Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ወጀቡ ቢበረታም…

0 649

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ወጀቡ ቢበረታም…

ወንድይራድ ኃብተየስ

ኢህአዴግ በአገራችን ልዩነቶችን  መፍጠር  የቻለ፤  ይህንንም  በተጨባጭ  ያሳየ ፓርቲ ነው። በአገራችን ለተመዘገቡት  ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ  ስኬቶች ሁሉ ኢህአዴግ የአንበሳውን ድርሻ  መውሰድ  የሚገባው  ፓርቲ ነው። በተመሳሳይ በአገራችን  ለተፈጠሩ ሁከቶችም ምንም ድርሻ የለውም ለማለት አልፈልግም።  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በከፍተኛ  አመራሮች መካከል  በሚታየው ያለመናበብ ሳቢያ በበርካታ አካባቢዎች አሳሳቢ የዘር ተኮር  ጥቃትን ጭምሮ  የንብረት ውድመት ተመልክተናል።

ዜጎች በማያውቁት፣ ባላዩት ባልሰሙት ነገር የእልህ መወጫ እስከመሆን በቅተዋል። የህግ የበላይነት ተጥሷል። ይሁንና የድርጅቱን አመጣጥና  የባለፉትን 27 ዓመታት ሁኔታ በጥልቀት ለተመለከተው  ተግዳሮቶችን  ጭምር   ወደ ስኬት  መቀየር   የቻለ  ነው።  አንድ ወዳጄ  እንደቀልድ እንዲህ አለኝ ኢህአዴግ አፈር ልሶም ቢሆን  የመነሳት  ብቃት  ያለው ፓርቲ  ነው። በአገራችን  የከፋ ጉዳት ሊያስከትሉ  የሚችሉ  ነገሮችን ሁሉ ወደ  ስኬት የመለወጥ ብቃት እንዳለው በተግባር አሳይቷል።  ባለፉት ሁለት ዓስርት ዓመታት  ኢህአዴግ ሶስት  አራት  ጊዜ  የከፋ ችግር ውስጥ  ገብቶ  የነበረ  ቢሆንም  ችግሮችን ወደ ስኬት መቀየር የቻለበት ሁኔታዎች እንዳለ እንዲህ ሲል አወጋኝ።

በእኔ እይታ ባለፉት 27 ዓመታት ኢህአዴግን  ገጠሞታል ብዬ ከማስባቸው ችግሮች መካከል አንኳር ያልኳቸውን እስኪ ላንሳላችሁ። የመጀመሪያውና የኢህአዴግ ፈተና የነበረው  በ1983 ዓ.ም አምባገነኑ ደርግ ስርዓት ውድቀትን ተከትሎ በርካታ የታጠቁ አካላት አገሪቱን ለመቀራመት  የተነሱበት ወቅት  ነበር።  በኢህአዴግ የበሰለና የተጠና አካሄድ አገሪቱ ሳትበታተን፣ የህዝብ እልቂትም ሳይከሰት የአገሪቱን አንድነትን ማስጠበቅ የቻለ ፓርቲ ነው። ያ ወቅት አገራችንን  ከገጠሟት የከፉ አደጋዎች መካከል ቀዳሚው ነበር ማለት ይቻላል።  ያንን ወቅት ተከትሎ  ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተስማምተው  ሁሉን  የሚያስማማ፣ አብሮነታቸውን የሚያጸና፣ ዘላቂ ሰላም ያሰፈነ  ህገመንግስት  አጽድቀዋል።  ይህ ህገመንግስት ለዘመናት በህዝቦች መካከል የነበረን  የተዛባ አስተሳሰብ በማረም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመረጧቸው ተወካዮቻቸው መተዳደር እንዲችሉ፤ በማንነታችው እንዲኮሩ አድርጓል።  ያ አስከፊ  ወቅት  አልፎ ዛሬ ላይ አገራችን በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት የነገሰባት፣ ዘላቂና ዋስትና ያለው ሰላም  የሰፈነባትና  የህግ የበላይነት  የተረጋገጠባት አገር ለመሆን በቅታለች።

እንደእኔ እንደኔ ሌላው አስቸጋሪ ወቅት የነበረው  የኤርትራ  ወረራ ወቅት ነበር። ከኤርትራ ወረራ ቀደም ባሉ ጊዜያት ኢህአዴግ  እንኳን  ከኤርትራ  ከሌላ ጎረቤት አገር ጋር  ግጭት ይፈጠራል  የሚል ዕምነት  ያለው አይመስልም ነበር። ለዚህ ጥሩ ማረጋገጫ የሚሆነው  በዚያን ወቅት ኢትዮጵያ  የነበራት  የመከላከያ ሃይል ቁጥር እጅግ አናሳና የታጠቀውም መሳሪያ  ከሻቢያ ጋር የሚመጣጠን አልነበረም።  እውነቱን እንነጋገር ከተባለ በዚያን  ወቅት ኢህአዴግ መንገድና ትምህርት ቤት ሲያስፋፋ፣ ድህነትን ለመቀነስ ሲውተረተር የነበረ ሲሆን   የኤርትራ መንግስት  ጦሩን አደራጅቶ ራሱን አጠናክሮ  በአገራችን ላይ  ወረራ ፈጸሞባት ነበር። በርካቶች የኤርትራ መንግስት ከነበረው የመከላከያ  ሃይልና ከታጠቀው መሳሪያ  አኳያ ተመልክተው ኢትዮጵያ  ሉዓላዊነቷን ማስከበር አትችልም  የሚል አስተያየታቸውን ሲሰጡ ነበር። ይሁንና ኢህአዴግ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ማስተባበርና  ሰፊ ህዝባዊ  ድጋፍ  ማሰባሰብ  በመቻሉ  አጭር  ጊዜ  በሚባል ጊዜ  የኤርትራን ጦር ከመሸገበት ጠራርጎ እንዲወጣ አድርጓል። በዚህም የአገሪቱን ሉዓላዊነት ማስከበር  ችሏል። በቀጣይም ጠንካራና ህዝባዊ የመከላከያ ሰራዊት መገንባት ችሏል።  ይህ ለእኔ ሌላው የኢህአዴግ   ስኬት እንደሆነ  ይሰማኛል።

የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት ማብቃት ተከትሎ በኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረው መከፋፈል ሌላው ለኢህአዴግ  ፈተና እንደነበር  የሚዘነጋ  አይደለም። አንዳንድ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የመንግስትን ስልጣን ለግል ጥቅም ለማዋል የተደረገው  ሙከራ ምክንያት በኢህአዴግ  አመራሮች መካከል ከፍተኛ መከፋፈል ታይቶ  አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ኢህአዴግ ተከፋፈለ አበቃለት ሲሉ ተደምጠው ነበር። ይሁንና  ኢህአዴግ ሁኔታዎችን በሰከነ ሁኔታ  በመያዝ  መስመሩን ማስተካከል ችሏል።  ያንን ወቅት ተከትሎ  የድርጅቱ አካላት   አዳዲስ  ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን  በመንደፍ  አገሪቱ ፈጣንና ተከታታይ  የኤኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ እንድትችል አደረጉ።  ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አገራችን ባለሁለት አሃዝ እድገት በማስመዝገብ የህዝቦችን የቆየ የልማት ጥያቄዎች መመለስ ጀመረች። በዚህም አገራችን ዛሬ ላይ ፈጣን እድገት ማስመዝገብ ከቻሉ ጥቂት የዓለማችን አገራት መካከል አንዷ ለመሆን ችላለች። ይህ ውጤት ኢህአዴግ በተከተለው ትክክለኛ መስመር ሳቢያ መመዝገብ የቻለ ነው።

ሌላው ለአገራችን ፈታኝ የሆነ የምለው ጊዜ የ97ቱን ምርጫ ተከትሎ የተነሳው ሁከት ነበር። በወቅቱ ቅንጅት አጠቃላይ ምርጫውን ያሸነፍኩት እኔ ነኝ በሚል ያስነሳው ሁከት የበርካቶችን ህይወት ቀጥፏል፣ ንብረት አውድሟል እንዲሁም የአገራችንን የዴሞክራሲ ሂደት ከፉኛ ጎድቶታል።  ያ ወቅት ብዙዎች ለአገራችን አስቸጋሪ ብለው ቢሉትም ኢህአዴግ በተከተለው የሰከነ አካሄድ ሁኔታዎች ተረጋግተው አገራችን የጀመረችው ፈጣን የኤኮኖሚ ዕድገት ማስቀጠል ተችሏል። ይኸው አገሪቱ ለበርካታ ዓመታት በተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኤኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ነች።  በዚህም  በርካታ ዜጎች   በፍጥነት በሚባል መልኩ ከድህነት መውጣት ጀምረዋል። በእርግጥ አሁንም በርካታ ዜጎች በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ቢሆኑም በጀመርነው አካሄድ ከቀጠልን በጥቂት ዓመታት ውስጥ በርካታ ዜጎችን ከከፋ ድህነት መላቀቅ እንደሚቻል በተግባር ታይቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች የተነሱ ሁከቶች ምክንያታቸው በአብዛኛው  የመልካም አስተዳደር እጥረቶች ናቸው። የመልካም አስተዳደር ችግሮች በየትኛውም አገር የሚፈጠሩ በሂደትም የሚፈቱ ናቸው።  እነዚህን ችግሮች መፍታት የሚቻለው በሁከትና ብጥብጥ ሳይሆን  በመቀራረብና በመነጋገር በመሆኑ ኢህአዴግ  ከመመለከተው አካል ጋር ሁሉ መነጋገር መመካከር መቻል ይኖርባተል።  የሰላማዊ ትግል  ባህል እንዲጎለብት  ኢህአዴግ  ምህዳሩን የሚያሰፋ  አካሄድን ሊጎለብት ይገባል። የመልካም አስተዳዳር ችግሮችን መፍታት ወይም መፍትሄ ማፈላለግ የኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካል  ጭምር መሆን መቻል አለበት።  ኢህአዴግ ወጀቡ ቢበረታበትም፤ ፈታኝ ጊዜ የተፈጠረበት ቢሆንም ድርጅቱ ካለው የቆየ  ልምድ አኳያ ይህን የውጥረት ወቅት በስኬት እንደሚሸጋገርና  እንደቀድሞው ጊዜ ሁሉ  ለአገራችን ብሩህ ጊዜ እንደሚያመጣ በዕርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy