Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከመሰረተ ድንጋይነት ያላለፉት የአዲስ አበባ ሶስት ሆስፒታሎች

0 1,161

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአዲስ አበባ ከተማ ሶስት ሆስፒታሎችን ለመገንባት ከሶስት ዓመት በፊት የመሰረት ድንጋይ ቢቀመጥም ግንባታቸው እስካሁን አልተጀመረም።

ሆስፒታሎቹ እያንዳንዳቸው በ30 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የሚገነቡና የካንሰር፣ የኩላሊትና የአይን ህክምና አገልግሎቶችን ጨምሮ ሌሎች ህክምናዎችን የሚሰጡ ዘመናዊ  ሆስፒታሎች ናቸው ተብሎ ነበር።

በከተማዋ የጤና ሽፋን ለማሳደግ የጤና ተቋማት የማይገኝባቸውና በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ተመርጠው በጀሞ፣ ቤተልና ሰሚት አካባቢዎች ሶስት ሆስፒታሎችን ለመገንባት ከንቲባ ድሪባ ኩማ በ2007 ዓ.ም የግንባታ መሰረት ደንጋይ አስቀምጠው ነበር።

በወቅቱ የከተማዋ አስተዳድር በ750 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚገነቡና ለ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ ታስቦ ነበር ሆስፒታሎቹን ለመገንባት የታቀደው።

ሆስፒታሎቹን  በአራት አመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለአገልግሎት ይበቃሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም እስካሁን በአካባቢዎቹ ባደረግነው ምልከታ የተጀመረ ነገር የለም።

ለሆስፒታሎቹ ግንባታ ከተዘጋጁ ቦታዎች ሁለቱ የመኪና መለማመጃና ማቆሚያ አንዱ ደግሞ ለእርሻ መዋላቸውን ባደረግነው ምልከታ አረጋግጠናል።

የአካባቢው ነዋሪዎችም ሆስፒታል ይገነባል ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ በተስፋ ቢጠብቁም እስካሁን ምንም የተጀመረ ነገር እንደሌለና በአቅራቢያቸው ሆስፒታል ባለመኖሩ እየተቸገሩ መሆኑን ይናገራሉ።

ወጣት ፍቅር አወቀ ጀሞ 3 አካባቢ ነዋሪ እዚህ አከባቢ ሆስፒታል የለም፤ጤና ጣቢያ ነው እየሄድን የሚንገለገልበት፤ያም ቢሆን በሁለተኛና ሶስተኛ ቀን ተራው ከመጠን በላይ በመሆኑ ላይደርስም ይችላል ብሎ ተናግሯል፡፡

በወቅቱ ሆስፒታሉ ከጀሞ በላይ ያሉትን ነዋሪዎች ይይዛል ተብሎ ነበር ነገር ግን ሆስፒታሉ እስካሁን አልተሰራም ብሏል ወጣቱ፡፡

ቶላ ሰይፉ ሰሚት አካባቢ ነዋሪ በበኩሉ መሰረተ ድንጋይ ሲተከል በወቅቱ ትልቅ ተስፋ ነበረን፤ እዚህ አካበቢ ሆስፒታል አልነበረም፤ትልቅ ሆስፒታል ነው የሚገነባው ተብሎ ነበር፤ ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ  ስለ ሆስፒታሉ የሚወራ ነገርም የለም ብሏል፡፡

ለሆስፒታሉ የተባለው ቦታ የኳስ ሜዳ እና የመኪና ማለማመጃ ቦታ ሆኗል ያሉት ደግሞ አቶ ታምሩ ታዬ የቤተል ነዋሪ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በበኩሉ የሆስፒታሎቹ ግንባታ እስካሁን ያልተጀመረው በግንባታ ዲዛይን ማሻሻያና በጨረታ ሂደት ነው ብሏል።

የቢሮው የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የስራ ሂደት መሪ አቶ ሙሉጌታ አድማሱ ግንባታዎቹ የተጓተቱት ሆስፒታሎቹን ከከተማዋ የወደፊት እድገት ጋር ለማመጣጠን እና ዓለም የደረሰበትን የሕክምና ቴክኖሎጂ ያካተቱ እንዲሆኑ ስለተፈለገ የዲዛይን ማሻሻያ በመደረጉና በጨረታ ሂደት ነው ብለዋል።

“አሁን ላይ የዲዛይን ስራው ተጠናቆና ጨረታ ወጥቶ የጨረታው የፋይናንስና የቴክኒክ ግምገማ በግዥ ኤጀንሲ በኩል እየተደረገ ነው፤ግምገማው በአንድ ወር ይጠናቀቃል አሸናፊው ሲታወቅም በፍጥነት ወደ ስራ ይገባል” ብለዋል።

ግንባታው ከሶስት እስከ አምስት አመት ሊወስድ እንደሚችል ጠቁመው ሲጠናቀቁ አጠቃላይ አገልግሎት የሚሰጡና አሁን ካሉት ሆስፒታሎች በተሻለ ሁኔታ በጥራትና በቴክኖሎጂ የታገዙ ይሆናሉ ብለዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy