Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የብልጽግና መሰላል

0 233

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የብልጽግና መሰላል

ብ. ነጋሽ

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ አቅም ከዓለም ሃገራት የመጨረሻው ተርታ ላይ ነበረች። ምናልባት አንድ ወይም ሁለት ሃገራት ነበሩ ከኢትዮጵያ በታች የሚጠቀሱት። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት፣ በተለይ ከአስራ አምስት ዓመታት ወዲህ ግን ይህ የሃገሪቱ ገጽታ እየተቀየረ መጥቷል። በእነዚህ አስራ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በአማካይ ከ10 በመቶ በላይ እድገት ማስመዝገብ ችላለች። ይህ የኢኮኖሚ እድገት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመሰከረለት ነው። ኢትዮጵያ አሁን በዓለም ፊት ባለተስፋ ሃገር ነች። ይህ እድገት ቀጣይነት እንደሚኖረው የኢፌዴሪ መንግስት ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፍ ተቋማት ትንበያዎችም ያመለክታሉ።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ.ኤም.ኤፍ) ኢትዮጵያ በተጀመረው የፈረንጆቹ 2018 ዓ/ም የ8 ነጥብ 5 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት እንደምታስመዘግብ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት አስታውቋል። አይ ኤም ኤፍ  ሃገሪቱ ለምታስመዘግበው ፈጣን እድገት የወጪ ንግዱና ኢንቨስትመንት መነቃቃት እንዲሁም ከድርቅ እያገገመች መምጣቷን በምክንያትነት አስቀምጧል። ኢትዮጵያ ባለፉት አስርት ዓመታት በሰው ሃብት ልማት ላይ የሰራችው ስራ ውጤት እያሳየ መምጣቱን ያነሳው የአይ ኤም ኤፍ ትንበያ፣ የግል ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ ረገድም እድገት መመዝገቡን አመልክቷል።

የአይ ኤም ኤፍ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት ትንበያ ያሳወቀበት ሪፖርት የሃገሪቱ የድህነት ምጣኔ እ ኤ አ 2000 ዓ/ም ከነበረበት 44 በመቶ በ2015/16 ወደ 23 ነጥብ 5 በመቶ ዝቅ ማለቱን አስታውሷል። በ2016/17 በመሠረተ ልማት እና የአምራች ኢቨስትመንት እድገቱን በማስቀጠል የኢንዱስትሪ ዘርፉ መስፋቱንም ይገልጻል።

ልብ በሉ፤ ከአስር ዓመታት በፊት አይ ኤም ኤፍ ሃገሪቱ የምትከተለው ልማታዊ የእድገትና ልማት ሞዴል ኢኮኖሚውን ማሳደግ አይችልም የሚል አቋም የነበረው ተቋም ነው። የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ሊሰወርና ክርክር ሊጋብዝ የማይችል ተጨባጭ እድገት ማስመዝገብ መቻሉ አይ ኤም ኤፍ እውነታውን እንዲቀበል አድርጎታል። በቅርቡ የተቋሙ ዳይሬክተር ክርስቲና ላጋርድ ያደረጉት ጉብኝት አንዱ ዓላማ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት ሞዴል መረዳት ነበር።

በተመሰሳይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርት ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቧን እንደምትቀጥል አሰታወቋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከአስር ቀናት በፊት በአዲስ አበባ ይፋ ያደረገው የ2018 ዓ/ም ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሁኔታና ትንበያ ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት፣ በኢንቨስትመንትና በቢዝነስ በኩል የሚያሰሩ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መምጣታቸው ለዕድገቱ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው አመልክቷል።

በመሰረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪና በውጭ ኢንቨስትመንት የሚደረገው የፋይናንስ ማበረታቻ፣ እንዲሁም በቱሪዝም መስክ ከፍተኛ የሃገር ውስጥ ፍላጎት እየጨመረ መምጣት ዕድገቱን እየደገፈ እንደሚቀጥልም ነው የተነበየው። በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት ሃገሪቱ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች በዓለም አቀፍ ዋጋ ቢቀንስም፣ እንዲሁም በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር ቢያጋጥምም ኢኮኖሚዋ ጠንካራ የመቋቋምና የማገገም ሁኔታ አሳይቷል ይላል የተመድ ሪፖርት።

የዜጎች የግል ፍጆታና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የገበያ ፍላጎት መጨመር እንዲሁም መንግስት በመንገድ፣ በኃይልና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ መሰረተ ልማቶች የሚያውለው በጀት ማደግ ለኢኮኖሚው እድገት ጉልህ ሚና መጫወቱንም ሪፖርቱ አስቀምጧል። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የአገልግሎት ዘርፉ በሃገሪቱ አጠቃላይ ምርት ውስጥ ቀዳሚ ቢሆንም ድርሻው እየቀነሰ የኢንዱስትሪ ዘርፉ እየተስፋፋ መሆኑንም ሪፖርቱ አመልክቷል።

በአጠቃላይ፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማስመዝገብ የሚያስችለውን መሰላል ጨብጧል። በኢንደስትሪው ዘርፍ በተለይ በአነስተኛ ኢንደስትሪ በሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ከሚካሄደው ኢንቨስትመንት ባሻገር፣ ሃገሪቱ በአፍሪካ የውጭ ኢንቨስትመንት የስበት ማዕከል ለመሆን በቅታለች። የኢትዮጵያ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት በየዓመቱ የ12 በመቶ እድገት በማስመዝገብ አሁን ዓመታዊ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠኑ ከ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር በላይ ደርሷል።

የተባበሩት መንግስታት የንግድ እና ልማት ድርጅት በአውሮፓውያኑን የ2017 ዓ/ም የኢንቨስትመንት ትንበያን በተመለከተ ሰኔ፣ 2009 ዓ/ም ያወጣው ሪፖርት፣ ከጥር ወር 2008 እስከ ታህሳስ ወር 2009 ዓመተ ምህረት ድረስ ኢትዮጵያ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መጠን ያለው ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት አግኝታለች። ሪፖርቱ ኢትዮጵያ ያገኘችው ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት፣ ምስራቅ አፍሪካ ትልቅ ለውጥ  የታየበትና ከዚህ ቀደም ያልነበረ ነው ብሏል። በ2016 ምስራቅ አፍሪካ 7 ነጥብ 1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ያገኘች ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ግማሽ ገደማ የሚሆነውን የወሰደችው ኢትዮጵያ ነች። በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ያገኘችው አጠቃላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን ከቀደመው ዓመት በ46 በመቶ እድገት አሳይቷል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመታት ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት መጠኗን እንደምታሳድግ በተጨባጭ ያለው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታም ያመለክታል። በተለይ የውጭ ኢንቨስተሮችን ከመሬትና ከመሰረተ ልማት ዝርጋታ ጋር በተያያዘ ይገጥማቸው የነበረውን ረጅም ጊዜ የሚወስድና አታካች ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የሚያስቀረው የኢንደስትሪ ፓርኮች ግንባታ፣ የሃገሪቱ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት በከፍተኛ መጠን ሊያድግ እንደሚችል ያመለክታል።

ኢትዮጵያ አሁን ያላትን 7 የኢንደስትሪ ፓርኮች ቁጥር በያዝነው ዓመት ወደ 15 ታሳድጋለች ተብሎ ይጠበቃል። በተያዘው ዓመት የቂሊንጦ ፋርማሲቲካል፣ ቦሌ ለሚ ቁጥር 2፣ የባህር ዳር፣ የጅማ፣ የደብረ ብርሃንና አረርቲ፣ የድሬዳዋ እንዲሁም የአዳማ ኢንደስትሪያል ፓርኮች ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። በቅርቡ የተመረቁት፣ የኮምቦልቻና የመቀሌ የኢንደስትሪ ፓርኮች ወደማምረት ስራ በመሸጋጋረ ሂደት ላይ ሲሆኑ፣ በ2008 ማገባደጃ ላይ የተመረቀው የሃዋሳ የኢንደስትሪ ፓርክ ፋብሪካዎች የጨርቃጨርቅ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀምረዋል። እነዚህ የኢንደስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚቋቋሙ በተለያየ ዘርፍ የሚሰማሩ ፋብሪካዎች ወደስራ ሲገቡ አጠቃላይ የኢንደስትሪ ምርት የውጭ ገበያ ድርሻው ወደ 50 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ከላይ ለማሳያነት የተጠቀሱ ሁኔታዎች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ላይ መሆኑን ያመለክታሉ። ሃገሪቱ በዚህ ከቀጠለች ከሰባት ዓመት በኋላ፣ ማለትም በ2017 ዓ/ም ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ያላት ሃገር መሆን ትችላለች። ይህ ደግሞ ሃገሪቱ ነድፋ ስራ ላይ ያዋለቻቸው የእድገትና የልማት ፖሊሲዎችን ትክክለኝነት ያሳያል። በአጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ ሃገሪቱ ድህነትን ቁልቁል ለማየትና ታሪክ ለማድረግ በሚያስችላት ጠንካራና የብልጽግና ማማ ላይ በሚያደርሳት መሰላል እየተወጣጣች ትገኛለች።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy