Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምህዳሩን ለማስፋት የጋራ ርብርብ ያስፈጋል

0 234

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምህዳሩን ለማስፋት የጋራ ርብርብ ያስፈጋል

 

ዮናስ

ባሳለፍናቸው 26 ዓመታት በሃገራችን የልማት፣ የዴሞክራሲና የፖለቲካ ምኅዳር  በርካታ ለውጦች የተመዘገቡ መሆኑ እሙን ነው። ይህ በሆነበት አግባብ ደግሞ ከ26 ዓመታት በኋላ አገሪቱን ቋፍ ውስጥ የከተቱ በርካታ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡ ችግሮቹን ለየት የሚያደርጋቸው እና አሳሳቢው ደግሞ የፌዴራል ሥርዓቱን እና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ጥያቄ ውስጥ የከተቱና የአገሪቱን ህልውና የሚፈታተኑ ችግሮች መሆናቸው ነው። በዚህም  ከዛሬ ነገ ምን ይመጣ ይሆን የሚለው የብዙዎች ሥጋት ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የግለሰቦች ግጭት የብሔር ገጽታ እየተላበሰ የዜጎች ሕይወት ተቀጥፏል፣ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡  የነበረው ሰላምና መረጋጋት ደፍርሷል፡፡ በአገሪቱ ሕዝብ መካከል አንዳችም ዓይነት ቁርሾና ጥላቻ ሳይኖር፣ አገሪቱን ለውድመት ያጋለጡ አሳዛኝ ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡ የወጣቱን ትውልድ መሠረታዊ ችግርች በመፍታት መረጋጋት ለመፍጠር የሚያስችል ፕሮግራም ተነድፎ ወደተግባር ቢገባም፤ የበለጠ ትርምስ የሚፈጥሩ እንካ ሰላንቲያዎች አሁንም ሊቆሙ አልቻሉም።

ይህን እና መሰል ሃገሪቱን ቀውስ ውስጥ የከተቱ ጉዳዮችን ተከትሎ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከታህሳስ 3 ቀን ጀምሮ አገራችን የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ 17 ቀናት የፈጀ ሰፊና ዝርዝር የሁኔታዎች ግምገማ አካሂዷል፡፡ ስራአስፈፃሚ ኮሚቴው በዚህ ስብሰባ ቀደም ሲል የተጀመረው የመታደስ ሂደትና የደረሰበትን ደረጃ፤ እንዲሁም በአገራችን የሚታዩ የቆዩና ወቅታዊ ችግሮችን ከነዝርዘር መገለጫቸው በመለየት በመንስኤና መፍትሄዎቻቸው ላይ መክሮ የሃሳብ አንድነትና መተማመን መፍጠሩንም አመልክቷል ፡፡  

በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን ከሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶችና ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመቅረፍ መንቀሳቀስ እንደሚገባ መወሰኑም ይታወሳል፡፡ ምሁራንና የሲቪክ ማህበረሰቦች ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ተገቢ ሚናቸውን የሚጫወቱበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርም በተመሳሳይ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ያስከበራቸውን ሰብአዊና ዴሞከራሲያዊ መብቶች የመጣስ አዝማሚያዎችና ተግባራት በጥብቅ እንዲመከቱ ወስኗል፡፡ በዚህ ረገድ የህዝብን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በአስተማማኝ ደረጃ ለማስከበር ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ተጨማሪ ርምጃዎች እንዲወሰዱም ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ማእከላዊ የተባለውን እስር ቤት በመዝጋትና የሰው ህይወት ከማጥፋት እና መሰል ተግባራት በመለስ  በግጭት ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ አካላትን ከእስር በመፍታት ጀምሯል፡፡ ጅማሮውም ከፌደራል ሲሆን በክልሎች ደረጃም እንደሚከናወን በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከአንድ ዓመት በፊት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ብጥብጥ ተከትሎ፣ ታስረው የነበሩ ከ2ሺ በላይ ዜጎችን በመፍታት አቅጣጫው መቀጠሉን አረጋግጧል፡፡ ከሰሞኑ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በሰጡት መግለጫ፤ 2ሺ 345 እስረኞች  በምህረት መፈታታቸውን የተናገሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 1ሺ 568 ያህሉ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብለው የተፈረደባቸው ናቸው፡፡ መንግስት አገሪቱን ለማረጋጋትና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት፣ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ የፖለቲካ አባላት እንደሚፈቱ መግለጹን ተከትሎ፣ ባሳለፍነው ሰሞን ዶ/ መረራ ጉዲናን ጨምሮ 500 የሚደርሱ እስረኞች የተፈቱ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል እርምጃም የዚሁ ውሳኔ አካል እንደሆነ ታውቋል፡፡

ይህ ደግሞ መንግሥት ለህዝብ የገባውን ቃል ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን እና፣ የኦሮሚያው ደግሞ ቀጣይነቱን የሚያረጋግጥ ነው። ከፍተኛ አመራሩ አገሪቱ ያስመዘገበቻቸውን መልካም ነገሮችንና እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን በሐቀኝትና በተሟላ ሁኔታ መገምገሙን ነግሮናል። ከዚህ በመነሳት ይህ እርምጃ የራሱንና የአገሪቱን ችግሮች ለመቅረፍና መልካም ውጤቶችን ለማስፋት ቆርጦ መነሳቱን የሚያጠይቅ ነው።

ከፍተኛ አመራሩ በግልፀኝነትና በመተማመን መንፈስ ተወያይቶ  በመርህ ላይ የተመሰረተ መግባባት ላይ ስለመድረሱም ነግሮናል። በዚህም ላይ በመመስረት ግልጽና ዴሞክራሲያዊ ውይይት መጀመር ግን በአፋጣኝ ይጠበቅበታል። ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓታችን የሕዝቦችን እኩልነት ያረጋገጠና ከዘመን ጋር እየዳበረ የሚሄድ እንዲሆን የሚያጋጥሙ የአፈፃፀምና የአመለካከት ችግሮችን ለመቅረፍ ተዘጋጅቻለሁ ባለው ልክ በተግባር የሚገለጽ ስራም ሊያሳየን ይገባል። ሕገመንግስታዊ ዲሞራሲያችን በአፈፃፀም ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን በማረም የሁሉንም ሰፊ ተሳትፎ ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት መዘጋጀቱን የተመለከተው ግን መሬት የነካ ይመስላል። የእስረኞች መፈታት እና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እየተደረገ ያለው ድርድር የዚህ ማሳያ ነው።

ይህ ማለት ግን የህግ የበላይነትን በመጣስ ልዩ ልዩ ጥፋቶችን የሚፈጽሙ አካላትን ያለአንዳች ማመንታት አግባብ ያለውን ስርዓት ተከትሎ ህጋዊ ተጠያቂነት እንዲኖር አያደርግም ማለት እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል። አንዳንዶች ሁሉም ወንጀለኞች ስለምን አልተፈቱም በሚል ግርግር ማሽተታቸው ከዚህ መነሾ መሆኑ አያጠያይቅምና።

መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የእስረኞች መፈታት ዋነኛው ጉዳይ እንደሆነ አስመስለው የግርግር አጀንዳ ለማንሳት እየተሟሟቱ መሆኑን አመላካች የሆኑ ፍንጮች እያየን ነው። ስለሰላም የቆሙ ዜጎች አጀንዳ መሆን ያለበት ግን የአገራችንን ወቅታዊ ችግሮች ለመፍታት፣ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትና የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ መንግሥት ልዩ ልዩ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡና እነዚህንም ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ ላይ ነው።

የእስረኞች መፈታት ጉዳይ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ሥር ከተጠቃለሉ በርካታ ጉዳዮች አንዱ ጉዳይ ብቻ መሆኑ ሊጤን ይገባል፡፡ ሃገሪቱን ለትርምስ እያመቻመቸ የሚገኘው ኃይል ሙሉ ትኩረቱን በእስረኞች መፈታት እንዲያም ሲል በአንድ እስረኛ ጉዳይ ላይ በማተኮር እገሌ ተፈታ፣ እገሌ ቀረ፣ የተፈታው እገሌ እንዲህ ሲል ተናገረ ወዘተ በሚል ቁንጽል ጉዳይ ላይ የህዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማሳት እየሞከረ ነው።  

ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ ባስቀመጡት መሰረት ”በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት በፍርድ ቤት የተፈረደባቸው አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች ህግና ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ በምህረት ተለቀዋል፤ ይህም ይቀጥላል። ክልሎችም ይሁኑ የፌዴራል መንግስት ታሳሪዎችን ሕጉ በሚፈቅደው ልክ ለመልቀቅ አስፈላጊውን የማጣራት ስራ በማካሄድ ላይ መሆናቸውን በምህረት የሚለቀቁትንም እየለዩ መሆናቸውን የተመለከቱ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡

 

ከዚያ ውጭ ሁሉም እስረኞች መፈታት አለባቸው የሚሉት አስተያየቶች የህግ የበላይነትን የሚሸረሽርና ፍፁም ተቀባይነት የሌለው፣ ነገ ተነገ ወዲያ ወንጀልን የሚያበረታታ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። በዋናነት ግን የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ እስረኞች በመፍታት የሚወሰን ሳይሆን ዘርፈ ብዙ በሆኑ የዴሞክራሲ ሰላምና ልማት ጉዳዮች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ተገንዝቦ በዚህ አግባብ ብቻ ቅደም ተከተሉን እየለዩ መሟገት ተገቢ ይሆናል። የፖለቲካ ውሳኔ የሚሹትን ከድርጅታዊ ጉባዔዎች ጋር፤ የመንግስት ውሳኔን የሚጠይቁትን ደግሞ ከአጭርና የመካከለኛ ጊዜ እርምጃዎች ጋር እያገናዘቡ መንግስትን ማስጨነቅ በራሱ ዴሞክራሲያዊነት ነው።

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለአስራ ሰባት ቀናት ባደረገው ግምገማ በየደረጃው ባሉ የአመራር እርከኖች በተለይ ደግሞ በከፍተኛው አመራር ደረጃ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ እጦት ስር እየሰደደ እንደመጣ አረጋግጧል፡፡ ይህም ሐሳብ በነፃነት የሚንሸራሸርባቸውን የመታገያ መድረኮች የሚገድብና የሚያጠብ ስለዚም ደግሞ በአመራሩ ውስጥ የአመለካከትና የተግባር አንድነትና ጥራት እንዳይፈጠር መሰናክል ሆኖ እንደቆየ ተመክልቷል፡፡ ይህ ችግር በዋነኛነት በድርጅቱ ከፍተኛ አመራር ደረጃ ከታየው የተዛባ የስልጣን አተያይና አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የተከተሰተ ሲሆን ችግሩ የድርጅቱን አይነተኛ መለያ የሆነውን ዴሞክራስያዊነት በማዳካም ሳይወሰን ስልጣን የህዝብ መገልገያ እንዲሆን የተጀመረውን መልካም ጉዞ ለአደጋ ያጋለጠ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህ ደግሞ እስረኞችን ከመፍታትም በላይ ስለምህዳሩ መስፋት ትልቅ ስራ የሚጠይቅ መሆኑንም ታሳቢ ያደረገ ግንዛቤን መያዝ ከህዝብ ይጠበቃል።

ዴሞክራሲ እየጠበበ አድርባይነት በመስፋፋቱ ምክንያት በግልጽነትና በመርህ ላይ ተመስርቶ ከመተጋገል ይልቅ መርህ አልባ ግንኙትና አካሄድ ማስፈን የተለመደ ስልት ወደመሆን መሸጋገሩን ገዥው ፓርቲ አምኗል፡፡ ይህን የመሰለው በጠባብ ቡድናዊ ጥቅሞች ላይ የተመሰረተ መርህ አልባ ግንኙነት ኢህአዴግና አባል ድርጀቶቹን የማዳከም ውጤት አስከትሏል፡፡ ልማታዊ መንግስትታት በጠንካራ ዲስፒሊንና የሃሳብና የተግባር አንድነት የሚታወቁ ሆኖ እያለ ተገቢ ባልሆኑ ጥቅሞች ላይ የተመሰረቱት የቡድን ትስስሮች ልማታዊ መንግስቱና ድርጅቱ ተልእኮአዋቸውን በብቃት እንዳይፈፅሙ ከፍተኛ መሰናክል ሆኖ እንደቆየ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አረጋግጦአል፡፡ ይህም በተመሳሳይ እስከታችኛው የድርጅት መዋቅር የሚዘልቅ ሰፊ ስራ የሚጠይቅና ጊዜ የሚያስፈልገው መሆኑንም ታሳቢ ያደረገ መጠበቅ ያስፈልጋል።  

በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ግምገማ መሰረት ማንኛውም መርህ አልባ ቡድናዊ ትስሰር ከምንም ነገር በፊትና በላይ እያንዳንዱን ብሄራዊ ድርጅትና በእሱም የሚመራውን ህዝብ የሚጎዳ አደገኛ ጉደይ ነው፡፡ በመቀጠልም በግንባሩ የሚመራውን የጋራ ትግልና አገራዊ የለውጥ ሂደቱን ለአደጋ የሚያገልጥ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በየትኛውም ክልል ሆነ ብሄራዊ ድርጅት ውስጥ የሚከሰቱ መርህ አልባ ጉድኝቶች በጥልቅ እየተፈተሹ ሊወገዱ እንደሚገባ ወስኗል፡፡ ይህንን በጥልቀት ለመፈተሽ ደግሞ በወራት የሚቆጠር ጊዜ የሚጠይቅ እንደሆነ መረዳትም ያስፈልጋል።

እንደሚታወቀው በአገራችን የሚገነባው ፌዴራላዊ ስርዓት መላ የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች ለዘመናት ያካሄዱት ትግል ውጤት ነው፡፡ አዲሲቱ ኢትዮጵያ ከየትኛውም ህብረብሄራዊ አገር የምትለየው በዝሃነትን በማወቅና በማክበር ነው፡፡ ለ26 አመታት የተገነባው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የቋንቋ፣ የባህል፣ የታሪክ እኩልነትን አረጋግጧል፡፡ የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ካልሆነ በቀር በሌላ የማይተዳደሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በፊዴራላዊ አስተዳደራዊ ስርአታችን በእኩልነትና በመተሳሰብ የሚሳተፉበትን ሁኔታም አመቻችቷል፡፡ በዚህ የተነሳ ስርዓቱ ለበላይነትና የበታችነት የማይመች ሆኖ ተዋቅሯል፡፡ በተግባርም እኩልነት እንጂ የባላይነትም ሆነ የበታችነት የማይፈጠርበት ስርዓት ተገንብቷል፡፡ ይህንን መሰረታዊ መርሆ የሚነካ ማንኛውም ዝንባሌ የበላይነትን በዘላቂነት ሊፈጥር የማይችልና ከመናቆር ውጭ ሌላ ውጤት የማያስገኝ እንደሚሆንም ይታመናል፡፡ በመሆኑም በማንኛውም ሽፋን ይህንን የእኩልነት ስርዓት ለማዳከም የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት እንደሌለውና ሊመከት እንደሚገባው መወሰኑም ተገልጿል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአንድ ወይም በሌላ ብሔር ህዝብና ድርጅት ስም እየማሉና እየተገዘቱ ጥገኛ ፍላጎታቸውን ለማርካት የሚንቀሳቀሱ ወገኖችን እንቅስቀሴ ማክሰም እንደሚገባ ስምምነት ላይ መደረሱም በተመሳሳይ ተገልጿል፡፡ ሁሉም ብሔራዊ ድርጅቶች በሚያስተዳድሩት ክልል ውስጥ ያሉ ጥገኞችን ያለልዩነትና ማመንታት መታገል እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ እነዚህን ጥገኞች የማጥራቱ ነገር ደግሞ እንደምናስበው ቀላል አይደለም። የሁሉንም ተሳትፎ ከመጠየቅ በላይ ስልታዊ አካሄድን ይጠይቃል። አንዳንዶች እንደሚሉት ለእርምጃ መቸኮል ደህናውንም ከማስቀየም አልፎ አቅም በፈጠረው ጥገኛ ተመልሶ መመታትም ሊያጋጥም እንደሚችል ማጤን ያስፈልጋል። ስለሆነም ዘላቂነት ላለው ሰላም ከዚህም ለሚገኘው ልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የውሳኔዎቹን ደረጃ ታሳቢ ያደረገ ጥያቄና ሙግት እንጂ በነሲብ የጥቅል ጥያቄና ሙግት የትም አያደርስም። ስለዚህ፣ ጠበበ የሚባለውን የፖለቲካና ዲሞክራሲ ምህዳር ለማስፋት እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት መሰረታዊ ናቸውና መንግስትና ህዝብ በእነሱው ላይ ሊያተኩሩና በጋራ ሊረባረቡ ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy