Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የት ነበርን፤ የት ደረስን

0 300

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የት ነበርን፤ የት ደረስን

ኢብሳ ነመራ

ብሄራዊ ማንነት በቋንቋ፣ ባህልና ወግ፣ ታሪክ . . . ይገለጻል። እነዚህ የብሄራዊ ማንነት መገለጫዎች ግንጥል ጌጥ አይደሉም። ከሰዎች ኑሮ ጋር ጥብቅ ትስስር አላቸው። ቋንቋ የማሰቢያ መሳሪያ ነው። ሰዎች የሚያስቡት በቋንቋ ነው። መረጃ የሚቀበሉትና የሚሰጡት በቋንቋ ነው። ቋንቋ ውስብስብ ግንዛቤ የሚፈጠርበትና የሚያዝበት መሳሪያ ነው። ቋንቋ ማምረቻ መሳሪያ ነው። ባህል ሰዎች ተፈጥሯዊና ማህበራዊ አካባቢያቸው ላይ ያፈሩትን የዘመናት ግንዛቤን መሰረት አድርጎ የሚፈጠር በአንድ ወቅት ያለ የቁሳዊና መንፈሳዊ የኑሮ ዘይቤ ነው። ይህ የኑሮ ዘይቤ የማህበረሰቡ ማንነት መገለጫ ነው። ታሪክ አንድ  ማህበረሰብ ያለፈበትን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እውነታዎች የሚያሳይ መረጃ ነው። የማህበረሰብን ማንነትም ይገልጻል።

ለብሄራዊ ማንነት እውቅና መንፈግ – ሰዎች በቋንቋቸው እንዳይሰሩ፣ በቋንቋቸው እንዳይማሩ፣ በቋንቋቸው ሃሳባቸውን እንይገልጹና የሌሎችን ሃሳብና መረጃ እንዳይቀበሉ መከልከል፤ እውነተኛ ታሪካቸውን እንዳያውቁና እንዳይከባከቡ፣ በባህላቸው መሰረት እንዳይኖሩና ባህላቸውን እንዳያሳድጉ ማቀብ መኖር በሚገባቸው ልክ እንዳይኖሩ መከልከል ነው። በመሆኑም ለብሄራዊ ማንነት እውቅና መንፈግ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው። ሰዎች በብሄራዊ ማንነታቸው መሰረት የመኖር የማይገሰስ መብትና ነጻነት አላቸው።

ኢትዮጵያ ይህ መሰረታዊ ሰብአዊ መብት በህግ ተጥሶ ከነበረባቸው ሃገራት መሃከል አንዷ ናት። ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ በኋላ ወደደቡብ፣ ምስራቅና ምእራብ ወሰናቸውን በማስፋት የአሁኗን ኢትዮጵያ የፈጠሩት ነገስታት በግዛታቸው ስር ለቀላቀሏቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በህግ እውቅና ነፍገዋል። በዚህ ሁኔታ በሃይልና በዲፕሎማሲ ስልት ከፍቃዳቸው ውጭ በነገስታቱ ዘውዳዊ ስርአት አገዛዝ ስር የወደቁት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በቋንቋቸው የመንግስት አገልግሎት ማግኘት እንዳይችሉ ተደርገዋል። በብቸኝነት በሚጋቡበት የራሳቸው ቋንቋ ለፖሊስ ጣቢያ አቤቱታ ማቅረብ አይችሉም፣ ፍርድ ቤት ቀርበው በቋንቃቸው መሟገት አይችሉም ወዘተ።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በቋንቋቸው መረጃ የማግኘት መብት ተነፍገው ነበር። ልጆች በቋንቋቸው መማር አይችሉም። ቋንቋቸው በመሰረተ ትምህርትም ይሁን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የማስተማሪያ ቋንቋ መሆን አይችልም ነበር። የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ቋንቋዎች የጥናትና ምርምር፣ የፍልስፍናና ስነጽሁፍ ቋንቋ በሚሆኑበት ደረጃ እንዳያድጉ የሚያግዝ  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥናት እድል ተነፍገው  ነበር። በስነጽሁፍና በሚዲያ ቋንቋነት ማገልገል እንዳይችሉም ተደርጓል።

እነዚህ ሁኔታዎች ህዝቡ ግብር በሚከፍለበት ሃገር አገልግሎት ፍለጋ ወደመንግስት ተቋማት መሄድ እንዳይችል በማደረግ ተጠቃሚነቱ ላይ ገደብ ጥልዋል። ልጆች አካባቢያቸውን ስርአት ባለው እውቀት እንዲገነዘቡ ማድረግ በሚያስፈልግበት ወሳኝ እድሜያቸው ላይ በማያውቁት ቋንቋ የሚሰጣቸው ትምህርት ለግንዛቤ ክፈተት እንዲጋለጡ አድርጓል። ዜጎች በመንግስት የሚተላለፍን መረጃ ማግኘት እንዳይችሉ፣ የራሳቸውንም ሃሳብ እንዳይገልጹ ገድቧል። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋዎች ከገበያና ከመንደር ወሬ ያለፈ ሰፊና ጥልቅ ሃሳብ መግለጽ በማይችሉበት ሁኔታ እንዲቀነጭሩ ተደርጓል። ይህ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው። ህግን መሰረት በማድረግ የተፈጸመ የሰብአዊ መብት ጥሰት።

ብሄሮችና ብሄረሰቦች ባህላቸውንና ወጋቸውን እንደኋላ ቀርነት እንዲወስዱት በተለያየ ስልት  ጫና ይደረግ ነበር። ስርአቱ ብሄር ብሄረሰቦችን ጨፍልቆ አንድ አሃዳዊ ስርአት ለመመስረት የሚከተለውን ስትራቴጂ ለማስፈጸም በሚያመች አኳኋን የማያውቁት ታሪክ ይጻፍላቸው ነበር። እውነተኛ ታሪካቸው እንደ መናኛ ነገር ይቆጠር ነበር። እነዚህ ሁኔታዎች በማነነታቸው እንዲሸማቀቁ አድርገዋቸዋል። ከነማነነታቸው ምሉዕ የዜግነት ስሜት እንዳያድርባቸው አድርገዋል።

ይህ በብሄራዊ ማነነት ላይ የተጫነ ጭቆና የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ስርአቱን እንዲቃወሙ አድርጓል። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ያደረባቸው ተቃውሞ የሃገሪቱን የፖለቲካ አቅጣጫ የሚወስን መሰረታዊ ቅራኔ ለመሆን በቅቷል።

የብሄራዊ ጭቆና ምንጭ የሆነው ዘውዳዊ ስርአት፣ በሃገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ላይ ከፊውዳላዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ባህሪው የመነጨ የመደብ ጭቆናም አስከትሏል። ዘወዳዊው ስርአት በወሰን ማስፋት እርምጃው የተቆጣጠራቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይዞታ ስር የነበረን መሬት ነጥቆ በንጉሰ ነገስቱና በመሳፍነቱ ትእዛዝ ስር እንዲተዳደር አድርጓል። ንጉሱና መሳፍነቱ የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች የታሪካቸውን ያህል ዘመናት የኖሩበትን መሬት የስርአቱ ጠባቂ ለሆኑ ታጣቂዎች (ነፍጠኞች)፣ ለመኳንነቱና ሌሎች ተሿሚዎች፣ እንዲሁም ለስርአቱ ባለሟሎችና ለመሳፍንቱ ወዳጆች በላዩ ላይ ከሚኖሩት አርሶ አደሮች ጋር በርስትነትና ጉልት ያከፋፍሉ ነበር። በመሬቱ ላይ ይኖሩ የነበሩት አርሶ አደሮች ለባለርስቶችና ባለጉልቶች ገባር ሆኑ። የራሳቸውን መሬት አርሰው የሚያገኙትን መርት፣ ከብቶቻቸውን፣ ጉልበታቸውን ጭምር የሚገብሩ በራሳቸው ላይ የማዘዝ ስልጣን የሌላቸው ገባር ጭሰኞች ሆኑ። በዚህም ለአስከፊ የኢኮኖሚ ጭቆና ተዳረጉ። ይህ የፊውዳሊዝም ፖለቲካል ኢኮኖሚ በሰፊው ገባር አርሶ አደርና በጥቂት ባለርስች መሃከል የከረረ የመደብ ቅራኔ ፈጠረ። ይህ የስርአቱ ሌላኛ መገለጫ የሆነውን የመደብ ቅራኔ አስከትሏል።

እነዚህ ሁለት መሰረታዊ ቅራኔዎች – የብሄርና የመደብ ቅራኔዎች እንዲፈቱ ስርአቱ መወገድ ነበረበት። ቅራኔዎቹ ዘውዳዊው ፊውዳላዊ ስረአት እንዲወገድ ያስገደደ ታሪካዊ ሁኔታን (historical necessity) ፈጥሯል። ስርአቱን ለማስወገድ የተቀጣጠለው ትግል መነሻ ይህ ታሪካዊ ሁኔታ ነው። በመጨረሻም ከ43 ዓመታት በፊት ስርአቱ የተወገደው በዚህ ከስርአቱ ባህሪ በመነጨ ታሪካዊ አስገዳጅ ሁኔታ በተቀጣጠለ ትግል ነበር።

ዘውዳዊውን ስርአት ያስወገደው ትግል ያልተደራጀ መሆኑ በፈጠረው ክፍተት ወደስልጣን የመጣው ወታደራዊ መንግስት በመሬት ለአራሹ አዋጅ በተወነ ደረጃ የመደብ ቅራኔውን የፈታ ቢመስልም፣ የአርሶ አደሩን የምርት ባለቤትነት መብት ስላላረጋገጠ ጭቆናው በሌላ መልክ ቀጥሎ ነበር። አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት በአይነትና በመጠን ኮታ ተቆርጦ እጅግ በአነስተኛ ዋጋ የእርሻ ሰብል ገበያ ድርጅት በተባለ መንግስታዊ ተቋም አማካኝነት ለከተሜ ሸማች እንዲያቀርብ ግዳጅ ተጥሎበት ነበር። ይህ አርሶ አደር የመንግስት ጭሰኛ እንዲሆን አድርጎታል። ወታደራዊው ደርግ የብሄር ጭቆናው ግን በነበረበት እንዲቀጥል ተደረገ። የብሄር ቅራኔው የሃገሪቱን የፖለቲካ አቅጣጫ የሚወስን መሆኑም ቀጠለ።

በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የስርአቱ መገለጫ የሆነውን የብሄር ቅራኔ በመፍታት ብሄራዊ ጨቆና የሌለበትን ስርአት ለመመስረት የተደራጀ የትጥቅ ትግል ማካሄድ ጀመሩ። የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች በየአቅጣጫው የከፈቱት የትጥቅ ትግል በ1983 ዓ/ም ወታደራዊውን ስርአት አስወገደ። ከዚህ በኋላ መሰረታዊውን የብሄር ቅራኔ የፈታና  ጭቆናውን ያቃለለ ፌደራላዊ ስርአት ተመሰረተ።

የወታደራዊውን ደርግ መወገድ ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሚኖሩበት መልከዓምድራዊ ወሰን ውስጥ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ፣ በፍቃዳቸው ከሌሎች ጋር በእኩልነትና በመከባበር ላይ በተመሰረተ አንድነት በአንድ ሃገር ስር ለመኖር ተስማሙ። ይህን ስምምነታቸውን የቃል ኪዳን ሰነዳቸው በሆነው የኢፌዴሪ ህገመንግስት አሰሩ። አሁን ያለው ፌደራላዊ ስርአት የተመሰረተው በዚህ ህገመንግስት መሰረት ነው።

ይህ ፌደራላዊ ስረአት ቀደም ሲል የነበረውን ብሄራዊ ቅራኔ ሙሉ በሙሉ ፈትቷል። አሁን የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች በሚኖሩበት አካባቢ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ራሳቸውን የሚያስተዳደሩበት የመንግስት መዋቅር ዘርግተዋል። በዚህ የመንግስት መዋቅር ውስጥ በቋንቋቸው የመንግስት አገልግሎት ያገኛሉ። አሁን የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ፍርድ ቤት ቆመው በማያውቁት ቋንቋ ለመሟገት የሚገደዱበት ሁኔታ የለም። የመንግስተ አገልግሎት ለማግኘት አስተርጓሚ አስከትለው ለመሄድ አይገደዱም።

የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እያስተማሩ ነው። ቋንቋቸው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደ አንድ የትምህርት አይነት ይሰጣል። በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንደ አንድ የእውቀት ዘርፍ ለመጠናት የበቁ ቋንቋዎችም አሉ። ለምሳሌ ኦሮሚኛ፣ ትግርኛ፣ ሲዳምኛ፣ ሶማሊኛ በዩኒቨርሲቲዎች ከሚጠኑ ቋንቋዎች መሃከል ተጠቃሾች ናቸው። የተወሰኑት እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ የሚጠኑ ናቸው። የብሄሮችና ህዝቦች ቋንቋዎች የሚዲያ ቋንቋ ለመሆን በቅተዋል። በርካታ ቋንቋዎች የብሮድካስት ሚዲያ ኮሚኒቲ ሬድዮን ጨምሮ ማሰራጫ ቋንቋ ለመሆን በቅተዋል። የህትመት ሚዲያ ቋንቋ የሆኑም በርካቶች ናቸው። አነዚህ ሁኔታዎች ቋንቋዎቹ  የስነጽሁፍ፣ የሳይንስና የፍልስፍና ቋንቋ መሆን በሚችሉበት ደረጃ እንዲጎለብቱ አድርገዋል።

በፌደራላዊ ስርአቱ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸው የተረጋገጠላቸው የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ባህላቸውን እያሳደጉ ነው። ሆን ተብሎ ተደብቀው የነበሩ ባህሎች ይፋ ወጥተው አጠቃላይ ሃገራዊ እሴት ለመሆን በቅተዋል። ከሃገራዊ እሴትነት አልፈው በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለመመዝገብ የበቁም አሉ። የሲዳማን ፊቼ ጫንባላላ፣ የኦሮሞን የጋዳ ስርአት ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል። የተለያዩ ብሄሮች ዜማዎች፣ የሙዚቃ መሳሪያዎችና ዳንሶች አደባባይ ወጥተው የሃገሪቱን ሙዚቃ የማሳደግ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አሁን እውነተኛ ታሪካቸውን እያጠኑ፣ እየመዘገቡና እየተንከባከቡ ይገኛሉ።  አሁን ያለችው ፌደራላዊት ኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በማንነታቸው የሚሸማቀቁበት ሳይሆን ራሳቸውን ለዓለም ለማስተዋወቅ የሚሰሩበት ነው።

በአጠቃላይ ፌደራላዊ ስርአቱ የሃገሪቱ መሰረታዊ የፖለቲካ ቅራኔ የነበረውን የብሄር ጥቆና በመፍታት ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩ ማድረግ ያስቻለ ሁኔታን ፈጥሯል። በዚህም ብሄራዊ ጭቆናው ተሽሮ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል።

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy