Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ካለመነጋገር ምንም አይገኝም

0 257

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ካለመነጋገር ምንም አይገኝም

                                                         ታዬ ከበደ

ዴሞክራሲ በአንድ ጀንበር የሚገነባ ሳይሆን የሂደት ውጤት ነው። በአሁኑ ሰዓት በአገራችን በገዥውና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ድርድርና ውይይት እየተካሄደ ነው። የውይይቱና የድርድሩ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ በአገር ጉዳይ ላይ መወያየት በራሱ የአገራችን ዴሞክራሲ ስር እየሰደደ በመሄድ ላይ መሆኑን የሚያመላክት ነው።

ቁጭ ብሎ መወያየቱ በራሱ የሚያስረዳው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ ውስጥ ለመስማማትም ይሁን ላለመስማማት መነጋገር ትክክለኛ አሰራር እንደሆነ ሁሉም ወገኖች እያመኑበት መምጣታቸውን አረጋጋጭ ይመስለኛል። ዴሞክራሲም በዚህ መልኩ ይበልጥ ሊያብብ እንደሚችል የሚያስረዳም ጭምርም ነው። ከመነጋገር ብዙ ማግኘት እንደሚቻል፣ ካለመነጋገር ግን ምንም እንደማይገኝ ተወያይ ፓርቲዎች ግንዛቤ የወሰዱ መሆናቸውን አስረጅ ነው።

መነጋገር የሀገርን ችግር የሚፈታ ነው። የአገራችንን ችግር የሚፈቱት ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች እንጂ ሌሎች አካል ሊሆኑ አይገባም።  የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በህዝቡ ፍትሐዊ ድምጽ የተመሰረተ ነው። የሥርዓቱ ምሶሶ የሆነው የኢፌደሪ ህገ መንግስት በሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፍላጎትና እምነት ፀድቆ ስራ ላይ የዋለ ሰነድ ነው። ስለሆነም እያንዳንዱ ዜጋ ለዚህ ሰነድ ጥብቅና ይቆማል።

በመሆኑም በእኔ እምነት ሁሉም ፓርቲዎች የበኩላቸውን ድርሻ በማበርከት ተገዥነታቸው ለህገ መንግስቱ ብቻ መሆኑን ማስመስከር ይኖርባቸዋል። ዋናው ጉዳይ በህገ መንግስቱ አማካኝነት ህዝቡ ያገኘውን መብት ለማስከበር እንደ ፓርቲ መበርከት የሚገባው ህዝባዊ አስተዋፅኦ ነውና።

በመሆኑም ገዥው ፓርቲም ይሁን ተቃዋሚዎች ከውይይታቸው፣ ከክርክራቸውና ከድርድራቸው ተጠቃሚው ህዝቡ መሆኑን መረዳትና ይህንንም ገቢራዊ ለማድረግ ቁርጠኝነታቸውን ማሳየት የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል።

ያም ሆነ ይህ ግን የውይይቱ፣ የክርክሩና የድርድሩ ዋነኛ ጉዳይ የሀገራችንን የፖለቲካ ምህዳር ይበልጥ ለማስፋት ታስቦ ሲሆን፣ በዚህ ቀና መንገድ ዙሪያ መጓዝ ደግሞ ተቃዋሚዎችም ይሁኑ ገዥው ፓርቲ መሰባሰብና የሚበጀውን ለህዝባቸው ማበርከት ይኖርባቸዋል። ከመነጋገር የሚገኘው ፋይዳ ከፍተኛ ነውና።

ሁሉም ፓርቲዎች የአገራቸው ተስፋ ከህገ መንግስቱ ከሚመነጭ በሚከናወኑ ተግባራት እንጂ በሌሎች ሃይሎች የሚወሰን አለመሆኑን ግንዛቤ መያዝ ያለባቸው ይመስለኛል። በመሆኑም የገዥው ፓርቲም ይሁን የመንግስት ‘እንወያይ፣ እንከራከር፣ እንደራደር’ ግብዣ መሰረታዊ መነሻው አገርና ህዝብ ነው።

መነጋገር የሰለጠነ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ መገለጫ ነው። ባለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ችግሮችን በጠረጴዛ ውይይት የመፍታት አካሄድ የዘመናዊነት መገለጫ እየሆነ ነው። ይህ ሁኔታም በተለይም ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በሚከተሉ ሀገሮች ውስጥ ትክክለኛ አካሄድ እየሆነ መጥቷል። ይህን ማንም ሊሽረው አይችልም። ሰጥቶ መቀበልና ስምምነት በማይኖርባቸው ጉዳዩች ላይም ተከራክሮ ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበት መንገድ ያለንበት ጊዜ መገለጫ ሆኗል። ስለሆነም ይህን የሰለጠነ አካሄድ ሁሉም ተወያይ ወገኖች ይበልጥ ገቢራዊ ሊያደርጉት ይገባል። መነጋገር መሰልጠን ነውና።

እንደሚታወቀው ሁሉ የተቃውሞውም ይሁን ገዥው ፓርቲ እንወክለዋለን የሚሉት ይህንን ህዝብ ነው። የሌላን ሀገር ህዝብ አይደለም። በመሆኑም ሁለቱም ወገኖች የሚደግፋቸውን ህዝብ ፍላጎት ብሎም የሀገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም ለአደጋ ማጋለጥ አይኖርባቸውም። የሚወያዩት፣ የሚከራከሩትና የሚደራደሩት ለህዝባቸውና ለሀገራቸው ሲሉ ነው። ከዚህ ውጪ ለየትኛውም አካል አጀንዳ ማራገቢያነት ፍጆታ ሊውሉ አይገባም። በውይይታቸው ላይ ሊያነሱት የሚገባው የህዝባቸውንና የሀገራቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ መሆን ይኖርበታል።

እግጥ በመገንባት ላይ ያለው የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ገና ጨርቃ ነው። በሚገባው ደረጃ አልጎለበተም። እናም በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ ችግሮች መኖራቸው አይቀርም። ዋናው ጉዳይ ችግሮቹን በአግባቡ ከመፍታት ላይ ነው። ለዚህ ደግሞ የሁሉም ወገኖች አገራዊ ቅንነትንና ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን የተላበሰ የሰከነ ንግግር ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ንግግሩ ሁሉም ወገን ሊያገኘው የሚችለውን ህዝባዊና ሀገራዊ ጥቅምን ብቻ ሊማክል ይገባል። በየትኛውም የውጭ ሃይል አሊያም በሀገራችን ህጋዊ ስርዓት ውስጥ የማያልፉ ሃይሎች ሊጠለፍ አይገባም።

የንግግሩ ማጠንጠኛው መሆን ያለበት የሀገራችን ጅምር ዴሞክራሲን ከማስፋትና ላላፉት 26 ዓመታት እየጎለበተ የመጣውን የፖለቲካ ምህዳር ይበልጥ እንዲሰፋ ለማድረግ ካለው ፋይዳ አኳያ ሊመዘን ይገባል። እናም መነጋገሩን ከዚህ አኳያ በመገንዘብ ውይይቱን በፍጥነት ማካሄድ ያስፈልጋል።

አገራዊ የንግግር መድረኮች በበዙና በተበራከቱ ቁጥር የሀገራችን ዴሞክራሲ ይበልጥ አሳታፊ፣ ግልፅነት የተሞላበትና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በበቂ ሁኔታ ሊያሳትፍ የሚችል ይሆናል። እናም በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል የሚካሄደው ክርክርና ድርድር ከዚህ ዴሞክራሲያዊ አውድ አንፃር መታየት አለበት።

እንደሚታወቀው ገዥው ፓርቲ ከአምባገነኑ የደርግ ስርዓት ጋር ያደረገው መራርና እልህ አስጨራሽ ትግል የነበረው አንዱ ጉዳይ የዴሞክራሲ እጦት ነው። ደርግን አስወግዶ ስልጣን ከያዘም በኋላ ቢሆን፣ ይህን የህዝቦችን ጥያቄ ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን ጥረት አድርጓል።

ገዥው ፓርቲ ገና ከስልጣን መባቻው ወቅት ጀምሮ የታጠቁና ወደ 17 የሚጠጉ የፖለቲካ ድርጅቶችን በማወያየትና በማከራከር ባህሉ የሚታወቅ ነው። ይህም ዴሞክራሲን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማስቻል ክርክርና ድርድር ማድረግ ለገዥው ፓርቲ አዲስ ጉዳይ አለመሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል።

እዚህ ሀገር ውስጥ ልማትንም ይሁን ዴሞክራሲን ለማሳለጥ የሚከናወኑ ማናቸውም ሁነቶች ማንንም ለማስደሰት አሊያም ለማስከፋት ሳይሆን የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የታገሉላቸውን መብቶች በፅኑ መሰረት ላይ ለማቆመ ታስቦ የሚከናወን ተግባር መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል።

ስለሆነም  በገዥው ፓርቲም ይሁን በመንግስት በኩል የሚከናወኑ ጉዳዩች ሁሉ ለሀገርና ለህዝብ ጠቀሜታ ሲባል እንጂ፣ ለታይታ አሊያም ለሌላ ጉዳይ የሚከናወኑ አይደሉም፤ ሊሆኑም የማይቸሉ መሆናቸውን በሰከነ አዕምሮ ግንዛቤ መያዝ ያስፈልጋል። እናም ለመነጋገር ሁሉም ሆደ ሰፊ መሆን አለባቸው። ቀደም ሲል ለመጠቀስ እንደሞከርኩት ሁሉም ፓርቲዎች የንግግሩን ፋይዳ ህዝባዊና አገራዊ ጥቅምን ማዕከል ባደረገ መልኩ ማከናወን የኖርባቸዋል።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy