ሕግ ተጥሶ የሚለቀቅ እስረኛ…
ደስታ ኃይሉ
አገራችን ውስጥ በጥፋታቸው ሳቢያ በወንጀል ተከስሰው በህግ ጥላ ስር የበሩት እስረኞች እየተለቀቁ ያሉት ህግና ስርዓት ተጥሶ ሳይሆን የአገሪቱን ህጎች በመንተራስ ነው። ምህረትም ይሁን ይቅርታ እየተሰጠ ያለው መስፈርቶች ወጥተው በዚያው መሰረት ነው። የሚጣስ ወይም ይደር ተብሎ የሚታለፍ ህግ የለም።
ሆኖም አንዳንድ ወገኖች ሁሉም ታሳሪ ይለቀቅ መስፈርቶቹን ያላሟላ ታሳሪ ሊለቀቅ አይችልም። ስእንዲህ ዓይነት ህግንና ስርዓትን የሚጻረር አካሄድ መፈፀም አይቻልም። ህግና ስርዓት በየጊዜው እየተሸረሸሩ በሄዱ ቁጥር የህግ የበላይነትን ለማስከበር አደገኛ ሁኔታ ይፈጠራል። ይሁን እንጂ በህጉ መሰረት የተቀመጠውን መስፈርት ያሟላ ማንኛውም እስረኛ መለቀቁ ግን አይቀርም። ህግና ስርዓትን ግን መቼም ለድርድር ማቅረብ አይገባም።
የዴሞክራሲው ግንባታም ይሁን የህግ የበላይነት ጉዳዩች በአገራችን ውስጥ ለድርድር የማይቀርቡ ናቸው። ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታዎች እንዲሁም ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች አኳያ እየታዩ ላለፉት 26 ዓመታት ተግባራዊ እየተደረጉ የመጡ ፅንሰ ሃሳቦች ናቸው።
በየትኛውም አገር ውስጥ ዴሞክራሲ በማህበረሰቡ ዕይታ የተቃኘ በመሆኑ “ለሰናይ” ምግባሮች ቅድሚያ ይሰጣል—ተከታዩ ማህበረሰብ የሚፈልገውን የሞራል ፈርጅ ካልወገነ ሊከተለው የሚችለው ሊቅም ይሁን ደቂቅ የለምና።
በመሆኑም ተደራዳሪ ወገኖች ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ‘ሰናይ’ መንገድ መከተል ብቻ ሳይሆን መንገዱንም ለህብረተሰቡ በማሳየት ፋና ወጊ መሆንም አለባቸው። አሊያ ግን ሁሉንም ተግበራት በአንክሮ በሚከታተለው ህዝብ ዓይን ውስጥ ለትዝብት መዳረጋቸው የሚቀር አይመስለኝም።
እርግጥ ህዝብ ሁሉንም ነገር የሚያይ፣ ሚዛናዊና ለየትኛውም ወገን የማይወግን በመሆኑ፤ ማን ምን እንደሚሰራ፣ የትኛው ወገን ሀገሩንና እርሱን ማዕከል አድርጎ እንደተንቀሳቀሰ፣ የትኛውስ ከዚህ ውጭ ሆኖ ራሱን ብቻ በማዳመጥ እንደተንቀሳቀሰ ያውቃል። እናም በእንቅስቃሴው ልክ ይሰፍረዋል። በሰፈረው ልክም ለህግ የበላይነት በመቆም አጥፊዎች ህግ ፊት እንጢቀርቡ ያደርጋል።
እንደሚታወቀው ሁሉ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የህግ የበላይነት ሊሸራረፍና ህገ-ወጦች እንዳሻቸው የሚሆኑበት አውድ የለም። ይህ የህግን የበላይነት የማረጋገጥ ጉዳይ በመከባበበርና በመቻቻል ላይ የተመሰረተውን ፌዴራላዊ ሥርዓቱ የመሰረቱት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔሰቦችና ህዝቦች ያስገኙት ነው። የአገራችን ህዝብ ላለፉት 26 ዓመታት የህግ የበላይነትን ፅንሰ-ሓሳብ የተገነዘበና የሚያጋጥሙትን ነባራዊ ችግሮችን በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ እየፈታ ዛሬ ላይ የደረሰ ነው።
የህግ የበላይነት መብት ሰጪና ነሺ በጉልበታቸው የሚተማመኑ ኃይሎች ይሆናሉ። ጉልበተኞቹም ልክ እንደ ሁሉም እስረኞች ይፈቱ እንደሚሉት ወገኖች ሌሎች ዜጎችን እንዳሻቸው ለማድረግ መሻታቸው አይቀሬ ነው።
እንኳንስ ዜጎችን ቀርቶ፣ ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ለማድረግ የሚተጉ የፖሊስና የፀጥታ ኃይሎችን ጭምር በአጉራ ዘለለልነት እስከመግደል ሊደርሱ ይችላሉ። ለዚህም የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ህገ ወጦች ፖሊስንና የፀጥታ ሃይሎችን መግደላቸውን የኢፌዴሪ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለፓርላማ ካቀረበው ሪፖርት መገንዘባችንን እናስታውሳለን።
እናም ይህን ሁኔታ ለመከላከልና በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የህግ የበላይነት መኖር የግድ ይላል። መንግስት ባለበት ሀገር ውስጥ ማንም ሰው ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየደረጋቸው ከመጣው መንገድ መውጣት የለበትም።
መንግስት መብትም፣ ኃላፊነትም ሆነ ግዴታ ያለበት አካል በመሆኑ በህጉ አግባብ መሰረት ተጠርጣሪዎችን ህግ ፊት በማቅረብ ተገቢውን ትምህርት የሚያገኙበትን ሁኔታ በመፍጠር የተጎጂዎችን እምባ ማበስ ይኖርበታል። ይህን ካላደረገ ህዝቡንም ይሁን በህዝቡ የተመሰረተውን ስርዓት በአግባቡ ሊጠብቅ አይችልም።
ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችም የዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዘቦች መቻቻልን መፍጠር የቻሉ እንዲሁም ዴሞክራሲያቸውን ስር እንዲሰድ ለማድረግ የህግ የበላይነትን የሚያፀና ሥርዓትን ዕውን በማድረግ ላይ የሚገኙ እንጂ፤ በደማቸው ፍላፃነትና በአጥንታቸው ወጋግራነት የገነቧት ሀገራቸው እነርሱ እንደሚመኙት ዓይነት በጩኸት፣ በህገ-ወጥነትና በሴራ የምትናጋ እንዲሁም ሁሉም እስረኞች መፈታት አለባቸው በሚል ዲስኩር እጅን ጠምዝዞ ማስፈፀም የሚቻልባት አገር አለመሆኗን እንዲያውቁ ያደርጋል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዝቦች ህገ-ወጦችን፣ አሸባሪዎችንና ሴረኞችን ሊፈጥሩ የሚችሉትን ችግሮች በሰከነና ብልሃት በተሞላበት ሁኔታ ፍትሐዊነትንና የህግ የበላይነትን እያረጋገጡ እንዲሁም ለሚፈፀምባቸው ማናቸውም የትንኮሳ ተግባራት ተገቢውን ምላሽ እየሰጡ ከተያያዙት ድህነትን ድል የመንሳት ትግል አንድም ስንዝር ቢሆን ፈቀቅ ሊሉ አይችሉም።
እንደሚታወቀው ሁሉ ህገ መንግስቱ የህጎች ሁሉ የበላይ መሆኑ፤ ማንኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት እንደሆነ፤ ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማህበራት እንዲሁም ባለስልጣኖቻቸው ህገ መንግስቱን የማክበርና ለህገ መንግስቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት እንዳለባቸው ይደነግጋል። ይህን የህግ የበላይነት አለመፈፀምና ለድርድር ለማቅረብ መሞከር መልሶ ከህገ መንግስቱ ጋር መጋጨት ይሆናል።
ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶችን የምታከብረው የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት ስለሚያዛት ብቻ ነው። ስርዓቱ ደግሞ ህዝቦች በበርካታ መስዕዋትነት ያመጡት ነው። ራሳቸው ይሁንታ እነዚህ ሀገር ውስጥ እውን እንዲሆን የፈቀዱት ነው። ሰብዓዊ መብቶችን በማይነካና ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ የህግ የበላይነትን የማስከር ስራ እንዲከናወን ይፈቅዳል።
ምህረትም ይሁን ይቅርታ ሲሰጥ በአገሪቱ ውስጥ በተቀመጠው የህግ አሰራር እንጂ ሁሉንም ታሳሪዎች በጅምላ መፍታት የህግ የበላይነትን አለመተግበር ያስከትላል። ዜጎችን ለሌላ ጊዜ ወንጀል ማመቻቸት ነው።
ዛሬ የህግ ተበላይነት ሳይረጋገጥ ሁሉም እስረኛ ይፈታ ከተባለ፤ ነገም ሌሎች እፈታለሁ በሚል ወንጀል መስራታቸው አይቀርም። እናም በተቀመጠው መስፈርትና በህጉ መሰረት ይቅርታና ምህረት መስጠት እነዚህን ችግሮች የሚያስወግድ መሆኑ መታወቅ አለበት። ከዚህ ውጭ አንዳንድ ወገኖች ስላሉ ብቻ ሁሉም እስረኛ በጅምላ የሚፈታበት አሰራር ሊኖር አይችልም።