Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመቻቻላችን ምስጢሮች

0 244

Get real time updates directly on you device, subscribe now.


የመቻቻላችን ምስጢሮች

                                                          ታዬ ከበደ

በአገራችን ያለውን የሃይማኖት መቻቻል የሚያኮራ ነው። የሃይማኖት እኩልነትና የእምነት ነፃነት በኢፌዴሪ ህገ መንግስት በመከበሩና በመረጋገጡ ሁሉም ሃይማኖት እኩል ሆነዋል። የእምነት ነፃነታቸውም የተጠበቀ ነው። አንዱ ሃይማኖት በሃይል የእኔን ተቀበል የሚልበት ዘመን አክትሟል። የኢትዮጵያ ህዝቦች አንዱ የሌላውን እምነትና ሃይማኖት በማክበር አብሮ የመኖር ባህልና እሴት ያለው ነው። እንዲያውም አንዱ ሃይማኖት ወይም እምነት ቤተ እምነቱን ሲያሰራ ሌላው የእምነት ተከታይ ገንዘብ እያዋጣ በመቻቻል የሚኖር ህዝብ ነው። ይህን መሰሉ መቻቻል ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

የዛሬዋ ኢትዮጵያ ከትናንትዋ የተሻለችና የሃይማኖት ብዝሃነት የሚስተናገድባት ሀገር፣ ማንኛውም ዜጋ የመረጠውን ሃይማኖትና እምነት የመያዝና የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱንም ያለአንዳች ቅድሚያ ሁኔታ የማምለክ ብሎም የመከተልና የማስፋፋት መብቱን እንዲያጣጥም አድርጓል።

በሃይማኖቱና በእምነቱ ጣልቃ የሚገባ የትኛውንም አካል የማስቆም መብቱን መጠቀም የመቻሉ ጉዳይንም በተግባር እያረጋገጠ ነው፡፡ እናም የሀገራችን ህዝቦች የሃይማኖት እኩልነት አጀንዳ በማይሆንበት ዘመን ላይ ይገኛሉ፡፡ የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት የግልና የቡድን መብቶችን የሚያስከብር በመሆኑ የሃይማኖት ጉዳይ በዚሁ አግባብ ምላሽ ማግኘት ችሏል፡፡

እናም  በህገ-መንግስቱ ስፍረው የሚገኙትና ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው 3ቱ መርሆዎች (የእምነት ነፃነት፣ የሃይማኖት እኩልነትና የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት) ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ማደግና ማበብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኙ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል፡፡

ዛሬ በሀገራችን መንግስታዊ ሃይማኖት የለም። ሃይማኖታዊ መንገስትም አይኖርም። መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ፣ ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ መግባት የሚታሰብ አይደለም፡፡ ማንኛውም ግለሰብ የመረጠውን ሃይማኖትና እምነት የመያዝና የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱንም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የማምለክ፣ የመከተል፣ የማስፋፋት መብቱም በይፋ ተረጋግጧል፡፡

በዚህም ሃይማኖትና መንግስት የተለያዩበት፣ የመንግስታዊ ሃይማኖት አመለካከት የከሰመበት ሁኔታን ዜጎች የቃል ኪዳናቸው ሰነድ በሆነው ህገ – መንግስታቸው አማካኝነት የሃይማኖት እኩልነትን ያስከበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት በመቻላቸው፤ የሃይማኖት ብዝሃነትን ማስተናገድ የምትችል አዲሲቷ ኢትዮጵያን ማየት ተችሏል፡፡  እናም ሀገራችን በእኩልነትና በመቻቻል ባህል የሃይማኖት ብዝሃነት የሚስተናገድባት ሀገር በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆትን ማትረፍ ችላለች፡፡

አገራችን ውስጥ ማንኛውም ዜጋ የመሰለውን እምነት የመከተል መብት ያለባት እንዲሁም የሃይማኖቶች እኩልነት የተረጋገጠባት ሀገር መሆኗና ለተግባራዊነትም በኢፌዴሪ ህገ- መንግስት በተለያዩ አንቀፆች ተደንግጎ ወደ ተግባር በመሸጋገር ለሀገራዊው ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው መፋጠን ከፍተኛ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል፡፡ ይህም አሁን ሀገራችን ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ሃይማኖት የመቻቻልና የመከባበር እንጂ የግጭት መንስኤ ሊሆን እንደማይችል የሚያስገነዝበን ነው።

እርግጥም የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ሃይማኖት የግጭት መንስዔ ሊሆን እንደማይችል ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም፡፡ የሃይማኖት እኩልነት በተረጋገጠባት ኢትዮጵያ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚካሄድ ማናቸውም እንቅስቃሴ ቦታ የለውም። ሊኖረውም አይችልም። ምክንያቱም ህዝቦች ከዘመናት የሃይማኖትና የእምነት ጭቆና ተላቀው ሃይማኖትና መንግስት የተለያዩበትን፣ መንግስታዊ ሃይማኖት የሌለባትን ብሎም የማይታሰብባትን ሀገርን በመገንባት ላይ በመሆናቸው ነው፡፡

የሀገራችን ህዝቦች የቃል ኪዳናቸው ሰነድ በሆነው የኢፈዴሪ ህገ መንግስት የሃይማኖት እኩልነትንና የእምነት ነፃነትን በማስፈርና በተግባር በመተርጎምም የሃይማኖት እኩልነትን ያስከበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት በመቻላቸው፤ የሃይማኖት ብዝሃነት የምታስተናግድ አገርን ፈጥረዋል፡፡

ስለሆነም ዛሬ ከትናንቱ የተለየ የሃይማኖት ብዝሃነት በሚስተናገድባት ኢትዮጵያ ማንኛውም ዜጋ የመረጠውን ሃይማኖትና እምነት የመያዝና የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱንም ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ የማምለክ ብሎም የመከተልና የማስፋፋት መብቱን ማጣጣም ችሏል፡፡ በዚህም የሀገራችን ህዝቦች የሃይማኖት እኩልነት አጀንዳ በማይሆንበት ዘመን ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ለዘመናት ይዘናቸው የመጣነው የመቻቻል ባህል በአገራችን የእምነት ነፃነትና የሃይማኖት እኩልነትን ያጠናከረ ነው፡፡

ምንም እንኳን የጎላ ባይሆንም ከዚህ የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በሚፃረር መልኩ የሃይማኖት አክራሪነትን ለማራመድ የተካሄደው ጥረት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በሁሉም የእምነት ተከታዮች አማካኝነት በእንጭጩ እንዲቀር ተደረገ እንጂ።

አገራችን ውስጥ ከአክራሪነት ይልቅ መቻቻልና መከባባር ከፍ ያለው ለዘመናት የዘለቀው ሃይማኖታዊ ጭቆናና በደልን ጠንቅቆ የሚገነዘበው መላው ኢትዮጵያዊ፤ ትናንትን የሚጠላ እንጂ የሚያማትር አለመሆኑን እንዲሁም ለዘመናት ባካሄደው ትግልና ባስመዘገበው ውጤትም የሚረካና ሁሌም ለሰላም ቀናዒ እንጂ የሚማረር ባለመሆኑ ነው፡፡

እንደሚታወቀው የሀገራችንን ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ ስርዓት ለየት የሚያደርገው አንድ ወሳኝ ነጥብ ቢኖር፤ በህገ -መንግስቱ ላይ የሰፈሩ መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች ይበልጥ ተግባራዊ እንዲሆኑ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑ ነው፡፡ በህገ -መንግስቱ ውስጥ ህጋዊ ከላላ ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የእምነት ነጻነትና የሃይማኖት እኩልነት በመሆናቸው፤ እነዚህን መብቶች ሳይሸራረፉ ገቢራዊ ለማድረግ መንግስት ያልተቆጠበ ጥረት አድርጓል፡፡

የማንኛውም እምነት ተከታይ ያለማንም አስገዳጅነት በመረጠው ሃይማኖት እንዲመራ፣ ሃይማኖታዊ ግዴታውን ያለማንም ጣልቃ ገብነት እንዲፈጸም እንዲሁም መንግስትና ሃይማኖት ብሎም ሃይማኖትና የትምህርት ተቋማት ተነጣጥለው ተግባራቸውን እንዲከውኑ በማድረግ ረገድ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌው ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ በተግባር እንዲተረጎም አድርጓል፡፡

ባለፉት 23 ህገ መንግስታዊ ዓመታት ሁሉም ሃይማኖቶች አምልኳቸውን የሚፈጽሙባቸው የእምነት ቦታዎች ከመስፋፋታቸው በተጨማሪ፤ የመቻቻል ባህላችን ማሳያ የሆኑት የሃይማኖት በዓላት ክብደት በሚሰጣቸው ሁኔታ እንዲከበሩ አስፈላጊ የሚባሉ ጉዳዮች ተመቻችተዋል፡፡ እነዚህ የሃይማኖትት እኩልነትን በተግባር ለመተርጎም የተከናወኑ ሃቆች ሀገራችን ውስጥ በማንኛውም እምነት ተከታይ ዘንድ ነባሩን የመቻቻል ባህል ይበልጥ ያሰፉና ያረጋገጡ ናቸው፡፡ በመሆኑም ዛሬም ቢሆን የእያንዳንዱ እምነት ተከታይ ለዘመናት የዘለቀውን መቻቻላችንን ለማቆርፈድ የተሰለፉ ሃይማኖታዊ ያልሆኑ ፖለቲከኞችን ከውስጡ ለይቶ በማጋለጥና ሴራቸውን ይፋ በማድረግ ለሰላሙ መትጋት ይኖርበታል፡፡ ይህን በማድረግም ለዘመናት የገነባነውን የመቻቻላችንን ምስጢሮች በማጎልበት መብቶቻችንን በተጨባጭ ማጠናከር እንችላለን፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy