Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሃገር ውስጥ አምራቾች፤ ምርቶችን እና ሸማቾች

0 532

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሃገር ውስጥ አምራቾች፤ ምርቶችን እና ሸማቾች

 

ዮናስ

 

አገራችን ኢትዮጵያ ከምትታወቅበት አስከፊ ድህነት ተላቃ ወደ ቀድሞ ሥልጣኔዋና ታላቅነቷ ለመሸጋገር የሚያስችላትን የህዳሴ ፕሮጀክት ነድፋ መንቀሳቀስ ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡ ይህም ዕውን ይሆን ዘንድ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር ሃገሪቱ ያላትን ሰፊ የኢንዱስትሪ መሠረት በመያዝ ዓለምን የሚያስደምም የምርቶች መፍለቂያ አገር ለመሆን የሚያስችል ራዕይ በመሰነቅ፣ በትልቁ አቅዳ በመስራት ላይ ትገኛለች።

 

ከተሞች እንዲለሙ፣ ስራ አጥነት እንዲቀረፍ፣ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንዲፋፋ፣ የአገር ውስጥ ምርታችን እንዲጨምር፣ የቴክኖሎጂና ዕውቀት ሽግግር እንዲስፋፋ፣ በአጠቃላይ የአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ ከማድረግ አንጻር የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የሚያስገኘውን ፋይዳ በመገንዘብ ለዚሁ የሚያግዙ በርካታ ዘመናዊ እና ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገነቡ ተደርገዋል፤ እየተገነቡም ይገኛሉ፡፡ የጥረቱ ፍሬም ከወዲሁ መጎምራት ጀምሯል።

 

በአገሪቱ እየተገነቡ ያሉት በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በብዙ   ሺህ ለሚቆጠሩ  ወገኖቻችን የስራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ወደ ውጭ የምንልካቸውን ምርቶች በዓይነት እና በመጠን በማሳደግም ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ አምራችነት ያሸጋግረናል፡፡

 

በአሁኑ ጊዜ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የውጭ አገራትን ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ከቪዬትናም ቀጥላ ሁለተኛዋ ተቀዳሚ የዓለማችን አገር የኛዋ ኢትዮጵያችን ናት። በ2017 ዓ.ም የአፍሪካ ቀዳሚ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን ራዕይ ሰንቃ እየተጓዘች ነው።  

 

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ሲነሳ ብዙ ጊዜ የሚወሳው የውጭ ኢንቨስትመንት ከፍ ካለም ስለስራ ዕድል ብቻ ነው፡፡ ዋናውና ሃገራችንን ከፍ የሚያደርጋት ግን በዘርፉ የአገር ውስጥ ባለሃብቶቻችን ሚና ነው። ለአብነት በሃዋሳ ፓርክ ወደ ተግባር የተሸጋገሩት 18 ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የዓለም ሥመጥር ኩባንያዎች ሲሆኑ ሌሎች ስምንት ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ናቸው።

 

መንግስት በያንዳንዱ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከ15 እስከ 30 በመቶ ያህሉ የማምረቻ ቦታ ለኢትዮጵያውን መተው እንዳለበት አስቀድሞ በዕቅድ ያካተተው ስለዚሁ የከፍታ ፋይዳ ነው። ከአገር ውስጥ ባለሃብት ተሳትፎ ባለፈ ዛሬ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምሁራንን እያፈራች ባለችው አገራችን በጊዜ ሂደት ከተቀጣሪነት አስተሳሰብ እየወጡ ራሳቸውን ለስራ ፈጣሪነት በሚያበቁ የአገር ዋልታና ምሰሶ ዜጎችን ለመፍጠር ነው።እነዚህን ለማፍራት ግን የመንግስት ድጋፍ ለብቻው ወንዝ አያሻግርም። በዋናነት በውጭ ገበያም ጭምር ሳይቀር ተወዳዳሪ መሆን ለጀመሩት የሃገር ውስጥ ምርቶች ሸማቹም ያለውን እይታ ሊያስተካክል ግድ የሚለው ይሆናል ማለት ነው። በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያችን ልታድግና ወደ ቀድሞ ታላቅነቷ ትመለስ ዘንድ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የምታደርገው ጥረት የህብረሰቡን ሁለገብ ተሳትፎ የሚጠይቅ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በአለም ገበያ ተወዳዳሪ ከሆኑት እና በሃገር ልጅ ብዙም ቁብ ካልተሰጣቸው ምርቶቻችን የተወሰኑትን እዚህ ጋር ማንሳቱ የሸማቹን ሚና ስለተመለከተው የህዳሴ ጉዞ ተገቢ ይሆናል።

እስከ 1940ዎቹ ድረስ የአገር ባህል ልብስ የመደበኛ ቀን ልብስ እንደነበር ይነገራል፡፡ የወንዶች ተነፋነፍና እጀ ጠባብ እንዲሁም የሴቶች ጥልፍ የቤት፣ የሥራና የክት ልብስም ነበር፡፡  ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን በአሠራር ከተለመደው ወጣ ያሉ የአገር ባህል ልብሶች ማስተዋል ተጀምሯል፡፡ እንደየአካባቢው ባህል የተለያየ አሠራርና ስያሜ ያላቸው የአገር ባህል ልብሶች፣ ለበዓላት ወይም ለተለየ መርሐ ግብር ብቻ የሚለበሱ ከሆኑ በኋላ በአቀራረባቸው ለውጥ ተደርጎባቸው በሃገር ልጅ እየተመረቱ ቢሆንም ገበያው ግን ወደ ነጮች ያደላ ይመስላል፡፡ ጫማና ሌሎችም የቆዳ ውጤቶች በተመሳሳይ በአይነት እና በጥራት የጨመሩ ቢሆንም ገበያው እንደጨርቃጨርቁ ወደውጭ ያደላ ይመስላል።

 

የሃገር ውስጥ ምርት ከሆኑና በአለም ገበያም ተወዳዳሪ እየሆኑ ከመጡት መካከል አንዱ የሆነውን የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ መንግስት መደገፍ የቻለበት ዋነኛ ምክንያት ዘርፉ ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ፣ ግብርናን መሰረት ያደረገ አሰራርን ስለሚከተል፣ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ምርት በማምረት የውጭ ምንዛሪን ማስፋት የሚችል በመሆኑ ነው። አገሪቱ በዚህ ዘርፍ የተሻለ አቅም ስላላት ድጋፉ ልዩ እንዲሆን ስለመደረጉም መንግስት በተደጋጋሚ ገልጿል።

 

ለኢንዱስትሪው የሚሆነውን ጥሬ ዕቃ አቅርቦት፣ በሰፊው ከማምረት ጀምሮ አልባሳትን እስከ ማዘጋጀትና ለገበያ እስከማቅረብ ድረስ ባለው የምርት ሰንሰለት ውስጥ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማሳተፍ ሰፊ አስተዋጽኦን የሚያደርግ በመሆኑ ዘርፉ እንዲያድግ የተለያዩ እገዛዎች በመደረግ ላይ ናቸው። ከዚህም ባሻገር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ መዳበር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

 

የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች በስፋት በማሳተፍ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ከሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች ጋር እንዲጣጣሙ እየተደረገ ነው። ይሁን እንጂ ሥራውን በቋሚነት ለማንቀሳቀስ የሚችሉ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ቁጥር ግን የተፈለገውን ያክል እየታየ አይደለም። አብዛኛው በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ አንቀሳቃሾች ወይም የኢንዱስትሪው ባለሀብቶችንም ስንመለከት የውጭ ባለሀብቶች የሚበዙ ስለመሆናቸው ከላይ በተመለከተው የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተሳትፎ ማጠየቅ ይቻላል።  

 

አገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂውን ስታወጣ የራሷ አላማን አንግባ ነው። የመጀመሪያው በኤክስፖርት መር ኢንዱስትሪ እንድትንቀሳቀስ በመፈለጉ፣ ሁለተኛው የኢንዱስትሪው ሴክተር የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቀነስና በኤክስፖርት መስኩ ዘርፉ እንዲመራ ለማድረግ ታስቦ ነው። እነዚህ ደግሞ አገሪቱ በዓለም ገበያ ላይ ጠንካራ ውድድር እንድታደርግ ያግዟታል። ይህን ለማምጣት በዓለም ገበያ የመወዳደር ብቃቱ ያላቸው፤ የምርት ጥራታቸውና ዋጋቸውን የሚያሻሽሉ ሞዴል ኢንዱስትሪዎችን መፍጠር ይገባል። ስለሆነም ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ባለሀብቱ እኩል የኢንቨስትመንት አማራጮች ተቀምጠዋል፡፡ ጠቀሜታቸውም በዚያው ልክ እንዲሆንም ለማድረግ በየደረጃው ለሁለቱም እገዛ ይደረጋል፡፡

የአገር ውስጥ ባለሀብት ልክ እንደ ውጪው የገበያ ውድድር ውስጥ ገብቶ ችግሮችን መቋቋም የሚችለው በእኩል ደረጃ ማሳተፍ ሲቻል መሆኑም ይታወቃል። የመወዳደር ብቃት ያለው ኢንዱስትሪ ለመገንባትም ሆነ በኤክስፖርት የተመራ ዕድገት መፍጠር የሚቻለውም ሁለቱን በእኩል ደረጃ ማሳተፍ ሲቻል ነው፡፡ በውጭ ንግድ ላይ የተመረኮዘ ኢንዱስትሪ የመሪነት ሚና ሊኖረው ይገባል ሲባልም ዋናው የኢንዱስትሪ ምርቶች በውጭ ገበያ ብቻ ሳይሆን ለአገር ውስጥ ገበያም ጭምር ጥራት ያላቸው ሆነው የሚቀርቡበትን አማራጭ መፍጠር ነው። በተመሳሳይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ ኢንዱስትሪዎች በአገር ውስጥ በማስፋፋት የውጭ ምርቶችን አገር ውስጥ ማምረት ሲቻል ነው፡፡ ስለዚህም አቅምን ያማከለ እንዲሆን ለማድረግ ለአገር ውስጥ ባለሀብቱ 15 በመቶ የሚሆነውን ከእራሱ አድርጎ 85 በመቶ ደግሞ ተበድሮ ወደ ሥራው እንዲገባ እየተደረገ ነው። በተመሳሳይ የውጭ ባለሀብቱ ለሥራው የሚሆን መሳሪያም ሆነ ገንዘብ ይዞ ስለሚመጣ የሚደረግለት ድጋፍ ከዚህ ያንሳል።  

 

ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ለአገር ኢኮኖሚ ፋይዳ ቢኖራቸውም የአገር ውስጥ ባለሀብቱን ያህል የውጭ ባለሀብቱ ጠቀሜታው የጎላ አይደለም። ለዚህ ደግሞ እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡት የአገር ውስጥ ባለሀብቱ ኢንዱስትሪዎችን በአገር ውስጥ ገንብቶ ትርፉማ እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር ትርፉንም ሆነ ዋናውን በአገር ኢኮኖሚ ላይ ማዋል የሚችል መሆኑን ነው፡፡

 

ሌላም አስረጅ ይጠቅሳሉ። የአገር ውስጥ ባለሀብቱ እንደውጭ አገሩ ሁሉ የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት ባሻገር የሰው ኃይል መቅጠሩም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ያስረዳሉ። ለዚህ በምክንያትነት የሚያነሱት  ጉዳይ ለእያንዳንዱ ሥራ ከውጭ አገር ባለሙያ ይልቅ የአገር ውስጥ ባለሙያን መጠቀማቸውን ነው።

 

የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች  ከጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ ባሻገር በየትኛውም መስክ ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑና ለአገር ኢኮኖሚ ፋይዳቸው የላቀ መሆኑን የሚገልጹ የምጣኔ ሃብት ምሁራን፤በአገር ውስጥ መሳተፋቸው በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን ተወዳድረው ማሸነፍ እንዲችሉ የሚያግዛቸው መሆኑን በአብነት ይጠቅሳሉ፡፡

 

የውጭ ምንዛሪን በብዛት በማስገባት የውጭ ባለሀብቱ ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ አለው። ባለሀብቱ መጀመሪያ ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ የራሳቸው ካፒታልና ቴክኖሎጂን ይዘው ነው። ይህ በአገር ውስጥ ያሉ ባለሀብቶች ቴክኖሎጂውን እንዲያውቁት ከማድረጉ በተጨማሪ የእርስ በርስ ውድድሩ እንዲፋጠን ያግዛል። የምርት ሁኔታውም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ስለሚሰራ ምርቱ እንዲጨምር ያደርጋል። በሌላ በኩል ዘመናዊ አሰራሮች ወደ አገር ውስጥ እንዲመጡ በማድረግ የአገር ውስጥ ባለሙያዎች የገበያውን ሁኔታ እንዲያውቁት ይረዳል። የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ዓለም አቀፍ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን መተንተንና ውጤቱን ማሣየት እንዲችሉም ያደርጋቸዋል።  

 

የመንግስት የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ብዙ ዘርፎችን የሚያካትት በመሆኑም እያንዳንዳቸው ልማቱን ለማሳካት ከሚጫወቱት የማይተካ ሚና በተጨማሪ በሌሎች ዘርፎች አፈጻጸም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዲያሳድሩ ያስችላል፡፡ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ልማትን ለማረጋገጥም የማገዛቸው አመክንዮ ፋይዳቸውን የጎላ ያደርገዋል።

 

በሌላ በኩል ጥራታቸውን የጠበቁ የሀገር ውስጥ ምርቶች ለአገሪቱ ገጽታ ግንባታ የጎላ ሚና አላቸው።ሆኖም ምርቶቹን በስፋት በማስተዋወቅ የሕብረተሰቡን አመለካከትና አጠቃቀም በማሳደጉ ረገድ የሚሰሩት ሰራዎች በሚፈለገው ደረጃ አይደሉም። የሀገር ውስጥ ምርቶች አጠቃቀም መጎልበት የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ለአገሪቱ ልማት፣ ሰላምና ዲሞክራሲያዊ ግንባታ ትልቅ ሚና ይጫወታል።

 

ያም ሆኖ ግን በሁሉም ዘርፍ  ያሉ ባለሙያዎችና ነጋዴዎችን ጨምሮ ሸማቾች ይልቁንም አምራቾቹ ጭምር ምርቶችን በሳይንስና በገበያ መርህ ከመመዘን ይልቅ በተመረቱበት አገር የመፈረጅ አመለካከታቸው በትጋታችን ልክ ተጠቃሚ እንዳንሆን አድርጎናል። ከዚህ በተጨማሪም የአገሪቱን የጥራት ደረጃ መመዘኛዎች ያለመቀበል፣ የጨረታ ሰነዶችን ለውጭ አገር ምርቶች የመስጠትና  የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶች መኖራቸውም በተመሳሳይ እጀ ሰባራ እንድንሆን አድርጎናል።ስለሆነም የሃገር ውስጥ አምራቾችን በሃገር ውስጥ ሸማቾች መደገፍ የሁሉም የቤት ስራ ይሆናል።

 

ከዚህም ባሻገር እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የአገሪቱን የምርት ፍተሻና ቁጥጥር ስርዓት ማጠናከር፣ የመገናኛ ብዙኃን የአገር ውስጥ ምርቶች መረጃዎችን ለሕብረተሰቡ በተከታታይ የሚያቀርቡበትን አሰራር መዘርጋት እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ማካሄድ ያስፈልጋል ።እንደ ቻይናና ህንድ ያሉ አገራትን ተሞክሮ በመውሰድ የአገር ውስጥ ምርቶችን በአገር ውስጥና በውጭ አገራት በስፋት የማስተዋወቅና አጠቃቀማቸውን የማሳደግ ስራዎችም ሊሰሩ ይገባል ።

 

የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ሀይል አገልግሎት የህዝብና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ እንዳሉት የሕብረተሰቡን የሀገር ውስጥ ምርቶች የመጠቀም አመለካከትና የአጠቃቀም ልምዱን ለማሳደግ የምርቶቹ ጥራት መሻሻል ያስፈልጋል። ከሁሉም በላይ ግን ሃገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ጥራት ማስጠበቅና ደህንነታቸውን ማረጋገጥ የዘወትር ስራ ሊሆን ይገባል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy