Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ወገንተኝነት…

0 331

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ወገንተኝነት…

                                                             ዘአማን በላይ

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ሁሌም ወገንተኝነቱ የህዝቡ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት ለሚረጋገጥበት ህገ መንግስትና መላው ህዝቦች በሙሉ ፈቃዳቸው ላቋቋሙት ህገ መንግስታዊ ስርዓት ነው። ይህ የሰራዊቱ ወገንተኝነት ትናንትም ይሁን ዛሬ የሚከናወንና ወደፊትም በፍፁም ህዝባዊ መንፈስ ተፈፃሚ የሚሆን ነው። ሰራዊታችን በህገ መንግስቱ አንቀፅ 87 (ከአንድ እስከ አምስት ድረስ) “የመከላከያ መርሆዎች” በሚል ርዕስ ተለይተው የተሰጡትን ድንጋጌዎች በፅናት ሲያከናውን የመጣና አሁንም በማከናወን ላይ የሚገኝ ሃይል ነው።

በቅድሚያ ከሀገር ውስጥ ተግባሮቹ መነሳት እንችላለን። የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በሀገር ውስጥ የሚያከናውናቸው ተግባራት የልማት ሃይል መሆኑን ያረጋገጠ ነው። ሰራዊቱ በሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህል የመከላከያ መሠረተ- ልማት ዘርፍ የተቋሙን የልማት ስራዎች ከመስራት በዘለለ፤ እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ቦታዎች ላይ ለህዝቡ ወሣኝ የሆኑ የመንገድ፣ የድልድይ፣ የመስኖ ልማት..ወዘተ ቁልፍ ስራዎችን እያከናወነ ነው።

ከዚህ በተጓዳኝም በብረታ ብረትና ኢንዱስትሪ ኮርፖርሬሽን ውስጥ የሚገኙ የሠራዊቱ አባላት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ኮርፖሬሽኑ የወሰዳቸውን የሜካኒካል ስራዎች ከውጭ እንዳይገቡና ሀገር ውስጥ እንዲመረቱ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ወጪን የማዳን ተግባራትን ገባራዊ እያደረጉ ነው። ይህ ብቻ አይደለም። የኮርፕሬሽኑ ሰራዊት አባላት የትራንስፖርት እጥረትን ለመቅረፍ የከተማ አውቶብሶችንና ሌሎች ተሽከርካሪዎችን ሀገር ውስጥ በመገጣጠም እንዲሁም የሀገሪቱ ልማት ወሣኝ የሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳይቆራረጥ ከፍተኛ ሃይል መሸከም የሚችሉ ትራንስፎርመሮችን በመስራት…ወዘተ. ተግባራትን በማከናወን የልማት አጋርነታቸውን እያረጋገጠ ነው። ሌላ ሌላም።…

እነዚህ ጥቂት አብነታዊ ሃቆች የሚያመላክቱት፤ ሰራዊታችን በመንግስት የተመደበለትን በጀት አብቃቅቶ ከመጠቀም ባሻገር በሀገራዊ ልማት ውስጥ እጁን በማስገባት ጭምር የውጭ ምንዛሪን በማዳን በኢኮኖሚያዊ እመርታችን ላይ ጉልህ አሻራውን እያሳረፈ መሆኑን ነው፡፡

የሠራዊታችን ልማታዊነት በዚህ ብቻ የተገደበ አይደለም። ቀደም ሲል ከተጠቀሱት አብነቶች ባሻገር በየዕዙ፣ በየክፍለጦሩና በየሬጅመንቱ በጉልበቱ፣ በገንዘቡ፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና በሌሎች ዘረፎች የልማት አጋርነቱን በተግባር በማረጋገጥ ላይ ይገኛል። ሰራዊቱ ለተለያዩ የልማት ስራዎች ከደመወዙ በማዋጣት ከሚያደርገው እገዛ ባሻገር፤ በተሰማራባቸው አካባቢዎች ጊዜውንና ጉልበቱን መስዋዕት በማድረግ የህብረተሰቡን ችግሮች በሚፈቱ ተግባራት ላይ በንቃት እየተሳተፈ ነው።

በሀገሪቱ ውስጥ ተሰማርቶ በሚገኝባቸው የግዳጅ ቀጠናዎች ሁሉ ለአቅም ደካማ አባወራዎችና አማወራዎች ድጋፍ የመስጠት ስራዎችንም አከናውኗል፤ በማከናወን ላይም ይገኛል። ማሳቸው ላይ ሰብሎችን በመዝራት በማረም በማጨድና በመሰብሰብ ህዝባዊነቱንና የልማት አጋርነቱን እያረጋገጠ ነው። የአርሶ አደሩ ምርት በፍጥነት ለገበያ እንዲደርስ ለማስቻልም የትራንስፖርት መንገድ በሌላቸው ቦታዎች ከየአካባቢው ህብረተሰብ ጋር እየተቀናጀ በመንገድ ስራ ላይ በንቃት ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ሰራዊቱ ከህብረተሰቡ ጋር አብሮ ስለሚኖርና ችግሩንም ስለሚገነዘብ የሚመደብለትን በጀት በማብቃቃት ከደመወዙ እያዋጣ ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ኬላዎችን፣ መንገዶችን ..ወዘተ በመገንባት እንዲሁም የውስጥ ቁሳቁሶቻቸው እንዲሟላ በማድረግ ለየአካባቢው ህዝብ አስረክቧል።

የአካባቢን ስነ ምህዳር በመጠበቅ ረገድም ከህብረተሰቡ ጋር በመሰለፍ ችግኞችን ይተክላል፤ እንዲፀድቁም በመንከባከብ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል። በተለይም ችግኞች እንዳይጠወልጉ “አንድ ኮዳ ውሃ ለአንድ ችግኝ” በሚል መርህ ተገቢውን ክትትል በማከናወን እንደ ዜጋ ልማታዊ ተግባርን ከህዝቡ ጋር ተሳስሮ እየፈፀመ ነው።

መከላከያ ሰራዊታችን ተልዕኮውን በሚወጣባቸው አካባቢዎች በራሱ የውስጥ አቅም፣ ጥረትና ተነሳሽነት ከሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች በተጓዳኝ ምግባረ ሰናይ ተግባራትንም ያከናውናል። በመሆኑም በተለያዩ የሰራዊቱ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ አባላት ከደመወዛቸው ተቆራጭ እያደረጉ በኤች-አይ-ቪ/ኤድስ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን እንደ ወላጅ አባት ሆነው ያስተምራሉ፤ ይደግፋሉ።

ሀገራችን ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱት ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በህዝብ በእንስሳትና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱም ሰራዊታችን ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በደረሰባቸው አካባቢዎች ሰራዊታችን በእግረኛ፣ በኮማንዶና በአየር ሃይል ቀድሞ በመድረስ የከፋ ጥፋት እንዳይከሰት በማድረግ የህዝቡን ህይወትና ንብረት በመታደግ ህዝባዊነቱንና የልማት ደጋፊነቱን በማያሻማ መልኩ አረጋግጧል። በሀገራችን ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች በጎርፍ አደጋ ሲደርስ ህይወቱን ለአደጋ አጋልጦ በመስጠት ህዝቡን ታድጓል። የደቡብ ሱዳን ሙርሌ ታጣቂዎች የህዝብ ልጆችንና ከብቶችን ሲወስዱ ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ ያስመለሰ የህዝብ ልጅ ነው።

ከልማቱ በመለስም በተፈጥሮ የአየር ንብረት መዛባት ምክንያት በተከሰቱት የድርቅ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ሰራዊቱ ከደመወዙ ተቆራጭ በማድረግ ወገኑን ከመደገፉ ባሻገር፤ ለተጐጂው ወገን ዕርዳታው እንዲደርስለት በተሽከርካሪዎቹ በማጓጓዝ ብሎም ዕርዳታው የሚፈለገው ቦታ እንዲደርስ እጀባ በማድረግ አኩሪ ተግባራትን ፈፅሟል፤ እየፈፀመም ይገኛል።

የሀገራችን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አንድ አካል የሆነውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለመገንባት በተያዘው ህዝባዊ ዕቅድ፤ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ገንዘብ ቦንድ ገዝቷል። ይህም ሰራዊቱ በሀገር ውስጥ “የልማቱ ጠባቂ ብቻ ሣይሆን አልሚም ነኝ” በሚል መንፈስ ለልማት የተጋ ሃይል መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

ታዲያ እነዚህ ህዝባዊና ልማታዊ ተግባሮቹ ከምንም ተነስተው የተገኙ አይደሉም። ሰራዊቱ በሀገር ውስጥም ተልዕኮው ለህገ መንግስቱና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ባለው ወገንተኝነት ስላለው ነው። ርግጥ ህገ መንግስታዊ እምነቱ የፀና ብቻ ሳይሆን የስርዓቱ የመጨረሻ ምሽግ በመሆን ጭምር ተግባሩን እየተወጣ ነው።

ሰራዊቱ ከላይ የጠቀስኳቸውንና በሀገ መንግስቱ ላይ ተለይተው የተሰጡትን መርሆዎች በሚገባ በመፈፀም ለህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ታማኝና ታዛዥ በመሆን ተግባሩን እየከወነ ነው። በቅርቡም በህገ መንግስቱ አንቀፅ 93 ላይ በተደነገገው መሰረት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ከሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን ተፈፃሚ እያደረገ ነው። ይህ ሰራዊት ታማኝነቱ ህዝቡ በፈቃዱ ላፀደቀው ህገ መንግስትና እንዲመሰረት ለፈቀደው ህገ መንግስታዊ ስርዓት ብቻ ነው። በየትኛውም የግዳጅ አፈፃፀሙ ወቅት ህዝቡን ከጎኑ በማድረግ ተግባሩን የተወጣ ሃይል ነው።

ይህ ለህገ ህገ መንግስቱና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ባለው ወገንተኝነት የሚያከናውናቸው ተግባሮች ከሀገር ውጭም በፅናት የሚተገበሩ ናቸው። ሰራዊቱ ሀገር ውስጥ ሲሆን ህዝባዊ ከሀገር ውጭ ሲሆን ደግሞ ሌላ ዓይነት አቋም የሚይዝ አይደለም—የትም ቢሆን ህዝባዊ ባህሪው አብሮት የሚጓዝ ነውና።

በዚህ መሰረት በህገ መንግስቱ አንቀፅ 86 (6) ላይ እንደተደነገገው፤ ሀገራዊ ደህንነትን በማረጋገጥ በአካባቢያዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የሠላም ማስከበር ስራ ላይ በብቃት መሳተፍ ይገባል። በዚህ መሰረትም በተለያዩ ሀገራት ጥያቄዎች ሲቀርበቡለት ተልዕኮውን ህዝባዊ ወገንተኝነቱን ተላብሶ በብቃትና በጀግንነት ፈጽሟል፤ እየፈፀመም ነው። በሩዋንዳ፣ በብሩንዲና በላይቤሪያ ህዝባዊነትን ተላብሶ የተሰጠውን ድጋጅ በመፈፀም ከየሀገራቱ ሜዳሊያና ሽልማት ተበርክቶለታል። እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ተልዕኮውን እያከናወናቸው ባሉበት በሱዳን ዳርፉር፣ በአብዬ ግዛት፣ በሶማሊያና በጁባ በዚሁ መንፈስ ተግባሩን እየተወጣ ነው። በዚህም ከየሀገሮቹ ምስጋና እና አክብሮት እየተቸረው ነው።

ታዲያ እዚህ ላይ ሰራዊቱ በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ የሚፈፅማቸው ተግባራት መነሻቸውም የሁን መድረሻቸው ህገ መንግስቱና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል። ለህገ መንግስቱና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ባለው ታዛዥነት እንዲሁም በየተልዕኮዎቹ ውስጥ በደጀንነት ከህዝቡ ጋር የሚሰራ መሆኑ ለስኬታማነቱ ወሳኝ ድርሻ እንዲኖረው አድርጓል። ይህ ሰራዊት ከራሱ አልፎ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ የሰላም አምባሳደር መሆን የቻለው የህዝቡን ውሳኔዎችና ተጠቃሚነት ማዕከል አድርጎ ስለሚንቀሳቀስ ነው።

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy