Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“መጀመሪያ…” አለች ያቺ እንስሳ

0 541

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“መጀመሪያ…” አለች ያቺ እንስሳ

                                                      ደስታ ኃይሉ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰሞኑን ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አገራችን በአሁኑ ወቅት የምትገኝበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የታወጀ ነው። ጠቀሜታውም የአገራችንን ሰላምና መረጋጋት ከህዝቡ ጋር በመሆን ወደ ነበረበት ቦታ ለመመለስ መሆኑ ግልፅ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሴክሬታሪያትና የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስርት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በሰጡት መግለጫ፤ አዋጁ ሰላምን ለማስፈን ጠቀሜታ አለው። የአዋጁ መውጣት አሁን ከምንገኝበት ችግር የምንወጣበት ቀዳዳ ነው። ከሁሉም በላይ “መጀመሪያ መቀመጫዬን” እንዳለችው እንስሳ ዓይነት በቅድሚያ ሰላምና መረጋጋታችን በተገቢው መንገድ ሊጠበቅ ይገባል። እናም የአዋጁ አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም።

ማንኛውም አገሪቱ የሚያጋጥማትን በወቅቱ የሚያጋጥማትን ችግሮች ፈጣን መፍትሔ ለመስጠት እንዲቻል በማሰብ ነው። በስራ ላይ ያሉት መደበኛ አሰራሮች የተፈጠረውን ችግር መቋቋም ሲያቅታቸው አዋጁ እውን እንዲሆን ይደረጋል። በዚህም የተፈጠረውን ችግር ተቆጣጥሮ  አገሪቱ ከተደቀነባት ወቅታዊ አደጋ ለማውጣትና ችግሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቀልበስ እንዲቻል የአዋጁ እውን መሆን አስፈላጊ ይሆናል።

በዚህም መሰረት በህገ መንግስቱ አንቀፅ 93 (5) መሰረት ታውጇል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያትና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ አዋጁን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ስርዓት አልበኝነት ተፈጥሮ የዜጎች ህይወት በአሳዛኝ ሁኔታ እየጠፋና ዜጎች ለዘመናት ያፈሩት ሃብት እና ንብረት በቀላሉ እየወደመ መሆኑን አስታውሰዋል። በተጨማሪም የህዝቦች ለዘመናት በመከባበር እና በመተሳሰብ አብሮ የመኖር ባህሉን የሚሸረሽሩ ቅስቀሳዎች እና አልፎ አልፎ ብሔርና እምነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ሲያጋጥሙ መስተዋሉን ገልፀዋል። እነዚህ ሁኔታዎችም ህዝቡና መንግስት ከሚሸከሙት በላይ እየሆኑ መጥተዋል። በመሆኑም የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሀገሪቱንና የህዝቦቿን ሰላምና መረጋጋት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስጠበቅና የዜጎችን ህገመንግስታዊ መብት ለማስከበር በመላው ሀገሪቱ ተፈፃሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መወጁን አስታውቀዋል።

እዚህ ላይ በአዋጁ ወቅት ስለሚወሰዱ እርምጃዎች የተወሰኑ ነጥቦችን ማንሳት ያስፈልጋል። ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስከበር፣ ከአደጋ ለመጠበቅ፣ የህዝብና የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን ማንኛውም ሁከት እና ብጥብጥ በህዝቦች መካከል መጠራጠርን እንዲሁም መቃቃርን የሚፈጥር ይፋዊም ሆነ የድብቅ ቅስቀሳ ማድረግን፣ ፅሁፍ ማዘጋጀትን እና አትሞ ማሰራጨትን፣ ትእይንት ማሳየትን፣ በምልክት መግለፅን ወይም መልዕክትን በማንኛውም ሌላ መንገድ ለህዝብ ይፋ ማድረግን ክልክል መሆኑ ተገልጿል።

ኮማንድ ፖስቱ ማንኛውም የመገናኛ ዘዴ እንዲዘጋ ወይም ደግሞ እንዲቋረጥ የማድረግ፣ የህዝብና የዜጎች ሰላምና ፀጥታን ለማስጠበቅ ሲባል የአደባባይ ሰልፍ ማድረግን፣ መደራጀት፣ በቡድን ሆኖ መንቀሳቀስን ይከለክላል። እንዲሁም በህገ መንግስቱና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የሚቃጡ ወንጀሎችን የጠነሰሰ፣ የመራ፣ ያስተባበረ፣ የጣሰ ወይም በማንኛውም መንገድ በወንጀል ድርጊቱ የተሳተፈ ወይም ተሳትፏል ተብሎ የሚጠረጠር ማንኛውም ሰውን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ስር እንደሚውል ተመልክቷል። ተገቢውን ማጣራት በማድረግም በመደበኛው ህግ ተጠያቂ ይደረጋል።

ኮማንድ ፖስቱ ወንጀል የተፈፀመባቸውና ሊፈፀምባቸው የሚችሉ እቃዎችን ለመያዝ ሲባል ከፍርድ ቤት ትእዛዝ ውጪ ማናቸውንም ቤት፣ ቦታ፣ መጓጓዣ ለመበርበር እንዲሁም ማናቸውንም ሰው ማስቆም፣ ማንነቱን መጠየቅ እና መፈተሽ ይችላል። በብርበራ ወይም በፍተሻ የተያዙ እቃዎችን በማስረጃነት ለፍርድ ቤት መቅረባቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ተጣርቶ ለባለመብቱ የሚመለስ ይሆናል። የሰዓት እላፊ ተፈፃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ኮማንድ ፖስቱ ይወስናል።

ለተወሰነ ጊዜ አንድን መንገድና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለመዝጋት እንዲሁም ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ ወደ ተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ያደርጋል። የተቋማትን የመሰረተ ልማትን የጥበቃ ሁኔታንም ኮማንድ ፖስቱ ይወስናል።

የህዝብንና የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሲባል የጦር መሳሪያ ወይም ስለት፣ እሳት የሚያስነሱ ነገሮችን ይዞ መንቀሳቀስ የማይቻልባቸውን ቦታዎች በኮማንድ ፖስቱ ተለይተው ይወሰናሉ።

በሰላም መደፍረስ ምክንያት የፈረሱ የተለያዩ የአስተዳደር እርከኖችን ከክልል እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር መልሶ እንዲቋቋሙ ያደርጋል። ብሔር ተኮር በሆነ ወይም በሌሎች ግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎችን ከክልል መንግስታት እና ከአካባቢው ህዝብ ጋር በመተባበር ወደ ቀድሞ መኖሪያ ስፍራቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙና ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲመሩ ድጋፍ የማድረግ ስራዎች በኮማንድ ፖስቱ ይከናወናሉ።

ህዝብ የሚገለገልባቸው የአገልግሎት ተቋማት፣ የንግድ ስራዎች ወይም የመንግስት ተቋማት ከሚሰጡት አገልግሎት እንዳይስተጓጎሉ ተገቢውን ጥበቃ ያደርጋል። ይህን ተላልፎ አገልግሎት ያቋረጠ ማንኛውም ሰው በህግ ተጠያቂ እንደሚሆንም ተመልክቷል።

ኮማንድ ፖስቱ በቀጣዩቹ ስድስት ወራት የመሰረታዊ ሸቀጦች እና አገልግሎቶች አቅርቦት የዝውውር እና የስርጭት ደህንነትን ያረጋግጣል። የትራንስፖርት ፍሰት ደህንነትን ይቆጣጠራል፤ ያረጋግጣል። በትምህርት ተቋማት የመማር እና ማስተማር ሂደት ከሚያውኩ ተግባራት የፀዱ እንዲሁም መደበኛ ስራን የሚያስተጓጉሉ እንከኖች እንዳይፈጠሩ ይሰራል። ህገመንግስቱ እና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለማስከበር፣ ከአደጋ ለመጠበቅ የህዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ሁሉንም እርምጃዎች ይወስዳል።

እነዚህ እርምጃዎች ኮማንድ ፖስቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚወስዳቸው ናቸው። እርምጃዎቹ በቀጣይ በሚወጡ የአፈፃፀም መመሪያዎች በዝርዝር የሚገለፁ መሆናቸውም ተመልክቷል።

በህገ መንግስቱ መሰረት የታወጀው ይህ አዋጅ በዋናነት የሚመራው በኮማንድ ፖስቱ ነው። ኮማንድ ፖስቱም በአባልነት ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን፣ የደህንንት አገልግሎትን፣ የመከላከያ ሚኒስቴርንና በየክልሉ ያሉ የጸጥታ ምክር ቤት አባላት እንዲሁም ሌሎች አካለትንም የሚያካትት ነው። ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከየካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት 15 ቀናት ውስጥ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርብ ቀርቦ የሚፀድቅ ሲሆን፤ እንደ አስፈላጊነቱም እየታየ ሊራዘም ይችላል።

እርግጥ በመጀመሪያ አገራዊ ደህነታችን መጠበቅ ይኖርበታል። ሰለማችን መጋገጥ አለበት። አገራችን በአዋጁ የስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ነበረችበትና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ወደምትታወቅበት የሰላም ተምሳሌትነት እንድትመለስ እያንዳንዱ ዜጋ ለአዋጁ የበኩሉን ትብብር ማድረግ ይኖርበታል።

በመሆኑም በቅድሚያ ሁሉም ዜጋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማክበር አለበት። ለጥቆም ለአዋጁ ተፈፃሚነት ትብብር ማድረግ ይጠበቅበታል። አዋጁን የማያከበርና ለተፈፃሚነቱም ከኮማንድ ፖስቱ አባላት ለሚቀርብለት የድጋፍ ጥያቄ የማይተባበር ማንኛውም ግለሰብ በአዋጁ መሰረት ቅጣት ይጣልበታል። ያም ሆኖ ግን ጉዳዩ ሀገርን ከውጭና ከውስጥ አሸባሪዎችና ፀረ-ሰላም ኃይሎች የጥፋት ተልዕኮ የመታደግ ብሎም ዕድገታችን ያስኮረፋቸውን አንዳንድ የውጭ ሀገራትን የእጅ አዙር ሴራ መከላከል በመሆኑ ሁሉም ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት የሚኖርበት ይመስለኛል።

እርግጥም የትኛውም ሀገር ወዳድ ዜጋ  በእነዚህ ኃይሎች ሰላሙ እንዲደፈርስ፣ ማናቸውም ህገ-መንግስታዊ መብቶቹ ተነጥቀው የስርዓት አልበኞች መፈንጫ ሆኖ ህይወቱን፣ ሃብቱንና ንብረቱን እንዲያጣ ብሎም ሀገር አልባ ሆኖ በትርምስ ውስጥ እንዲኖር አሊያም በጎረቤት ሀገር ውስጥ የጥገኝነት ህይወትን እንዲገፋ የሚፈልግ አይመስለኝም።

ስለሆነም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማክበርና ተፈፃሚነቱን መተባበር ማለት እነዚህን መጥፎ ክስተቶች በስድስት ወራት ውስጥ ገትቶ በተለመደው ሰላማዊ የህይወት መስመር ውስጥ መግባት ነው። “መጀመሪያ መቀመጫዬን” እንዳለችው እንስሳ በመጀመሪያ ሰላሙን ለማረጋገጥ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለአዋጁ ስኬት ሊተባበር ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy