Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሌ/ጄኔራል ፃድቃንን ታዘብኳቸው! (ክፍል አንድ)

0 835

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

ሌ/ጄኔራል ፃድቃንን ታዘብኳቸው!
ድረስ ማርዬ
(ክፍል አንድ)
ይህን ፅሑፍ እንዳሰናዳ ምክንያት የሆነኝ ሪፖርተር ጋዜጣ በቅርቡ በ‘ቆይታ’ አምዱ ላይ “አንድነታችን ሊጠናከር የሚችለው ስልጣን የሚያዝበት ስርዓት በህዝብ የሚታመን ሲሆን ነው” በሚል ርዕስ የቀረበ ቃለ ምልልስ ነው። የሪፖርተሩ ቋሚ አምደኛ ዮሐንስ አንበርብር ቃለ ምልልሱን ያደረገው፤ ከደርግ ውድቀት መባቻ ጀምሮ ለሰባት ዓመታት ያህል የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትን በጠቅላይ ኤታማዦር ሹምነት ያገለገሉትንና ኋላ ላይም ከህወሓት/ኢህአዴግ ለሁለት መሰንጠቅ ጋር ተያይዞ፤ እንደ አንድ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራር (ለዚያውም እንደ የሰራዊት መሪ) ህገ መንግስቱ በአንቀፅ 87 (5) ላይ “መከላከያ ሰራዊቱ ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነፃ በሆነ አኳኋን ያከናውናል” የሚለውን ድንጋጌ በመተላለፍ የፖለቲካ ወገንተኝነት ታይቶባቸዋል በሚል “በአንጀኝነት” ተፈርጀው ከሰራዊቱ በጡረታ እንዲሰናበቱ የተደረጉት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገ/ተንሳይ ናቸው።
የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ እንደ ማንኛውም ዜጋ ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን በተለያዩ ወቅቶች በህትመት ሚዲያዎች የሚያቀርቧችውን ትንታኔዎች እከታተላለሁ። አንዳንዶቹን ሃሳቦች ገንቢ በመሆናቸው አከብራቸዋለሁ፤ እጋራቸዋለሁም። ሆኖም አብዛኛዎቹ ሃሳቦቻቸውን ግን ለመቀበል ይከብደኛል። እንዲያውም እነዚህን ሃሳቦች በአርምሞ ስመለከታቸው፤ ትናንት ወጣትነታቸውን ሰውተው፣ ሞትን ከመጤፍ ካለመቁጠር ‘ዱር ቤቴ’ ብለው ለህዝቦች ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ጥያቄዎች መስዋዕት ለመሆን ቆርጠው በመሰለፍ ደርግን ከተፋለሙ ታጋይና ኋላ ላይም የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ከነበሩ ግለሰብ የሚሰነዘሩ መስለው አይታዩኝም። እንደ እውነቱ ከሆነ ምንም ነገር ባለበት ቦታ አይቀጥልም—የሃሳቦች መለዋወጥ መኖሩ ነባራዊ ነው። በዚህ ረገድ ማንም ሰው ጥያቄ ያነሳል ብዬ አልገምትም። አንድ ሰው ትናንት የሰማውን ዛሬ በማይደግምበት ፈጣን ዓለም ውስጥ እየኖረ፤ እንቅስቃሴ እንደሌለው ኩሬ (Stagnant) ሆኖ ሊቆም አይችልም። ዳሩ ግን እንቅስቃሴው መሰረታዊ እምነትን የሚሸረሽሩ ሃሳቦች ሲቀርቡበት፣ ግላዊነትን ማዕከል ሲያደርግና አንዳንዴም ሃሳቦች የተምታቱና አንባቢን ለማደናገር ተብለው ሲቀርቡ፤ “ለምን?፣ እንዴት?፣ ወዴት?…ወዘተ.” ብሎ መጠየቅ ይገባል፤ ያስፈልጋልም።
ርግጥ የፃድቃን ገ/ተንሳይ (ሌ/ጄኔራል) በተለይ ትንታኔ ነክ ሃሳቦች ገሚሶቹ በግል ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ፣ አንዳንዶቹ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑና መፍትሔ ያልሆኑ መፍትሔዎች የታጨቁባቸው ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ደግሞ ምናልባትም የሃሳቦቹ ባለቤቶች እርሳቸው ሳይሆኑ “ሌሎች” ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ እንዳስብ የሚያደርጉኝ ናቸው። ይህን የምለው እርሳቸው በህትመት ሚዲያና በአንዳንድ ድረ ገፆች አማካኝነት የሚለቋቸውን ትንታኔዎችና ቃለ ምልልስ ዙሪያ በግሌ የተሰማኝን ጥቅል እይታ ለመግለፅ ያህል እንጂ፤ የፅሑፌ ዋነኛ ማጠንጠኛ በሰሞነኛ ቃለ ምልልሳቸው መሆኑን ውድ አንባቢያን እንዲገነዘቡልኝ እሻለሁ።
እንዳልኩት በዚህኛውም ቃለ ምልልሳቸው ላይም በንድፈ-ሃሳብ (theory) እና በትግበራ ደረጃ የምስማማባቸው ሃሳቦች ይኖራሉ። በተለይም ማናቸውንም ጉዳዩች በህገ መንግስቱ መሰረት መከናወን እንዳለባቸው፣ አንድን ብሔር በመለየት የሚከናወኑ የጥቃት ተግባሮች ፈፅሞ መቆም እንደሚኖርባቸውና የፀጥታ ሃይሎች ይህን ችግር ማስቆም እንደሚገባቸው እንዲሁም አንድነታችንን ማጠናከር እንደሚገባን ያነሷቸው ነጥቦች ለክፉ የሚሰጡ ሆነው አላገኘኋቸውም። በአንፃሩ ደግሞ፤ የሀገራችንን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት ተብለው ከህገ መንግስቱ ውጭ በሞራል ግዴታና ኃላፊነት እንዲከናወን የተጠየቁና ህገ መንግስቱን የሚቃረኑ ብሎም የሚጥሱ፣ ይተግበሩ ቢባል እንኳን ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ አኳያ መያዣና መጨበጫ የሌላቸው ጉዳዩች እንዲሁም ከሚዛናዊ ዕይታ በመነሳት የተሰጡ ድምዳሜዎች አይደሉም ብዬ የማምንባቸውን ጉዳዩች መኖራቸውን ታዝቤያለሁ። እርሳቸውም በቃለ ምልልሱ ላይ “የምሰጠው አስተያየት ጉድለት የለውም ብዬ አላምንም” ብለው ባቀረቧቸው ሃሳቦች ላይ እምነት እንደሌላቸው እንደነገሩን ሁሉ፤ ይህ በዚህ ፅሑፍ በማልስማማባቸው ትላልቅ ጉድለቶች ዙሪያ ትዝብቴን አስቃኛለሁ።
እውነትም ጡረተኛውን ጄኔራል መኮንን የተነሳሁበትን ነጥብ ያስረዱልኛል ባልኳቸውና በውስጣቸው በርካታ ጉዳዩች በታጨቁባቸው ሁለት አንኳር ጉዳዩች ታዝቤያቸዋለሁ። አንደኛው፤ አሁን ያለውን የሀገራችንን ተጨባጭ ችግር ለመፍታት በፕሬዚዳንቱ ፅህፈት ቤት ስር መቋቋም ይኖርበታል ያሉትን “ገለልተኛ ኮሚሽን”ን የሚመለከተው አስገራሚ ሃሳብ ነው። ሁለተኛው ደግሞ፤ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 71 (6) መሰረት፤ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለ61 የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛና ጄኔራል መኮንኖች ከብርጋዲየር ጄኔራልነት እስከ ሙሉ ጄኔራልነት ድረስ በሰጡት ወታደራዊ የማዕረግ ዕድገት ያቀረቧቸው ትክክለኛ ያልሆኑና በቀናነት ያልቀረቡ እሳቤዎችን የሚዳስስ ነው።
ጡረተኛው ሌ/ጄኔራል ፃድቃን ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ወዲህ እንደተዳከመ በነገሩን የፕሬዚደንቱ ፅህፈት ቤት አማካኝነት “ገለልተኛ ኮሚሽን” በማቋቋም በሀገራችን ውስጥ የተፈጠረውን የፖለቲካ ቀውስ ልናስተነፍሰው እንችላለን ብለው ያምናሉ። ይህ “ኮሚሽን” በፓርላማው የሚቋቋም ሆኖ፤ እስከ ምርጫ 2012 ድረስ የሚቆይ ነው። ህዝቡም ቀልቡን በዚህ ኮሚሽን ላይ ያደርጋል ሲሉም ነግረውናል። ኮሚሽኑ ነፃ ሆኖ የሚሰራ፣ ዋና ዓላማውም ከሁለት ዓመት በኋላ የሚደረገው ምርጫ ነፃና ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን የማስተካከል ያከናውናል ብለው ያምናሉ። ታዲያ ይህን የ“ገለልተኛ ኮሚሽን” ሃሳብ ሲያቀርቡ አንዳንድ የኢህአዴግ ባለስልጣናት “የሽግግር መንግስት ይመስረት እያልክ ነው” በማለት ሃሳቡን አጣመው እንደሚመለከቱባቸው አልሸሸጉም። “እኔ ግን እንደዛ አላልኩም፤…ሆኖም (የሽግግር መንግስት ጉዳይ) ህገ መንግስታዊ መሰረት የሌለው ሃሳብ ነው” በማለት የኮሚሽኑ ተግባር ግን ህገ መንግስታዊ እንደሆነ አስመስለው በገደምዳሜው ሊነግሩን ሞክረዋል። በጄ! ማለፊያ ነው።
ሆኖም ጡረተኛው ሌ/ጄኔራል ያነሱት “ገለልተኛ ኮሚሽን” ለማንም የሚገባ ጉዳይ አይደለም። ርግጥ በሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንቱ ስር የፕሬዚዳንት ፅሀፈት መኖሩ ግልፅ ነው። በእኔ እምነት ይህ ፅህፈት ቤት የሚያከናውነውና ከህገ መንግስቱ ምስረታ ማግስት ጀምሮ እየፈፀማቸው የመጣቸው በህገ መንግስቱ ከአንቀፅ 69 ጀምሮ እስከ አንቀፅ 71 ድረስ የተዘረዘሩትንና ለሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት (ርዕሰ ብሔር) ተለይተው የተሰጡ ስልጣንና ተግባሮችን ነው። አንድ ፅህፈት ቤት የሚወክለው የተሰጠን ተግባርና ሃላፊነት ብቻ ስለሆነ። እናም ህገ መንግስቱ ላይ ያሉት የፕሬዚዳንቱ ስልጣንና ሃላፊነት የስልጣኑ ሉዓላዊ ባለቤት በሆኑት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እስካልተሻሩ ወይም እስካልተቀየሩ ድረስ፤ በዶክተር ነጋሶ ይሁን በቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዩርጊስ አሊያም በአሁኑ ርዕሰ ብሔር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የስልጣን ጊዜያት እንዴት ሊዳከሙ እንደሚችሉ ግልፅ አይደለም።
በህገ መንግስቱ አንቀፅ 71 የተዘረዘሩት የፕሬዚዳንቱ ስልጣንና ተግባር የሚገልፁት፤ የህዝብ ተወካዩችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶችን ዓመታዊ የጋራ ስብሰባ ስለ መክፈት፣ በህገ መንግሰቱ መሰረት የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ያፀደቃቸውን ህጎችንና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በነጋሪት ጋዜጣ ስለ ማወጅ፣ ሀገሪቷን በውጭ ሀገራት የሚወክሉትን አምባሳደሮችና ሌሎች መልዕክተኞችን በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ስለ መሾም፣ የውጭ ሀገር አምባሳደሮችንና የልዩ መልዕክተኞችን የሹመት ደብዳቤ ስለ መቀበል፣ በህግ መሰረት ኒሻኖችንና ሽልማቶችን እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በህግ በተወሰነው መሰረት ከፍተኛ የውትድርና ማዕረጎችን ስለ መስጠት እና በህግ መሰረት ይቅርታ ማድረግ ናቸው። ታዲያ ከእነዚህ ስልጣንና ተግባሮች ውስጥ የትኞቹ ናቸው የተዳከሙትና ሳይተገበሩ የቀሩት?፣ ከተዳከሙስ መቼና እንዴት ነው ሊዳከሙ የቻሉት?… ጡረተኛው ሌ/ጄኔራል በዚህ ረገድ ያሉት ነገር ስለሌለ እኔም “ለማለት ብቻ የተባለ” ብዬ ላልፈው አልችልም። በእኔ እምነት የፕሬዚዳንቱ ፅህፈት ቤት በተሰጠው ህገ መንግስታዊ ስልጣንና ተግባርና መሰረት የተጠናከሩ ስራዎችን እያከናወነ እንጂ እየተዳከመ የመጣ አይደለም። ሌሎቹን ተግባሮች ትቼ በቅርቡ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ታራሚዎች በህጉ መሰረት በይቅርታና በምህረት እንዲለቀቁ መደረጉን ባነሳ እንኳን፤ ፅህፈት ቤቱ ምን ያህል ስራውን ሀገራዊ መግባባትን በሚያጠናክር መልኩ እየፈፀመ ስለመሆኑ አንድ ማሳያ ማቅረብ እችላለሁ። ታዲያ ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን ከቶ ምን እያሉን ይሆን?…ርግጥ በዚህ ድፍን ያለና ሆን ተብሎ አንባቢን ለማምታታት በተነገረው የእርሳቸው አባባል መታዘብ ያንሰኝ ያንሰኛል ብዬ አላምንም።
እንደ እውነቱ ከሆነ፤ የፕሬዚዳንቱ ፅህፈት ቤት ሀገር ፖለቲካዊ ቀውስ ሲያጋጥማት ኮሚሽን አቋቁሞ “ማስተንፈሻ ገለልተኛ ኮሚሽን ያቋቁማል” የሚል ነገር በህገ መንግስቱ ላይ ተፈልጎ አይገኝም። የለምና። ሌ/ጄኔራል ፃድቃን ግን ፅህፈት ቤቱ ሞራላዊ ኃላፊነት አለው ይሉናል። ግና ህገ መንግስትን እንደምን በሞራላዊ ሃላፊነት ተክቶ መቀየር እንደሚቻል ለእርሳቸውም ግልፅ የሚሆን አይመስለኝም። በአንድ በኩል፤ በቃለ ምልልሳቸው ላይ ህገ መንግስቱን ብቻ ተከትለን መሄድ ይገባል የሚሉን ሰው፤ አሁን ደግሞ ህገ መንግሰቱን በሞራላዊ እሳቤ መተካት አለብን እያሉን ነው— ሁለት እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ሃሳቦች። ህገ መንግስቱ ተሸርሽሮ የህዝብ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነት ሲነጠቅ ሊመጣ የሚችለውን ቀውስ እንዲሁም የህግና ስርዓት መፋለስ ችግሮችን ብሎም ሌሎች ሀገራዊ ኪሳራዎችን፤ ለእኚህ ከዚህ ቀደም ታጋይ ለነበሩ፣ ህገ መንግስቱ ሲፀድቅ የእርሳቸው ድርሻ ይኖራል ብዬ ለምገምታቸው፣ የደቡብ ሱዳን ሰራዊት “አማካሪ” ለነበሩት እና ከሁለትና ከሶስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ “በአንጃነት” ከተፈረጁት አንዳንድ ግለሰቦች ጋር በመሆን ‘የሁከት ጊዜ ተንታኝ’ ሆነው ብቅ ላሉት ግለሰብ ለመንገር ትንሽ የሚከብደኝ ይመስለኛል። እኔ እርሳቸውን እንደታዘብኳቸው ሁሉ ውድ አንባቢዎቼ ደግሞ እኔንም ሊታዘቡኝ ይችላሉና።
ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን “ገልልተኛ ኮሚሽኑን” አስመልክተው “አንዳንድ የኢህአዴግ ባለስልጣናት የሽግግር መንግስት ይመስረት እያልክ ነው ይሉኛል። እኔ ግን እንደዚያ አላልኩም። (የሽግግር መንግስት ምስረታ ጉዳይ) ህገ መንግስታዊ አይደለም” ቢሉም ቅሉ፤ በእኔ እምነት ግን የኢህአዴግ ባለስልጣናቱ ያሉት ትክከል ይመስለኛል—እርሳቸው እንዲመሰረት በሚፈልጉት “ገለልተኛ ኮሚሽን” እና የሽግግር መንግስት መካከል የስም እንጂ የግብር ልዩነት የለምና። ነገርዬው የሀገራችን አርሶ አደር “ስልቻም ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎም ስልቻ” እንደሚለው ዓይነት ነው። የእርሳቸው ሃሳብ-ወለድ “ኮሚሽን” አሁን ያለውንና በሀገሪቱ የምርጫ ህግ መሰረት ተወዳድሮ አሸንፎ ሀገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘውን ገዥ ፓርቲና ስራ አስፈፃሚውን አካል (መንግስትን) ተክቶ ለሁለት ዓመት ማናቸውንም ተግባራት እንዲያከናውን ይሻሉ። ፓርላማውም የነበረውን ስራ አስፈፃሚ ሽሮ የሌ/ጄኔራል ፃድቃንን “ኮሚሽን” አፈፃፀም ይቆጣጠራል ማለት ነው። ይህ በእውነቱ ለእኔ ሽግግር መንግስት ብቻ አይደለም— የህዝብን ድምፅ በድምፅ አልባ መፈንቅለ መንግስት ለመቀማት ማሰብ ጭምርም እንጂ።…ኧረ ለመሆኑ የሽግግር መንግስት ከዚህ የተለየ ምን ተግባር ያከናውናል? የሽግግር መንግስት ግብሩ ቋሚ መንግስት እስኪመሰረት ድረስ መንግስታዊ ስራዎችን መፈፀም አይደለምን?…እናስ ‘ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የሚደፈጥጠው የእርሳቸው “ገለልተኛ ኮሚሽን” እንደምን ህገ መንግስታዊ ሊሆን ይችላል?’ ብለን ብንጠይቃቸው፤ እውነት…እውነት እላችኋለሁ ምላሹ የሚያጥራቸው ይመስለኛል። ምክንያቱም እርሳቸው የሚያልሙት “ኮሚሽን” ህገ መንግስቱ ፈፅሞ የማያውቀው ስለሆነ ነው። ኢ-ህገ መንግስታዊ ስለሆነ ነው። ያም ሆነ ይህ ግን፤ እርሳቸው እያሰቡት ያሉት ነገር በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የሚያውቁትን የድሮውን የሽግግር መንግስት በስም ቀይረው እውን ማድረግ ከሆነ፤ ያ ወቅት ፋይሉ ተዘግቶ የኢፌዴሪ መንግስት ከተመሰረተ 23 ዓመታት ማለፋቸውን ከትዝብት ጋር ላስታውሳቸው የሚገባኝ ይመስለኛል።
እንደ ፃድቃን ገ/ተንሳይ (ሌ/ጄኔራል) ዓይነት “ተመራማሪና ለሀገር አሳቢ” ግለሰብ፤ ለማቋቋም የሚፈልገው “ኮሚሽን” የችግር ማስተንፈሻ እንዲሆን የሚሻ አይመስለኝም ነበር። ግና ተሳስቻለሁ። ርግጥ እርሳቸውም በቃለ ምልልሳቸው ‘የለም ተሳስተሃል’ ያሉኝ ይመስለኛል—‘ኮሚሽኔ እንደ ህመም ማስታገሻ (Pain killer) ያገለግላል’ ብለውናልና። ሆኖም የህመም ማስታገሻ በቋሚው ህመም ምክንያት የተፈጠሩ ሌሎች ተቀፅላ ምልክቶችን ከማጥፋት በስተቀር በሽታውን ዘላቂነት ባለው ሁኔታ እንደማይፈውስ የተገነዘቡት አልመሰለኝም። አሊያም ሊገነዘቡት አልፈለጉም። ርግጥ ዋናውን በሽታ ለመፈወስ የህመሙን ትክክለኛ መድሃኒት እንጂ፣ በበሽታው ምክንያት ለተፈጠሩ የራስ ምታት ዓይነት በሽታዎች ማስታገሻን ማዘዝ ማለት፤ ዝንቧን ከሚስቱ ግንባር ላይ አባርራለሁ ብሎ ባለቤቱን በያዘው መዶሻ ግንባሯ ላይ መትቶ እንደ ገደላት አባወራ ዓይነት ጅልኛ እሳቤ ይመስለኛል።
ይህን የጡረተኛው ጄኔራል መኮንንን “የህመም ማስታገሻ” (Pain killer) ሳስበው ልጅ እያለሁ የሰፈራችንን የመንደር መርፌ ወጊን ተግባር እንዳስታውስ ያደርገኛል—“ከበደ ሀኪሙ” እያልን የምንጠራቸውን ግለሰብ። “ከበደ ሀኪሙ” የባህል አዋቂም ዘመናዊ ሃኪምም አይደሉም። ትልቅ ቦርሳ፣ ግን በውስጡ አንድ ሲሪንጋና ጥቂት መርፌዎች እንዲሁም የተወሰኑ ብልቃጦችን ቤታቸው አስቀምጠው የሚያክሙ የመንደር መርፌ ወጊ ናቸው። የመንደራችን ሰው ከእርሳቸው ምን እንዳየ ባላውቅም—ራሱን ሲያመው፣ ሆዱን ሲቆርጠውም ይሁን ውጋት ቀስፎ ሲይዘው ወደ “ከበደ ሀኪሙ” ጋ መሮጥ ይወዳል። ከቤም የዋዛ ሰው አልነበሩም—ለሁሉም የበሽታ ዓይነቶች ሶስት ብር እየተቀበሉ፤ ሆዱን ለቆረጠውም፣ ብርድ ብርብ ላለውም፣ ቁርጠት ላሰቃየውም ይሁን ውጋት ቀስፎ ለያዘው ያንኑ መድሃኒት በአንድ መርፌ እየመላለሱ ይወጋሉ። አንዳንዴም ዳጎስ ያለ መቀመጫ ያላቸው የመንደራችን ባልቴቶች ታመው ወደዚያው ሲያመሩ መርፌውን ሰክተው በዚያው በሃሳብ ጭልጥ ብለው ይጠፋሉ እየተባሉ በራሳቸው ታካሚዎች የሚታሙት ጋሼ ከቤ፤ በአንድ መርፌና በአንድ ዓይነት መድሃኒት ስንቱን የመንደራችንን ሰው ህመሙን እንዳስታገሱለት ወይም እንዳባባሱበት ቤቱ ይቁጠረው።…
በእኔ እምነት፤ የጡረተኛው ጄኔራል ሃሳብም በሽታውን ሳይገነዘቡ በማስታገሻነት “ገለልተኛ ኮሚሽን” እናቋቁም ማለታቸው፤ እንደ መንደራችን መርፌ ወጊ “ከበደ ሀኪሙ” ዓይነት አሰራርን ከመፈለግ የመነጨ ይመስለኛል—ልክ ጋሽ ከቤ የህክምናን ሙያ እንደደፈጠጡት ሁሉ፤ እርሳቸውም ህገ መንግስቱንንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በመደፍጠጥ ህመም አስታጋሽ “ኮሚሽናቸው”ን እያለሙ ነውና። ታዲያ እንዲህ ያለውን “የከበደ ሀኪሙን” አሰራር የትኛውም የሀገራችን ብሔር፣ ብሔረሰብም ይሁን ህዝብ ፈፅሞ ሊቀበለው የሚችል አይመስለኝም—የተነጣጠረው በሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነቱ ላይ ስለሆነ።
ያም ሆነ ይህ፤ በአንድ ሀገር ውስጥ የህዝብን ጥያቄ ተከትሎ የሚደረግ የሪፎርም ሂደት ጥገናዊና ለማስተንፈሻ ብቻ የሚደረግ ለውጥን የሚያመጣ መሆን የለበትም—ዘላቂና ስር ነቀል (Radical) ለውጥን እንጂ። ከዚህ አኳያ፤ ገዥው ፓርቲና መንግስት በሀገራችን ህዝብ የተጠየቁትን ትክክለኛ ጥያቄዎች ለመመለስ ለህዝቡ ቃል ገብተው እየሰሩ ነው። እንደ ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን “ጊዜያዊ ማስተንፈሻ” ሳይሆን ዘላቂና የህዝቡን ችግር ስር ነቀል በሆነ መንገድ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል በጥናት ላይ የተመሰረተ ፍኖተ ካርታ (road map) ያለው ሪፎርም አዘጋጅተው ወደ ተግባር ገብተዋል። በሪፎርሙ መሰረት ችግሩን ሊፈታ የሚችል እንደ ፓርቲዎች ጥልቅ ግምገማና ሹም ሽር፣ በመንግስት ስራ ውስጥም ትክክለኛውን መንገድ የተከተለ የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ ለመፍጠር እየተደረገ ያለው ጥረት የስር ነቀል መፍትሔ ሰራዎች አካል ይመሰሉኛል። እንዲሁም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በሀገራችን ላይ ያንዣበበውን አደጋ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመቀልበስ በሪፎርሙ መሰረት የመፍትሔው አካል በመሆን ስልጣናቸውን ለመልቀቅ መወሰናቸው የዚሁ ተግባር ማሳያ ነው። ይህን ፅሑፍ እስካሰናዳሁበት ድረስ ለፓርላማ ያልቀረበውና ሰሞኑን በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሌላኛው ትክክለኛ የችግሩ መፍትሔ አካል ነው ብዬም አምናለሁ። ይህ ደግሞ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 93 ላይ በግልፅ የተቀመጠ ህገ መንግስታዊ አሰራር መሆኑን ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን ይስቱታል ብዬ አልገምትም።
ፃድቃን ገ/ተንሳይ (ሌ/ጄኔራል) በሚያልሙት “ኮሚሽን” አማካኝነት በውጭ ያሉ ተቃዋሚ ድርጅቶች በነፃነት እንዲሳተፉ ድርድር ተደርጎ ጥሪ ሊደረግላቸው ይገባል ብለውናል። በእኔ እምነት ይህና ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውና “በኮሚሽኑ” ላይ ያነሷቸው ነጥቦች ኢ-ህገ መንግስታዊ ናቸው። ምክንያቴን እንደሚከተለው አስረዳለሁ። እርሳቸው ‘በውጭ ያሉ ተቃዋሚዎች’ የሚሏቸው እንደ አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ ኦነግና ኦብነግ የመሳሰሉት በሀገራችን ጠላቶች ሳንባ የሚተነፍሱ ተቃዋሚዎች ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የጠብ-መንጃ አፈሙዝን ጨምሮ በማናቸውም መንገድ ለመጣል እንደሚሰሩ በይፋ ያወጁ ናቸው። የሀገራችን ህዝቦች እንደ ራሴዎችን ባቀፈው ፓርላማም በአሸባሪነት የተሰየሙ ናቸው። ጥቂቶቹ ደግሞ “ሸንጎ…ምንትስ ነን” እየተባባሉ በሚያስቅ ሁኔታ አሜሪካና አውሮፓ ካፌዎች ውስጥ ቁጭ ብለው ‘የሽግግር መንግስት መስርተናል’ የሚሉ ጉደኞች ናቸው—መጥተው ስልጣን የሚይዙት በቦሌ ይሁን በባሌ ባይታወቅም።
ለእኔ እነዚህን ተቃዋሚዎች መጋበዝ ማለት ከማያውቁት አውድ (context) ጋር በግድ ለመደባለቅ መሞከር ነው። በሌላ ቋንቋ፤ አንድን ትልቅ ብሎን በትንሽ አቃፊው ውስጥ በሃይል ቀጥቅጦ ለማስገባት የመሞከር ያህል ይመስለኛል። ሰላማዊነትን የሚያቀነቅነው የሀገራችን ተጨባጭ ምህዳር ለእነዚህ ሃይሎች ይመቻቸዋል ብዬ አላስብም። እነዚህን ሃይሎች በሀገራችን እየተካሄደ ያለው ሰላማዊና ህጋዊ የፖለቲካ ማህበረሰብ (political society) አካል አይደሉም። ኢ- ህገ መንግስታዊ ናቸው። ርግጥ አሸባሪዎቹም ይሁኑ “የሽግግር መንግስት መስርተናል” ባይ ኮሜዲያኖቹ ጥፋታቸውን አምነውና ተፀፀተው ህዝቡን ይቅርታ በመጠየቅ ሀገር ቤት መጥተን በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን ብለው ከወሰኑ፤ በህጉ መሰረት እንደ ማንኛውም ሀገር በቀል ፓርቲ በህገ መንግስቱ ጥላ ስር ሆነው ተወዳድረው የህዝቡን ይሁንታ ካገኙ የመንግስት ስልጣን ሊይዙ የማይችሉበት ምክንያት የሚኖር አይመስለኝም። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ግን፤ እነዚህ ሃይሎች የራሳቸው አጀንዳ የሌላቸውና ለባዕዳን ሃይሎች በተላላኪነት የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም ፖለቲካን ለህዝብ ካለው ጠቀሜታ አኳያ ሳይሆን፤ በገንዘብ አስገኚነቱ የሚመዝኑና ስራውንም የዕለት እንጀራቸው አድርገው የያዙ የሌላ ዓለም ሰዎች ናቸው። ለእነርሱ ተቃዋሚነት እንደ ማንኛውም ሸቀጥ ንግድና ንግድ ብቻ ነው።
በመሆኑም የጡረተኛው ጄኔራል መኮንን ምናባዊ “ኮሚሽን” በመጀመሪያ እነርሱን ለመጥራት ህገ መንግስቱን ሊጥስ የግድ ይለዋል፣ ሲቀጥል ደግሞ እነርሱን በአሸባሪነት የፈረጃቸው ፓርላማ መፍረስ ይኖርበታል አሊያም አሸባሪነታቸውን ማንሳት አለበት ማለት ነው። ይህ ደግሞ በተለያዩ ፖለቲካዊና ህጋዊ ጉዳዩች ሳቢያ የሚሆን አይመስለኝም። በአጭሩ የሌ/ጄኔራል ፃድቃን ኢ-ህገ መንግስታዊ ሃሳብ-ወለድ “ኮሚሽን” ጥሪውን ሊያደርግ የሚችለው፤ ህገ መንግስቱን ደፍጥጦና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ተቃርኖ ነው። ይህ ደግሞ፤ የጄኔራል መኮንኑ “ገለልተኛ ኮሚሽን” የማስተንፈሻነት ምክረ-ሃሳብ (Proposal) ችግር ፈቺ ሳይሆን ችግር ፈጣሪ፣ ምናልባትም ‘እኔም የመፍትሔው አካል ነኝ’ በማለት በግል ዕይታ ስልጣንን አጮልቆ የመመልከት ፍላጎትን የያዘና የአንዳንድ ኒዮ ሊበራል ሃይሎች ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ አስተሳሰብ ትክክለኛ ግልባጭ (carbon copy) ሆኖ የተነገረ ሳይሆን የሚቀር አይመስለኝም።
ለነገሩ ይህ ህገ መንግስቱን ያለማከበር ጉዳይ እርሳቸው የዛሬ 16 ዓመታት ገደማ ሲፈፅሙት የነበረ ነው። ዛሬ የተፈጠረ አዲስ ክስተት አይመስለኝም። ዳሩ ግን እርሳቸው ለመፍጠር እየሞከሩ ያሉት አዲሱ ጉዳይ በህገ መንግስቱ እየማሉ ከላይ በጠቀስኳቸው ኢ-ህገ መንግስታዊ ኩነቶችን ገቢራዊ እናድርግ በማለት መልሶ ህገ መንግስቱን ከጀርባው በጦር የመውጋት ጨዋታ ይመስለኛል። ይህ ኢ-ህገ መንግስታዊ ጨዋታም በእኔ በትንሿ አቅም እርሳቸውን በትልቁ እንድታዘባቸው አድርጎኛል። ያም ሆኖ ሌ/ጄኔራል ፃድቃን መንግስት ለኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛና ጄኔራል መኮንኖች የሰጠውን የማዕረግ ዕድገት አስመልክተው ባነሷቸው ሃሳቦች ይህን ትዝብቴን እንድቀይር ያደርጉኝ ይሆን?…እስቲ ጉዳዩን በክፍል ሁለት ፅሑፌ ላይ አብረን ለመመልከት ወደዚያው እንዝለቅ።…

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy