Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከማረጋገጫው በስተጀርባ

0 304

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከማረጋገጫው በስተጀርባ

                                                           ታዬ ከበደ

በቅርቡ ለአርሶ አደሮች የተሰጠውን የመሬት ማረጋገጫ ደብተር ተሰጥቷል። የማረጋገጫ ደብተሩ አርሶ አደሩ የመሬቱ ባለቤት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ደብተሩ የመሰጠቱ ምክንያት ወይም መሰረት የሀገራችን የመሬት ፖሊሲ መሆኑ ግልፅ ነው። በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ላይ በግልፅ እንደተደነገገው መሬት የህዝብና የመንግስት ነው። ይሀም ዜጎችና መንግስት የመሬት ባለቤት እንዲሆኑ መሰረት የጣለ ነው። በዚህ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ መነሻነትም የአገራችንን የመሬት ፖሊሲ በመጠኑም ቢሆን መመልከት ለግንዛቤ ጠቃሚ ነው።

ቀደም ሲል እንደገለፅኩት የመሬት ፖሊሲያችን ሃብቱ የህዝብና የመንግስት ነው፡፡ ይህም አርሶ አደሩን የመሬት ባለቤት እንዲህን አድርጎታል፡፡ ይሁንና በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ መሬት እንዲሸጥና እንዲለወጥ ማድረግ አይቻልም፡፡ ለምን ቢባል፤ ድርጊቱ በሰፊው ህዝብ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳይገነባ  ከፍተኛ እንቅፋት ስለሚፈጥር ነው፡፡

መሬት እንዲሸጥና እንዲለወጥ ቢደረግ፤ በአንድ ወገን ገንዘብ ያለው ሰው ይገዛል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ድሃው አርሶ አደር መሬቱን እየሸጠ ባዶ እጁን ይቀርና ያለው ሀብት በጥቂቶች እጅ እንዲከማች ያደርጋል፡፡ ይህም በሀገሪቱ ፍትሐዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፤ ህዝቦች በየደረጃው በልማቱ ከሚገኝ ዕድገት እኩል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ደንቃራ ይሆናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም መሬት ቢሸጥና ቢለወጥ ሀገራችን ለማስመዝገብ የምትፈልገውን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ማስቀጠል አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት፤ አንድ ሀገር ለማደግ ከፈለገች ያላትን እጥረት መቆጠብ ይኖርባታል፡፡

ከዚህ አኳያ የሀገራችን እጥረት ገንዘብ ነው፡፡ ታዲያ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች  መሬትን እየገዙ የሚያከማቹ ከሆነ፤ ያለን ውስን የገንዘብ አቅም ልማታዊ አስተዋጽኦ ላለው ስራ ከመዋል ይልቅ፤ የንብረት ባለቤትነትን ከአንድ ሰው ወደ ሌላው በማዞር ላይ ይውላል ማለት ነው፡፡ ይህም እጥረት ያለብንን ገንዘብ እንዳንቆጥብና በላቀ የልማት ስራ ላይ እንዳናውለው በማድረግ የዕድገታችን ማነቆ ይሆናል፡፡  

እነዚህን ህዝባዊና መንግስታዊ መነሻዎችን መሰረት ያደረገው የሀገራችን የመሬት ፖሊሲ፤ አርሶ አደሩን ባለቤት ያደረገ ነው፡፡ የሀገራቸን የመሬት ፖሊሲ አርሶ አደሩን የሃብቱ ባለቤት የሚያደርግ እንጂ፤ የሚያፈናቅል አለመሆኑ ነው፡፡

እርግጥም መንግስት በዋነኛነት በአርሶ አደሩ ማሳ አማካኝነት የጀመረውን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ይበልጥ ለማስቀጠል እየተከተለ ያለው አቅጣጫ  ይኸው ብቻ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ከቀየው የሚፈናቀል አርሶም ይሁን አርብቶ አደር ሊኖር አይችልም፡፡

ይህ ፖሊሲ በአገራችን ተቃዋሚዎች ዘንድ ቅቡል ባይሆንም የአርሶ አደሩን ህይወት የለወጠ ነው። አንዳንድ የአገራችን ጥገኛ ተቃዋሚዎች ጎራ መርህም ይሁን ወጥ አቋም የሌላቸው መሆኑ ከማንም የተሰወረ ጉዳይ አይደለም፡፡ የጎራው ሁሉም ተዋንያን ሊባል በሚችል መልኩ በትናንት ታሪክ የሚኖሩና የትናንት ቅሪቶች ናቸው ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ የራሳቸውን ፖሊሲ ቀርጸው በዛሬና በነገ ታሪክ ሰሪነት የሚያምኑ አለመሆናቸው የትላንት ተግባራቸው ይናገራል፡፡

ተቃዋሚዎች ቀደም ባሉት ጊዜያት የማያውቁትን የኒዩ-ሊበራሊዝም ቅንጭብጫቢ ሃሳቦችን በመቃረም የርዕዮተ- ዓለሙ ተከታይ በመምሰል “መሬት መሸጥ፤ መለወጥ አለበት” እያሉ ዲስኩራቸውን ሲያነበኑብልን ነበሩ። ዛሬም ያው ናቸው። የኒዮ- ሊበራሉን ሚዲያ አጀንዳ በሰሙ ማግስት “መሬት በውጭ ባለሃብቶች ለምን ይሰጣል?” በሚል የተለመደውን “ለመቃወም ብቻ መቃወም”  የተባለውን  ፖሊሲያቸውን ሲያሰሙን ኖረዋል፡፡

ተቃዋሚዎች ባለፉት ዓመታት በአንድ በኩል “የመሬት መቀራመት አለ” እያሉ፤ በሌላው ወገን ደግሞ መንግስት በመሬት መቀራመት ላይ ተሳትፎ በነበራቸውና መዋቅሩ ውስጥ በተሰገሰጉ ኃላፊነት በጎደላቸው ግለሰቦች እንዲሁም በጥቂት ህገ- ወጥ ባለሃብቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ ሲወስድ “ባለሃብቶችን እየጎዳው ነው” በማለት ለኪራይ ሰብሳቢዎች ጠበቃ ሆነው ሲሞዳሞዱ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ለኢትዮጵያዊያን መሬታችን ትልቁ ፀጋችን ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ማንኛውም የተፈጥሮ ሀብታችን ‘ይህን ፀጋ እንዴት ብንጠቀምበት ነው ልማታችንን ሊያፋጥንልን የሚችለው?’ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ እርግጥ ለጥያቄው ምላሽ ስንሻ፤ አብዛኛው የሀገራችን አርሶ አደር በደጋና በወይና ደጋ የአየር ፀባዮች ውስጥ የሚኖር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የሀገራችን በርካታ የቆላ አካባቢዎችም ለም እና ሰው ያልሰፈረባቸው እንዲሁም በእኛ አቅም የማይታረሱ ጠፍ መሬት መሆናቸውንም ጭምር፡፡

ታዲያ በእነዚህ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት በእኛ አቅም መልማት ያልቻለ፣ ነገር ግን ጦሙን የሚያድር ሦስት ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት አለን፡፡ እናም ይህ ለዘመናት ታርሶ የማያውቅ መሬታችን በልማታችን ላይ የራሱን እሴት እንዲጨምር ከተፈለገ፤ አቅም ያለው ማንኛውም አካል እንዲያለማው መፍቀድ የግድ ይላል፡፡

በአቅም ውስንነታችን ሳቢያ ማልማት ያልቻልነውን መሬት ገንዘብ ላላቸው ወገኖች በጥቂቱ በመስጠት ለጋራ ጥቅም እንዲውል እየተደረገ ነው፡፡ ይህም ወደ ነበርንበት የድህነት አረንቋ ዳግም እንዳንመለስ በራሳችን እምቅ አቅም ከምናደርገው ጥረት ባሻገር፤ ልማታችንን ከሚደግፉ ሃይሎች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን የዕድገት መወጣጫ መሰላል ገመድን አጥብቀን መያዝ ይኖርብናል።

መንግስት ልክ እንደሌሎቹ የኢንቨስትመንት ተግባራት ሁሉ፤ በእኛ የውስጥ አቅም መልማት የማይችል መሬትንም በሊዝ የኮንትራት ክፍያ ይሰጣል፡፡ በሚሊየን የሚቆጠር ያልለማ መሬት ይዘን ቁጭ ከምንል፤ ገንዘብ ላላቸው ሃገራት በኮንትራት የሊዝ ኪራይ መስጠቱ አዋጪና የሁለትዮሽን ጥቅም የሚያስጠብቅ ትክክለኛ አሰራር ነው፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ አሰራርም ሀገራችንንና ህዝቧ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ በግብርናው ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ያሳዩት የውጭ ባላሃብቶች፤ የሚያመርቷቸው የምግብ እህሎች እንደመሆኑ መጠን፤ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አኳያ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡

ይህ አሰራርም ዛሬ አርሶ አደሩን የመሬቱ ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ መሬቱን ከፈለገ ያወርሳል፣ ቢያሻውም ያከራያል፡፡ መሬት በመንግስትና በህዝብ እጅ ሆኖ ፈጣን ዕድገት እየተረጋገጠ ነው፡፡ ለዚህም ነው— ለከታታይ 16 ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት ማስመዝገብ የተቻለው፡፡ መንግስት ቀደም ባሉት ስርዓቶች ያላደረጉትን አርሶ አደሩን በመሬቱ የመጠቀም መብት የማረጋገጥ እንዲሁም በምርቱ በነጻ የመጠቀም መብትን የማጎናጸፍ ተግባራትን ለመተግበር በቁርጠኝነት ተንቀሳቅሷል፡፡

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት ትክክለኛ በሆኑ ፖሊሲዎቹ እየተመራ በስፋት የሚገኙትን የተፈጥሮ ሀብቶቹን አቅም በፈቀደ መጠን በአግባቡ በመጠቀም እና ምልዓተ ህዝቡን ከጫፍ እስከ ጫፍ በማነቃነቅ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ውስጥ ገብቷል፡፡ በዓለም አቅፍ ደረጃም አድናቆትን ያተረፈ ልማትን በሀገሪቱ ውስጥ ማምጣት ችሏል፡፡ የተፈጥሮ ሀብቶቹን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች እንዲያለሙት በመፍቀዱም የህዝቡን ተጠቃሚነትን አረጋግጧል፤ በማረጋገጥ ላይም ይገኛል፡፡ በዚህም በአነስተኛ መሬት ላይ የአርሶ አደሩን ህይወት ቀይሯል፡፡ ይህም የመሬት ፖሊሲውን ትክከለኛነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy