Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የከፍታው ዘመን ችቦ

0 326

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የከፍታው ዘመን ችቦ
ዳዊት ምትኩ
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ለመጣል ታግለዋል። ከእነዚህ ህዝቦች ውስጥ በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሃት) የሚመራው የትግራይ ዝዝብ ትግል አንዱ ነው። ህወሓት በአስር ሰዎችና በጥቂት መሳሪያ የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም ነው ተመሰረተው።
ይህ የህዝብ ብሶት የወለደው ትግል አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ገርስሶ ለመጣል ቀዳሚው ምዕራፍ ነው። ታዲያ በዚህ ፈታኝና እልህ አስጨራሽ ትግል ከ70 ሺህ በላይ ውድ የህዝብ ልጆች ህይወታቸውን አጥተዋል፣ በርካታዎች አካላቸው ጎዶሎ ሆኗል፤ ንብረታቸውም ወድሟል። ካደጉበት ቀዬም ተፈናቅለዋል።
ይህ ሁሉ መስዋዕትነት ግን በከንቱ አልቀረም። የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም በደደቢት በረሃ ላይ የተለኮሰው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ያነገበ ችቦ የሀገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድ ጥላ ስር በማሰባሰብ የከፍታው ዘመን አብሳሪና መነሻ ሆኗል።
ይህ የከፍታው ዘመን አብሳሪ ችቦ ዛሬ ለምንገኝበት የህዳሴ ጉዞ መሰረት ነው። ችቦውን በቅድሚያ ለለኮሱትና ኋላ ላይም መራርና እልህ አስጨራሽ የሆነውን ትግል በመቀላቀል የህይወትና የአካል መስዋዕትነትን ለከፈሉት ውድ የህዝብ ልጆች ምስጋና ይገባቸዋል። ምክንያቱም ያኔ ትግሉ ባይጀመር ኖሮ፤ ሀገራችን ዛሬ የተለመችውን የህዳሴ ጉዞ ባልተያያዘችው ነበር።
በዚህ ዕለት በተለኮሰው ችቦ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የዛሬ 23 ዓመት ገደማ ሁሉንም ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ያረጋገጠና በተግባር ላይ ውሎ ተጠቃሚ ያደረጋቸውን ህገ-መንግስት እንዲፀድቅ ማድረግ ችሏል። በሌላ በኩል ደግሞ ላለፉት 23 ዓመታት በህገ-መንግስቱ መሰረት ገቢራዊ የሆነው ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንጂ፣ በኃይል ወይም ለይስሙላ ሲባል የተደረገ አንድነት እንዳይኖር ማድረግ የቻለ ነው።
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የተመሰረተው አንድነት ሁሉም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ነፃነታቸውንና እኩልነታቸውን በማወጅ፤ አንዱ የሌላው የበላይ ሳይሆን በጋራ መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ ሁኔታም አንዱ ብሔር የሌላውን ብሔርና ህዝብ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክና ትውፊቶችን የማክበር፣ የመተዋወቅና የልምድ ልውውጥ የማድረግ ተግባሮችን ፈጥሯል። እነዚህ ሁሉ የተገኙት በችቦው አብሳሪነት ነው።
ባለፉት ስርዓቶቹ ተገልለውና ተረስተው የነበሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርም ሆነ ከሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን በብሔራዊ ጉዳዮቻቸው ላይ በእኩልነት የመሳተፍ መብት አልነበራቸውም። ይህ ሁኔታ እንዲከትም የደደቢቱ ችቦ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።
ችቦው ህዝቦች የየራሳቸውን አኩሪ ባህልና ቋንቋ የሚጠቀሙበትና የሚያበለፅጉበት ዕድል ፈጥሮላቸዋል። በእነዚያ ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ስርዓቶች የአብዛኛዎቹ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ቋንቋና ባህል የሀገሪቱ ቋንቋና ባህል ተደርገው ካለመቆጠርም እንዲድኑ ምክንያት ሆኗል።
ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በቋንቋቸው የመዳኘት፣ የመማር…ወዘተ. መብት ስላልነበራቸውም፣ አብዛኛዎቹን ቋንቋዎች እንኳንስ በአደባባይ ለመጠቀምና ስራ ላይ ለማዋል ይቅርና በአንዳንድ አጋጣሚዎች ለመጠቀም እጅግ የሚያሸማቅቅ ሁኔታ እንደነበረም የሚዘነጋ አይመስለኝም። ባህላቸውን የመግለፅ፣ የማዳበርና የማስፋፋት መብታቸው ተነፍገውም ነበር። ይህ ሁኔታ በደደቢቱ ህዳሴ አብሳሪ ችቦ እንዲሻር ተደርጓል።
የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባለፉት ስርዓቶች ሰብዓዊ መብታቸውንም ተገፈፈው ኖረዋል። የአካል ደህንነት፣ በህይወት የመኖር መብት፣ ክብርን ከሚያዋርዱ አያያዞች የመጠበቅ… ወዘተን. ከመሳሰሉ መብቶች ጋር አይተዋወቁም ነበር። ከዚህም አልፎ በህግ ባልተደነገገ ሁኔታ ኢ-ሰብዓዊ ለሆነ እስር የመዳረግ፣ በስውር የመታገት…ወዘተ. ወንጀሎች እየተፈፀመባቸው ለከፋ ስቃይና እንግልት ሲዳረጉ መቆየታቸው የታሪክ ድርሳናቸው ያስረዳል። ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእኩል ዓይን የማይታዩ ነበሩ። ችቦው ይህንን አስተሳሰብ መቀልበስ የቻለ ነው።
የህዳሴው አብሳሪ ችቦ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችም እስከ ታች ድረስ በዘለቀ ህዝባዊ ውይይት ታጅበውና ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ መክረውና ዘክረው የዛሬ 23 ዓመት ገደማ ባፀደቁት ህገ መንግስት አማካኝነት እውን እንዲሆን አድርጓል።
ችቦው የድህነት ተምሳሌት የነበረችውን አገራችንን በሀሉም መስክ አርአያ እንድትሆን አድርጓታል። የህገ መንግሥቱ ድሎችና ውጤቶች ከመቼውም በላይ ተስፋፍተው፤ የዜጎች ማንነትና ባህላዊ እሴቶች ጎልተው ወጥተው፤ መልካም ተሞክሮዎችም ይበልጡን ጎልብተው የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ ሆነው እንዲቀጥሉ ዜጎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ አድርጓል።
በእነዚህ ጊዜያት የክልሎችን እኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል በተለይም በልማትና ዕድገት አፈጻፀም ረገድ በጎ እርምጃዎች ተወስደው መልካም ውጤቶች እንዲታይባቸውም ምክንያት ሆኗል። በህገ መንግሥት በተደነገገው እኩል የመልማት መብት በመጠቀም በሁሉም ክልሎች በተነፃፃሪ ፈጣን የሚባል ልማትና ዕድገት እንዲመዘገብ አድርጓል።
ችቦው በማሟሻነት የወለደው የፌዴራል ሥርዓቱ ያለፉት አፋኝ መንግሥታት የቀበሩትን የማንነትና የምጣኔ ሀብት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄን በአስተማማኝ ደረጃ መልሷል። በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለማስቀጠልና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ቃል ኪዳን ያሰሩበትን አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በህዳሴው እንዲቀላጠፍም አድርጓል።
በችቦው አብሳሪነት የተለኮሰው የለውጥ አብዮት የህዝቦች ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ተሳትፎ በየደረጃው እንዲጎለብት አድርጓል። በዚህም ሳቢያ ዜጎች በአሁኑ ሰዓት አካባቢያቸውን በማልማት ለአገር ብልፅግናና እድገት ከፍተኛ ደርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ።
የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አንፃር ልማታዊው መንግሥት ግልፅ የሆኑ ምጣኔ ሀብታዊ ህጎችን፣ የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ነድፎ በየአካባቢው ተጨባጭ እቅድ እየተመነዘሩ የሚፈፀሙበትን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። በአፈጻፀም ሂደት የተገኙ በጎ ልምዶችም እየተቀመሩ በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎችና ለምልዓተ ሕዝቡ የሚደርስበት ስልቶች ተቀይሰዋል። ከአንዴም ሁለቴ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተነድፏል። ኢትዮጵያም በሁለንተናዊ ለውጥና ግስጋሴ ውስጥ አንድትገባ ምክንያት ሆኗል፤ የደደቢቱ ድል አብሳሪ ችቦ። ምስጋና ለትግሉ ሰማዕታት ይሁን!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy