Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ማገልገያ እንጂ መገልገያ አይደለም

0 383

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ማገልገያ እንጂ መገልገያ አይደለም

ለሚ ዋቄ

ሃሙስ የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሲታወስ የሚኖር ዕለት ነው። ዕለቱ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ  የጠቅላይ ሚኒስተርነታቸውን፣ የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና የእናት ድርጅታቸው ደኢህዴን ሊቀመንበርነታቸውን በፈቃዳቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን ጋዜጠኞች ጠርተው በይፋ የተናገሩበት ነው። ዕለቱን ታሪካዊ የሚያደርገው የመሪ ለውጥ የተበሰረበት መሆኑ አይደለም። ለኢትዮጵያ የመሪ ለውጥ አዲስ አይደለም። እድሜያችን ከሰላሳዎቹ አጋማሽ በላይ የሆን ኢትዮጵያውያን አራት አምስት የመሪ ለውጥ የተካሄደባቸው አጋጣሚዎችን አልፈናል። በሃገሪቱ የአራት አስርት ዓመታት ታሪክ ውስጥ በርካታ የመሪ ለውጦች ተካሂደዋል።

በ1967 ዓ.ም መስከረም 2  ቀን ለ43 ዓመታት ያህል ሃገሪቱን የገዙት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ በአብዮት ከስልጣናቸው ተወግደዋል። በወቅቱ ህዝባዊ የተቃውሞ ንቅናቄ አይሎ የነበረ ቢሆንም፣ ከየካቲት 1966 ዓ.ም ጀምሮ ከተለያዩ ወታደራዊ ክፍሎችና ከፖሊስ ሰራዊት የተወጣጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከፍተኛና የመስመር መኮንኖች እንዲሁም የበታች ሹማምንት ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ መስርተው ስልጣን ለመረከብ አቆብቁበው ሲንቀሳቀሱ የነበረ ቢሆንም ንጉሱ ግን ከስልጣናቸው ላይ ፈቀቅ የማለት ፍቃደኝነት አላሳዩም ነበር። እናም ንጉሱ በአብዮት ከስልጣናቸው ተወገዱ፤ የስርአት ለውጥም ሆነ።

ንጉሱን አስወግዶ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት የመሰረተው ቡድን የመጀመሪያውን ሊቀመነበሩን ወይም የሃገሪቱን መሪ ጄነራል አማን ሚካኤል አንዶም አድርጎ ሾሞ ነበር። ጄነራል አማን ሶስት ወር እንኳን ሳይቆይ የአብዮቱ ሰይፍ በላቸው። በግድያ ከስልጣናቸው እንዲሰናበቱ ተደረገ። ደርጉ ከዚህ በኋላ ጄነራል ተፈሪ በንቲ፣ ኮሎኔል አጥናፉ አባተንና ሻለቃ መንግስቱ ሃይለማርያምን ሊቀመነበር፣ ምክትል ሊቃነመናብርት አድርጎ ሾመ። ሃገሪቱን የሚመሩት ሶስቱ ነበሩ። ይሁን እንጂ የካቲት 1969 ዓ.ም የአብዮቱ ሰይፍ ጄነራል ተፈሪን በላቸው። ይህ ሆኖ አመት እንኳን ሳይሞላ ጥቅምት 1970 ዓ.ም ላይ ደግሞ የአብዮቱ ሰይፍ ኮሎኔል አጥናፉ አባተን በሞት አሰናበተ። የደርግ የሶስት ዓመት እድሜ የመሪዎች ለውጥ በግድያ የተካሄደ ነበር።

ከዚህ በኋላ ከሻለቃነት ወደኮሎኔልነት ያደጉት መንግስቱ ሃይለማርያም በኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ህብረት (ኢማሌድህ) ውስጥ አልፈው፣ የኢማሌድህ አባል ድርጅቶችን መሪዎችና ድርጅቶቹን ቅርጥፍ አድርገው በልተው በሊቀመነበርነት የሚመሩትን የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን (ኢሰፓኮ) መሰረቱ፤ ሰኔ 1972 ዓ.ም ላይ። እናም የኢሰፓኮና የደርጉ ሊቀመነበር ሆነው ሃገሪቱን ይመሩ ጀመር። በ1977 ዓ.ም ከኢሰፓአኮ ውስጥ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) መፍለቁን ነግረውን የኢሰፓና የወታደራዊ ደርግ ሊቀመነበርነታቸውን ቀጠሉ። በ1980 ዓ.ም ደግሞ ኢሰፓ የኢትዮጵያ ህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ (ኢህዲሪ) መንግስት መሰረተ። መንግስቱ ሃይለማርያም የኢሰፓ ሊቀመነበርና የኢህዴሪ ፕሬዝዳንት ሆኑ።

ፕሬዝዳንት መንግስቱ የኢትዮጵያየ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የትጥቅ ትግል እያያለ መጥቶ ወደቤተመንግስታቸው ተጠጋ። ይህን ተከትሎ ኦሮሞው ይወጋናል፣ ትግሬው የወጋናል፣ አማራውም የወጋናል። በአጠቃላይ 23 ድርጀቶች በብሄር ተደራጅተው እየወጉን ነው የሚለውን የመጨረሻ ንግግራቸውን አድርገው ከሃገር ኮበለሉ። ይሄኔ ከብሄራዊ አሰተባባሪ ኮሚቴ እስከ የአህዲሪ መንግስት ለአስራ ሰባት ዓመታት የቆየው የወታደራዊ ስርአት አከተመ፤ በአብዮት የስርአት ለውጥ ተካሄደ።

ከላይ ለማስታወስ ያህል በአጭሩና በግርድፉ የጠቀስኩት ያለፉ አራት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ የስልጣን ሽግግር ታሪክ፣ ሽግግሮቹ የስርአት ለውጥን ያስከተሉና በግድያ የተካሄዱ መሆናቸውን ያሳያል። እናም የመሪ መነሳት ወይም ለውጥ በቀጥታ ከስርአት ለውጥ አለበለዚያም ከመሪ መገደል ጋር ይያያዛል።

ከ1983 ዓ/ም ወዲህ ግን ይህ ሁኔታ ተለውጧል። የኢፌዴሪ መንግስት ከተመሰረተ በኋላ ባሉት ሀያ ሶሰት ዓመታት አምስት ሃገራዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል። በእነዚህ ዓመታት የመንግስት ከፍተኛ የስልጣን አካል በሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ በአብላጫ ድምጽ ከፍተኛ ቁጥር ያለው መቀመጫ በማሸነፍ ገዢ ለመሆን የበቃው ፓርቲ  ኢህአዴግ ቢሆንም፣ ስርአቱ ሶስት ፕሬዝዳንቶችና ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትሮችን አስተናገዷል።

በተለይ በ2004 ዓ/ም ማብቂያ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድንገተኛ ሞትን ተከትሎ በህዝቡ ዘንድ መደናገጥ ቢጤ ታይቶ ነበር። የኋላ ታሪካችን የመሪን ለውጥ ከአብዮት ውጭ ስለማያውቅ የስርአት ለውጥ እንዳያመጣ የሚል ስጋት ነበር መደናገጡን የፈጠረው። ይሁን እንጂ ያለምንም ችግር በህገመንግስቱ መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሃገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር መርጧል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያምን።

ታዲያ በጽሁፌ መግቢያ ላይ እንደጠቀሰኩት ሃሙስ የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን መለቀቂያ ጥያቄ ማቀረባቸው ሲሰማ መደናገጥ ተፈጥሯል። የፌደራል መንግሥቱን አስፈፃሚ የሚመራው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህይወት እያለ ሲለወጥ የመጀመሪያው በመሆኑ አንዳች ያልተጠበቀ ነገር ይመጣል በሚል ነበር መደናገጥ የተፈጠረው። በሃገሪቱ ታሪክ መሪ በፍቃዱ ስልጣን የለቀቀበት ጊዜ ባለመኖሩ እንደሽሽት ቆጠረው የስርአት ለውጥ ምልክት አድርገው የወሰዱትም ነበሩ። ይህ ግን አልሆነም። ስርአቱ እንደቀጠለ ነው። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመንፈቅ እረፍቱ ሲመለስ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሥልጣን መልቀቂያ ጠያቄ ተቀብሎ፣ ህገመንግስቱ በሚፈቀደው መሰረት ከ5ኛው ዙር የመንግስት የስራ ዘመን የቀሩትን ሁለት ተኩል ዓመታት የሚመራ ጠቅላይ ሚኒስትር ይመረጣል።

የመሪነት ሥልጣንን በፍቃድ መልቀቅ በአፍሪካ ታሪክ ታይቶ አይታወቅም። በቀርቡ የዚምቧቤው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤና የደቡብ አፍሪካው ጃኮብ ዙማ የያዙትን አቋም ለዚህ አስረጂነት ማንሳት ይቻላል። እነዚህ መሪዎች መምራት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰው፣ የወከላቸውና የሚመሩት ፓርቲ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው እንዲለቁ ቢጠይቅም ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል። በመጨረሻ ፓርቲዎቻቸው በግድ ነው ከስልጣናቸው ያነሳቸው። እናም የሰሞኑ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ያቀረቡት ጥያቄ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፈሪካም የመጀመሪያው ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በድንገት ነበር ወደሥልጣን የመጡት። በድንገተኛው መለስ ዜናዊ ሞት ምክንያት፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስልጣን አስረክቦ ሃገር የመመራት አደራ ጣለባቸው። በዚህ ሁኔታ ወደስልጣን የመጡት ኃይለማሪያም ደሳለኝ በስልጣን ላይ በቆዩባቸው ያለፉ አምስት ዓመታት የሃገሪቱ ዋና ትኩረት የሆነውን የኢኮኖሚ እድገትና የድህነት ቅነሳ ተግባር በመጣበት ፍጥነት እንዲቀጥል አድርገዋል። ሃገሪቱንና ህገመንግስታዊ ስርአቱን በቀጥታና በእጅ አዙር ለማጥቃትና ለማፍረስ ከተሰለፉ ጠላቶች ተከላክለዋል። ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላም ላይ ያላትን ድርሻ፣ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ረገድ ያፈራችውን ተሰሚነትም ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ እንዲቀጥል ማድረግ አስችለዋል። ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያየዘ ከታችኞቹ የተፋሰስ ሃገራት ጋር በተለይ ከግብጽ ጋር ያለውን ግንኙነት የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ በማይሰጥ ጽኑ አቋም ላይ በመመስረት መግባባት ላይ ለመደረስ ሰርተዋል። በዚሀ ረገድ እስካሁን ውጤታማ ተግባር ተከናወኗል።

በተለይ ባለፉ ሁለት ዓመታት በመንግስት የአፈጻጸም ችግር የተፈጠረውን የህዝብ ተቃውሞ ለጥያቄዎቹ ተገቢ ምላሽ በመስጠት እርካታ በመፍጠር ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ከሚመሩት ከገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ጋር ብዙ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። በገዢው ፓርቲና በመንግስት ውስጥ ተሃድሶ በማካሄድ የመንግስት ስልጣንን ህዝብን ለማገለገል ብቻ እንዲውል ማድረግ የሚያስችሉ እርምጃዎች ወስደዋል። በዚህም 5ኛውን ዙር የመንግስት ስልጣን እንደተረከቡ አዋቅረውት የነበረውን ካቢኔ አፍርሰው በ2009 ዓ.ም በአዲስ መልክ አዋቅረዋል። ወደየሃይል ተቃውሞነት እያደገ ለመጣው የህዝብ ቅሬታ ዋነኛ መንስኤ የሆነውን የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር፣ በችግሩ ስፋት ልክ ማቃለል የሚያስችል አሰራርና በጀት እንዲመደብም አድርገዋል። በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም በስልጣን ላይ በቆዩባቸው ዓመታት የተጣለባቸው ሃላፊነት ተወጥተዋል ማለት ይቻላል።

ይህም ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ አቅርበዋል። የመልቀቂያ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ በተከሰተው አለመረጋጋትና የፖሊቲካ ችግር ምክንያት በርካታ የሰው ህይወት መጥፋቱን፣ ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውን፣ ንብረት መውደሙን፣  ኢንቨስትመንት መስተጓጎሉን አስታውሰዋል። የተከሰተውን ችግር ለማቃለል እንዲቻል በኢህአዴግና በመንግስት ደረጃ የተለያዩ ማሻሻያዎችን በመጀመር እነዚህን ማሻሻያዎች ለማሳካት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በመጨረሻም በእነዚህ ማሻሻያዎች ለተቀመጡት የመፍትሄ አቅጣጫዎች መሳካትና የመፍትሄው አካል ለመሆን በማሰብ በፍላጎታቸውና ፈቃዳቸው ከኢህአዴግና ከመንግስት ሃላፊነታቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን አሳውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሷቸው የሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ተያያዥ ችግሮች መኖራቸው ግልጽ ነው። ለዚህ የሠላምና መረጋጋት እጦት መነሻ የሆኑትን ተገቢ የህዝብ ቅሬታዎች ለመፍታት መንግስት የሚቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው። ይሁን እንጂ የሃይል ተቃውሞዎችና አድማዎቹ ሰበብ እየፈለጉ በተደጋጋሚ መከሰታቸውን ቀጥለዋል። ማንነት ላይ የታከኩ ግጭቶችም እያጋጠሙ ነው። ይህ ሁኔታ መንግስት ለህዝቡ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እያደረገ ያለውን ጥረት እያደነቃቀፈ ነው። በመሆኑም ከህዝቡ የመነጨ ቀወስ ነው ብሎ መውሰድ የሚያስቸግርበት ሁኔታ ነው ያለው። በዚህ የቀወስ ሁኔታ ውስጥ ሃገሪቱን መምራት በሰላም ወቅት ልማት ላይ ከሚያተኩር አመራር የተለየ ክህሎት ይሻል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ስልጣናቸውን በፍቃዳቸው የለቀቁት ሃገሪቱን አሁን ካለችበት ቀውስ ውስጥ የማውጣት ክህሎት ያለው መሪ እድል እንዲያገኝ ነው። ስልጣኔን የለቀቁት የተቀመጡት የመፍትሄ አቅጣጫዎች እንዲሳኩና የመፍትሄ አካል ለመሆን ነው ሲሉም ይህን እየገለጹ ነው። ስልጣን ላይ ሙጭጭ ብለው፣ በቀውስ ወቅት አመራር ብቃት ያለው መሪ እድል እንዳያገኝ በመዝጋት አደጋ ላይ ከመውደቅ፣ የተሻለ ክህሎት ላለው መሪ እድል በመስጠት መፍትሄውን የማገዝ እርምጃ ነው የወሰዱት። ለተሻለ መሪ እድል መሰጠት መፍትሄውን የማገዝ እርምጃ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም የወሰዱት በገዛ ፍቃድ ስልጣንን የመልቀቅ በሃገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ እርምጃ ስልጣን ህዝብን ማገልገያ መሳሪያ እንጂ የግል የተመቸ ኑሮ ማደላደያ መሳሪያ እንዳልሆነ በሚገባ መገንዘባቸውን ያሳያል። ይህ ደግሞ ብቸኛው የስልጣን ምንጭና ባለቤት ህዝብ መሆኑን ከመገንዘብና ከመቀበል የመነጨ የዴሞክራሲያዊነት ባህሪ መለያ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ርምጃ የሃገሪቱ ዴሞክራሲ የደረሰበትን ከፍታም ያሳያል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy