ላብን እንጂ ደምን …
ወንድይራድ ኃብተየስ
የአስተሳሰብ፣ የዕምነት፣ የቋንቋ፣ ወዘተ ልዩነቶችን ሊያስተናግድ የሚችል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በአገራችን መገንባት ተችሏል። ይሁንና የዴሞክራሲ ስርዓታችን የጎለበተ፣ ያለቀለትና የበቃለት ነው ማለት እንዳልሆነ ግን ይታወቅልኝ። ሲጀመርም ዴሞክራሲ በሂደት የሚዳብር እንጂ በ20ና 30 ዓመታት ሂደቱን ጨርሶ ሊበቃ የሚችል ነገር አይደለም። የአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ጅምር ቢሆንም ልዩነቶቻችን ሊያስተናግድ የሚችልበት ትክክለኛ መስመር ላይ እንደሆነ ግን ነባራዊ ሁኔታዎች ያመላክታሉ። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብረውላቸዋል፤ ከአካላዊም ሆነ ስነ-ልቦናዊ ጥቃት ነጻ ናቸው በመረጧቸው ወኪሎቻቸው ይተዳደራሉ፣ ባህላቸውን ያዳብራሉ፣ ቋንቋቸውን ይጠቀማሉ፣ በማንነታቸው እንዲኮሩ ሆነዋል።
በአገራችን እየተገነባ ያለውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማምጣት የዛሬ 43 ዓመት በፊት ህወሃት በደደቢት የጀመረው ትግል የአስርት ሺዎችን ህይወትንና የአካል መሰዋትነትን ቢጠይቅም የታሰበውንና የተናፈቀውን ነጻነት፣ እኩልነትና ልማት ማረጋገጥ ግን ችሏል። በጥቂት የህዝብ ልጆች በደደቢት በረሃ ተጠንስሶ የነበረው የነጸነት ትግል ህዝባዊ ድጋፍና የዓላማ ጽናት የነበረበት በመሆኑ ውጤታማ መሆን ችሏል። ህወሃት/ኢህአዴግ በትጥቅ ትግል ውጤታማ መሆን የቻለው ታጋዮቹ ፍተሃዊ ጥያቄን ይዘው መነሳታቸውና የዓላማ ጽናት ያላቸው መሆኑ እንጂ ከደርግ ጋር የሚወዳደር ዘመናዊ መሳሪያ እንዲሁም የሰለጠነ ሰራዊት ኖሯቸው አልነበረም። የዓላማ ጽናትና ህዝባዊነትን መላበስ ህወሃት/ኢህአዴግን ከዚህ አድርሶታል። ዛሬም ህወሃት/ኢህአዴግ አለኝ የሚለው ሃብት ጠንካራ ህዝባዊ ድጋፉን ነው። የዛሬው ወጣት ሃይል ህዝባዊ ድጋፍንና የዓላማ ጽናትን ከእነዛ ቁርጠኛ የህዝብ ልጆች ሊማር ይገባል። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ እጣ ፈንታ በዚህ ወጣት ሃይል እጅ ላይ ነች።
ለዛሬው ሰላምና ዕድገት መረጋገጥ እነዚያ ቁርጠኛ የህዝብ ልጆች ህይወታቸውን ገብረዋል፣ አካላቸውን አጉድለዋል፣ በዱር በገደል ተንከራተው፣ እርቧቸዋል ጠምቷቸዋል። ለዚያ ትውልድ ምስጋና ይግባውና የእኛ ትውልድ የህይወትም ሆነ የአካል መስዋዕትነት የሚጠበቅበት አይደለም። የእኛ የትግል መስክ ከቀድሞ የተለየ ነው። የዛሬው የጸረ ድህነት ትግል ለነጻነትና እኩልነት እንደተከፈለው የ17 ዓመታት መራራ ትግል የህይወት መሰዋትነትም ሆነ የአካል መጉደልን አይጠይቅም። በሁሉም መስኮች በፖለቲካው፣ ኤኮኖሚውና ማህበራዊ ዘርፎች አገራችን የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሳለች።
በርካቶች የወደቁለት የነጻነትና እኩልነት ጥያቄ መልስ እንዳገኘ ሁሉ ድህነትንም የማስወገድ ጥያቄ በአዲሱ ትውልድ መልስ ማግኘት ይኖርበታል። ያ ትውልድ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን ዕኩልነትና ነጻነትን አውርሶናል። የእኛ ትውልድ ደግሞ ከድህነት ጋር ታግሎ በኢኮኖሚዋ የተሻለች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ይጠበቅበታል። ከአሁኑ ትውልድ የሚጠበቀው በተሰማራንበት መስክ ሁላችንም አገራችንን በቅንነትና ታማኝነት በማገልገል የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ማፋጠን ነው። ድህነት የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ በመሆኑ ሁሉም ሊዋጋው የሚገባ የጋራ ጠላታችን ነው። ድህነት ወደ አለመረጋጋት፣ ግጭት፣ ወደኪራይ ሰብሳቢነት ብቻ ለአገራችን ውድቀት ምክንያት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። በመሆኑም የአሁኑ ትውልድ መስዋዕትነት የሚለካው ድህነትን በመዋጋት መሆን መቻል ይኖርበታል።
የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላት ድህነት እንደሆነ አበክረው ይገልፁ የነበሩት ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ዋንኛ ጠላታችን የሆነውን ድህነትን ማሸነፍ ካልቻልን አገራችን ያሉባትን ውስብስብ ችግሮች መቅረፍ አንችልም ሲሉ ይገልጹ ነበር። ይህ ታላቅ አገላለጽ ነው። ሁላችንም ራሳችንን እንድናይ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ እንድናጤን የሚያደርግ አባባል ነው። ከለንበት ሁኔታ ለመውጣት የሚያስችለን ለድህነታችን መንስኤዎቹም ሆነ መፍትሄ አምጪዎቹ እኛው ራሳችን መሆናችንን መገንዘብ ስንችል ነው። በጦርነትና ድርቅ ትታወቅ የነበረች አገር ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ገጽታዋ እንዲሻሻልና በዓለም ዓቀፍ መድረክ የነበራት ተሰሚነት እየጎለበተ የመጣው መንግስትና ህዝብ ትኩረታቸውን ወደ ጸረ-ድህነት ትግሉ ማድረግ በመቻላቸው ነው። አሁን ያሉትን ስኬቶቻችንን ማስቀጠል ከቻልን በመጪዎቹ ሁለትና ሶስት ዓመታት የመጀመሪያውን ደረጃ የመካከለኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ማለትም 1005 ዶላር ማሳካት ይቻላል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ሁለት ገጽታ ተላብሳለች። የመጀመሪያው የምታጓጓና በለውጥ ምዕራፍ ላይ ያለች በለተስፋ አገር ስትሆን ሁለተኛው ደግሞ በሁከትና ነውጥ ሳቢያ አፋፍ ላይ የቆመች አገር ትመስላለች። ሁለቱም አማራጮች በእጃችን ላይ ነው። አገራችንን በስኬት ጎዳና ልንመራት አሊያም ወደ ጥልቁና አረንቋ ልንከታት የምንችለው እኛ የአሁኑ ትውልድ ነን። ካወቅንበት አገራችን አሁን ላይ በታላቅ እመርታዊ ለውጥ ላይ የምትገኝ፣ ለራስዋ ዜጎች ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የምትተርፍ ባለተስፋ ምድር ልናደርጋት እንችላለን። ምክንያቱም በሁሉም ዘርፍ እየተመዘገበ ያለ ፈጣን ለውጥ ስለሚስተዋል ነው። ይህን በእጃችን የገባ የመለወጥ የማደግ ተስፋ በአግባቡ መያዝ ካልቻልን የመፍረስ የመበታተን እድላችንም ሰፊ እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው።
ኢህአዴግ ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና አንድነት መሰረቶች የዜጎች ሰባዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መጠበቅ እንዲሁም ዘላቂና ፈጣን ልማትን ማረጋገጥ እንደሆነ ስለሚገነዘብ እነዚህን ሁለት ነገሮች የሞት ሽረት ትግል አድርጎ በመውሰድ ለውጤት በመትጋት ላይ ነው። ህወሃት/ኢህአዴግ የእኩልነትና ነጻነት ጥያቄዎች መደፍጠጥ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ከማንም በላይ የሚረዳ ድርጅት በመሆኑ የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ከልማት ጥያቄዎች እኩል ለማራመድ ጥረት አድርጓል። በማድረግም ላይ ነው። በመሆኑም ልማትን ለማፋጠን ተብሎ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ በኢትዮጵያ ሊተገበር የሚችል ነገር አይደለም። በርካታ ልዩነቶች በሚስተዋሉባት አገር ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድን ለመተግበር መሞከር ትርፉ ጦርነትና እልቂት እንደሚሆን ህወሃት/ኢህአዴግ ካለፉት ስርዓቶች ጥሩ ትምህርት ተቀስሟል። በመሆኑም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ሊተገበር አይቻልም። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን መብት የማያከብር መንግስት ምንም ያህል ልማትን ማረጋገጥ ቢችል እንኳን ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። ለዚህም ነው ልማትና ዴሞክራሲ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሊነጣጠሉ የማይችሉ ነገሮች ናቸው ሲል ኢህአዴግ የሚገልጸው።
የዛሬው ሰላም፣ እድገትና ዴሞክራሲ በእነኛ ህይወታቸውንና አካላቸውን በገበሩ የህዝብ ልጆች የመጣ መሆኑን ማሰብ ተገቢ ነው። የ17 ዓመታት የትጥቅ ትግሉ እጅግ ፈታኝና እልህ አስጨራሽ ቢሆንም የታለመለትን ግብ መምታት ችሏል። የዛሬው ትግል የጸረ-ድህነት ትግል ነው። ይህ ትግል ደግሞ የህይወትና የአካል መሰዋዓትነትን የሚጠይቅ አይደለም። ዛሬ አገራችን ከእኛ የምትፈልገው በተሰማራንበት የስራ መስክ ጠንክረን በመስራት ድህነትን መዋጋት ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ላብን እንጂ ደምን መገበር አያስፈልገውም። የህወሃት/ኢህአዴግ ከህዝብ ተፀንሶ በህዝብ ያደገ፣ ጨቋኝ የነበረው የደርግ ስርዓት ለማስወገድ ታግሎ ያታገለ ህዝባዊ ድርጅት ነው። አሁንም ቀድሞ የነበረውን ህዝባዊነት በመቀጠል በጸረ ድህነት ትግሉም የህዝብ አጋርነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል። የጸረ-ድህነት ትግሉ ውስብስብና መሰረተ ሰፊ በመሆኑ እንደትጥቅ ትግሉ በ17 ዓመታት ትግል ብቻ ሊወገድ እንደማይቻል ሁላችንም ግንዛቤ ልንወስድ ይገባናል።
የህወሃት/ኢህአዴግ የስኬት ምስጢር የአባላቱ ዓላማ ፅናት፣ የድርጅቱ የጠራ ፓሊሲና ራዕይ እንዲሁም ጠንካራ ህዝባዊ ደጋፍ ያለው ድርጅት መሆኑ ነው። በቀጣይም ህወሃት/ኢህአዴግ ይህ ጠንካራ ህዝባዊ መንፈሱ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ለአገራችን ቀጣይ ስኬት ህወሃት/ኢህአዴግ ራሱን በመፈተሽ ህዝብንና ድርጅቱን ሊያቃቅሩ የሚችሉ ነገሮችን ማስወገድ ይኖርበታል። ህወሃት/ኢህአዴግ እንደትላንቱ ህዝባዊ ባህሪውን በመላበስ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የህዝብ ችግር የሆኑትን የመልካም አስተዳደር ዋንኛ ጠንቅ የሆነውን የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብን ተግባርን መዋጋት ይኖርበታል። በ17 ዓመቱ መራራ ትግል ወቅት መሰዋዓት የሆኑትን ወገኖቻችንን የምንዘክራቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተፈቃቅረው ፣ ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩባትን ህዳሴዋን ያረጋገጠች ኢትዮጵያን ዕውን ስናደርግ ነው።
የጸረ ድህነት ትግል እንደ ትጥቅ ትግሉ ወቅት ህይወት መገበርን፣ አካል መጉደልን፣ መራብ መጠማትን፣ በባዶ እግር ተራራ መውጣት ቁልቁለት መውረድን፣ መሮጥ መቀመጥን፤ መውደቅ መነሳትን፣ በጸሃይና ቁሩ መጠበስን ብቻ የስቃይና መከራ ህይወትን የሚጠይቅ አይደለም። እንደነዚህ ያሉ ከባድ መሰዋዓትነት የሚጠይቀው የመከራው ጊዜ አልፏል። እነዛ የህዝብ ልጆች የተነሱለትን የነጻነትና እኩልነት ዓላማ ከዳር ለማድረስ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ አስቸጋሪ ውጣ ውረዶችን ሁሉ ታግሰው ውጤታማ ሆነዋል። የአገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች የወቅቱን ነባራዊ ሁኔታ የሚመጥን አመራር መስጠት መቻል ይኖርባችኋል። በጫካው፣ በዱር በገደሉ፣ በተራራው፣ በሸለቆው፣ በሜዳው፣ ወዘተ ህይወታቸውን የሰጡ፤ አካላቸውን የገበሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች አጥንታቸው የሚለመልመው የተሰውለት ዓላማ ማሳካት ሲቻል በመሆኑ ሁላችንም ለአገራችን ህዳሴ እንትጋ። ክብር ለትግሉ ሰመዓታት!