Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የእነርሱ ሰላም የእኛም…

0 632

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የእነርሱ ሰላም የእኛም…

                                                       ቶሎሳ ኡርጌሳ

ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላም ፋና ወጊ ሀገር ናት። የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች ሰሞኑን የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ውስጥ እያደረጉትን ያለውን ገንቢ ውይይት የዚህ አባባሌ አስረጅ ይመስለኛል። ይህ ውይይት እውን እንዲሆን ሀገራችን ለማንም በማይወግነው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ እየተመራች በመጫወት ላይ ያለችው ገንቢ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። ይህ የኢትዮጵያ አቋም ወንድም የሆነው የደቡብ ሱዳን ህዝብ እንደተቀረው የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች ከጦርነት ተላቆ ወደ ሰላም በመግባት በሀገራችን በሚመራው ቀጣናዊ ትስሰር ተጠቃሚ እንዲሆን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊትን እስከ መላክ ድረስ የደረሰ ሚናን ጭምር ያካተተ ነው።

እንደሚታወቀው በደቡብ ሱዳን መንግስትና በተቀናቃኙ ሪክ ማቻር መካከል በመዲናችን እየተካሄደ ያለው ድርድር ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መሰረት ያደረገ ነው። አንደኛው በተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ መግባባት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሥልጣን ክፍፍል ማድረግ ነው። በውይይቱ ላይ በሀገሪቱ ያለውን ግጭት ለማስቆምና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የሀገሪቱ መንግስት ለመላው ተቃዋሚ የፖለቲካ አባላት የስልጣን ክፍፍል ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ተገልጿል።

በደቡብ ሱዳን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ ለመስማማት በአደራዳሪው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) አማካኝነትም ችግሩን ለመፍታት የስልጣን ክፍፍል እንዲኖር ሃሳብ ቀርቧል። የሀገሪቱ መንግስትም ይህን ለማድረግ ዝግጁ ነው። ርገጥ ሁለት የተለያዩ ወታደራዊ ኃይል ያለው ሀገር በዓለማችን ላይ ያለ አይመስለኝም። እናም ከሁሉም ወታደራዊ ቡድኖች የተውጣጣ አንድ ብሔራዊ ወታደራዊ ኃይል ለማቋቋም መግባባቱ ወሳኝ መሆኑ አያጠያይቅም።

እንደ እውነቱ ከሆነ ወንድሞቻችን ደቡብ ሱዳናዊያን ዴሞክራሲን ተርበዋል፤ መሪያቸውንም ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መምረጥ ይፈልጋሉ። እናም በይህን ለማድረግ መጀመሪያ በሀገሪቷ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን በዘላቂነት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ መግባባት ተገቢ ነው። በዚያች አዲስ ሀገር ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ነፃ ምርጫ ለማካሄድ መጀመሪያ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ይህ ሃሳብ በኢትዮጵያ ሊቀመንበርነት በሚመራው ኢጋድና በሌሎች ገለልተኛ ወገኖች የቀረበ ነው።

ርግጥ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚዋ አገር እንደመሆኗ መጠን፤ በደቡብ ሱዳን ሙሉ በሙሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ የህዝብ ቆጠራ ከተካሄደ በኋላ ላልተወሰነ ጊዜ በሀገሪቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውሳኔ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ሃሳብ አቅርባለች። ይህም ሀገራችን ለድርድሩ መሳካት እንደ ኢጋድ አባልነትና እንደ ጎረቤት  ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተች መሆኗን የሚያስረዳ ይመስለኛል።

ሀገራችን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብና በአፍሪካ ህብረት ጥያቄ ለድርድሩ መደላድል የሚፈጥር የሰላም ማስከበር ተግባርን በደቡብ ሱዳን በመወጣት ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ በጎረቤት ሀገራት ሰላም ማስከበር በመሰማራት ያስገኘችው ውጤት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ያደረገ መሆኑ ይታወቃል። ርግጥ በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ረጅም ዓመታት ያስቆጠረችው ኢትዮጵያ፤ በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በላይቤሪያ፣ በብሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ በሱዳን-አብዬ ግዛትና በዳርፉር እንዲሁም በሶማሊያ አንፃራዊ ሰላም እንዲሰፍን ሰፊ ስራን ያከናወነች ሀገር ናት።

በአሁኑ ወቅትም በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና በአፍሪካ ህብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በሰሜንና ደቡብ ሱዳን እንዲሁም በሶማሊያ ከ13 ሺህ የሚበልጡ የሰላም አስከባሪ ሰራዊቷን አሰማርታ አህጉራዊ ሃላፊነቷን በብቃት በመወጣት ላይ ትገኛለች። ሰላም አስከባሪ ሃይሉ ያሳየው ህዝባዊነትና ተልዕኮውን የመፈፀም አቅሙ አሁንም ድረስ በተለያዩ ሀገራት ተመሳሳይ ጥያቄዎች እንዲቀርቡለት ምክንያት እየሆነ ነው።

በአሁኑ ወቅትም ፖለቲካዊ መፍትሄ ያላገኘው የደቡብ ሱዳን ግጭት ከዚህ የባሰ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳያስከትል የኢፌዴሪ ሰላም አስከባሪ ሃይል በጁባ ተሰማርቶ ግዳጁን በህዝባዊ መንገድ እየተወጣ ነው። ሀገራችን የደቡብ ሱዳንን ሰላም እጦት ለመፍታት በኢጋድ በኩል ከምታደርገው ጥረት ባሻገር፤ ሰራዊቱ ከሌሎች ሀገራት ወታደሮች ጋር በመሆን በሀገሪቱ ሰላም የማስከበር ሃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል።

ይህ ህዝባዊ፣ ልምድና ብቃት ያለው እንዲሁም በዲሲፕሊን የታነፀ ሰራዊት የዚያችን ሀገር ሰላም በአንፃራዊነት እውን ሊያደርግ እንደሚችል በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ምክንያቱም ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በሚወዛገቡበት የአብዬ ግዛት ተሰማርቶም ሁለቱንም ተቀናቃኝ ወገኖች በሚያረካ መልኩ ተግባሩን በመወጣት ላይ የሚገኝ ህዝባዊ ሰራዊት መሆኑን ሁለቱም ጎረቤቶቻችን የመሰከሩለት ስለሆነ ነው።

ርግጥ ሀገራችን ለጎረቤት ሀገራት ሰላም እንዲህ ያሉ ተግባራትን መከወኗ አብሮ ለመልማት ካላት ፍላጎት አኳያ የሚታይ ነው። ሀገራችን ከቀጣናው ሀገራት ጋር ለምታደርገው ኢኮኖሚያዊና የልማት መስኮች ትስስር በአካባቢው ያለው ቀውስ እልባት ማግኘት ወሳኝነት ሊኖረው ይገባል። ከዚህ እምነቷ በመነሳትም ለየትኛውም ወገን ሳትወግን የሰላም ማስከበር ተግባሮቿን ስትጠየቅ በተገቢው ሁኔታ ታከናውናለች።

እንደ እውነቱ ከሆነ የማንኛውም ጎረቤት ሀገር ሰላም የጋራ ዕድገትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሰረት ይጥላል። ከዚህ አኳያ ደቡብ ሱዳን ከእኛ ጋር በንግድና በኢንቨስትመንት ብሎም በህዝብ ለህዘብ ግንኙነት ልትተሳሰራቸው የሚያስችሉ ሰፊ አማራጮች ያሉ መሆናቸው እውነት ነው። የደቡብ ሱዳን የሰላም እጦት ጠንካራ የሆነ የልማት ትስስር እንዳይፈጠር የሚያሳድረው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚገመት ሊሆን አይችልም። ለአብነት ያህልም ያቺ ሀገር መረጋጋት ባለመቻሏ ምክንያት ዜጎቿ የሆኑት የሙርሌ ጎሳ አባላት የሀገራችንን ድንበር ተሻግረው ህፃናትንና ከብቶችን መውሰዳቸውን መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል። ይህ ሁኔታም በአንድ ጎረቤት ሀገር ውስጥ የሚከሰተው የሰላም እጦት ምን ያህል ሌላኛውን ጎረቤቱን ሊጎዳ እንደሚችል ሁነኛ ማሳያ ነው።

ደቡብ ሱዳን በህዝብ ውሳኔ ራሷን የቻለች ሀገር ለመሆን የበቃችበትን ዕድል እንድታገኝ የአንባሳውን ድርሻ የተጫወተችው ኢትዮጵያ፤ የትኛውንም ወገን ከመደገፍና ከመጥላት ሰላምን ለማረጋገጥ አትሰራም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳንና ለህዝቦቿ መፃዒ ብሩህ ህይወት ብሎም ለጋራ ተጠቃሚነት በማሰብ የምታከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት ከግለሰቦችና ከፓርቲዎች ፍላጎት የነፃ ስለሆነ ነው።

ርግጥ ደቡብ ሱዳን ነፃ ሀገርነቷን ካወጀች ካለፈው በጣት የሚቆጠር ዓመት ወዲህም ቢሆንም በቀጣናው የተጠበቀው ሰላምና መረጋጋት ሊፈጠር አልቻለም። በአዲሲቷ ሀገር ውስጥ አዲስ የጦርነት አደጋ ሊያንዣንብብና የቀጣናው ሰላምም ለዳግመኛ ችግር ሊጋለጥ ችሏል። ይህን ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያ የአደራዳሪነት ሚና ተጫውታለች። በቀድሞው የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ስዩም መስፍን የተመራው አደራዳሪ ቡድንም ለየትኛውም የደቡብ ሱዳን ሃይል ባልወገነ መልኩ በገለልተኝነት የሰላም ስምምነት እንዲፈረም የማድረግ ስራዎችን በብቃት አከናውኗል።

በኢጋድ አማካኝነትም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጁባ ድረስ በመመላለስ ሁለቱ የሀገሪቱ ተቀናቃኝ ወገኖች ችግራቸውን በሰለጠነ መንገድ እንዲፈቱ ጥረት አድርገዋል። ይህ ጥረታቸውም ኋላ ላይ “ኢጋድ ፕላስ” በተሰኘው ቡድን አማካኝነት በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲትና በዶክተር ሪክ ማቻር አማካኝነት የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ምክንያት ሆኗል። ይህም ቀየውን ለቆ ለተሰደደው የደቡብ ሱዳን ህዝብ ታላቅ እፎይታን ያስገኘ፣ ያቺ ሀገር እንደ ሀገር የመቀጠል ህልውናዋ እንዲያንሰራራ የሚያደርግ ነበር። ሆኖም ሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች ከስምምነቱ በኋላ ለተኩስ አቁም ስምምነቱ ተገዥ ባለመሆናቸው ደቡብ ሱዳናዊያን ሰላም እንደ ሰማይ ርቆባቸዋል።

ያም ሆኖ ወንድም የሆነው የደቡብ ሱዳን ህዝብ ከጦርነት እንዲላቀቅና የሰላም አየር እንዲተነፍስ ብሎም በአዲስ ሀገርነት በመንግስታቱ ድርጅት ባህር መዝገብ ላይ ስሟ የሰፈረው ጎረቤታችን ከሰላም የሚገኘውን ማናቸውንም ሀገራዊና ቀጣናዊ ትስስሮችን በሚፈለገው መጠን አሟጣ እንድትጠቀም ኢትዮጵያ ብዙ ደክማለች። ሰሞኑን ሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች በአዲስ አበባ ሲደራደሩ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ “በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሠላም ለማምጣት የሠላም ስምምነቱን መተግበር ብቸኛው አማራጭ ነው። ሁሉም የደቡብ ሱዳን ኃይሎች ቃል ከመግባት በዘለለ ለሰላም ስምምነቱ ትግበራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሊያሳዩ ይገባል” በማለት የተናገሩት። ይህ የሀገራችን አቋም ቀጣናው እንዲረጋጋና ደቡብ ሱዳንም ከምስራቅ አፍሪካ የልማት ትስስር ትሩፋት እንድትጠቀም ያላትን አቋም የሚያሳይ ነው።

 

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy