Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የተሰሚነታችን እውነታዎች

0 232

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የተሰሚነታችን እውነታዎች

ዳዊት ምትኩ

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ፣ በአፍሪካና በዓለም ደረጃ ያላትን የዲፕሎማሲ ተሰሚነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። አገራችን በኢጋድ በኩል የቀጠናውን ሰላም ለማጠናከር፣ የኢኮኖሚ ትስስርን ለመፍጠር በምታደርገው ስራ ያላትን ተሰሚነት አላት። በአህጉር ደረጃም ለአፍሪካ ይበጃል የምትለውን ሃሳብ በማፍለቅ፣ የአህጉሪቱ ቃል አቀባይና ተቆርቋሪነት እንዲሁም እንደ “ኔፓድ” ዓይነት አህጉራዊ ድርጅቶች ውስጥ በምታደርገው አስተዋፅኦ ተሰሚነቷ እየጨመረ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃም በአየር ንብረት ለውጥ፣ በዓለም ኢኮኖሚ ፎረም፣ በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በምታደርገው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ተሰሚ መሆን ችላለች።

የኢፌዴሪ መንግስት ለሀገራችን ሰላምና ልማት  እውን መሆን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ሁሉ፤ የጎረቤት ሃገሮች ሰላምና ልማትም እንዲፋጠን ካለው ጽኑ እምነት በመነጨ በጋራ ማደግ ቀዳሚ ምርጫው ነው። ለምን ቢሉ የሀገራችን ሰላምና ልማት ለአካባቢያችን ዕድገት ድርሻ እንዳለው ሁሉ፤ የአካባቢያችን ሰላምና ልማትም ለሀገራችን ዕድገት መፋጠን የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ የላቀ እንደሚሆን በፅናት ስለሚያምን ነው።

ታዲያ በሀገራችን በመካሄድ ላይ ያለው የተፋጠነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እንዲሁም የተጀመረው የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ሀገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ዓላማን የሰነቀና ውጤቱም ለሀገራችንም ሆነ ለአካባቢያችን ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ መሆኑ የሚታበይ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መንግስት ሀገራዊና አካባቢያዊ ሰላምን ከማስፈን አኳያ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ይህም በቀጠናው ውስጥ ተሰሚ እንድንሆን አድርጎናል።

የቀጠናውን አገራት በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር እየተደረገ ያለው ጥረት ሌላኛው የተሰሚነታችን እውነታ ነው። አገራችን ዛሬም እንደ ትናንቱ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ውስጥ ካሉት ሀገራት ጋር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ትስስር እየፈጠረች መሆኑን ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዘለግ ላሉ ዓመታት በትስስር ከሚገኝ ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ ጥቅም ምንም ነገር አላገኘም። ለዚህ ደግሞ በቀጣናው ውስጥ የነበረው ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ጦርነት በምክንያትነት ይጠቀሳል።

ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት ይህ የጦርነት ታሪክ በአንፃራዊ ሁኔታ ጋብ በማለቱ፤ የቀጣናው ሀገራት ከሁለንተናዊ ትስስር የሚገኘውን ጥቅም ለማጣጣም በርካታ ውጥኖችን ይዘዋል። በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኳቸው አብነታዊ ስምምነቶች የዚህ አባባሌ አስረጅ ይመስሉኛል። ይህ ሁኔታም ሀገራችን በተጎናፀፈችው ሰላም የተገኘ መሆኑ አይታበይም።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ መድረክም በአዲስ ገፅታ መታየት ከጀመረች ሰነባብታለች። በዚህም ሳቢያ ሀገሪቱ በምስራቅ አፍሪካም ይሁን በዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ መድረኮች ተሰሚነቷ እየጎለበተ መጥቷል። የዲፕሎማሲው ተሰሚነቷ ሁሉንም የቀጣናውን ብሎም የአህጉሪቱን ሀገራት እየሳበ በመምጣቱም ዛሬ የኢትዮጵያን ምክርና ልምድ ለመጠየቅ ወደ መዲናችን የሚያቀኑ የአፍሪካ መሪዎች እየተበራከቱ እንዲመጡ ምክንያት ሆኗል።

ለዚህም በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ላይ የሰፈሩት ወሳኝ የዲፕሎማሲ አቅጣጫዎች የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። ህገ መንግሥቱ የአካባቢውንና ጎረቤት ሀገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሠላም እንዲሰሩ የሚጋብዝና በገራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲ መሰረትን እውን አድርጓል። ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና ሀገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ ተልዕኮንም ተጫውቷል።

እርግጥ ኢትዮጵያ ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖራት ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ በሚቀንስ ደረጃ የተተለመ ነው። ይህም ዲፕሎማሲው በበቂ ጥናት ላይ ተመስርቶ አደጋዎችን የመቀነስ እንዲሁም ቀጣናዊ ግጭቶች ሲፈጠሩ በድርድር እንዲፈቱ የማድረግ መንገድን የሚከተል ነው።

በአፍሪካም ዘንድ ተሰሚነታችን ጨምሯል። አድዋ ላይ የፓን አፍሪካ ዩኒቨርስቲ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተጥሏል። ቀደምት አባቶቻችን በነጮች በጥቁር አፍሪካ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ፋሽሽቶችን ድል ባደረጉበት አድዋ ላይ ይህ ዮኒቨርስቲ ግንበታን ለመጀመር ዝግጅቱ ተጠናቋል። የግንባታው መሰረት ድንጋይ እንዲጣል መደረጉ ሀገራችን ለአፍሪካ ያበረከተችውና እያበረከተችው ያለውን አስተዋፅኦ የሚያሳይ ነው።

ይህም በቀደምት ዘመናት ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የነፃነት ጮራ መሆኗ፣ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ አገዛዝ እንዲወጡ በፋና ወጊነት መንቀሳቀሷና በአሁኑ ወቅት የአፍሪካዊያን ድምፅ በመሆን እየተጫወተች ላለችው ሚና እውቅና የሰጠ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ አህጉራዊ የሆነውን ድርጅት ከማዋለድ ጀምሮ በማሳደግና ወደ ኅብረትነት እንዲቀየር በማድረግ ኢትዮጵያ ታሪካዊ ድርሻዋን ተወጥታለች።

ሀገራችን እንደ መስራችና እንደ ዋና መቀመጫነቷም የትኛውም የፖለቲካ ሥርዓት ይሁን የቱም በአፍሪካዊ ወንድማማችነትና መንፈስ ተቀብሎ በማስተናገድ፣ ጭቆናና በደልን፣ ግፍና ብዝበዛን በመቃወም አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ አድርጋለች። አለመግባባትና ግጭቶች ሲከሰቱም በማብረድ ረገድ ተሳትፎዋ ቀላል አልነበረም።

ይህ ብቻ አይደለም። በአህጉሪቱ የሚፈጠር አለመረጋጋትን በመረጋጋት በመተካት፣ የተጎዱትን በማቋቋምና የተቸገሩትን በመርዳት የማይናወጥ አቋሟን ስታንጸባርቅ ኖራለች። ኢትዮጵያ አህጉሪቱን ከቅኝ አገዛዝ ሙሉ በሙሉ በማውጣትና አፍሪካውያን ነጻነታቸውንና ክብራቸውን ለመመለስ እንዲሁም አፍሪካን ወደ ኢኮኖሚ ዕድገት ለመምራት በተደረገው ትግል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስታደርግም መቀየቷ አይዘነጋም።

ሀገራችን በኢኮኖሚው መስክ ያላት አህጉራዊ ትብብር ኮሜሳ በሚሰኘው በምሥራቅና ማዕከላዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ የተጠናከረ ውህደት ለመፍጠር ያላት ሚናም ከፍተኛ እንደነበር ይታወቃል። በመሠረተ ልማት ግንባታ መስክ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለመሳብም ጥረት ታደርጋለች። የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግም በመሥራት ላይ ነች። በአፍሪካዊያን የርስ በርስ መገማገሚያ መድረክ “ኔፓድ” አገራችን ሃሳቡን ከማመንጨት ባሻገር ንቁ ተሳታፊም ናት።

በዓለም አቀፍ ደረጃም ተሰሚነታችን እየጨመረ ነው። ኢትዮጵያ ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ ለአፍሪካም ይሁን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የበኩሏን ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። በተለይም በሩን ለዓለም አቀፉ የሰላም ማስከበር ተግባራት ጥርቅም አድርጎ ዘግቶ የነበረው አምባገነኑ የደርግ ስርዓት ግብዓተ-መሬት ወዲህ በህዝቦች ትግል እውን የሆነው የኢፌዴሪ መንግስት ለከባቢውም ይሁን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሰላም ማስከበር ተግባሮች ዙሪያ በርካታ ተግባራትን ፈፅሟል። በዚህም ዓለም በኢትዮጵያና በሰራዊቷ ላይ እምነትን አሳድሯል።

ዛሬ ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ናት። አፍሪካን በመወከል በሚካሄዱ የበለፀጉ ሀገራት ስብሰባዎች፣ የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረምና የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤዎች ቀዳሚ ተጋባዥ ናት። በእነዚህ ታላላቅ ጉባኤዎች ላይ የራሷን ልምድና የአፍሪካን ጥቅሞች በማስጠበቅ እየተንቀሳቀሰች ነው። እነዚህ ሁኑ ድምር ውጤቶች ኢትዮጵያ ከቀጠናው እስከ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድረስ ያላትን ተሰሚነት የሚያሳዩ እውነታዎች ናቸው።

 

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy