሌት የሌሎች የበላይ ሊሆን አይችልም። ልሁን ቢልም ሀገራችን የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት አይፈቅድም። የልኬታ መስፈሪያው “ዜሮ” ወይም “ምንም” ነው። ደፈናዊ ጥላቻ የወለደው ተረክ ነው። አራት ነጥብ።

እውነታው ይህ ከሆነ ዘንዳ፤ ‘የዚህ ትርክት ደራሲዎች እነማን ናቸው?፣ ምክንያታቸውስ?’ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። እንዳልኩት የኢትዮጵያ ጠላቶች የድርሰቱ ባለቤቶች ናቸው። ምክንያታቸውም ግልፅ ነው። ይኸውም እነዚህ ሃይሎች አንግበው የተነሱት አጀንዳ ‘የትግራይ ህዝብን ከቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እንደ ምንም ብለን ማጋጨት ከቻልን፤ ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር ብትንትኗን ልናወጣና ደብዛዋን ልናጠፋ እንችላለን፤ ስርዓቱንም እናፈርሳለን’ የሚል በመሆኑ ነው። በዚህ የአጀንዳ ምርኩዝነትም የትግራይ ህዝብ የበላይነት ልቦለዳዊ ትረካ በምክንያትነት ወይም ፈረንጆች እንደሚሉት የጉዳዩ ማስፈፀሚያ ስልት (means) ሆኖ ይቀርባል። በጥቅሉ ስርዓቱን የማፍረስ አጀንዳ (end) ተደርጎ የትግራይ የበላይነት በማስፈፀሚያ ስልትነት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ—የሀገራችን ጠላቶች።

ግና ይህን ሃቅ በመጀመሪያው ክፍል ፅሑፌ ላይ የጠቀስኳቸውና ከአባባ ይመር ጎን ተቀምጠው ስለ ፌስ ቡክ ትረካ ሲያወሩ እንደነበሩት ዓይነት ጥልቅ ግንዛቤ የሌላቸው አንዳንድ ወጣቶች አያውቁትም። እነዚህ ወጣቶች እንክርዳዱን ከስንዴው ለይተው አይመዝኑም። በየማህበራዊ ሚዲያው ላይ የተለጠፉ ጉዳዩች ሁሉ እውነት ይመስሏቸዋል። በዚህም ሳቢያ ባለማወቅ የፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች አጀንዳ አስፈፃሚዎች ሲሆኑ ይስተዋላል።

ለዚህም ነው— አንዳንድ ወጣቶች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሀገራችን ፅንፈኞች (በተከፈላቸው መጠን የሚጮሁትንና በኤርትራ መንግስት እንዲሁም በሌሎች የሀገራችንን መዳከም በሚሹ ጠላቶቻችን የሚታዘዙ የግንቦት ሰባት ስራ ፈት አባላትን ወሬ እየቀዱ ‘ዳውን…ዳውን ወያኔ፣ ዳውን ዳውን…’ መፈክርን እንደ ዕውቀት ቆጥረውት የሚያስተጋቡት። ለዚህም ነው— በውጭ ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች በተቀነባበረና በውስጥ ፖለቲኞች የአፈፃፀም ድክመት የተነሳ በኦሮሚያ ውስጥም ይሁን በቆቦና በወልዲያ አካባቢዎች ዓይነት “ዳውን….ዳውን ወያነ!” ዓይነት ተመሳሳይ ዜማን እንዲያሰሙ ምክንያት የሆነው። ኦሮሚያን የሚያስተዳድረው አህዴድ ሆኖ ሲያበቃ፤ ዳውን ዳውን ወያነን ምን አመጣው?—አማራ ክልልን የሚመራው ብአዴን መሆኑ እየታወቀ፤ ጣትን በወያነ ላይ መቀሰርን ምን ይሉት ተቃውሞ ነው?፣ በዘረኝነት ስሜት አንዱ ለዓመታት ጥሮና ግሮ የቋጠራትን ጥሪት ማቃጠልና ማውደም ምን ዓይነት የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ነው?…እኔ በበኩሌ እንዲህ ዓይነቱን ፈፅሞ ከኢትዮጵያዊ ወግና ባህል ያፈነገጠ አስተሳሰብንና ተግባርን መጋፈጥ ያስፈልጋል። ፊት ለፊት መነጋገርና ሁሉም ሃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል። መንግስትም ይሁን ህብረተሰቡ የድርሻውን መወጣት አለበት። የዘረኝነት ተግባር ሚዛናዊነትና መቋጫ የሌለው በመሆኑ ነገ ‘የኦሮሞ የበላይነት፣ የአማራ የበላይነት፣ የደቡብ የበላይነት….ወዘተ’ የማይባልበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም። የዘረኝነት ስሜት ድንቁርና የሚወልደው ልጓም አልባ ፈረስ በመሆኑ ነገ ችግሩ የሁሉንም ቤት ማንኳኳቱ አይቀርም። ‘እገሌ የሚባለው ብሔር ከአካባቢዬ ውጣልኝ’ መባሉ የሚቀር አይመስለኝም። ይህም እርስ በርሳችን በመባላትና በመዳከም ተበታትነን ሀገር አልባ እንድንሆን የሚሹ የሀገራችን ጠላቶች በሸረቡልን አጀንዳ ውስጥ እንድንገባ የሚያደርገን ነው።

ርግጥ በትግራይ ህዝብ ላይ የጥላቻ አታሞ መደለቅ የጀመረው ዛሬ አይደለም። በእኔ እድሜ እንኳን ይህን ህዝብ በአምባገነኑ መንግስቱ ኃይለማርያም የስልጣን ዘመን ህዝቡን በፀያፍ ቋንቋ ሲናገሩት፣ የኤርትራ መንግስት በደመኛ ጠላትነት ሲፈርጀውና ድንበር እየተሻገረ ሲገድለው ብሎም አፍኖ ሲወስደው ታዝቤያለሁ። በምርጫ 97 ወቅት ስርዓቱን የአንድ ብሔር በማስመሰል ‘ወደ መጡበት እንመልሳቸዋለን’ እየተባለ በተላላኪ የሀገር ውስጥ ተቃዋሚዎች ሲወገዝ እንደነበር አስታውሳለሁ። አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ጠላቶች በተላላኪዎቻቸው አማካኝነት ‘የትግራይ የበላይነት አለ’ የሚል የልቦለድ ትረካን በመቀመር ህዝቡን ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ በመነጠል ስርዓቱን ለማፍረስ እንደ ምክንያት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። በርግጥ አዕምሮ ያለው ዜጋ ይህን ሴራ ማወቅ ይኖርበታል። መንቃት አለበት።

ሁሌም “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” እንደሚባለው፤ በአንድ ተግባር ላይ ከመሰማራት በፊት የጉዳዩን ምንነትና ሀገራዊ ፋይዳውን ለይቶ ማየት እንደሚገባ ለመጠቆም እወዳለሁ። ምንም እንኳን ለዚህ ዓይነቱ ተግዳሮት የዳረገን ውስጣዊ ችግራችንን በተገቢው መንገድ ባለመፍታታችን ቢሆንም፤ አሁንም በፈጣን መንገድ የወጣቶች አስተሳሰብ የመቀየር እንዲሁም ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ የማረጋገጥ ጉዳይ ማስፈን ይገባል። መንግስት ይህን ተግባሩን በተፋጠነ መንገድ መስራት ካልቻለና ህብረተሰቡም እንደ ሀገር ይህን ችግር ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ፋና ወጊ ሆኖ ካልተሰለፈ ከዚህ ዓይነቱ የግንዛቤ እጥረት የሚመጣ የችግር ድግግሞሽ ልንላቀቅ አንችልም። እናም ይህን የትግራይ የበላይነት የፈጠራ አጀንዳን ለመመከት በተለይ ወጣቶችን ማስተማርና ማሳወቅ ይገባል።

የትግራይ የበላይነት አጀንዳ መለኪያና መጨበጫ እንዲሁም ማሳያ የሌለው የፅንፈኞች አሉባልታ ነው። እንዳልኩት አጀንዳው ስርዓትን የማፍረስ ማስፈፀሚያ ስልት እንጂ ሁለት እግር ኖሮት በራሱ የቆመ አይደለም። ዳሩ ግን እንዲህ ዓይነቱ የበላይነትም የሁን የበታችነት አጀንዳ ፌዴራላዊ ስርዓቱ ፈፅሞ የሚያስተናግደው አይደለም። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የትግራይም ይሁን የሌላ ብሔርና ብሔረሰብ የበላይነት የለም። ሊኖርም አይችልም። በስርዓቱ ውስጥ አንዱ “ልጅ” ሌላው ደግሞ “የእንጀራ ልጅ” የሚሆንበት ህጋዊ አሰራር የለም። አዲሲቷ ኢትዮጵያ ሁሉም የሀገራችን ህዝብ በፍትሃዊነት እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታን የፈጠረች እንጂ፤ አንዱን የበላይ ሌላውን የበታች በማድረግ የምታበላልጥ  አይደለችም። ጭቆናን፣ ኢ-ፍትሃዊነትንና ፀረ-ዴሞክራሲያዊነትን ሲታገሉ የመጡት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለእንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ምንም ዓይነት ቦታ የላቸውም። እንደ ሌሎቹ ህዝቦች ሁሉ የትግራይ ህዝብም ከዚህ የተለየ ምልከታ የለውም። እናም የበላይም የበታችም ሊሆን አይችልም።

ታዲያ እዚህ ላይ በየብሔሩ ውስጥ ጥገኞች የሉም እያልኩ አይደለም። ልክ በኦሮሞ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በአፋር፣ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በጋምቤላ ወይም በሌሎች የሀገራችን ብሔሮች ስም የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ጥገኞችና ኮንትሮባንዲስቶች እንዳሉት ሁሉ፤ በትግራይ ህዝብ ስም የሚነግዱ ጥገኛ ኪራይ ሰብሳቢዎች መኖራቸው አይቀርም። እነዚህ ጥገኞች ግን የትግራይንም ይሁን ሌላውን የሀገራችንን ህዝብ የሚወክሉ አይደሉም። ጥገኞቹ በዜሮ ድምር የፖለቲካ ስሌት የሚንቀሳቀሱ ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው። ጥገኞቹ በሀገራችን ህዝቦች ስም እየማሉ ኪራይ ሰብሳቢነትንና ኮንትሮባንዲስትነትን የሚያካሂዱ “ሲራራ ነጋዴዎች” ናቸው። እነዚህን ሃይሎች እንደ ህዝብ ፊት ለፊት መጋፈጥ ይገባል። በሀገራችን ህዝቦች ላይ እንደ ተውሳክ ተጣብተው የሚንቀሳቀሱ ጥገኞችን በማጋለጥ ከየትኛውም ዜጋ የሚጠበቅ ቢሆንም፤ የሀገራችንን ሀዘቦች እየመሩ ያሉት ብሔራዊ ድርጅቶች (ኦህዴድ፣ ህወሓት፣ ብአዴን…ወዘተ. ማለቴ ነው) እነዚህን ኃይሎች ከራሳቸው መነጠል ቀዳሚ ተግባራቸው ማድረግ የሚኖርባቸው ይመስለኛል። ሃቀኛና ብርቱ ትግል ማድረግ አለባቸው። ይህ ካልሆነ ነገም በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሞ፣ በደቡብ…ህዝብ ስም የሚነግዱና በሌለ ስርዓታዊና ህጋዊ ቁመና ‘የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የአፋር…ብሔር የበላይነት አለ’ የሚያስብሉ ጥገኞች እንደ አሸን መፍላታቸው የሚቀር አይመስለኝም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy