የቁርጠኝነቱ ምክንያቶች
ዳዊት ምትኩ
በአሁኑ ሰዓት አርሶና አርብቶ አደሩ ለተፋሰስ ልማት ቁርጠኛ ሆነው በመስራት ላይ ይገኛሉ። የቁርጠኝነት ምክንያቶች በርካታ ናቸው። በዋነኝነት ግን መንግስት እየተከተለ ያለው ትክክለኛ የልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውጤት እያመጡላቸው መሆኑን ስለተገነዘቡ ነው። መንግስት በተፋሰስ ሥራዎች ላይ እያካሄደ ያለው ድጋፍ እያደረገ ነው።
ቀደም ሲል ከእጅ ወደ አፍ የነበረው የአርሶ አደሩ የአስተራረስ ዘዴ ዛሬ ተቀይሯል። አንዴ ያመርት የነበረው አርሶ አደር ከሁለት ጊዜ በላይ በማምረት ተጠቃሚ እየሆነ ነው። አርብቶ አደሩም በተፋሰስ ሥራዎች አማካኝነት ወደ ከፊል አርብቶና አርሶ አደርነት እየተቀየረ ነው። በተፈጥሮ ዝናብ ላይ ጥገኛ የነበረው አርሶና አርብቶ አደር በተፋሰስ ስራዎች ምክንያት የውሃ ችግሩ እየተቀረፈለት ነው። እነዚህ ክንዋኔዎች አርሶና አርብቶ አደሩ ህይወቱን እየለወጡ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ናቸው። ይህ የተፋሰስ ስራ በተለይም የወጣቶችን ስራ አጥነት በመቅረፍ ህይወታቸውን በመለወጥ ላይ ይገኛል።
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለእርሻ ሊውል የሚችል ሰፊና ለም መሬት እንዲሁም የአርሶ አደሩ ጉልበት አለ። በአገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ታዲያ ይህ ግብርናው ውጭ ከፍተኛ እምቅ ሃብት ነው። ይህ ሃብት ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ሲሆን፤ ገና ምንም ያልተነካ እምቅ በመሆኑም ውጤት ሊያመጣ የሚችል ነው። ሀገሪቱን ለመለወጥ ወሳኙ ሃብት ተደርጎ መወሰዱም እንዲሁ።
በያዝነው አምስት ዓመታት የግብርና ዘርፍ በየዓመቱ ቢያንስ በአማካይ የስምንት በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ተደርጎ ውጤት ተገኝቶበታል። ምርጥ ተሞክሮ ያላቸውን አርሶ አደሮች ውጤት ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች በማስፋፋት የዋና ዋና ሰብሎችን ምርት በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ ነው። በዚህም መሠረት የግብርናን ዘርፍ አማካይ ዓመታዊ ዕድገት በመሠረታዊ አማራጭ ከነበረው ስምንት በመቶ ወደ 11 በመቶ ከፍ እንዲያደርገው ዕቅድ ተይዟል። ይህ ዕቅድ ይሳካ ዘንድም በዋናነት አስተዋፅኦ የሚያደርጉት ዋነኛ የሰብል ምርቶች በ16 በመቶ እንዲያድጉ ወሳኝ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
የዋነኛ የሰብል ምርቶች ከጠቅላላው የግብርና ምርት ተጨማሪ እሴት ያላቸው ድርሻ በአማካይ 40 በመቶ ነው። በዚህ ምክንያት ይህ የዕድገት ጭማሬ በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ዕድገት ላይ ሊኖረው የሚችለው ግብረ መልስ ሳይካተት በግብርና ዕድገት ምክንያት ብቻ በዕቅዱ ዘመን አማካይ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት በከፍተኛ የዕድገት አማራጭ 12 ነጥብ ሁለት በመቶ ያደርሰዋል ተብሎ ይታመናል። ይሁንና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመንም ግብርና በጥቅሉ ዋነኛው የዕድገት ምንጭ ሆኖ መቀጠሉ ይቀጥላል።
ይህን ለመከወንም መንግሥት ለዘመናዊ ግብርና ያልተደፈረውን የአገሪቱን አርሶ አደር የአስተራረስ ዘይቤ የመለወጥን አስፈላጊነት ተገንዝቦ በቀየሰው መስመር እነሆ የሚታየ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው። አርሶ አደሩ በድርቅ በቀላሉ መጠቃት ምክንያቱም ደግሞ የዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ አለመኖር እንደሆነ ተረጋግጧል።
በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ኑሮው እንዲሻሻል ተገቢ ትኩረት አግኝቷል። ለዚህም በቂ ማሳያዎችንም ማቅረብ ይቻላል። መንግሥት የዘመናት ቁጭቱን አገራዊ መሠረት ባላቸው አቅጣጫዎች የመፍታት ትግሉን እያካሄደ ነው። አርሶ አደሩ ከራሱ ተርፎ ለገበያ በማምረት ተጠቃሚ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ ሀገሪቱም ከግብርናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን አረጋግጧል።
በአርሶ አደሩ እጅ እንዳለ የሚታሰበው መሬት አነስተኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ካለችው መሬት የሚያገኘው ምርት ዝቅተኛ ነው። ይህን መንግሥት በሚገባ በመገንዘቡ ዘርፈ ብዙ የማሻሻል ጥረቶች አድርጓል። በውጤቱም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን ይዞ ለውጥ ማምጣት አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ መስበር ችሏል።
አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ለሰፋፊ እርሻዎች ትኩረት መስጠትና ለውጥ ማምጣትን የሚሰብኩ ወገኖች እንዳሉ ግልጽ ነው። እነዚህ ወገኖች የሚሰብኩት በግብርናው ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ትኩረት የመስጠትን አስፈላጊነት የሚሰብክ ነበር። ይህ ደግሞ ሀገራዊና ህዝባዊ ጥቅም የሚመጣበትን ምስጢር ካለመረዳት ወይም ለመረዳት ካለመፈለግ የመጣ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።
መንግሥት አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ገልጿል። ይህን የመንግሥትን ፖሊሲ ትክክለኛነት ለማረጋገጥም ተችሏል። የሚታይና አሳማኝ ውጤት ማምጣትም እንደተቻለም ከአርሶ አደሩ በላይ ምስክር የሚያሻው አይመስለኝም።
ምንም እንኳን ለውጡን የማይፈልጉ ኃይሎች ስህተት ፈላጊ ሆነው ቢቀጥሉም፤ በግብርናው ዘርፍ ባመጣነው ለውጥ ብዙዎች በመስማማት ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ፣ ለምርቱ ገበያ በማመቻቸትና ከግሉ ዘርፍ ጋር ትስስር በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን አሳድጋ ተጠቃሚ በመሆን ላይ ትገኛለች።
አርሶ አደሩ የለውጥ መስመሩን ተረድቶ በእምነት ወደ ሥራው በመግባቱ በዓመት ሁለቴና ከዚያም በላይ ለማምረት ችሏል። እንዲሁም በከርሰ ምድርና በገጸ -ምድር ያለውን የውኃ ሃብት የመጠቀም ሰፊ ተግባር አከናውኗል።
በውኃ ማሰባሰብና ማቆር፣ የጉድጓድ ውኃን በመጠቀም የወንዝ ውኃን ጠልፎ ጥቅም ላይ በማዋል ብዙ ርቀት ተጉዟል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለከተማው ነዋሪዎች ከፍተኛ ፍላጎት የሆኑትን ምርቶች ማቅረብ ችሏል። ከነዚህ ውስጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ናቸው።
ከዝናብ ጥገኝነት በተላቀቁ አመራረት የተገኙትን ምርቶች መጠቀምም እየተቻለ ነው። የመስኖ ልማት ሥራው በበጋ የበቆሎ እሸት ተመጋቢዎች እንዲሆን አስችሎናል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ሥራው ከሁለት እጥፍ በላይ አድጓል።
ለአርሶ አደሩም በዚያው ልክ ገበያው ተመቻችቷል። አርሶ አደሩ በራሱ ባቋቋማቸው የአርሶ አደሮች የህብረት ሥራ አማካይነት ምርቱን ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል። በዚህም ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ነው።
የግብርናው ዘርፍም በአስተማማኝ ሁኔታ ገበያው ሳያሳስበው ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ላይ ብቻ አተኩሮ ለልማት ለውጥ ሽግግሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርበት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል።
ይህ የሆነውም መንግስት ለተፋፈስ ስራዎች ቅድሚያ በመስጠቱ ምክንያት ነው። ግብርና ለወጣቶች ስራን የሚፈጥር ሆኗል። ይህ የስራ ፈጠራ በተፋሰስ ልማት ስራዎች እጅግ እንዲጠናከር እየተደረገ ነው። መንግስት በተፋሰስ ስራዎች አማካኝነት ለወጣቱ እየፈጠረ ያለው ስራ አርሶና አርብቶ አደሩን እንዲሁም ከፊል አርብቶ አደሩን በስራው ላይ ቁርጠኛ አቋም እንዲይዝ አድርጎታል። ይህ ቁርጠኛ እምነትም የተፋሰስ ስራው ውጤታማ እንዲሆን እያደረገው ነው።