Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሌ/ጄኔራል ፃድቃንን ታዘብኳቸው!

0 870

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሌ/ጄኔራል ፃድቃንን ታዘብኳቸው!

                                                         ድረስ ማርዬ

(ክፍል ሁለት)

በክፍል አንድ ፅሑፌ ፃድቃን ገ/ተንሳይን (ሌ/ጄኔራል) ከህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ውጭ በማስተንፈሻነት “ገለልተኛ ኮሚሽን” እንዲቋቋም ባነሱት ሃሳብ ዙሪያ ምላሽ ሰጥቻለሁ። በዚህኛው ክፍል ደግሞ፤ በቅርቡ የኢፌዴሬ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለመከላከያ ሰራዊቱ ከፍተኛና ጄኔራል መኮንኖች የሰጡትን ወታደራዊ ሹመት አስመልክተው ባነሷቸው ሃሳቦች ዙሪያ ግላዊ ዕይታዬ እንዲህ የሚነበብ ነው።…

ጡረተኛው ጄኔራል ለኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት አባላት የተሰጠውን የማዕረግ ዕድገት አስመልክተው የተለያዩ ሃሳቦችን ከሰነዘሩ ዜጎች መካከል አንዱ ናቸው። እርሳቸውን ለየት የሚያደርጋቸው ግን በክፍል አንድ ፅሑፌ ላይ እንደጠቀስኩት፤ በአተገባበሩ ልዩ የሆነውን የውትድርና ሙያ የዛሬ 16 ዓመት ገደማ ሲመሩ የነበሩ ወታደር መሆናቸው ነው። ከሌላው ዜጋ ይልቅ፤ ከሰራዊቱ የተሰናበቱበት ጊዜ ቢረዝምም እርሳቸው የተሻለ አስተያየት ይኖራቸዋል ብዬ በማሰቤ ነው። በዚህም ምክንያት ስለ ውትድርና ሙያ ባላቸው ግንዛቤ የተሻለ ሃሳብ ያቀርባሉ የሚል ምልከታ ነበረኝ። አዬ የእኔ ነገር!…ለካስ እዚህም ላይ ተሳስቼ ኖሯልና።…’እንዴት?’ ትሉኝ ይሆናል። ርግጥ ነገሩ እንዲህ ነው።…

ጡረተኛው ሌተና ጄኔራል ፃድቃን በቃለ ምልልሳቸው ላይ ፕሬዚዳንቱ ለጄኔራል መኮንኖቹ ያለበሱት የማዕረግ ዕድገትን አስመልክተው “…እንደዚህ ዓይነት ሹመት በአንድ ጊዜ ሲመጣ ፖለቲካዊ ግፊትና በሌላ በኩል ፖለቲካዊ አንድምታም አለው። ሲመጣ በፖለቲካ ግፊት ነው የሚመጣው።…” ብለዋል። በእርሳቸው እምነት ለጄኔራሎቹ የተሰጠው ሹመት አንድም፤ ‘በአንድ ጊዜ ያለ ዕቅድ የተደረገ’፤ ሁለትም፤ ‘የፖለቲካ ግፊት’ (politically motivated) ያለው ነው የሚሉ አባባሎችን የያዘ ነው። እውነታው ግን እንዲያ አይደለም። በቅድሚያ በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ የሚሰጠው የጄኔራል መኮንንነት የማዕረግ ዕድገት እንዲያው “በአቦ ሰጠኝ” ዝም ብሎ ያለ አንዳች ዕቅድ የሚታደል አይደለም። የውትድርና መያ የህይወት መስዋዕትነትን የሚጠይቅ ክቡሩን የሰው ልጅ ህይወት የመምራት የተለየ ተልዕኮና ግዳጅ ያለው እንደመሆኑ መጠን፤ ይህን ሃይል የሚመሩት አመራሮች (ከመጀመሪያው ምክትል አስር አለቃ እስከ ሙሉ ጄኔራልነት ድረስ ማለቴ ነው) የሚሰጣቸው የማዕረግ ዕድገት በቆይታ ጊዜና በላቀ የአፈፃፀም ብቃት የሚመዘን፣ ተሿሚው ወደፊት የተሰለፈለትን ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊ ስርዓት ለማገልገል ያለው እምቅ አቅም የሚለካ፣ ተጠንቶ በዕቅድ የሚዘጋጅና የመንግስትንም በጀት ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚከናወን መሆኑ እየታዘብኳቸው ያሉት ጡረተኛው ጄኔራል የሚያውቁት እውነት ነው። ምክንያቱም ይህ አሰራር ትናንትም ይሁን ዛሬ የነበረና ያለ በመሆኑ ነው። ምናልባት በእኔ እምነት ሊለይ ይችላል ብዬ የማስበው ነገር ቢኖር፤ የማዕረግ አሰጣጡ መከላከያ እንደ ተቋም በአሁኑ ወቅት ከደረሰበት ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ አኳያ ተሿሚዎቹ ሊመዘኑ የመቻላቸው ሂደት ይመስለኛል።

እናም ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ማዕረግ ያለበሷቸው 61ዱ የሰራዊቱ ከፍተኛና ጄኔራል መኮንኖች ከብርጋዲየር ጄኔራልነት እስከ ሙሉ ጄኔራልነት እንዲያድጉ መንግስት ሲፈቅድላቸው ከላይ የጠቀስኳቸው ጥብቅ የመሾሚያ መስፈርቶች ከግምት ውስጥ ገብተው እንጂ በዘፈቀደ እየታየ አይደለም። ያገኘኋቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በዚህ አሰራር መሰረት ከ2007 ዓ.ም በስተቀር ላለፉት አምስት ዓመታት የተሰጡትን የጄኔራል መኮንንነት ሹመቶችን መመልከት እንችላለን። ይኸውም በ2005 ዓ.ም ለ35፣ በ2006 ዓ.ም ለ37፣ በ2008 ዓ.ም ለስድስት፣ በ2009 ዓ.ም ለ38 እንዲሁም በያዝነው ዓመት ደግሞ ለ61 ጄኔራል መኮንኖች የማዕረግ ዕድገት ተሰጥቷል።

ታዲያ ይህ የማዕረግ ዕድገት በጥናትና በዕቅድ ላይ ተመስርቶ በየጊዜው ካለው ሁኔታ ጋር እየታየ እንዲሁም መንግስት ለተቋሙ ከሚይዘው በጀት ጋር እየተገናዘበ የተሰጠ መሆኑ እየታወቀ፤ ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን ጉዳዩን “በአንድ ጊዜ የመጣ ነው” ለማለት ለምን እንደፈለጉ ግልፅ አይደለም። በውትድርና ሙያ ውስጥ ጄኔራልነት መኮንንነት ዝም ተብሎ የሚሰጥ የሲቪል ሹመት አይደለም። እንዳልኩት የውትድርና ሙያ የራስን ህይወት የመስጠትና የተመሪውን ሰራዊት ህይወትንም በካበተ ሙያዊ ጥበብ ከሞት በማዳን በአነስተኛ ኪሳራ የላቀ ድል የማስመዝገብ የአሸናፊነት ተግባር ስለሆነ በአንድ ጊዜ የሚሰጥ ሹመት አለመሆኑን እርሳቸው ጠንቅቀው ያውቁታል። ምክንያቱም ‘ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ’ እንዲሉት ካልሆነ በስተቀር፤ እርሳቸው ኤታማዦር ሹም በነበሩበት በዚያ ወቅት እንኳን ጄኔራል መኮንንነት በአንድ ጊዜ ታፍሶ የሚሰጥ ስላልነበረ ነው። እናም ይህን በየትኛውም ዓለም የማይሰራበትን አሰራር ለምን በዚህ ወቅት ተፈፅሟል ለማለት እንደፈለጉ የሚያውቁት እርሳቸው ብቻ ይመስሉኛል። በመሆኑም አንባቢያን በዚህ ጉዳይ ላይ ትዝብቴን አስፍሬ ማለፌን እንዲገነዘቡልኝ ከማስታወስ በስተቀር የምለው ነገር አይኖረኝም። አንድ በጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹምነት ሀገሩን ያገለገለን ወታደርን የማይመጥን ተራ ሃሳብ ነውና።   

በሌላ በኩልም፤ የማዕረግ አሰጣጡ እርሳቸው እንዳሉት በፖለቲካ ግፊት (political motivated) ምክንያት የተሰጠ አይመስለኝም። ነገሩ እርሳቸው እንደሚሉት የፖለቲካ ግፊት ማዕረግ የሚሰጥ ቢሆን ኖሮ፤ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ቀውስ ባልነበረባቸው በ2005 እና 2006 ዓመተ ምህረቶች በየቅደም ተከተላቸው ለ35 እና ለ37 ጄኔራሎች ዕድገት መስጠት ባላስፈለገ ነበር። እንዲህ ዓይነት አሰራር ቢኖር ኖሮ፤ የፖለቲካ ትኩሳቱ ጡዘት ላይ በነበረበት በ2008 ዓ.ም ለስድስት ሳይሆን ለ66 ጄኔራሎች ማዕረግ መስጠት ይገባ ነበር ማለት ነው። ግና አሰራሩ እንዲያ አይደለም። ይልቁንም የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር፤ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 87 (1) ላይ “የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ሚዛናዊ ተዋፅኦ ያካተተ ይሆናል” በሚለው ድንጋጌ መሰረት፤ በአዋጅ ከተቋቋመበት ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ ይህን የማመጣጠን ስራን በዕቅድ ላይ ተመርኩዞ አውን ለማድረግ ሰርቷል፤ ወደፊትም የሚሰራ ይመስለኛል—ህገ መንግስቱ ያዘዋልና።

ያም ሆኖ በእኔ እምነት መከላከያ እንደ ተቋም ስትራቴጂክ ዕቅድ ነድፎ ላለፉት 23 ዓመታት ህገ መንግስቱ በሚያዘው መሰረት የማመጣጠን ስራውን በአጥጋቢ ሁኔታ አከናውኗል፤ እያከናወነም ይገኛል። በአሁኑ ወቅት መከላከያ ሰራዊቱ የሁሉም የሀገራችን ህዝቦች መገለጫ እየሆነ መምጣቱ በተለይ ባለፉት 17 ዓመታት የተካሄደው የማመጣጠን ስራ በፈጠነ ሁኔታ መካሄዱን አመላካች ይመስለኛል።

ርግጥ የትጥቅ ትግሉ የተጀመረው ከሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል መሆኑ፣ ሰራዊቱ በአዲስ መልክ ሲዋቀር በወቅቱ አማራጭ ባለመኖሩ የኢህአዴግ ሰራዊት አብሮ እንዲቀጥል መደረጉ እንዲሁም ምንም እንኳን የደርግ ሰራዊት የነበረው አስተሳሰብ ፀረ ህዝብ ስለነበር ቢበተንም (ያም ሆኖ የተሻሉና ህዝባዊ ምልከታ የነበራቸው የደርግ ሰራዊት አባላትን የተሃድሶ ትምህርት ወስደው በአዋጅ የተቋቋመውን አዲሱን ሰራዊት እንዲቀላለቀሉ መደረጉን ያስታውሷል!)፤ አብዛኛዎቹ የትግሉ ጀማሪዎች የሰሜን ሰዎችና በኢህአዴግ ሰራዊት ውስጥ የነበሩት የተወሰኑ ብሔር ታጋዩች በጄኔራልነት ደረጃ የነበረውን መስፈርት ሊያሟሉ ችለዋል። መቼም ጡረተኛው ሌ/ጄኔራል የሰራዊቱን መመጣጠን ለማስተካከል ሲባል በኢህአዴግ ሰራዊት ውስጥ የነበሩት ታጋዩቹ ከሌሎች የሀገራችን ብሔር አባላት በአንድ እርከን ማዕረግ ዝቅ እንዲሉ ተገርጎም ጭምር የማስተካከያ ስራው ሲከናወን እንደነበር ይዘነጉታል ብዬ አላስብም—ጉዳዩ እርሳቸው ኤታማዦር ሹም በነበሩበት ወቅት መንግስት እንዲፈፀም የሰጠው የሰጠው ውሳኔ ስለነበር።

ያም ሆነ ይህ፤ አሰራሩ እንደ ጡረተኛው ሌ/ጄኔራል ፃድቃን የመሳሰሉ የሰሜን ተወላጆች ጄኔራል መኮንን ለመሆን ቅርብ እንዲሆኑ ማድረጉ አልቀረም። ሌሎችንም እንዲሁ። በእኔ እምነት፤ ይህን ሁኔታ የፈጠሩት ሁለት ምክንያቶች ይመስሉኛል። አንደኛው ምክንያት፤ ትግሉ የተጀመረው በሰሜን በኩል መሆኑ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የውትድርና ሙያ የማዕረግ ዕድገት የሚሰጠው በጊዜ ቆይታ (Seniority)፣ በተልዕኮ በአፈፃፀም ብቃትና በሌሎች ቀደም ሲል በጠቀስኳቸው መስፈርቶች ምክንያት ስለሆነ ነው። በቅርቡ የጄኔራል መኮንንነት ማዕረግ የተሰጣቸው የሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች በዚህ ሂደት ውስጥ እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትነው አልፈው የመጡ ናቸው። እናም ከመሰንበቻው የተሰጠው ማዕረግ የተቋሙን አሰራር ተከትሎ የተፈፀመ እንጂ፤ እርሳቸው እንደሚሉት ከፖለቲካ ግፊት የተነሳ አሊያም ለማስተንፈሻነት ሲባል የተሰጠ ወታደራዊ ሹመት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ተቋሙ በስትራቴጂክ ዕቅዱ ላይ ተመስርቶ ሳይዘገይ ጊዜውን ጠብቆ እያከናወነ ያለው የማመጣጠን ስራ አካል ነው ቢባል የሚያስኬድ ይመስለኛል። እናም እርሳቸው የሰጡት ሃሳብ ቅንነት የጎገለውና ሆን ተብሎ አንባቢን ለማደናገር የቀረበ ብቻ በመሆኑ ሃሳባቸውን የትዝብቴ አካል አድርጌዋለሁ።

ፃድቃን ገ/ተንሳይ (ሌ/ጄኔራል) ሁሌም የሚያቀርቧቸው ሃሳቦች እርስ በርሳቸው የሚጋጩ መሆናቸውን በወታደራዊ ሹመቱ ዙሪያ ባነሱት ምልከታቸውም ታዝቤያቸዋለሁ። በአንድ በኩል፤ የተሰጠው ሹመት ፖለቲካዊ ግፊት ያለበት ነው ይላሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ፤ በምክትል ኤታማዦር ሹምነት የሙሉ ጄኔራልነት ወታደራዊ ማዕረግ ከተሰጣቸው ሶስት ጄኔራሎች ውሰጥ አንዱን በመምረጥ “የፖለቲካ ትኩሳቱን ለማብረድ ሲባል ምርጫዬ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ናቸው” በማለት የፖለቲካ ግፊትን ደጋፊ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። በእኔ እምነት ቀጣዩ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑም ይሁኑ ቀሪዎቹ ሁለቱ ጄኔራሎች ምንም ዓይነት ችግር የለውም። ችግሩ እርሳቸው የሚያቀርቡት “በፖለቲካ ግፊት ነው የማዕረግ አሰጣጡ የተከናወነው” እያሉ በሌላ በኩል ደግሞ ራሳቸው የፖለቲካ ግፊት ሃሳቡ አራማጅ መሆናቸው ነው። በዚህ አስተሳሰባቸውስ ለይስሙላም እንኳን ቢሆን እንደምን ህገ መንግስታዊ ነኝ ሊሉ እንደሚችሉ ፈፅሞ ሊገባኝ አይችልም።

እንደሚታወቀው የምክትል ኤታማዦር ሹምነት የተሰጣቸው ጄኔራሎች፤ ጄኔራል ሰዓረ መኮንን፣ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላና ጄኔራል አደም መሐመድ ናቸው። እርሳቸው ግን ሁለቱን ብቻ (ማለትም ጄኔራል ሰዓረንና ጄኔራል ብርሃኑን) ለማወዳደር ሞክረዋል። ማወዳደር መብታቸው ቢሆንም ቅሉ፤ በአሁኑ ወቅት የአየር ኃይል አዛዥ በመሆን እያገለገሉ ያሉትን ጄኔራል አደምን ለምን ከውድድሩ ውጭ እንዳደረጓቸው ሊገባኝ አልቻለም። ጤነኛ ምልከታም አይመሰለኝም። ሆኖም የጄኔራል አደምን ግለ-ስብዕና (Profile) ለማግኘት ባደረግኩት ጥረት፤ ጄኔራሉ የሰራዊቱ ነባር ታጋይ፣ ልክ እንደ ጄኔራል ብርሃኑና ጄኔራል ሰዓረ ሁሉ፤ ጄኔራል አደምም ከታች ጀምረው፣ ክፍለ ጦርን መርተው የመጡ (እንዲያውም በእርሳቸው ጭምር በብቃታቸው የሚታወቁ) እና በአሁኑ ወቅትም የኢፌዴሪ አየር ኃይልን በመምራት ላይ የሚገኙ ለወደፊቱም ልክ እንደ ሁለቱ ጄኔራሎች ተስፋ የሚጣልባቸው የሰራዊት መሪ መሆናቸውን ተገንዝቤያለሁ።

ምንም እንኳን ጡረተኛው ጄኔራል የፈለጉትን ጄኔራል (ህጉ ከፈቀደላቸው ራሳቸውንም ጭምር ማለቴ ነው) ቀጣዩ ኤታማዦር ሹም አድርገው የመሾም ሃሳባዊ ፍላጎት ቢኖራቸውም፤ እንደ አንድ የቀድሞ የሰራዊት አመራር ምናልባት በውትድርና ሙያ ውስጥ የተሻለ አመራር ለመመደብ ቀደም ሲል ካነሷኋቸው መስፈርቶች አኳያ እንኳን ለማየት ሳይሞክሩና ፍላጎታቸውን የፖለቲካ ግፊቱን ለማስተንፈስ በማሰብ ብቻ ሃሳብ መስጠታቸው ትዝብቴን እጥፍ ድርብ አድርጎታል። እንዲያውም ሃሳባቸው ልክ እንደ ንግድ ስራ የራስን አዋጪ ስሌት ቀምሮ “አገሌ ምርጫዬ ነው” ለማለት የተነገረና አንዳንድ ሲራራ ነጋዴዎች እንደሚያስቡት አስቀድሞ ቀብድ የማስያዝ ፍላጎት ያለበት መስሎ ታይቶኛል። ያም ሆኖ ግን እኔም ሆንኩ እርሳቸው ያሻንን “ኤታማዦር ሹም እገሌ ይሁንልኝ” እያልን ብንመኝም፤ መንግስት በራሱ መስፈርት ለቦታው ይመጥናል ብሎ የሚያስቀምጠው ጄኔራል መኖሩ ግልፅ ነው።

በበኩሌ መንግስት ምናልባት ኤታማዦር ሹም የመተካት ሃሳብ ካለው፤ እንዳልኩት ቀጣዩ ሰው ጄኔራል ሰዓረም፣ ጄኔራል ብርሃኑም ሆኑ ጄኔራል አደም ቢሆኑ ምንም ችግር የለውም—መንግስት የራሱ አሰራርና እምነት ያለው ስለሆነ። ዳሩ ግን እርሳቸው ልክ ህገ መንግስቱን በመጣስ ለማስተንፈሻ ሲባል “ኮሚሽን መቋቋም” አለበት እንዳሉት ሁሉ፤ የሰሞኑን የጄኔራል መኮንንነት ማዕረግ አሰጣጥ አስታከው የውትድርና ሙያን ሳይንስን (military science) የአሰራር መስፈርቶችን ደፍጥጠው “ለማስተንፈሻነት እገሌ ኤታማዦር ይሁንልኝ” ማለታቸው በአያሌው የሚያስተዛዝብና የሚያጠራጥር ይመስለኛል። “ጠርጥር…” እንዳለው ዘፋኙ፤ እኔም ‘እውን ይህ ሃሳብ የእርሳቸው ነውን?’ የሚል የጥርጣሬ ጥያቄ እንዳጭር ምክንያት ሆኖኛል።

ታዲያ እዚህ ላይ ማንኛውም አንባቢ በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከተመሪ እስከ መሪ ድረስ ያለው የሰራዊቱ አባል፤ ምንግዜም ከራሱ በፊት ለህዝብና ለሀገር ቅድሚያ በሚሰጥ እሴት የታነፀ በመሆኑ፤ “እገሌ ይህን ክፍል ምራ” ተብሎ እንኳን ቢጠየቅ፤ የሰራዊቱ አመራርና አባል ከግል ጥቅሙና ክብሩ ይልቅ ለህዝብና ለሀገር ቅድሚያ የሚሰጥ እሴት ባለቤት በመሆኑ፤ “የለም ከእኔ ይልቅ እገሌ ይህን ክፍል ቢመራው ለተቋሙም ይሁን ለሀገር ይጠቅማል” ብሎ የሚሟገትና የተሰጠውን ቦታ የማይቀበል ኃይል ነው።  በተከታታይ የግንባታ ማዕቀፍ ውስጥ አልፎ በአሁኑ ወቅት ይህን በመሰለ ህዝባዊና ህገ መንግስታዊ አስተሳሰብ የተቃኘ ሰራዊት ባለበት ተቋምም ውስጥ፤ “የእገሌ ይሁን” ግላዊ የፖለቲካ ስሌት ‘እኔ ስላጣሁ እርሱም ይጣ’ የሚል የዜሮ ድምር የፖለቲካ ጨዋታ (zero sum game politics) ከመሆን የማይዘል እንዲሁም የሃሳቡ ባለቤት ያሉበትን የተሳሳተ ስፍራ በትዝብት ቁልጭ ብሎ እንዲታየን የሚያደርግ ከመሆን የሚዘል አይደለም።

ርግጥ ይህ የእርሳቸው ይህ “የእገሌ ይሁንልኝ” ሃሳብ በትናንት መነፅር የተቃኘ መሆኑ የሃሳባቸው ሌላኛው ጎዶሎ ክፍል ነው። እርሳቸው “ጄኔራሎቹንም ይሁን ተቋሙን አውቃቸዋለሁ” የሚሉን የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በተካሄደባቸው ከ1990 ዓ.ም እስከ 1992 ዓ.ም ድረስ በነበሩት ዓመታት ውስጥ ነው። ይህ ደግሞ እርሳቸው ሃሳባቸውን ከገለፁበት ከያዝነው 2010 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር ከ18 እስከ 20 ዓመታት ልዩነት አለው። እንደ እውነቱ ከሆነ አንድን ተቋም አሊያም ግለሰብ በድሮ ትውስታ ላይ ተመርኩዞ ብያኔ ለመስጠት ማሰብ “እንደ እኔ በትላንት በሬ እረሱ” ብሎ የመጠየቅ ያህል ይቆጠራል። በበኩሌ አሁን ያለንበትን ዘመን ለእርሳቸው ስንል ወደ ኋላ 20 ዓመት መጎተት ያለብን አይመስለኝም። በዛሬው ቴክኖሎጂ እንጂ በድሮ በሬም ልናርስ ፈቃደኞች አይደለንም። 2010 ዓ.ምን እንደ 1992 ዓ.ም አድርጋችሁ ተመልከቱልኝ ማለት፤ ስለ ስለ ጊዜ ፍጥነት፣ በጊዜ ውስጥ ስለሚለዋወጡ ጉዳዩች፣ ስለ ቴክኖሎጂ ለውጥ ስለ ተቋማዊና ግለሰባዊ አቅም እመርታ ሆን ተብሎ ላለመገንዘብ ከመፈለግ የመነጨ አተያይ ይመስለኛል።

ካልተሳሳትኩ ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ላለማገልገል የወሰኑት የዛሬ 16 ዓመት ገደማ ይመስለኛል። እርሳቸው መከላከያን በለቀቁ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ስለ ተቋሙ ተገቢው መረጃና ማስረጃ ይኖራቸዋል ብዬ አልገምትም። ይህ ሁኔታ የሚሰነዝሯቸው ሃሳቦች ወቅታዊና ምሉዕ እንዳይሆኑ የሚያደርግም ነው። ግና ብዙውን ጊዜ “በተመራማሪነት” ስማቸው ከሚነሳ ጡረተኛ ጄኔራል መኮንን ወቅታዊና ምሉዕ ያልሆኑ ሃሳቦችን መሰንዘር ተገቢ ነው ብዬ አላስብም። ትዝብት ላይም ይጥላል። በእኔ እምነት ይህና ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው የእርሳቸው ሃሳቦች፤ በአሁኑ ወቅት በህዝባዊውንና ከብረት በጠነከረ ዲሲፕሊን የሚመራውን መከላከያ ሰራዊት ስም በአሉባልታ ለማጠልሸት የሚደረገው ዘመቻ አካል ነው ብዬ አስባለሁ።

ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ የሚገኙትን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምን አስመልክተው ‘ምንም ዓይነት ብቃት ቢኖር 17 ዓመት በስልጣን ላይ መቆየታቸው ተገቢ አይደለም’ በማለት ያቀረቡት ሃሳብ ከትዝብት አልፎ እጅግ ያስደመመኝ መሆኑን ሳልገልፅ ማለፍ አልሻም። የድማሜዬ መነሻ ሌላ አይደለም— በሰራዊቱ ውስጥ የሚገኝ ተመክሮ፣ የቆይታ ዘመንና ሰራዊቱ ከሌሎች ሀገሮች ጋር በመሆን ግዳጁን ሲወጣ የሚያደርጋቸው የጎንዮሽና ቀጥተኛ መስተጋብሮች ለአንድ ወታደራዊ አመራር የብቃትና የክህሎት ማሳደጊያ ዓይነተኛ መሳሪያዎች መሆናቸውን ስለምገነዘብ ነው።

ርግጥ የመከላከያ ስትራቴጂክ አመራሮች፣ በየደረጃው የሚገኙ ተተኪ አመራሮችና አባላት እርሳቸው ለጠቀሷቸው 17 ዓመታት ሰራዊቱን በጠንካራ አቅም በመገንባት መከላከያ እንደ ተቋም በአሁን ወቅት ለሚገኝበት የላቀ የተልዕኮ አፈፃፀም ቁመና አብቅተውታል። በተቋሙ ተፈፃሚ በሆኑ እጅግ ጠንካራ የአቅም ግንባታ ስራዎች ውጤት መገለጫ የሆነው ይህ የተቋሙ ተክለ-ቁመና፤ ሰራዊቱ በሀገር ውስጥ ግዳጁም ይሁን በውጭ ሀገር የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችን በህዝባዊነት መንፈስ መወጣት እንዲችል ያደረገ፣ ለህገ መንግስቱና ህገ መንገስታዊ ስርዓቱ ታማኝ ሆኖ ባልተሸራረፈ ዴሞክራሲያዎ አስተሳሰብ እንዲመራ ያስቻለ፣ በአነስተኛ ኪሳራ የላቀ ውጤት እንዲያመጣ ብሎም በሰላም ወቅት ለሀገር የሚጠቅም የቴክኖሎጂ ሽግግር ማማ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ያስቻለው ይመስለኛል።

ታዲያ ለዚህ ውጤት መገኘት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለህገ መንግስቱ ተገዥና ታዛዥ በመሆን በመስራት ላይ የሚገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስና የስራ ባልደረቦቻቸው ሊመሰገኑ እንጂ፤ ቅንነት በጎደለው እይታ ‘ይህን ዓመት ያህል ምን ይሰራሉ?’ ሊባሉ የሚገባ አይመስለኝም። ምንም እንኳን ፃድቃን ገ/ተንሳይ (ሌ/ጄኔራል) እርሳቸው ለሰባት ዓመታት ስላገለገሉ፣ ‘ለምን ሌሎቹም እንደ እኔ አይሆኑም’ በሚል አንድምታ ሃሳባቸውን ያቀረቡ ቢሆንም፤ እርሳቸውም ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የሚፃረር ተግባር ባይፈፅሙ ኖሮ እስከ መቼ ድረስ ሰራዊቱን እየመሩ ይቆዩ እንደነበር ማንም በእርግጠኝነት መናገር የሚችል አይመስለኝም። ዛሬ እርሳቸው ከእኔ በላይ የሚያውቋቸው ሃያላን ሀገሮች የሀገራቸውን መከላከያ ሰራዊት ለማጠናከር በህጋዊና ኒዮሊበራላዊ ስርዓቱን ሳይቃረኑ በጡረታ የተሰናበቱ፣ ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉ ዕድሜ ጠገብ ጄኔራሎችን ዳግም እየጠሩ ባሉበት ወቅት፤ ‘እገሌ 17 ዓመት ስላገለገለ በቃው’ የሚል ብይን ጤናማ ሃሳብ ነው ብዬ ለመቀበል ያስቸግረኛል።

በእኔ እምነት ‘ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም 17 ዓመት መስራት የለበትም’ የሚል ህግ ያለ አይመስለኝም። ያም ሆኖ አንድ ሰው አቅምና ችሎታ እንዲሁም ክህሎት እስካለው ብሎም ‘ደከመኝ’ እስካላለ ድረስ፤ ለሀገሩ በቅንነት ቢሰራ ክፋቱ ምኑ ላይ ነው?…መንግስት ጄኔራል ሳሞራን በስራቸው ላይ እንዲቀጥሉ ያደረገበት የራሱ ምክንያት እንዳለው እየታወቀ፤ ጡረተኛው ሌ/ጄኔራል ፃድቃን ‘ለምን ከስልጣን አይወርዱም?’ የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ ያደረጋቸው ምክንያት ከእርሳቸው በስተቀር ለማንም ግልፅ ሊሆን የሚችል አይደለም።

ግና አንድ እውነታ ይታየኛል። ይኸውም ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን ከ16 ዓመት በፊት የነበራቸው የስልጣን አተያይ ዛሬም አለመቀየሩን ነው። እኔ ግን ዛሬ ነገሮች እየተለወጡ መምጣታቸውን መንገር ያለብኝ ይመስለኛል። እዚህ ሀገር ውስጥ ለስልጣን ያለው አተያይ እየተቀየረ መጥቷል። ዛሬ ስልጣን ህዝብን ማገልገያ እንጂ የግለሰቦች መገልገያ መሆኑ ቀርቷል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በፈቃዳቸው ስልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ማስገባታቸው፤ ስልጣን የግለሰቦችን ሳይሆን የሀገርን ግብና ራዕይ ለማሳካት ሲባል የሚሰጥ የስራ መደብ ስምሪት መሆኑ እየታወቀ መምጣቱን የሚያመላክት ሁነኛ አስረጅ ነው። እናም አንድ ግለሰብ በሚዲያ ላይ ወጥቶ ‘እከሌ ይብቃው፤ እንቶኔ ደግሞ ይሁን’ ስላለ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም—ወሳኙ ነገር ለህዝብና ለሀገር ጠንክሮ ከመስራቱ ላይ ነውና።

ያም ሆኖ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ 17 የአገልግሎት ዓመታት ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በማገልገል ያለፉ ውጤታማ ዓመታት ናቸው። በእኔ እምነት ጄኔራል ሳሞራ በእነዚህና ወደፊት በሚሰሩባቸው ዓመታት መንግስት የላቀ ወታደራዊ ክብርና ዕውቅና ሊሰጣቸው የሚገባ ይመስለኛል—ለህዝብና ለሀገር ያበረከቱት አስተዋፅኦ እንዲሁም ህገ መንግስቱን በፅናት በመተግበርና በማስተግበር ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ለሚገኝበት “አንቱታን” ያተረፈ ተክለ-ቁመና በመፍጠር ረገድ ከስራ አጋሮቻው ጋር ሆነው ያበረከቱትና ሊያበረክቱ የሚችሉት ብቃት ያለው አመራር ይኖራል ብዬ ስለማምን።

ዳሩ ግን ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን ከራሳቸው ውስጣዊ ፍላጎት በመነሳት ስለተናገሩ ሳይሆን፤ ጊዜው ሲደርስና መንግስት ሲፈቅድ በተቋሙ አሰራር መሰረት ጄኔራል ሳሞራም እንደ ማንኛውም የሰራዊት አባል በክብር ጡረታ ሊሰናበቱና ሊተኩ ይችላሉ። ከዚህ ውጭ ግን መንግስት እየፈለጋቸውና ስራቸውን በትጋት፣ በታማኝነት እንዲሁም በሂደት በጎለበተ አቅም እያከናወኑ ያሉትን ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ተግባራቸውን እንዳይወጡ በየሚዲያው በተሳሳተ መንገድ ማስተጋባት ከቶም ለሀገር ከማሰብ ሊመነጭ አይችልም። ዘይልቁንም ሀገርንና ሀገር ጠባቂውን መከላከያ ሰራዊት የሚያዳክም ተደማሪ ምልከታ ይመስለኛል። ለማንኛውም እኔም እንደ ዜጋ፤ ደግ ደጉን ማሰብ ቢያንስ ኪሳራ ላይ የማይጥልና አዎንታዊና ሞራላዊ ስነ ምግባር መሆኑን በመግለፅ፤ በሌ/ጄኔራል ፃድቃን ገ/ተንሳይ ሃሳቦች ላይ የነበረኝን ትዝብት በዚህ እቋጫለሁ።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy