Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መስመሩን እንዳይስት…

0 280

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መስመሩን እንዳይስት…

                                                            ዘአማን በላይ

ፅንፈኛው ሃይል በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ላይ እያደረጋቸው ያሉት ሴራዎች በርካታ ናቸው። በዚህ ፅሑፍ ላይ ግን ሁለቱን ጉዳዩች ብቻ ነጥለን ለመመልከት እንሞክራለን—መንገዶችንና የመገበያያ ቦታዎችን በመዝጋት በመመንደግ ላይ ያለውን ኢኮኖሚያችንን ለማዳከም የሚደረገውን እንዲሁም ህዝባዊውን መከላከያ ሰራዊት ስሙን ጥላኘት በመቀባት በአሉባልታ ከህብረተሰቡ የመነጠል አጀንዳን የማራመድ ሴራዎችን።

እነዚህ የፅንፈኛው ሃይል ሴራዎች በሀገር ኢኮኖሚና ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ሰራዊቱን ከማንኛውም የውጭና የውስጥ ፀረ ሰላም ሃይሎች እንዲሁም አሸባሪዎችን የመከላከል ተግባሩን በህዝባዊ ወገንተኝነት በመወጣት ላይ ያለውን ሰራዊት መልካም ስም ለማጠልሸት በማሰብ እየተከናወኑ ያሉ ናቸው። የእነዚህ ሴራዎች መንገድ፤ ሀገራችን እያረጋገጠች ያለችውን አስተማማኝ ሰላም የሚያደፈርስ፣ ፈጣንና ተከታታይ ልማታችንን እንዲሁም ስር በመስደድ ላይ ያለውን ዴሞክራሲያችንን ለማደናቀፍ ያለመ መሆኑን ሁሉም ዜጋ ሊገነዘበው ይገባል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት ፅንፈኞቹ ሀገራችን ውስጥ አንድ ክስተት በተፈጠረ ወቅት የሚያካሂዱት ተመሳሳይ ዝማሬ ያሰሙ ነበር። አገር ቤት የተፈጠረው ጊዜያዊ ችግር ምንም ይሁን ምን ፅንፈኞቹ ሁከት ቀስቃሽ አሉባልታዎቻቸውን ሰንቀውና የነገር ካራቸውን ስለው በየሚዲያዎቹ ሲያቅራሩ ማየት የተለመደም ነበር። አንዳንዶቹ ገንዘብ ተከፍሏቸው አሊያም ያለፈውን ማንነታቸውን በእዝነ ልቦና እያስታወሱ ፀረ-ኢትዮጵያ አቋማቸውን ስለሚያንፀባርቁ ሃፍረት የሚባል ነገር የሚነካካቸው አለመሆናቸውን ህዝቡ ቀስ በቀስ እየተገነዘበ ሲመጣ አሁን ደግሞ ፊታቸውን የሀገርን ኢኮኖሚ ወደ ማዳከሙ አዙረዋል።

እንደ ማንኛውም አገር ኢትዮጰያ ውስጥ የሚከሰቱ ተግዳሮቶችን በስርዓቱ ላይ በማላከክ መጥፎ ገፅታን ለመፍጠር መሯሯጣቸው ይታወቃል። ሆኖም ሥርዓቱ የህዝቦችን ተጠቃሚነት በየደረጃው ማረጋገጥ የቻለ ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ፤ ዜጎች በማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ውስጥ እኩል ተሳታፊ የመሆን ዕድል አግኝተዋል።

ይህንንም በተጨባጭ ስራ ላይ በማዋል የሀገራችንና የህዝባችን የማደግና የመበልጸግ ተስፋን በእጅጉ ለማለምለም ችሏል። መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመብቶቻቸው እየተገለገሉና ዘላቂ ጥቅሞቻቸውን እያስከበሩ በፈጣን ልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቅጣጫ ላይ የተያያዙት ፈጣን የዕድገት ጉዞም የፌዴራላዊ ሥርዓቱ እውን ሆነዋል።

በሀገራችን እውን የሆነው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሀገራችንና ለህዝባችን አንድነት፣ ሠላምና ዕድገት መጠናከር ወሳኝ አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው፤ በማበርከት ላይም ይገኛል። የዚህ አዲስ ሥርዓት ግንባታ ሂደት በተጨባጭ ተፈትኖ ፍቱንነቱ የተረጋገጠ ነው። የተገነባው ፌዴራላዊ ሥርዓት በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረውን የመበታተን አደጋ ያስወገደና በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ ለተመሰረተ ከብረት የጠነከረ የህዝቦች አንድነት ዘላቂ ዋስትናን እንዲያገኝ ያደረገ ነው። ይህም እዚህ ሀገር ውስጥ ጠንካራ ኢኮኖሚ እንዲገነባ ምክንያት ሆኗል። ፅንፈኛው ሃይል ግን ስርዓቱን ለመጣል በቅድሚያ ኢኮኖሚውን ማዳከም ይገባል የሚል አጀንዳ በመያዝ፤ በአሁኑ ወቅት መንገድ በመዝጋት፣ የህብረተሰቡ መገበያያዎች እንዲዘጉ የማድረግ ሴራን እያካሄደ ነው።  

ርግጥ ከመንገድ መዘጋትም ይሁን ከመገበያያ መዘጋት በቀዳሚነት የሚጎዳው ሁሉም የህብረተሰቡ ክፍል ነው። መንገድ ሲዘጋ የትራንስፖርት አውታሩ ይቆማል። ግብይት አይኖርም። ቀስ ብሎም ህብረተሰቡ የሚልሰውና የሚቀምሰው ላይኖረው ይችላል። ፅንፈኛው ሃይል ግን የሀገራችን ኢኮኖሚ እንዲዳከም በሚከፍለው ሃይል ተንደላቆ ይኖራል። ይህ ሁኔታ በህብረተሰቡ በፍፁም መፈቀድ ያለበት አይመስለኝም። ምክንያቱም በአንድም ይሁን በሌላ መልክ ተጎጂው ህዝቡ እንጂ የሴራው አራማጅ የሆነው ፅንፈኛው ሃይል አይደለም።

የሴራው ዓላማ ኢኮኖሚያችንን በማዳከም በህዝቦች መስዋዕትነት የተገኘውን ፌዴራላዊ ስርዓት ለመጣል መሞከር መሆኑን ህብረተሰቡ ሊገነዘብ ይገባዋል። በዚህ አዲስ ሴራ ተጠቃሚ ለሆኑ የሚችሉት ሴረኞቹ ብቻ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ህዝባዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ሴራውን በተናጠልም ይሁን በጋራ መመከት የሚኖርበት ይመስለኛል።

ፅንፈኛው ሃይል ስርዓቱን ለመጣል ያስችለኛል ብሎ የያዘው ሌላኛው ስልት በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ላይ የአሉባልታ ዘመቻ መክፈት ነው። ሰራዊታችን ህዝባዊ ተልዕኮ ያለውና ይህን ህዝባዊ ወገንተኝነቱን በብቃት ያስመሰከረ መሆኑ እየታወቀ፤ ፅንፈኛው ሃይል ግን ባልዋለበት ቦታ እያዋለው ስሙን ሲያጠፋ ይስተዋላል። ይህ ሴራው ሰራዊቱን ከህብረተሰቡ መነጠል ከቻልን ስርዓቱን መጣል ያመቸናል ከሚል ቀቢፀ-ተስፋ የመጣ ነው።

ዳሩ ግን ሰራዊቱ ፍርሃትን ሳይሆን አክብሮትን፣ በጥላቻ ፈንታ ጥልቅ ህዝባዊ ፍቅርን ማትረፍ የቻለ ነው። ሰራዊታችን በአንድ እጁ ጠብ መንጃ፣ በሌላኛው አካፋና ዶማ ይዞ በልማቱም ግንባር ቀደም ሆኖ ዪሰለፍ ህዝባዊ ሃይል ነው። ከአርሶ አደሩ ማሳም ተለይቶ አያውቅም። ያርሳል፣ ይዘራል፣ ያርማል፣ ያጭዳል፣ ይወቃል፣ ምርት እንዳይበላሽም ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል።

ሰራዊቱ ከሰው ሰራሽና ከተፈጥሮ አደጋ ጋር ተጋፍጦ፣ ለአንዴ ብቻ የሚኖራትን ህይወቱን ለእልፎች የመኖር ተስፋ ያለመለመ ነው። ምን ይህ ብቻ! ይህ ለህገ መንግስቱና ለህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ዘብ የቆመስው ሰራዊት፤ ጧሪ የሌላቸውን አረጋውያንና አረጋዊያትን የሚጦር፣ ኤች አይ ቪ/ኤድስን በመሳሰሉ ቀሳፊ በሽታዎችና በሌሎች ምክንያቶች ወላጅ አልባ የሆኑ ህፃናትን የሚያሳድግና የሚያስተምር፣ ከራሱ በላይ ለህዝቡና ለሀገሩ ጥቅም ሲታትር ውሎ የሚያድር ነው።

የዚህን ህዝባዊ ሰራዊት የሰላምና የልማት ተሳትፎ በሁለት ተከፍሎ ሊታይ ይችላል፡፡ አንደኛው ሀገራችን አድጋ የረሃብ፣ የድህነትና የመሃይምነት ተምሳሌነቷ ተፍቆ ማየት የማይፈልጉ፣ መበታተንና ተስፋ አልባነታችንን የሚናፍቁ የውጭና የውስጥ ፀረ ሰላም ኃይሎችን እኩይ ሴራ ማክሸፍ ነው። ይህን ከኤርትራ ወረራ እስከ አሸባሪው አል ሸባብ የግብረ ሽበራ ተግባርን በመመከት እንዲሁም ከሰሜን እስከ ደቡብ ባሉ የሀገራችን አካባቢዎች የኤርትራ መንግስት እያስታጠቀ በሚልካቸውን አሸባሪዎችና ፀረ ሰላም ኃይሎችን ላይ ህዝባዊ ክንዱን በማሳረፍ ህዝባዊነቱን አረጋግጣል። በእነዚህ ተግባሮቹ በህዝባችን አክብሮትን መጎናጸፍ የቻለ የህዝብ ወገን ነው።

ፅንፈኛው ሃይል ይህን የህዝብ ፍቅርና አመኔታ ለመሸርሸር የማያስወራው አሉባልታ የለም። በል ሲለው ሰራዊቱ ህዝቡን በአውሮፕላን ጨፈጨፈ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የውሸት ፎቶ በማቅረብ ሰራዊቱ የእገሌ ከተማ ህፃናትን ገደለ የሚል ፍፁም ውሸት የሆኑ ትረካዎችን ያቀርባል። ሰራዊቱ ግን በህዝባዊ ፅናቱ ለህዝቡ የሚሞት እንጂ ወደ ህዝብ የሚተኩስ አይደለም። ምክንያቱም በሚሄድባቸው ቦታዎች ሁሉ ከራሱ በፊት ለህዝብ መቆሙን በተግባር የሚያረጋግጥ የወደር የለሽ ዲሲፕሊን ባለቤት ስለሆነ ነው።

ርግጥ የሰራዊቱ ለህዝብ መሞት መቼም የሚቀየር አይደለም። ከራሱ በፊት ለህዝቡና ለሀገሩ ሲል ህይወቱን ለመስጠት የተሰለፈ ኃይል በምንም መልኩ ቢሀን የተነሳበትን ዓላማ አይስትም። ሰራዊቱ እንደ ወታደር ህዝብና ሀገር የምትጠብቅበትን ማናቸውንም ተግባር መወጣት የሚችል እንጂ በየትኛውም ፖለቲካዊ ስራዎች ውስጥ እጁን የሚያስገባ አይደለም።

ህገ መንግስቱን በፍፁም ፅናት የሚያከብር በመሆኑም ነሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ የሚያከናውናቸው ተልዕኮዎች ተግባሩን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ በሆነ አኳኋን የሚወጣ የህዝብ ልጅ ነው። ያም ሆኖ ፅንፈኛው ሃይል የሀገራችን ወቅታዊ ችግር መፍቻ የሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ እንደለመደው ‘ወታደሩ የፖለቲካ ስልጣን ሊረከብ ነው’ የሚል አሉባልታን የሚያስወራው ሰራዊቱና ህዝቡ ያላቸውን ጥብቅ ቁርኝት በጥሳለሁ እንዲሁም በዚህም የስርዓቱን ጠባቂ ከጥቅም ውጭ አደርጋለሁ ከሚል ከንቱ ምኞት የመጣ መሆኑን ሁሉም ወገን ሊገነዘበው የሚገባ ይመስለኛል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት እንኳንስ የሀገሩን ሰላም ቀርቶ የጎረቤቶቹንም ሰላም ማስከበር የቻለ ህዝባዊ ሃይል ነው። በሀገሩ ውስጥ ብጥብጥና ሁለት ለመፍጠር ለሚሹ ሃይሎች ወደር የማይገኝለት መድሃኒት ነው። ይህ ሃይል የተልዕኮው መሰረቱ ህዝብ መሆኑን የሚገነዘብና ለህዝብ ሲል ህይወቱን ለመስጠት የተሰለፈ መሆኑ ይታወቃል። ይህን ከህዝብ ጋር ያለውን የጠበቀ ፍቅር በአሉባልታ ማፍረስ አይቻልም። የህዝብ ክንድ የሆነውን ሰራዊት ስም በአሉባልታ በማጉደፍ የሚገኝ ትርፍ የለም። ስርዓቱም ይህ ክንድና የኢትዮጵያ ህዝቦች እሳካሉ ድረስ መኖሩ አይቀሬ ነው።

በአጠቃላይ ህብረተሰቡ ፅንፈኛው ሃይል እያካሄዳቸው ያሉትን እነዚህን ሁለት ሴራዎች ጠንቅቆ መረዳት ይኖርበታል። ይኸውም መንገድና መገበያያዎችን በመዝጋት ኢኮኖሚን ማዳከም እንዲሁም የህዝባዊውን ሰራዊት ስም በማጉደፍ ልጁ ከሆነው ህዝብ ጋር ያለውን ትስስር የመበጠስ ሴራዎች ናቸው። እነዚህ ሴራዎች ህዝቡ ያቀረባቸው ሰላማዊና ትክክለኛ ጥያቄዎች በአቋራጭ በመበጠስ መስመሩን የማሳት ተግባሮች ናቸው። ታዲያ ህብረተሰቡ የሴራዎቹ ግብ በሁከትና በግርግር ስርዓቱን ለማፍረስ መሞከር መሆኑን ተገንዝቦ፤ እኩልነትንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን እንዲሁም ሰላምንና ዕድገትን ያረጋገጠለትን ፌዴራላዊ ስርዓት ሊጠብቀው ይገባል—ባለቤቱ እርሱው ነውና። በዚህም ህብረተሰቡ ያነሳቸው ተገቢና ትክክለኛ ጥያቄዎች መስመራቸውን እንዳይስቱ ሊያደርግ ይችላል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy