Artcles

ለችግሮቻችን ግጭት መፍትሔ አይሆንም

By Admin

February 02, 2018

ለችግሮቻችን ግጭት መፍትሔ አይሆንም

                                                            ታዬ ከበደ

በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለተከሰቱት ችግሮች “ዋነኛው ተጠያቂ እኔ ነኝ” ብሎ መንግስት ሃላፊነቱን ከወሰደና ህዝቡንም ይቅርታ ጠይቆ ችግሮቹን ለመፍታት አቅጣጫዎችን አስቀምጦ ወደ ተግባር እየገባ ባለበት በዚህ ወቅት ግጭቶች ለምን እንደሚከሰቱ ግራ የሚያጋባ ነው።

እርግጥ በማንኛውም አገር ውስጥ ግጭት መኖሩ ነባሪያዊ ነው። አንዳንዴም ግጭት የመፍትሔው አካል ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እዚህ አገር ውስጥ ለሚፈጠሩ ችግሮች ግጭት መፍትሔ ሆኖ ሊወሰድ አይችልም። አይገባምም። እንዲያውም ግጭት ችግሮቻችንን የሚያወሳስብ ስለሆነ ልንከላከለው ይገባል። ምክንያቱም እዚህ ሀገር ውስጥ የሚካሄዱ ግጭቶች ምክንያት አልባና አንዳንዴም አሳፋሪ ከመሆናቸው ሌላ ግጭቶቹ ፈፅሞ የህዝቡን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ አለመሆናቸው ነው።

ያም ሆኖ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች መነሻውን ድንበር በማድረግ የሚከናወኑ የግጭት ተግባራት አሉ። እነዚህ ግጭቶች መነሻቸው ህዝብ አይደለም። ህዝብ ለሰላም እንጂ ለግጭት ቦታ ሊኖረው አይችልም። ይሁንና አሁንም ቢሆን ለግጭት የሚሆን ምህዳርን በተቻለ መጠን ማጥበብ ይገባል።

እንደሚታወቀው የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት ከመልካም አስተዳደር ችግር፣ ከሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት ጋር በተያያዘ ህዝቡን በማወያየት ዕርምጃ ለመውሰድ እየተንቀሳቀሱ ነው። በክልሎች በተካሄዱ ሰፋፊ የውይይት መድረኮች ከህዝቡ በተገኘው ግብዓት መሠረት ጥፋት በፈፀሙ አመራሮች ላይ ዕርምጃ መወሰድም ተጀምሯል፤ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

እርምጃውን በጥልቀትና በስፋት በማስቀጠል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመሠረቱ ለመፍታት መስራት የግድ ነው። የህልውና ጉዳይም ነው። ምክንያቱም ችግሩ በቅርቡ በተወሰኑ የሃገራችን አካባቢዎች ለሰላም እና መረገጋት መጥፋት መንስኤ ሆኖ ተስተውሏልና። ሰላም ደግሞ የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። ምንግስትም ይህን ተገንዝቦ እስከዛሬ ለተፈጠረው ችግር ሃያፊነቱን በመውሰድ ህዝቡን ይቅርታ ጠይቋል። መንግስት ችግሮቹን ለሚፈታበት መንገድ ተባባሪ መሆን ሲገባ አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ወደ ግጭት ለመግባት የሚደረገው ጥረት ህዝቡን የማይወክል በመሆኑ በምንም ዓይነት ስሌት ተቀባይነት አይኖረውም።

እርግጥ ከማናቸውም ችግሮች በስተጀርባ ግጭቶችን ተገን አድርገው የራሳቸውን አጀንዳ ለማሳከት የሚጥሩ ኃይሎች መኖራቸው የግድ ነው። እነዚህ የተጀመረውን የሠላም፣ የመልካም አስተዳደርና የህዳሴ ጉዞ ለመቀልበስ በመሯሯጥ ላይ የሚገኙ ኃይሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ሰላማችንን ለማድፍረስ፣ የዕድገት ግስጋሴያችንን ለማደናቀፍ ደፋ ቀና ማለታቸው በቅርቡ በኦሮሚያና በጋምቤላ የተከሰቱት ድርጊቶች ሁነኛ አስረጅዎች ናቸው።  

ያም ሆኖ ምክንያቶችን መድፈን ይገባል። ቀዳዳዎችን ያለ አንዳች ሽንቁር መድፈን የግድ ይላል። ለግጭት ሃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳርን ማሳጣት ወሳኝ ነው። ይህን ለመከወን የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና የማይፈልጉ፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ ድብቅ የጥፋት ኃይሎች ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ኃይሎችን በቁርጠኝነት መታገል ይገባል።

በተለይም ግጭትን ቦታ ለማሳጣት የትምክህትንና የጥበት አራማጆችን መታገል የግድ ይላል። እንደሚታወቀው በትምክህትና ጠባብነት አስተሳሰብ የተጠመቁ ኃይሎች ከሁሉ በላይ የቋንቋ፣ የባህልና የማንነት ብዝሃነትን አጥብቀው ይጠላሉ፡፡ የትምክህት ኃይሉ የእኔ ብሄር ብቻ ልዕለ ኃያል የሆነ፣ ቋንቋዬ፣ ባህሌና ማንነቴ ከሌላው የሚበልጥና የተለየ፣ ሁሌም ለመግዛት የተፈጠ ርኩ ነኝ ብሎ ያምናል፡፡

ከዚህ ጐን ለጐንም ሌላውን ብሔርና ዜጋ ተራና ርካሽ፣ ለመመራት እንጂ ለመምራት ያልተፈጠረ ቋንቋው፣ ባህሉና ማንነቱ የወረደ አድርጐ ይቆጥረዋል፡፡ የህዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትንም አይቀበልም። ስለሆነም ብዝሃነትን ደፍጥጦ የራሱን አስተሳ ሰብ፣ ቋንቋና ባህል በሌላው ላይ ለመጫን የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡

ይህ ካልሆነ ሀገር ትጥፋ ህዝብም ይለቅ የሚል ህሳቤም የተጠናወተው ነው። ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ብሔርተኝነትን የማይቀበል፣ የህዝቦች አንድነት ሳይሆን የግዛት አንድነት የሚያሳስበው ኃይል ነው። ከህዝብ ይልቅ ተራራና ወንዝ የሚናፍቅ ፀረ ህዝብ አመለካከት የተጠናወተውም ነው። የዚህ አስተሳሰብ ተቃራኒ የሆነው ጠባብነትን የተላበሰ ኃይል ደግሞ ሁሉንም ለእኔ እና ለእኔ ብቻ ብሎ የሚያስብ ነገሮችን ሁሉ በጠባብነት መነፅር የሚመዝን የዚህ ዓለም ዕውነታ የሆነውን ብዘሃነትን ተቀብሎና ተቻችሎ መኖር የእሬት ያህል የሚጎመዝዘው ኋላ ቀር አሳቢ ነው። በጠባብነት ድንበር የታጠረ እንደመሆኑ መጠንም ከሱ ብሔር ውጪ ያለ ህዝብ በአካባቢው እንዳይኖር ሌላ ቋንቋ እንዳይነገር ይሰብካል፡፡

ይህ የጥበት ሃይል በመስበክ ብቻ ራሱን አያቅብም፡፡ የብሔሩ አባል ሌላውን በጥላቻና በጥርጣሬ እንዲመለከተው ዕድሉ ሲመቻችለትም እንዲያጠቃና እንዲያጠፋው ተግቶ ይሠራል፡፡ በአኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን አይቀበልም። የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፀር በመሆንም ሌላውን ዜጋ ለመጨፍለቅ ይሞክራል—ቢሳካለትም ባይሳካለትም፡፡

ታዲያ የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፅኑ ጠላት የሆኑትና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የሃይማኖት፣ የብሔር፣ የቋንቋና የባህል ብዝሃነት ባለባቸው ሃገሮች ፈጽሞ ሊሠሩ የማይችሉት እነዚህ ሁለት አስተሳሰቦች፤ በአሁኑ ወቅት በሰላማችንና በልማታችን ላይ የተደቀኑ እንቅፋትና ጋሬጣዎች መሆናችው ፍንትው ብሎ እየታየ ነው።

ለግጭቱ መነሻ የሆኑት ጉዳዩች ከፌዴራላዊ ስርዓቱ ጋር የማይዛመዱ ናቸው። በአንዳንድ አካባቢዎች የሚደረጉ ግጭቶች ምክንያታቸው በአንድ ብሔር ላይ የሚያነጣጥር ዜጎች ለዘመናት ያፈሩትን ሃብትና ንብረት በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የሚያወድም መሆኑ እየታየ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ፈር የለቀቀ አስተሳሰብ ከወዲሁ መቀጨት ይኖርበታል። ፈፃሚዎቹም በህግ ጥላ ስር መዋል ይኖርባቸዋል።

ህዝቦች በጋራ ሰላም የመሆን፣ በጋራ የመልማትና የማደግ፣ በጋራ ዴሞክራሲን ለማጎልበት እምነትና ፈቃዳቸውን በሕገ መንግስታቸው ላይ ሳይቀርገልፀው ሲያበቁ፤ በጥላቻና ላይ በተመሰረተ የጥቂት ታጣቂዎችና የበታች አመራሮች ፍላጎት እውን ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም አስተሳሰቡ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ቦታ የሌለው ብቻ ሳይሆን፣ የሕገ መንግሥቱ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤቶች የሆኑት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሊፈቅዱት ስለማይችሉት ጭምርም ነው።

ያም ሆኖ ጊዜያዊ ግጭቶች የህዝቦችን ፍላጎት የሚወክሉ አይደሉም። ለዘመናት አብሮ የኖረ፣ በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኦኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ውጣ ውረዶችን አብሮ ያሳለፈ ህዝብ ለጊዜያዊ ሁኔታ ብሎ የሚጋጭበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም።

እናም ህዝቦች በወሰን መካለል ጉዳይ ሊጋጩ የሚችሉበት ነባራዊ ሁኔታ እዚህ ሀገር ውስጥ ሊፈጠር አይችልም። በመቻቻል፣ በመከባበርና አንደኛው ህዝብ የሌላኛውን በሚያከብርበት አገር ውስጥ ህዝቦች በጊዜያዊ ሁነት ሊጋጩ አይችሉም። ያለፈው ታሪካቸውና አብሮነታቸው ይከለክላቸዋል።

ሆኖም በተነሱት ግጭቶች ሳቢያ አንዳንዶች ዘረፋን የመሳሰሉ ህገ ወጥ አካሄዶችን የሚከተሉ ናቸው። ይህን ለማመቻቸት ሲሉም ደጋፊዎችን በማብዛት የጥቃት ዱላቸውን ሊሰነዝሩ ስለሚችሉ ህዝቡ ጥንቃቄ ከማድረግ በላይ እነዚህን አካላት ወደ ህግ ማቅረብ ይኖርበታል። ምክንያቱም ለሚፈጠሩ ችግሮች መቼም ቢሆን ግጭት መፍትሔ ሊሆን ስለማይችል ነው።