Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህወሃት ሆይ እንደንስሩ

0 630

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

ህወሃት ሆይ እንደንስሩ!
አባ መላኩ
አገር ቤት የማውቀው አንድ ወፈፍ የሚያደርገው ግለሰብ አላፊ አግዳሚውን ሁሉ “ወዳጆቼ ችግር ክፉኛ ፈተነኝ እባካችሁ የማይመለስ ገንዘብ ስጡኝ” ሲል ይውላል። አዎ ይህ ሚስኪን ጊዜ መቀየሩን ሳያጤነው እንኳን ለእንደሱ ያለ ሰው ይቅርና በቀነ ገደብ አበድሩኝ ለሚል እንኳን ገንዘብ የሚሰጥ እንደሌለ አልተገነዘበም። የዛሬ 43 ዓመት ገደማ በደደቢት በረሃ የተጠነሰሰውና 17 ዓመታት በዱር በገደል ያንከራተተው ትግል ግን አንዱ ለሌላው ገንዘቡን ሳይሆን ህይወቱንና አካሉን ሲለግስበት የነበር ሂደት ነው። ይህ የሰሚ ሰሚ ታሪክ አይደለም። በርካታ ህያው ምስክሮችን ማቅረብ የሚቻልበት ዕውነታ ነው። እኔ ቀድሜ በፈንጅ ላይ ልራመድ፣ እኔ እሻላለሁ እኔ ልቅደም፣ አንተ በትቆይ ትግሉን ከእኔ በተሻለ ትደግፈዋለህ በማለት በርካቶች ህይወታቸውንና አካላቸውን ለሌላው ሰጥተዋል። እነዛ የህዝብ ልጆች ከነበራቸው ህዝባዊነት የተነሳ ይሽቀዳደሙ የነበረው አንዱ ለሌላው ህይወቱንና አካሉን ለመስጠትና ትግሉን ለማቀጣጠል ነበር።
ዛሬ ያ ህዝባዊነት የት ይሆን? ህዝባዊነትን ከእነዛን ቁርጠኛ ታጋዮች ምነው መቅሰም ተሳነን? አንዱ ለሌላው ህይወቱንና አካሉን ባይሰጠው እንኳን እንዴት ያለበደሉትን ይገድላል? እንዴት ያለበደሉትን ያንገላታል? እንዴት ያለበደሉትን ይገፋል? እንዴት ያለበደሉትን ሰላማቸውን ያሳጣቸዋል? እንዴት ያለበደሉትን ስጋት ውስጥ ይከታቸዋል? እንዴት ያለበደሉትን ያፈናቅላቸዋል? የእኛ ትውልድ እስኪ ድርጊታችንን ቆም ብለን እንመልከት፤ አንዳችን ለአንዳችን ምን እያደረግን እንደሆነ አስበነው እናውቅ ይሆን?
ዛሬ በጥበትና ትምክህት አስተሳሰብና ተግባር ተዘፍቀናል፤ በተሳሳተና በጦዘ የብሄርና/ብሄረሰብ ፍቅር ዙሪያ ገባችንን አጥረን ጥቂት ናቸው፣ መጠጊያ የላቸውም የምንላቸውን በመንጋ ተሰባስበን እየመረጥን ያለሃጢያታቸው እያጠቃናቸው ነው፤ አንዳንዴም በጎጥ ሳይቀር ተከፋፍለን እርስ በርሳችን በመናቆር ላይ ነን፤ በማጭበርበርና በስርቆት ናውዘን የማንበላውን ሃብት ማጋበስ ውስጥ ተዘፍቀናል፣ የህዝብና የአገር አደራ ተሸርሽሯል፣ ህዝባዊነት እየደበዘዘ በአንጻሩ ህዝበኝነት እየገነገነ መጥቷል። ለጥቅም አገርን እስከመክዳት ደርሰናል፤ በስልጣን ፍላጎት ናውዘን አገርንና ህዝብን ሸጠናል። የትላንት ፍቅራችንንና አብሮነታችንን ክፉኛ ረስተናል። እነዛ የህዝብ ልጆች የወደቁለት ዓላማ ተረስቷል።
ጥቂት ህዝብ ልጆች በደደቢት በረሃ የለኮሶት ችቦ አገራችንን የብረሃን ጸዳል አላብሷታል። እውነተኛ የህዝብ ልጆች ለህይወታቸውና ለአካላቸው ሳይሳሱ፣ ምቾት ሳያምራቸው፣ ረሃብና ጥም ሳይበግራቸው ያለሙትን ነጻነት ተጎናጽፈው፤ አጎናጽፈውናል። ዛሬ ላይ ሰላም፣ ዕኩልነት፣ ዴሞክራሲና ልማት በአገራችን ፈንጥቋል። ይሁንና አስርት ሺዎች ህይወታቸውን ሌሎች አስርት ሺዎች ደግሞ አካላቸውን የገበሩበትን ሰላምና ዴሞክራሲ አዲሱ ትውልድ ተገቢውን ክብር አልሰጠውም። አዎ ደግሜ እለዋለሁ ይህ ትውልድ ለዚህ ስርዓት ተገቢውን እንክብካቤ የሰጠው አይመስለኝም። ሁላችንም በየፍላጎታቻችን ነጉደናል። አንድ የሚያደርጉንን እሴቶቻችንን ረስተናቸዋል። አንድነታችን እንዲሸረሸር በር ከፍተናል። ህወሃት/ኢህአዴግ ሆይ የትላንት የዓላማ ዕናትህና ህዝባዊነትህ ዛሬም ሊታደስና ለቀጣይ ስኬቶች ሊተጋ ይገባል።
እነዛ ጥቂት የህውሃት/ኢህአዴግ ታጋዮችን ለዚህ ታሪካዊና ህዝባዊ ድል ያበቃቸው ዓላማ ፅናትና ታማኝነት፣ ህዝባዊ ፍቅርና ወገንተኝነት፣ ተራማጅና ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እንዲሁም ህዝብን ከትግሉ ጎን ማሰለፍ መቻል፣ ሁሌም ተማሪ መሆን እና በየጊዜው ራስን ለበለጠ ድልና ስኬት ማዘጋጀት ነው። በእነዚህ እሴቶች የተመራው ህውሃት/ኢህአዴግ የተነሳበትን ዓላማ ከዳር ማድረስ ችሏል። ያ ትግል ዛሬ ፍሬ አፍርቶ የህዝቦችን ሰብዓዊ መብቶች የተረጋግጠዋል፤ የዜጎች አኗኗር እጅጉን ተሻሽሏል፤ ጅምር ቢሆንም ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ተጠቅመው ሕገመንግስታዊ አገር ዕውን አድርገዋል። ሕገ-መንግስታችን የአገራችን ህዝቦች የቆየ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትስስሮችን በአግባቡ በመዳሰስ የተዛቡ ታሪካዊ ግንኙነቶቻችን እንዳይደገሙ፤ አዎንታዊ ግንኙነቶቻችንና ዕሴቶቻችንን ደግሞ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያስችሉ መደላድሎችን የገነባ የሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ የቃል ኪዳን ሰነዳቸው ሆኗል። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ የህዝቦች አብሮነት ሰነድ ሲጣስ እየተመለከትን ነው።
ሕገ-መንግስታችን በህዝቦች መካከል እኩልነትን በማረጋገጥና ነባራዊ የአገራችን ገፅታ ለሆነው ብዝሃነት ዋስትና በመስጠት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል። ሕገ መንግስታችንን ዴሞክራሲያዊ ባህርያት ከሚያላብሱት መሰረታዊ መርሆዎች መካከል አንዱ የቡድንና የግለሰብ መብቶችን በተመለከተ ያስቀመጠው ዋስትና ነው። ሕገ መንግስታችን የግለሰብና የቡድን መብቶች ሳይሸራረፉና ሳይድበሰበሱ በተሟላ መንገድ ያለገደብ እንዲከበሩ በግልጽ ደንግጓል። በህገ መንግስቱ የግለሰብ መብቶች ከቡድን መብቶች ጋር የሚመጋገቡ እንጂ የሚጣረሱ አለመሆናቸውን፣ የግለሰብ መብቶች መጣስ፣ የቡድን መብቶችን መጣስን እንዲሁም የቡድን መብቶች መጣስ፣ የግለሰብ መብቶች ጥሰትን የሚያስከትል እንደሆነ በደንብ አስታውቋል። በተግባርም አረጋግጧል። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበርካታ አካባቢዎች የግለሰብ መብቶች ባለመብት ነን በሚሉ አካላት ሲደፈጠጥ እየተመለከትን ነው። ለዚህ ነው ህወሃት/ኢህአዴግን ያ ህዝባዊነት የት ይሆን? ስል ጥያቄዬን ለማቅረብ የወደድኩት።
ሕገ-መንግስታችን ለፈጣንና ቀጣይ የኢኮኖሚ እድገታችን እንዲሁም ለአስተማማኝ ሰላማችን ዋስትና በመሆኑ ሁላችንም ልናከብረው ብቻ ሳይሆን ልናስከብረው ይገባናል። ሕገ-መንግስታዊ የፌደራል ስርዓታችን ብዝሃነትን የተቀበለ የአገራችንን አንድነት ያስጠበቀ፣ እያንዳንዱ ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ሁኔታዎችን ያመቻቸ በመሆኑ በትንሽ በትልቁ በዚህ ስርዓት ላይ ጣት መቀሰሩ ዋጋ ያስከፍለናል የሚል ስጋት አለኝ። የልማታችን፣ የዴሞክራሲያችን፣ የሰላማችንና የአንድነታችን ዋስትና የሆነውን የፌደራል ስርዓት ለማፍረስ የሚንቀሳቀስ ማንኛውንም ሃይል በጽናት መታገል የሁላችንም ስራ ሊሆን ይገባል። ከዚህም ባሻገር ሁሉንም እንቅስቃሴያችንን ከአገራችን ጂኦፖለቲክስ ጋር ማዛመዱ የሚበጅ ይመስለኛል። የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ውጥንቅጡ የወጣ ከሆነ ሰነባብቷል።
የሕገ-መንግስታችን መሰረታዊ መርህ የህገ የበላነትን ነው፡፡ ማንኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር፣ እንዲሁም የመንግስት ውሳኔ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው ያስቀምጣል። በተጨማሪም ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማሕበራት እንዲሁም ባለስልጣኖቻቸው ሕገ-መንግስቱን የማስከበርና ለህገ መንግስቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት እንዳለባቸውም በግልፅ ይደነግጋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ መርህ እየተደፈለቀ ነው። አስርት ሺዎች ህይወታቸውን ሌሎች አስርት ሺዎች ደግሞ አካላቸውን የገበሩበት መርህ ሲደፈለቅ ህወሃት/ኢህአዴግ እየተመለከተ ነው። ይህ ነበር የዚህ ድርጅት አቋም? ይህን ስመለከት ነው ዛሬ ያ ህዝባዊነት የት ይሆን? ስል ህወሃት/ኢህአዴግን መጠየቅ የፈለኩት። በዕርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገዥው ፓርቲና መንግሥት ራሳቸውን ከሕዝብ ፍላጎት ጋር ማስተካከል ያስችለናል የሚሏቸውን እርምጃዎች በቅደም ተከተል በመውሰድ ላይ እንደሆኑ እየተመለከትን ነው። ህወሃት/ኢህአዴግ ከአበቃቀሉ ጀምሮ የአንድ ጎልማሳ ዕድሜ እስኪያስቆጥር ድረስ ከህዝብ ፍላጎት ውጪ ተንቀሳቅሶ አያውቅም። ዛሬም ያ ህዝባዊነቱ እንዲመለስ እንደንስር ራሱን መለወጥ፤ ራሱን መቀየር ይኖርበታል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy