Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከአድዋ ምን እንማር?

0 564

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከአድዋ ምን እንማር?

                                                      ዘአማን በላይ

የመላው ጥቁር አፍሪካዊያን የፀረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄ ታሪክ (Pan-African History) ተደርጎ የሚቆጠረውን የአድዋ ድል ሳስታውስ በርካታ ስሜቶች ይፈራረቁብኛል። ‘በዚያ ተስፋፊነትና ወራሪነት እንደ ጀብድ ታይቶ የቅርምት አጀንዳ በገነገነበት ዘመን ፋሽሽት ነጮች እንደምን የሽንፈት ፅዋን ተጎነጩ?’ የሚል ጥያቄ ይመላለስብኛል። ‘መላው ጥቁር ህዝብ በሐሴት ፀዳል እንዲፈካ ያደረገውና ነጮች በጥቁሮች ላይ ብቻ ሳይሆን፤ ጥቁሮችም በነጮች ላይ እንዴት የበላይ ሊሆኑ እንደቻሉ ድማሜ ውስጥ እገባለሁ። ምን ይህ ብቻ፤ ‘የዚያ ትውልድ ድል ለእኔ የሚያስተላልፈው ቁም ነገርስ ምንድነው?’ የሚለውም ጥያቄ የተዘበራራቂ ስሜቶቼ አካል ነው። ታዲያ የጥያቄዎቼን ምላሾች ጠንቅቄ ባውቃቸውም ቅሉ፤ የአድዋ ድል መታሰቢያ ቀን የሆነው የካቲት 23 በየዓመቱ በመጣ ቁጥር፤ ደግሜ ደጋግሜ ራሴን መጠየቅ ልማድ ሳላደርገው የቀረሁ አይመስለኝም። ዕለቱ በመጣ ቁጥር በድሉ እየተደመምኩ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊና ጥቁር አፍሪካዊ ነሸጥ ሲያደርገኝ ይታወቀኛል—ጦር፣ ጎራዴና ጋሻ ባልይዝም። እናም እንዲህ እላለሁ።…

አድዋ። ቃል ግን ቃል ያልሆነ ረቂቅ ሃቅ። ቃሉን በውስጥ እንጉርጉሮ ሳነበንበው ሐሴትን ደረብኩ። ፍሰሐን ተጎናፀፍኩ። አድዋ—አ-ድዋ—አንድዋ—አደይዋ…እላለሁ። እንደ ልጅ አሊያም እንደ ጅል ቃሉን ደጋገምኩት። ስለ ገናናው አድዋና የአድዋ ጀግኖች ሳውጠነጥን ከያኒነት አማረኝ። ከያኒነት ግን ከወዴት አባቱ!…ባዶ ሜዳ ላይ እህል የመዝራት ያህል ቆጠርኩት።…

አድዋን ከጀግንነት፣ ጀግንነትንም ከኢትዮጵያዊነት ጋር ማዛመድ ወይም አንዱን ከሌላው ነጥሎ ማየት ተሳነኝ። ኢትዮጵያዊነትና ጀግንነት ሁለት የማይለያዩ፤ እንደ ደምና ሥጋ የተዋሃዱ እውነታዎች መስለው ታዩኝ። ትክክል ነኝ። በዚህ ሰማያዊ እውነት ውስጡ የማይረሰርስ፤ የማይመካ ካለ፤ እሱ ኢትዮጵያዊነቱ የሟሟ መሆን አለበት፤ ወይም ሚጢጢዬ ‘ፋሽዝም’ በውስጡ  ያጎሸመጠ ሰው ዓይነት ይመስለኛል።

እደግመዋለሁ። ኢትዮጵያዊነትና ጀግንነት አይነጣጠሉም። ኢትዮጵያዊ ባለበት ሁሉ ጀግንነት፤ ጀግንነት ባለበትም አውድ ኢትዮጵያዊ መኖሩን ከቶ ማን ይጠራጠራል? ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻ በራሱ የጀግንነት ዘውድ ያስደፋል። ጀግንነት መለካት ካለበት መስፈሪያው ኢትዮጵያዊነት መሆን አለበት ብዬ ብከራከር ከእውነታው እምብዛም የመርቅ አይመስለኝም። አድዋ—ኢትዮጵያዊነት— ጀግንነት እንደ ባለ ሶስት ጎን ውህድ ይመሰሉብኛል።

ርግጥ ይህ አባባሌ ጥቁርና ነጭ ሃቅ ነው። ያለ፣ የነበረና የሚኖር። እንደ ኢትዮጵያዊው ግዮን (አባይ) ዝንተ-ዓለም የማይነጥፍ እውነት። ኮለል እያለ የሚወርድ የጠራ ሃቅ።  እንዲህ የምለው ኢትዮጵያዊነቴ ገዝፎ ውስጤን ስለደለለው እንዳይመስላችሁ። እውነት ስለሆነ ብቻ ነው። ዋሴ የጥቁር ህዝቦች ተምሳሌቱ፣ ድሉ የገዘፈው፣ የአድዋ ገድለኞች ሰማይ ጠቀስ ምግባር ጀግንነትና ኢትዮጵያዊነት የማይነጣጠሉ ሁነኛ እማኞቼ ናቸው።

እንደ እውነቱ ከሆነ ይህን እምነቴን እንጥፍጣፊ ኢትዮጵያዊነት በውስጡ የሚመላለስ ማንኛውም ዜጋ ይጋራኛል ብዬ አስባለሁ። እነ ቴዎዶር ቬስቴል፣ በርክሌና ሪቻርድ ፓንክረስትን ለእምነቴ እማኝነት መጥራት እችላለሁ። “ለምን?” ብሎ የሚጠይቅ ሰው ካለ፤   አድዋንና የአድዋን ጀግኖች አብጠርጥረው ስለሚያውቁት መሆኑን አስረግጨ እናገራለሁ። አድዋ ቅኔ ነው። እልፍ አዕላፍ ጥቁር ህዝቦችን ለነፃነት ትግል ያነሳሳ የዓለም ጭቁን ህዝቦች ቅርስ ነው። ቋሚ ሃውልት ነው። ያኔ በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ የነበሩ የካሪቢያን ሀገሮችንና ድፍን አፍሪካን ለፀረ ቅኝ አገዛዝ ንቅናቄ (Pan-Africanism) የቀሰቀሰው አድዋ ነበር—በውጤቱ አማልሎ፤ በድሉ ተንቦግቡጎ።

ለእምነቴ እማኝ ከሆኑት ውስጥ በርክሌይ ልጥቀስ። የያኔዎቹ ፋኖዎች ጀግንነትና አልደፈር ባይነት ምትሃት የሆነበት ይህ ግለሰብ፤ የአድዋን ጀግኖች በድፍረት ካሞካሹ ፀሐፊዎች መካከል አንዱ ነው። እንዲህም አለ—“20 ሺህ ዘመናዊ ጦር ያሰለፈው አውሮጳ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር የሽንፈትን ጽዋ ተጎነጨ።…” ፀሐፊው በዚህ ብቻ አላበቃም። በባህር ቀዛፊው ብዕሩ ፖለቲካና ታሪክ ማብቃቱን አወሳ። በአፍሪካ ምድር አንድ ታላቅ ህዝብ ብቅ አለ። አበሾች ከዘመነ ፍጥረት ጀምሮ ታላቅ ህዝቦች መሆናቸውን እየጠቀሰ ዘገበ። “አድዋ የሁላችንም ምኞት ዘውግ ነው” ሲልም አድዋንና የአድዋ ጀግኖችን ገድል በብዕሩ አደመቀ።

ርግጥ ነው—ስለ አድዋ ገናናነት የተደነቀው በርክሌይ ብቻ አይደለም። ድፍን ዓለም ነው። ስለ አድዋ እልፍ አዕላፍ መፅሐፍት ተፅፈዋል። የታሪክ ተመራማሪዎች፣ የሥነ-ማህበረሰብ ልሂቃን፣ የጥበብ ወዳጆች አድዋን በተባ ብዕራቸው አሞካሽተዋል— እኔ የሚገባውን ያህል ተብሏል ብዬ ባላምንም። ያም ሆኖ ከሁሉም በላይ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያንና ለዘመናት በቅኝ ገዥዎች ሲማቅቁ ለኖሩት ጥቁር ህዝቦች ትርጉሙ ላቅ ያለ ነው—ከፍ ያለ። ውበታችን፣ እምነታችንና አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንጓዝ ያደረገን ብሔራዊ ቅርሳችን ናት— አድዋ—አንዷ—አደይዋ!

እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ እንዳነሳ ውስጤን የሆነ ነገር ይጎነታትለኛል። ‘ይህን ያህል የገነነ ኢትዮጵያዊነት እንደምን ተጻፈ?’ የሚል። ወደ ውስጤ ስመለስ ዘመንን በዛፍ ልመስለው ወደድኩ። ትላንት የዛሬ ሥር ነውና የገድሉን ክዋኔ ደቂቃዎች ወስደን እንፈትሸው—በወፍ በረር ቅኝት። አድዋ የተገዛ—አልገዛም፤ የተንበርከክ—አልንበረከክም ሙግት አውድ የወለደው የእኛነታችን መስታወት ነው። አዎ! ማንነታቸውን ላለማስደፍጠጥና ራሳቸውን ላለማጣት በቆረጡ ኢትዮጵያዊያንና ባህር አቋርጦ በመጣው ፋሽሽት ጣሊያን (ጣል-ያን) መካከል በተካሄደው ፍልሚያ፤ ኢትዮጵያዊያን በአፍሪካ ልዩ ህዝቦች የሚያደርገንን ታላቅ ሥራ ከወኑ። ማንነትን ከመነጠቅ የበለጠ ቅጣት የለምና በዕድል ሳይሆን በድል ያገኘነውን  አድዋን ከፍ ላቅ ብናደርገው ተመፃደቁ የሚለን ይኖር ይሆን?—ከቶም።

ርግጥ ነገሩ ወዲህ ነው።…ወቅቱ ድፍን አፍሪካን አውሮፓዊያን ለመቀራመት የቋመጡበት ዘመን ነበር። በክፍፍሉ መሠረት ኢትዮጵያና ሶማሊያ ለጣሊያን ታደሉ። ነገርዬው የሻሞ ዓይነት ነበር። ታላቋ ኢትዮጵያ በጣሊያን ሞግዚትነት ስር እንድትተዳደር ተፈረደባት። አዬ ከንቱ ምኞት!…

የያኔው የጣሊያን መሪ ክሪስፒ ታዲያ በፍጥነት ሠራዊቱን በእጥፍ አሳድጎ ወደ ኢትዮጵያ ገሰገሰ። በርግጥ ከዚያ በፊትም ቢሆን ጣሊያን በበርካታ የኢትዮጵያ ግዛቶች ዘመናዊ ሰራዊቷን አሰማርታለች። አሁን እመውና አበው ባርነትን ከማይታገሱበት ደረጃ ደርሰዋል። እናም ለታላቁ ፍልሚያ ተዘጋጁ። ርግጥ ከአድዋ በፊት ጦርነት አልነበረም ማለት እያልኩ አይደለም። ከአድዋ በፊት የዶጋሊ፣ የአምባላጌና የመቐለ ውጊያዎች ተካሂደዋል። በጦርነቶቹ ኢትዮጵያዊያን ድል ቀንቷቸው ነበር። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ያገኘውን ዓይነት ቦምብ ወደ ህዝባችን የሚወረውረው ጣሊያን (ጣል-ያን) የግዛት ማስፋፋት ተግባሩን ማፋፋም ጀመረ። የፋሽሽት ጣሊያን አዛዥና ናዛዥ የነበረው ሞሶሎኒ በወቅቱ ኢትዮጵያዊያን ተከፋፍለዋል የሚል ከንቱ ግምት ነበረው።

የንጉሠ ነገሥትነታቸውን ማዕረግ የተቀበሉት ዳግማዊ ምኒልክ በፊናቸው ሀገራቸውን ከጠላት ለመታደግ ውስጥ ውስጡን እየሰሩ ነው። የየአካባቢውን መሳፍንትና መኳንንት ካደራጁና ሁኔታዎችን ካመቻቹ በኋላ ጣሊያንን ለማባረር ወገባቸውን ታጥቀው ተነሱ።

የኢትዮጵያና የጣሊያን ግንኙነት ወደ ጡዘት (ጦርነት) ለመሸጋገሩ እንደ ዋነኛ መንስኤ የሚጠቀሰው የውጫሌ ውል ነው። ውጫሌ በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ሥር የምትገኝ የአምባሰል ሰንሰለታማ ተራራ ወገብ ላይ የተቆረቆረች ትንሽ ከተማ ነች። የስምምነቱ 17ኛ አንቀፅ የአማርኛና የጣሊያንኛ ትርጓሜ ታዲያ ለየቀል ሁኖ ብቅ አለ። በቀለ። ጣሊያን ስምምነቱን ለራሷ በሚመቻት መልክ ተርጉማ ኢትዮጵያን በማታለል ለተለያዩ የዓለም ሀገሮች ደብዳቤ ላከች።

ደብዳቤው ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረጉ ማንኛውም ግንኙነት በጣሊያን በኩል ብቻ እንደሆነ ያውጃል። ይህን አሳሳች ቀጭን መልዕክት ታዲያ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ አውስትሪያና ቤልጂየም አጨብጭበው ተቀበሉት። ኢትዮጵያ የጣሊያን ድርሻ መሆኗን አረጋገጡ።  ሞስኮብ፣ ፈረንሳይና ቱርክ ግን ከኢትዮጵያ ጋር ለሚያደርጉት ግንኙነትና ጥቅም ሲሉ የጣሊያንን ይሁንታ ለመቀበል አቅማሙ።

ዳግማዊ ምኒልክ ደግሞ የንጉሠ ነገሥትነታቸውን ደብዳቤ ለጀርመን፣ እንግሊዝና አውስትሪያ ላኩ— ለማሳወቅ። ይሁን እንጂ ሀገራቱ በቀጥታ ከምኒልክ ጋር ግንኙነት መመሥረት እንደማይፈልጉና ኢትዮጵያ የጣሊያን ግዛት የመሆኗን ጎምዛዛ መርዶ አረዷቸው። ይባስ ብሎም ጣሊያን መልዕክተኛዋን በመላክ በተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ኢትዮጵያን ወክላ ተገኘች።

ሁኔታው አጤ ምኒልክን አበሳጫቸው። በመታለላቸው ተናደዱ። እናም ጣሊያን የፈፀመችው ወንጀል መሆኑን በመግለፅ ኢትዮጵያ የጣሊያን ግዛት አለመሆኗን የሚገልጽ የእርምት ደብዳቤ እንዲጻፍ ለንጉሥ ኡምቤርቶ መልዕክት ላኩ—አጤው። ዳሩ ግን ጣሊያን አውቃ የተኛች በመሆኗ የምኒልክ መልዕክት ሊቀሰቅሳት አልቻለም። ከመጤፍ ሳትቆጥረውም ቀረች። ጆሮ ዳባ ልበስ ያለችው ጣሊያን ነገረ ሥራ ያበሳጫቸው ዳግማዊ ምኒልክ ሀገራቸውን ከወራሪው መታደግ እንዳለባቸው አመኑ። ሰራዊታቸውን በአቅምና በሥነ-ልቦና መዘጋጀቱን በመገንዘባቸው ለፍልሚያ ተዘጋጁ።

ምታ ነጋሪት፣ ክተት ሠራዊት ብለውም የክተት አዋጅ አስነገሩ። መላው ኢትዮጵያዊም በብርሃን ፍጥነት ያለ አንድ ልዩነት ለሀገሩ፤ ስለ ሀገሩ የያዘውን ይዞ፤ ባገኘው ነገር ሁሉ ዘመናዊውን የጣሊያን ጦር ሰራዊት ለመፋለም “ኧረ ጥራኝ ጫካው ኧረ ጥራኝ ዱሩ፤ ለእኔም ይሻለኛል ብቻ ከማደሩ” ማለት ጀመረ። እዚህም እዚያም ቀረርቶው፣ ሽላሎው፣ ጃሎታው፣ መገንና ወኔ ቀስቃሹ ግጥም እብደ ክረምት ዝናብ ይዘንቡ ጀመር። እልም ያለው ጫካ፣ እልም ያለው ዱር፤ ሲነጋገር ያድራል ከመውዜሩ ጋር ይልም ገባ—የአውና የእመው ጦር። የማንን ሀገር ማን ሊደፍራት፣ የምን ማቅማማት ለማይቀር ሞት እየተባለ ይመሽ፤ ይነጋል ጀመር።

በርግጥም ኢትዮጵያዊ ሁሉ ወኔው እንደ ኤርታሌ ገንፍሏል። ኢትዮጵያዊ በማንነቱ ድርድር አያውቅምና እምቢኝ አለ። በእውነቱ ጀግና ደስ ያሰኛል። ሲታጠቅ ማለዳ፣ የሚያበላ መስሎ የሚሸኝ እንግዳ ተባለ፡፡ እንዲህም ተፎከረ፡፡ አያምርበትም አበሻ ቢያፍር፣ ጠላት ሲመጣ አንገት ማቀርቀር፡፡ ከባልንጀራው ማታ የተለየ፣ እንደ አጥቢያ ኮከብ ሲነጋ ታየ። ሌላም ሌላም ተባለ።

ሴት ወንድ፣ አራሽ፣ ቀዳሽ፣ ተኳሽ፣ እረኛና የቤት እንስሳ ሳይቀር ሁሉም ወደ አድዋ አቀና። የመጨረሻው መጀመሪያ፤ የፍፃሜው ክብሪት ከሚሎከስበት አምባ ኢትዮጵያዊያን ከተሙ—አድዋ። አዎ! በዚያች ሰዓት፣ ከዚያች ሥፍራ ተገናኝተው ጣሊያንን  ”ና ሞክረኛ!” ለማለት ተመሙ —100 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን።…ጊዜው እ.ኤ.አ የካቲት 22 ቀን 1888 ነበር። ራስ መንገሻ፣ ራስ አሉላ፣ ዋግሹም ጓንጉል፣ የጄኔራል ዳቦር ሜዳን ሊፋለሙ በአንድ ግንባር ተሰለፉ። ራስ መኮንንና ራስ ወሌ ደግሞ የጄኔራል አርሞንዴን ግንባር እንዲገጥሙ ትዕዛዝ ተሰጣቸው። ፊታውራሪ ገበየሁና ራስ ዳምጠው ደግሞ አልቤርቶን ገጠሙት። አጤ ምኒልክ እቴጌ ጣይቱም በደጀንነትና ልዩ ልዩ ተግባራትን በመከወን ፍልሚያውን እንዲከታተሉ፣ እንዲመሩና የማስተካከያ ርምጃዎችን እንዲሰጡ ተደረገ። ሁሉም በየፊናው ተሰማራ።

የካቲት 23 ቀን ጎህ ሲቀድ ኢትዮጵያውያን የአድዋ ተራሮችን እንደ ጦጣ እየተንጠላጠሉ ጠላትን ለማደባየት ተነቃነቁ። ቀኗ “ፈረሱም ሜዳውም ያው” ብላ ለኢትዮጵያውያንና ለጣሊያን ጦር አድዋን ለቀቀችላቸው። ጀግና እየጣለ መነሳት ጀመረ። …በሶስት ግንባር የተሰለፈው የጣሊያን ዘመናዊ ጦር ከልክ ያለፈ በራስ የመተማመን ግምት ነበረው። ኢትዮጵያውያን የተሰለፉት “ቆመህ ጠብቀኝ” በተሰኘ ጠብ-መንጃ ብቻ በመሆኑ ንቀት አድሮበታል—ጣሊያን። ወኔ፣ ልባምነትና ጀግንነት ባለ ድል እንደሚያደርጉ አልተረዳም፤ ወይም እንዲገባውም አልፈለገም።

እንደ እውነቱ ከሆነ የሆነው ግን ተቃራኒው ነበር። ኢትዮጵያውያን ወራሪውን ኃይል ቁርስ፣ ምሳና ራት ለማድረግ ወታደራዊውን ስሌት ቀምረው ይጠዘጥዙት ያዙ። ብዙም ሳይዘገይ አልቤርቶኒ ቁርስ ሆነ። ሽንፈትን ተጎንጭቶ ሰራዊቱ እንደ ገና ዳቦ ተፈረካክሶ ግንባሩን ሊለቅ ግድ አለው። እግሬ አውጭኝ ብሎም ተፈተለከ።…ብዘም አልቆየም—የምሳ ሰዓት እየደረሰ ነው። ተራው የጄኔራል አርሞንዴ ነበር። በጄኔራል አርሞንዴ የሚመራውን ዘመናዊ ጦር፤ ጎራዴ፣ አካፋና መጥረቢያ የታጠቁት ኢትዮጵያውያን እንዳልነበረ አደረጉት። አንድ ፍልሚያውን በብዕሩ ያስቀረ አውሮጳዊ ፀሐፊ ያሰፈረውን ልጥቀስ— “…የኢትዮጵያ ሰራዊት ከቃልም በላይ ኃያል ነው። ጣሊያኖች ሽሽት ጠናባቸው…” ብሏል።

የሩቁን በውጅግራ፣ የቅርቡን በጎራዴ እየቀላ መገስገሱን ቀጠለ—የኢትዮጵያ ሰራዊት። ሁሉም በየፊናውና በየግንባሩ እየተፋለመ ነው። የአልበርቶኒን ጦር ለቁርስ፣ የአርሞንዴን ደግሞ ለምሳው የሰለቀጠው የኢትዮጵያ ፋኖ፤ እግሬ አውጪኝ የሚለውን ቀሪ የጠላት ኃይል እየተከታተለ ይለቅመው ጀመረ። ተራውን እየተጠባበቀ የቆየው ጄኔራል ዳቦር ሜዳም እምጥ ይግባ ስምጥ ጨነቀው። በመጨረሻም ደም አስክሮት፣ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት እግሩ ወደ ወሰደው ፈረጠጠ። ግና ከኢትዮጵያውያን እጅ ለማምለጥ ከቶውንም አልቻለም። በዚህ ሁኔታ ለእውነት የተሰለፉት የያኔዎቹ እመውና አበው ከንቱ ህልመኛውን የጣሊያን ጦር ከእኩለ ቀን በፊት ወደ “ነበርነት” ዓለም ቀየሩት—የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም።

ኮንትሮስኒ የተባለ ፀሐፊ የፃፈውን ለምስክርነት ልቀንጭብ። “…አበሾች ፍጹም ልበ ሙሉ ናቸው። ጀግንነታቸውን መካድ አይቻልም። በጎራዴና በሳንጃ ባለ መድፈኛውንና ባለ መትረየሱን የጣሊያን ሰራዊት ምርኮኛ አደረጉት…” ሲል በድማሜ ፅፏል። አዎ! በትልቅ የሀገር ፍቅር ስሜትና አንድ በመሆን የተፋለመው የያኔው ትውልድ በቅንነትና በስሌት ተዋድቆ ለመላው ጥቁር ህዝብ ተስፋን ያጫረ ታላቅ ድል አስመዘገበ። የድሎች ሁሉ የበላይ ድል የሆነውን አድዋን አበውና እመው ለሰንደቅ ዓላማቸው ተዋድቀው ባንዴራችንን ከፍ…ከፍ አደረጓት። ኮርተው አኮሩን። የአፍሪካዊያን ቀንዲል እንድንሆን አደረጉን። እነሆ አፍሪካዊ ውለታውን አይረሳምና ድሉን በማሰብ አድዋ ላይ የፓን አፍሪካ ዩኒቨርስቲን መሰረት ጥሎ ስራው እየተሳለጠ ነው። የዚህ አኩሪ ታሪክ ማንም አይደለም። እኔ ነኝ፤ አንተ ነህ፤ እርሶ ነዎት፤ እርሷ ነች፤ እርሱ ነው። መላው ጥቁር ህዝብ ነው። በቃ (ካለስ!)። ሌላ ማንም አይደደም።…እናም ለአንድ አፍታ ይህ የያኔው ትውልድ ደማቅና አሸብራቂ አፍሪካዊ ድል እንደ ትውልድ ለእኔ የሚያስተምረኝን ቁም ነገር ማሰብ ጀመርኩ።…

እኔን አልፎ አፍሪካዊያን ወንድሞቼን ያኮሩት አበውና እመው ለእኔ የሰጡኝ ትምህር ቀላል አለመሆኑን ለመገንዘብ አላዳገተኝም። በእኔ የሚመሰለው ይህ ትውልድ ከባድ ኃላፊነትን የተሸከመ መሆኑን አወቅኩ። ፍፁም የሀገር ፍቅር፣ የአንድነት መንፈስ፣ በየጊዜው የሚመጣን ጠላት አሳፍሮ በመመለስ የአፍሪካዊያን ተምሳሌት መሆንን ከዚያ ትውልድ ተምሬያለሁ።

የእኔው ትውልድ የአያቱና የቅድመ አያቱ ደም በውስጡ የሚራወጥበት ነው። ትናንት በያኔው ሞግዚቱ ጣሊያን የተሳሳተ ስሌት እየተመራ “ኢትዮጵያዊያን ተከፋፍለዋል” ብሎ የመጣውን የኤርትራን ወራሪ ሰራዊት አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ፣አከርካሪውን በመስበር የመለሰው መሆኑን አልክድም። ሻዕቢያም አሳምሮ ያውቀዋል። ይህ ትውልድ የአበውና የእመው አደራን በፍፁም ሀገራዊ ስሜትና በአንድነት መንፈስ መወጣቱን ማንንም እማኝ አልቆጥረም። ፀሐይ ላይ የተዘረጋ እውነት ነውና።

የእኔው ትውልድ ዛሬ ፋሽሽትና ተስፋፊ የለበትም። ኢትዮጵያም በማንኛውም ሀገር ሞግዚትነት ትተዳደር የሚል ቀንበር አልተጫነበትም። ያም ሆኖ የዘመኑን ችግር ማለፍ ይኖርበታል። የእኔው ትውልድ ፊት ለፊቱ የሚጋፈጠው የውጭ ወራሪ ሃይል ባይኖርበትም፤ እጅግ አሳፋሪና አንገት የሚያስደፋ እንዲሁም አሸማቃቂ ደዌ ፊቱ ላይ ተደቅኖበታል።

ይህ ትውልድ ጠንክሮ በመስራት ለዚህ አሳፋሪ ደዌ ፈውስ ማግኘት አለበት። ርግጥ ይህ ትውልድ ለድህነት ምንም ዓይነት ፈውስ አልሰጠም እያልኩ አልነበረም። ቀደም ሲል የነበረውን የድህነት ልክ ከመንግስት ጋር በመሆን ወደ ግማሽ አውርዶታል። ግና አሁንም ድህነታችን የገነገነ ነው። የገነገነውን ደዌ ለመፈወስ ጠንክሮ መስራትን ይጠይቃል። ስራ ያለመናቅንና አለመምረጥን ይጠይቃል። ሁከትን መጠየፍን የግድ ይላል። ልማትን እያወደሙ ልማትን መጠየቅ የዚህ ዘመን አስገራሚ አያዎ (Paradox) እንደሆነ ሰክኖ ማሰብን ይጠይቃል። ይህ ምልከታዋነኛ ተግባር መሆን ያለበት ለእኔው ትውልድ ነው።

የእኔው ትውልድ የህዳሴውን ግድብ በፍፁም ሀገራዊ ስሜትና በአንድነት እየገነባ እንዳለው ሁሉ፤ ድህነት የተሰኘውን ደዌ እስከ ፍፃሜው ድረስ መፋለም ይኖርበታል። የድህነት ደዌ ፈውስ የሚመጣው በአንድነት ስሜት ለሀገር በመስራት ብቻ ነው። በመንግስት መሪነት በዚህ አሸማቃቂ ደዌ ላይ የተከፈተው ዘመቻ መሰላል ወገቡ ላይ የደረሰ ይመስለኛል። ይህ ትውልድ ከመሰላሉ ጫፍ ላይ መውጣት አለበት።

በንትርክ፣ በሁከትና በብጥብጥ ልክ እንደ ጣልያን እንድንሸመደመድና አንገታችንን ቀና እንዳናደርግ የሚፈልጉ ሃይሎች እያዘናጉት እዛው የመሰላሉ መሃል ላይ መቅረት አሊያም ከመሰላሉ መውደቅ አይኖርበትም። የእኔው ትውልድ ይህ እንዲሆን ከፈቀደ የአበውና የእመው አጥንት እሾህ ሆኖ ይወጋዋል። የያኔው ትውልድ መስዕዋትነት በከንቱነቱ እንዲመነዘርም ያደርጋል።

እናም በእያንዳንዱ ዜጋ ልብ ውስጥ ጥካቻ ሳይሆን የሀገር ፍቅር፣ ድህነትን ማምለክ ሳይሆን ከድህነት የመውጣት ወኔ፣ የተገኘን ማበላሸት ሳይሆን በተገኘ ድል ላይ መጨመርን፣ መለያየትን ሳይሆን ጠንካራ አንድነትን መቋጠር ይኖርበታል። ይህ ስልት ከላይ በአድዋ አውደ ውጊያ ላይ የጠቀስኩት የአበውና የእመው ጠላትን ድል የመንሳት ጥበብ ነው። ሁላችንም ከዚህ ጥበብ ልንማር ይገባል።

የእኔው ትውልድ ይህን ትምህርት ቀምሮ ዋነኛ ጠላቱ የሆነውን የድህነት ደዌ ያለ አንዳች ቪዛ ከሀገሩ ሊያስወጣው ይገባል። በተጀመረውና ለውጥ እያመጣ ባለው ደዌውን የማጥፋት ዘመቻ ላይ በንቃት ተሳትፎ ሀገሩን በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ የአፍሪካ መመኪያ ሊያደርጋት ይገባል— የእኔው ትውልድ። እናም ያኔ ይህ ትውልድ የዚያ ትውልድ ተሞክሮ ቀማሪና የአፍረካ ፋና ወጊ መሆኑን እጄን አውጥቼ የምመሰክረው እኔው እሆናለሁ።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy