Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኃይማኖቶች መቻቻል ለአሸባሪዎች መቅሰፍት

0 644

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኃይማኖቶች መቻቻል ለአሸባሪዎች መቅሰፍት

                                                           

                                                               ይልቃል ፍርዱ

የዓለም የሐይማኖታዊ ሕብረት ተጠሪዎችና ተወካዮች በሀገራችን ተገኝተው ውይይት አድርገዋል፡፡ ዛሬ አለማችን በተለይም ከሀይማኖት ጋር በተያያዘ የከፋ ችግር ውስጥ ትገኛለች፡፡ አለም የሐይማኖት እኩልነትን በማክበር ተቻችላና ተከባብራ መቀጠል  እስካልቻለች አደጋው ድረስ ለአለም ሰላም የከፋ ነው ሚሆነው፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሚቻለው በኃይማኖቶች መካከል ከመቸውም ግዜ በላይ መቻቻል፣ መከባበርና መደማመጥን ማስፈን ሲቻል ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የበርካታ ኃይማኖቶች፣ ባሕሎች፣ ቋንቋዎችና እምነቶች ሀገር ናት፡፡ ለዘመናት በዘለቀው በዚህ አብሮነት ውስጥ ጠንክሮና ጎልቶ የወጣ ሰፊ መቻቻል ያለባት፣ ሕዝቡ እንደ የእምነቱ ተከባብሮና ተቻችሎ፤ የአንዱን ባሕልና እምነት ሌላው አክብሮ፤ በክፉውም በደጉም ሳይለያይ የኖረባትና ዛሬም ከመቸውም ጊዜ በላይ የበለጠ ተከባብሮ የሚኖሩባት ሀገር ነች፡፡

በአንድ ሀገር ውጥ ያሉና የሚኖሩ የተለያዩ ኃይማኖቶች በመከባበር ተቻችለው ሲኖሩ ለሀገራቸው ሰላምና ደሕንነት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ የጎላ ነው፡፡ ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተካሄደውና በኃይማኖት ጉዳይ ላይ በመከረው ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ በመቻቻል ተምሳሌትነት ተወስታለች። በሀይማኖቶች መካከል ያለ የመከባበር ሳምንትን ምክንያት በማድረግ ከመላው አለም ለተገኙ የተለያዩ ኃይማኖት መሪዎች በመክፈቻ ስነስርአቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የኃይማኖት መቻቻል የሰፈነባት ምድር መሆኗን፤  የኃይማኖት መሪዎች በኃይማኖቶች መካከል ውይይቶችና ንግግሮችን በማድረግ ሰላምና መቻቻል እንዲጎለብት መስራት እንዳለባቸው ፕሬዚደንት ሙላቱ ተሾመ በጉባኤው መክፈቻ ንግግራቸው የገለጹ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊ ሀገር እንደመሆንዋ መጠን ለረዥም ዘመናት የምትታወቀው በተለያዩ ኃይማኖቶች መካከል ሰፍኖ በኖረው መቻቻልና ሰላም መሆኑን፤  በሰላምና በመቻቻል ሁሉም በጋራ ተባብረውና ተፈቃቅደው የሚኖሩባት ምድር መሆንዋን አስረድተዋል፡፡

ይህ ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ማነንት ዛሬም ይበልጥ ተጠናክሮና ዳብሮ ቀጥሎአል፡፡ ፕሬዚደንት ሙላቱ ተሾመ ከመላው አለም ስብሰባውን ለመሳተፍ ለተገኙት የሀይማኖት መሪዎች ያስተላለፉት መልእክት ሀይማኖታዊ አክራሪነት፣ ጽንፈኛነት፣ አሸባሪነት . . .  በሰፈነበት በዚህ ዘመን ሁሉም የሀይማት መሪዎች ሊወጡት የሚገባውን የጋራ ግዴታ ያመላካተ ነው፡፡ የሀይማኖት መሪዎቹ በበኩላቸው የሀይማኖት ተቋማትና መሪዎቹ  በየራሳቸው ሕብረተሰብና በሀገራቸው ውስጥ ሰላምን ለማስፈን የመጨረሻውን ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡ በሁሉም የሐይማኖት ሕጎች ውስጥ ተጽፎ የሚገኘው ወርቃማ ሕግ  የሰውን ልጅ ማክበር የተገባ መሆኑ የተገለጸበት ነው፡፡

ይህንን አክብሮና ጠብቆ መስራት የኃይማኖት አባቶች ሁሉ ግዴታና ቀዳሚ ስራ መሆን ይገባዋል፡፡ በሀይማኖቶች መካከል መቻቻልና መደማመጥ እንዲሰፍን መስራት ለሕብረተሰቡ ሰላምና ደሕንንት ወሳኝ ነው፡፡ በአክራሪና አሸባሪዎች የሚደርሱትን የከፉ አደጋዎች ለመቀነስ በሂደትም ለመግታት ያስችላል፡፡

በአለማችን ገኖ የሚገኘው ሀይማኖታዊ አክራሪነት፣ ጽንፈኝነትና አሸባሪነት ሀገራትን ለከፋ ዘግናኝ እልቂትና አደጋ እየዳረጋቸው ይገኛል፡፡ በጎረቤታችን ሶማሊያ እለት በእለት የሚታየው የአልቃይዳ እስላማዊ አክራሪና አሸባሪ ድርጊት በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ግድያ መነሻው ሀይማኖታዊ አክራሪነት ሲሆን ሌሎች የሌሎች ሰዎችን ሀይማኖታዊ መብትና የእምነት ነጻነት ካለመቀበል፤ ካለማክበራቸውም የሚመነጭ ነው፡፡

አክራሪነትና አሸባሪነት ጸረ ስልጣኔ፣ ጸረ ሰብአዊ መብትና ጸረ ዲሞክራሲም ተገባረ ነው፡፡ እኔ ከሚለው በግለኝነትት ከታጠረው ሀይማኖታዊ አስተሳሰቡ ውጪ የሌሎችን የእምነትና የአስተሳሰብ ነጻነት የማይቀበል፤ መኖራቸውንም የማይፈቅድ፤ ጭርሱንም በጠመንጃና በኃይል መጥፋት አለባቸው ብሎ የሚያምን አስተሳሰብና ድርጊት ነው፡፡

አክራሪ ጀሀዲስቶች በመላው አለም ያደረሱትና እያደረሱት ያለው ከባድ ፈተና፣ መከራና እልቂትም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አልቃይዳ፣ አይሲስ፣ አልሻባብ እና ሌሎችም ስመ ብዙ አክራሪና አሸባሪ ድርጅቶች የሰው ልጅ የመሰለውን፤ የፈቀደውን ኃይማኖታዊ እምነት መከተል መብቱ መሆኑን አጥብቀው የሚጻረሩ ናቸው፡፡ እኛን ያልተከተለ፤ ከእኛ ውጭ የሆነ መናፍቅ  ነው፤ መጥፋት አለበት በማለት ሰውን ያህል ፍጡር የሚገድሉ፤ የሚያሰቃዩ ናቸው፡፡

አክራሪና አሸባሪ የሀይማኖት መሪዎችና ተከታዮቻቸው የእነሱ ተከታይ ያልሆነውን ሰው ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ኢሰብአዊ ድርጊት ይፈጽሙበታል፤ ይገርፋሉ፤ ይደበድባሉ፤ በባርነት አግዘው ይሸጣሉ፤ ሴቶቹንም የወሲብ መጠቀሚያ ያደርጋሉ፡፡ በናጀሪያ ቦኮሀራም የሚፈጽመውም ይሄንኑ ነው፡፡ አለምን እየናጣት አውሮፓንም እያስጨነቃት የሚገኘው ኃይማኖታዊ አክራሪነት መነሻ ምንጩ የሌሎችን ኃይማኖታዊ መብትና እምነት አለማክበርና አለመቀበል ነው፡፡

ጭርሱንም የእኛን እምነት ያልተከተለ ከእኛ ያልሆነ ሁሉ መጥፋት አለበት የሚል እምነት ይዘው ነው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት፡፡ የተቃወሙዋቸውን ሁሉ ከማጥፋት ወደኃላ አይሉም፡፡ በአለማችን በተጨባጭ ያየነውና የእለት ተእለት እውነት የሚመሰክረው ይህንኑ ነው፡፡ ለዚህ ነው በመላው አለም ሰፊና የተለያዩ ኃይማኖቶች የመኖራቸውን ያህል የእያንዳንዱ ኃይማኖት መሪና ኃላፊ በያለበት ሕብረተሰብ ውስጥ ሰፊ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት የተቻለውን ሁሉ ጥረት ማድረግ ያለበት፡፡

የኃይማኖቶች እኩልነት፣ መቻቻል፣ ተከባብሮ መኖር ብቻ ነው በአለም ላይ ሰላምን ሊያሰፍን የሚችለው፡፡ የእምነት ነጻነት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ድንጋጌ ቻርተር ላይ የተቀመጠ እንደመሆኑ መጠን ሀገራት ይህንኑ መሰረታዊ ሰብአዊ መብት የማስከበርና የማረጋጋጥ የተናጠልና የወል ኃላፊነትና ግዴታም አለባቸው፡፡ ሰዎች በሚከተሉት ኃይማኖታዊ እምነት የተነሳ የጥቃት ሰለባ መሆን የለባቸውም፡፡ በነጻነት እምነታቸውንና ኃይማኖታቸውን የመከተልና የማራመድ መብታቸው በሕግ የተረጋገጠ ነው፡፡

አክራሪና አሸባሪ ኃይማኖተኞች ይህንን እውነት አይቀበሉም፡፡ እነሱ የሚያምኑት በመሳሪያ አፈሙዝ አስገድዶ በማሳመን ወይንም በመግደል ነው፡፡ ዛሬ በተለይ ክስተቱ በየእለቱ  የሚታይ ነው፡፡ አፍሪካ የዚህ ግዙፍ ችግር ሰለባ ሆናለች፡፡ ያለው ብቸኛ መፍትሄ ኃይማኖታዊ መቻቻልና መከባባር እንዲሰፍን ያለማቋረጥ መስራት፤ አክራሪና ጽንፈኛ አመለካከቶችን መዋጋት፤ ሕብረተሰቡ የመቻቻል ባሕልን እንዲያሳድግ ያለማቋረት ማስተማር ብቻ ነው፡፡ ለዚህም በየደረጃው ያሉ መሪዎች፤ የስራ ኃላፊዎች፤ ምሁራን፤ ተደማጭ ሰዎች፤ በኪነጥበቡ ዘርፍ የተሰማሩ፤ ጋዜጠኞች፣ የኃይማኖት መሪዎች ሁሉም በየመስኩ ሰፊ ትግልና ርብርብ በማድረግ ጽንፈኝነትንና አሸባሪነትን ማጋለጥና ኃይማኖታዊ እኩልነት እንዲሰፍን መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በርግጥ ይህ ግዴታና ኃላፊነት ለሀይማኖት መሪዎች ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ በአክራሪነትና አሸባሪነት ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምር ያደረጉ የዘርፉ ምሁራን ችግሩን መንቀል የሚቻለው በጠመንጃ ትግል ሳይሆን ሰፊ የሆነ የስነልቦና ስራ በሕብረተሰቡ ውስጥ በመስራትና በማስተማር ነው ውጤት ማስመዝብ የሚቻለው ብለው ያምናሉ፡፡ አክራሪነትና አሸባሪነት በመጀመሪያ ተንሰራፍቶና ተደላድሎ የሚኖረው ለዚህ ሲሉ በስፋት በሕብረተሰቡ ውስጥ በሚሰሩት የፕሮፓጋንዳና የቅስቀሳ ስራ በሰዎች ሕሊና ውስጥ በሚፈጥሩት ስእል ነው፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ ያን አስፈሪ ስእል በሰዎች ሕሊና ውስጥ በማሕበራዊ ድረገጾች (በፌስቡክና በመሳሰሉት) በብዛት እንዲሰራጭ በማድረግ በሰዎች አእምሮ ላይ ሰፊ ወረራ ያካሂዳሉ፡፡ በመገናኛ ብዙሀን፣ በመፃህፍት እና በሌሎችም የቅስቀሳና የፕሮፓጋንዳ ዘዴዎች በመጠቀም በብዛት እንዲሰራጭ ካደረጉ በኋላ ከፍተኛ ኃይል ያላቸው መሆኑን አምኖ በህሊናው የሚንበረከክ ሰው ይፈጥራሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ከፍተኛው የስነልቦና ጦርነት መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሊሸነፍና ከነአካቴውም ሊወገድ የሚችለው በህዝቦችና የተለያዩ ሀይማኖት አባላት መካከል ሰፊ ኃይማኖታዊ መቻቻል ሲፈጠር ብቻ ነውና ለዚህ ቅዱስ ተግባር ሁላችንም ልንረባረብ ይገባል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy