Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጣት ቅሰራው…

0 453

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጣት ቅሰራው…

አባ መላኩ

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች  የኢትዮጵያ  የፌዴራል ስርዓት አተካከል አገራችንን ለቀውስ እንደዳረጋት ሲናገሩ አደምጫለሁ፤ ጽፈውም አንብባለሁ። በእኔ አረዳድ  ትችቱ  ሚዛናዊነት የጎደለው እንደሆነ ይሰማኛል።  ህጸጽን ብቻ ነቅሶ ለትችት የመቻኮል ሁኔታ ይመስለኛል። ይህን አይነት አካሄድ የችኮላ ጣት ቅሰራ ይመስለሻል። ህመም ሲሰማን የምንወስዳቸው  በፈዋሽነታቸው  የሚታወቁት መድሃኒቶች እንኳን የየራሳቸው የሆነ አሉታዊ ጎን እንዳላቸው፤ እያወቅን ትርፍና ኪሳራችንን አስልተን እንጠቀማቸዋለን።  ይህ የፌዴራል ስርዓታችንም ለአገራችን ስኬት አንድ ሺህ ጥቅሞችን አስገኝቶ አንዲት ጉድፍ ብትታይበት እሷኑ የተለያየ ቀለም ቀባብተናት ልናጎናት መሯሯጡ  ውጤቱ  የከፋ እንዳይሆን ሰጋለሁ።  

የፌዴራል ስርዓታችን  ምንም እንከን የለበትም ባይባልም፣ በአገራችን አሁን ላይ ለተከሰቱ  ችግሮች ግን  ብቸኛ  ምክንያት እንዳልሆነ በዕርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ምክንያቱም አገራችን  ትላንት የነበረችበትን ሁኔታ የሚረሳ አይመስለኝም።  በአሃዳዊው ስርዓት ወቅት  በአገራችን  ምን ይፈጸም እንደነበር ከወጣትነት ዕድሜ  ዘለል ላሉ ዜጎች  ሁሉ መንገር  ለቀባሪው ማርዳት ስለሚሆንብኝ ወደዛ መግባት አልፈልግም። አህዳዊ ስርዓቱን ሞክረነው  አልሳካም ስላለን ይመስለኛል  የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች  መክረውና ዘከረው  ይሆነናል ይበጀናል ብለው የፌዴራል ስርዓትን ለመተግበር የተስማሙት። ደግሞም በአገራችን ተጨባጭ አዎንታዊ ለውጦችን ማስመዝገብ ችሏል።

የፌዴራላዊ ሥርዓት እንደ እኛ ላሉ ብዝሃነት ለሚስተዋልባቸው  አገራት በአግባብ መተግበር ከተቻለ አማራጭ የሌለው ምርጫ  ይመስለኛል።  አንዳንድ  ምሁራኖች  እንደሚመክሩት  የፌዴራል ስርዓት  ጠንካራ የዴሞክራሲ ስርዓትን ይፈልጋል። የአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ደግሞ ገና ለጋና ታዳጊ ነው። ጅምር የዴሞክራሲ ስርዓታችንን ከሚፈታተኑት  በርካታ ጉዳዮች  መካከል በተለይ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ትምክህትና ጥበት  ተግባራትና አስተሳሰቦች ዋንኞቹ ናቸው። ለአገራችን ሚበጃት  እነዚህ እጥረቶቻችንን መቅረፍ እንጂ “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” እንደሚባለው  ችግርና መፍትሄ ፍለጋችን ሳይገናኙ  እንዳይቀሩ እሰጋለሁ።  

እንደእኔ እንደኔ ይህ የፌዴራል ስርዓት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህልውና መሰረት ነው ሲባል የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ነጻነትና እኩልነት የተረጋገጡባት፣ ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት፣ ፈጣን ልማትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የነገሱባት  ማለት ነው። በተጨባጭም  ይህ ስርዓት  ልትፈረስ፣ ልትበተን መስቀልያ መንገድ ላይ የቆማለች የተባለች  አገርን በአጭር ጊዜ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና  ወደ ዕድገት ጎዳና እንድታመራ አደረጋት እንጂ ለግጭትና ሁከት አልዳረጋትም። ኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓትን መከተል የጀመረችው የዛሬ 27 ዓመት እንጂ   በ2008 ወይም 2009 ዓ.ም አይደለም።    

ዛሬ በአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት ይዟል፤ ፈጣን ልማትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በመረጋገጥ ላይ ነው። ይህ ከየትም የመጣ ሳይሆን ይህ የፌዴራል ስርዓት በመተግበሩ  የመጣ ለውጥ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው። በትንሽ በትልቁ እየተነሳን ወደ ፌዴራል ስርዓቱ ጣት መቀሰሩ ቢቆየን መልካም ይመስለኛል፤ ይህ ካልሆነ ግን  አገራችንን የማይገባ መስዋዕትነት ያስከፍላታል ብዬ እሰጋለሁ። ሚዛናዊ ብንሆን ሁሉንም ነገር በልክ በልኩ መስፈር ብንችል ችግሩን እንድንረዳው ከማገዙም በላይ  መፍትሄም ለመፈለግ  ይቀለናል የሚል እምነት አለኝ። ለአገራችን የሚበጃት  በጎደለው ላይ መሙላት እንጂ እያፈረሱ መገንባት አይደለም። ብልህ ከጎረቤት ይማራል እንደሚባለው እስኪ እኛም ከጎረቤታችን ሶማሊያ አለፍ ሲልም  ከሶሪያ፣ ሊቢያና የመን ትምህርት እንቅሰም።  

ይህ ስርዓት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ ሁኔታዎችን  በማመቻቸቱ  በህዝቦች  መካከል መቻቻልን አስፍኗል፣ አንድነትን አጽንቷል፣  ዘላቂ ሰላም በመስፈኑም መንግስትና ህዝብ ትኩረታቸውን ወደ  ልማት ማድረግ በመቻላቸው ዕድገትን  ማፋጠን  ተችሏል። በህዝቦች መካከልም ፍተሃዊ  የኢኮኖሚ  ተጠቃሚነት እንዲሰፍን ለማድረግ መንግስት  ጥረት በማደረግ ላይ ነው። እውነት እውነቱን እንነጋገር ከተባለ  አገራችን በታሪኳ አይታው የማታውቀው በየዘርፉ የተመዘገቡት ስኬቶች  የዚህ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ  ስርዓት ውጤቶች ናቸው።  ለዚህ በርካታ አስረጂዎችን  ማንሳት  ይቻላል።  

ሁሉም የፌዴራል  ስርዓትን የሚተገብሩ  አገሮች የተፃፈ ሕገ መንግስት ያላቸውና በርካታ ልዩነታቸውን ማቻቻል የሚያስችል አደረጃጀትን የሚከተሉ  ሆነው እናገኛቸዋለን።  የእነዚህ አገራት  ህዝቦችም  ለሁለት ህገመንግስት  ተገዥ የመሆ ግዴታ ይኖርባቸዋል። በእኛ አገር  ተጨባጭ ሁኔታ ስንመለከተው  የመጀመሪያው ለክልል ህገመንግስት  ሲሆን ሌላውው ደግሞ  ለጋራ ወይም ለፌዴራሉ ህገመንግስት ነው። በኢትዮጵያ ህገመንግስት መሰረት ከፌዴራሉ ህገንግስት የሚቃረን ማንኛውም ህግ ተፈጻሚነት አይኖረውም። ይህ የሚያመላክተው  የክልሎች ህገመንግስት የፌዴራሉን ህገመንግስት በማይጻረር መልኩ የተቀረጹ መሆናቸውን  ነው። ይሁንና በቅርቡ እንደተመለከትነው በአንዳንድ አካባቢዎች የፌዴራሉ ህገመንግስት  በክልል አመራሩ ጭምር ሲጣስ  ተመልክተናል።  እንዲህ ያሉ  መረን የለቀቁ ኢ-ህገመንግስታዊ  አካሄዶች  ሲፈጸሙ   አገር ወዳድ ዜጋ ሁሉ  መጮህ መቆጣት ነበረብን። ምክንያቱም  ነገ በጋራ  የሚያስተሳስረን  ነገር እንዳይበጠስ ስጋት ሊያድርብን ይገባል።  የጅብን ጥርስ በምን ፈራኸው  ቢሉት በአጥንት እንደሚባለው፤ ዘረኝነት ማቆሚያ የሌለው ሰደድ እሳት ነው።  

አንዳንድ ሰዎች  ህገመንግስትን ማክበርን ብቻ  እንደ ግዴታ አድርገው በመቁጠር ስለሌላው  እንደማያገባቸው አድርገው ይናገራሉ። ይሁንና ህገመንግስትን ማክበር ብቻ ምልዑ አያደርግም። ህገመንግስትን ማክበር አንድ ነገር ቢሆንም  ማስከበርም ሌላው  ትልቅ ጉዳይ ነው። ሕገ-መንግስት ማክበርና ማስከበር  የሁሉም አካላት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ መሆን መቻል አለበት። እንደእኔ እንደኔ ህገመንግስትንና የአገር ህልውና አንድና አንድ በመሆናቸው አገር ወዳድ ዜጋ ሁሉ ህገመንግስት ማክበርና ማስከበር እኩል ሃላፊነት አለበት። በተለይ እንደኢትዮጵያ ባሉ በርካታ ልዩነቶች በሚስትዋሉባት አገር የፌዴራል ስርዓት ፍቱን መድሃኒት መሆኑን በተገባር ታይቷል።  

ፌዴራሊዝም የኢትዮጵያ ህዝቦችን እንዲተማመኑና እንዲቀራረቡ  አደረጋቸው እንጂ አላራራቃቸውም። በህገመንግስቱ  መግቢያው ላይ የህዝቦችን አንድነትና ፍትሃዊ  ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ አንድ ትልቅ አስተሳሰብ ሰፍሯል።  የመጀመሪያው አንድ የፖለቲካ ማሕበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በውስጡ በርካታ የስርዓት ግንባታ አጀንዳዎች የያዘ ቢሆንም ጥቂቶችን ወስደን ስንመለከት ዋንኛው ጉዳይ በሕገ-መንግስትና በሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ግንባታ ላይ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ አገራዊ መግባባት እንዲሁም የጋራ አቋምና ተመሳሳይ አመለካከትን መያዝ ማለት ነው። ሌላው አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ግንባታ ሲባል የጋራ አገራዊ ራዕይ በመላበስና ተመሳሳይ አመለካከት በመያዝ አገራዊ ራዕይን ማሳካት ማለት ነው።

ከዚህም ባሻገር አንድ የፖለቲካ ማሕበረሰብ መገንባት ማለት  በአገራዊ እሴቶች፣ በመሰረታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነትና በወሳኝ አገራዊ ጥቅሞች ላይ ተመሳሳይ አመለካከትና የጋራ አቋም መያዝንም ያጠቃልላል።  የአገርንና የህዝብን  ጥቅም ማስቀደም፣ ብዝሃነትን መቀበል፣ እኩልነትን ማክበርና በአብሮነት ላይ የተመሰረተ ሕበረ-ብሄራዊነትን ማጎልበት ላይ የጋራ አቋም መያዝ አንዱ ያጋረ  የፖለቲካ ማሕበረሰብ የመፍጠር ዓላማ ነው። ለአገራችን ፀጥታና ደህንነት ዋስትና በሚሰጡ አገራዊ ፖሊሲዎች ላይ የማይዛነፍ አቋም  የእያንዳንዱ አገር ወዳድ ዜጋ መያዝ ይገባል። ለሕገ-መንግስት ተገዢ መሆን ማለት  ህገ-መንግስቱን ማክበር ብቻ ሳይሆን የማስከበር ሃላፊነትንም ያካትታል። በመንግስት ጥረት ብቻ   የሕግ የበላይነት የትኛውም አገር  ዋስትና ሊያገኝ አይችልም። በመሆኑም ዜጎች ህገመንግስትን ከማክበር ባሻገር ሌሎች እንዲያከብሩ የማድረግ  ሃላፊንት እንዳለባቸው ማወቅ ይኖርባቸዋል።   

አንድ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ ግንባታ ሌላው  ዓላማ ከኢኮኖሚያዊ ፍተሃዊ ተጠቃሚነት ጋር የተያዘ ነው። ልማታዊ አስተሳሰብን የበላይነት የሰፈነበትና ድህነትን ለማጥፋት በሚካሄዱ አገራዊ የልማት አጀንዳዎች ላይ ዜጎች የጋራ አመለካከት በመያዘ ለልማታዊነት የሚረባረብ ማህበረሰብን መፍጠር ማለት ነው።  በሁሉም አካባቢዎች  ፈጣን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች ላይ ህዝቦች  ተሳትፎ  የሚያደርጉበት  እንዲሁም  ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ኢኮኖሚ ስርዓት መገንባት ነው።  ይህም ማለት  ህብረተሰቡ በልማቱ ላይ ተሳትፎ እንዲያደርግ  ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዲሁም በሁሉም አካባቢዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሁሉም በየደረጃው ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ስርዓት ማረጋገጥ መቻል ማለት ነው።

በፌዴራል ስርዓታችን  አገራችን በተጨባጭ  ተለውጣለች። ልትበተንና ልትፈርስ የነበረች አገር በአጭር ጊዜ ውስጥ የዴሞክራሲ ስርዓት ልምድ መቅሰሚያ፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ተምሳሌት ለመሆን በቅታለች። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት ያለሟትን ኢትዮጵያን ዕውን አድርገዋል።  አዲሲቷ ኢትዮጵያም የህዝቦቿን  ፍላጎት ማሳካት ጀምራለች። በመሆኑም  በዚህ  የፌዴራል ስርዓት ላይ በሆነውም ባልሆነውም ጣት መቀሰሩ አግባብ አይመስለኝም።   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy