Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሠላምና ሕዝብ…

0 239

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሠላምና ሕዝብ…

አባ መላኩ

ለሠላም ሲባል በተደጋጋሚ  አዋጅ ሊታወጅ ይችላል። ነጋሪት ሊጎሰም ይችላል። በእነዚህ ጉዳዮች ብቻ በዘላቂነት ሠላምን ማስፈን ይቻላል ተብሎ አይታሰብም። እነዚህ ጉዳዮች ምናልባት ጊዜያዊ መፍትሄ ሊያመጡ ይችሉ ይሆናል። ዘላቂ ሠላምን እውን ማድረግ የሚቻለው በህዝብ ንቁ ተሳትፎ ነው። ለአገሪቱ ሠላም መረጋገጥ መሠረቱ ህዝቡ ነውና።

ስለዚህ የአገሪቱ ሠላም በአጭር ጊዜ ወደነበረበት እንዲመለስ ኅብረተሰቡን በከፍተኛ ደረጃ ማሳተፍ ያስፈልጋል። ከዚህ ቀደም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ እያንዳንዱ ዜጋ የየአካባቢውን ሠላም በመጠበቅ ለአዋጁ ስኬታማነት ያበረከተው አስተዋጽኦ የሚታወስ ነው፡፡

የአንድ አገር ሠላም የሚጠበቀው በህዝብ ንቁ ተሳትፎ ጭምር እንጂ በጦር ኃይል ብዛት ብቻ አይደለም። ስለ ሠላም በሚደረጉ ማናቸውም ክንዋኔዎች ውስጥ የህዝቡ ተሳትፎ ግንባር ቀደሙን ሥፍራ ይይዛል። የአገሪቱንና የህዝቦቿን ሠላምና መረጋጋት የማይሹ የውጭ ኃይሎችና ተላላኪዎቻቸው የፈፀሙት ፀረ ሠላም ድርጊት የት ድረስ እንደ ዘለቀ ከህዝቡ የተሰወረ አይደለም። ህዝብ ሁሌም ከማንኛውም ተግባር ቀድሞ ግራና ቀኙን ያያል። ህጋዊ አካሄዶችን ያጤናል ይፈትሻል። አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖቹን ይመረምራል። ከዚያም ሚዛናዊ ውሣኔን ይሰጣል። የቆየ ልማዱም ይኸው ነው።  

ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ ስለሠላም የዘመረ፣ ስለሠላም የሰበከ፣ ስለሠላም ያቀነቀነ አለ ቢባል እሞግታለሁ። የኢትዮጵያ ህዝብ ስለሠላም እጅግ ብዙ ዋጋ ከፍሏል። መንግሥት ሠላምን በተመለከተ አንድ ርምጃ በወሰደ ቁጥር ህዝቡ የጉዳዩ ባለቤት ሆኖ ቀናኢነቱን በተግባር አረጋግጧል። ሕዝቡ በየአካባቢው የሠላሙ ባለቤት ሆኖ የሚንቀሳቀሰውም ለዚሁ ነው።

እንደሚታወሰው የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በውጭ ኃይሎችና በውስጥ ተላላኪዎቻቸው ቅንጅታዊ እኩይ ሴራ ሁከት ተፈጥሮ ነበር። ሁከቱን በቁጥጥር ሥር ማዋል እንዲቻልም በህገ መንግሥቱ መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ ነበር። አዋጁም በወቅቱ ሠላሙን ተነጥቆ በነበረው ህዝብ ሙሉ ድጋፍ ስለነበረው አፋጣኝ ምላሽ አስገኝቷል። በአጭር ጊዜ ውስጥም መንግሥት ከህዝቡ ጋር በመሆን የተፈጠረውን ሁከት በቁጥጥር ሥር ማዋል ችሏል። የሁከቱ ተሳታፊ የነበሩ ወገኖችም የተሃድሶ ትምህርት ተሰጥቷቸው የበደሉትን ሕዝብ ለመካስ ቃል ገብተው ወደየአካባቢዎቻቸው መመለሳቸውም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።  

ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ችግሩ ዳግም አገርሽቶ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ የሚደረጉ ሁከቶችና ብጥብጦች በመበራከታቸው ከፍተኛ የሆነ የምጣኔ ሀብት ጉዳት ደርሷል፡፡ ዜጎች ከቦታ ቦታ በነፃነት መንቀሳቀስ አልቻሉም፡፡ የመንግሥትና የሕዝብ ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል፡፡ የኢንቨስትመንት ተቋማትም ከጥቅም ውጪ ሆነዋል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዓርብ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. በድጋሚ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡ አዋጁ የታወጀው በመደበኛው የሕግ አግባብ የአገሪቱን ሁለንተናዊ ሠላም ማረጋገጥ፣ በየአካባቢው የሚጠፋውን የሰው ሕይወትና የሚወድመውን የግልና የመንግሥት ንብረት ማስቆም ስላልተቻለ ነው፡፡

በአስቸኳይ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ከተከለከሉ ጉዳዮች መካከል ዋና ዋናዎቹ የአገሪቱን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ጽሑፍ ማዘጋጀት፣ ማተምና ማሰራጨት፣ እነዚህን ጉዳዮች የያዙ መልዕክቶችን ማስተላለፍ፣ በቡድን መደራጀትና በአደባባይ ሰልፍ ማድረግ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከሚወሰዱ ርምጃዎች መካከል የሰዓት እላፊ፣ በወንጀል ድርጊት የተሳተፉ ግለሰቦችን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝ፣ ማንኛውንም ሰው መፈተሽ፣ ሰዎችን ከተወሰነ ቦታ ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ፣ የጦር መሣሪያና ሌሎች ስለታማ ነገሮችን ግለሰቦች ይዘው እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ፣ በብሔር ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን ማቋቋም፣ መሠረታዊ ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን መቆጣጠር፣ መደበኛ ሥራን የሚያስተጓጉሉ እንከኖች እንዳይከሰቱ ማድረግና ሌሎች ርምጃዎች ይጠቀሳሉ፡፡

ህዝብ ከሁከት ፈጣሪዎች፣ ከአሸባሪዎችና ከግጭት ቀስቃሽ ኃይሎች ጎን እንደማይቆም ደጋግሞ አረጋግጧል። አጥፊዎችን በማጋለጥ የርምት ርምጃ እንዲወሰድባቸው ሙሉ አቅሙን ተጠቅሟል። ታዲያ እዚህ ላይ የህዝቡ የማይተካ ሚና አድናቆት ሊቸረው ይገባል። ይህም ማንኛውም አዋጅ ያለ ህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ ተፈፃሚ ሊሆን እንደማይችል የሚያሳየን ቁም ነገር ነው።

ሁልጊዜም ለሚደነገጉ ህጎችና ደንቦች ተፈጻሚነት ግንባር ቀደም ዋነኛ ተዋናይ የሚሆነው ህዝብ ነው። ህዝብ በማንኛውም መመዘኛ ሠላሙን ተፃርሮ አይቆምም። ለሠላሙ መረጋገጥ ፀረ ሠላም ኃይሎችን በማጋለጥ ለህግ እንዲቀርቡ ያደርጋል። አጥፊ ኃይሎች ከድርጊታቸው ተቆጥበው ወደ ሠላማዊ ህይወት ለመመለስ ጽኑ ፍላጎት ሲያሳዩ ህዝብ ድጋፍና እገዛውን ይቸራቸዋል። ይህ ተግባር ኅብረተሰቡ ለዘላቂ ሠላም የቱን ያህል የፀና አቋም እንዳለው ማሣያ ነው።

ሕዝቡ የወደፊት ዕጣ ፈንታውን የሚወስነው አገሪቱ የምትከተለውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር አጥብቆ በመያዝ ነው።  የሠላምን ዋጋ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ዘወትር ከሠላም ወዳድ ኃይሎች ጎን ይቆማል።

ዛሬ ህዝቡ በየቀየው ላለው የሠላም ሁኔታ ዋነኛ መሠረት ሆኗል። በየአካባቢው የሚፈጠሩ ፀረ ሠላም እንቅስቃሴዎች መልሰው ራሱኑ እንደሚጎዱት ጠንቅቆ ስለሚገነዘብ  ለሠላሙ መረጋገጥ ይበልጥ መትጋትን መርጧል። ሠላምን የሚያጎድሉ፣ ልማትን የሚያደናቅፉና ግጭትን የሚያባብሱ መስመሮችን ጠራርጎ በመጣል የሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተፈጻሚ በማድረግና በፀረ ድህነት ላይ የተጀመረውን ዘመቻ በማቀጣጠል ጉዞውን ቀጥሏል። ሕዝቡ በሁሉም አቅጣጫ ከልማቱ በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ተፈላጊውን የዕድገት ራዕይ ሰንቆ እየተጓዘ ነው።  

በቅርቡ በተወሰኑ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከመልካም አስተዳደር ችግሮች ጋር በተያያዘ እንዲሁም ፅንፈኛ ኃይሎችና የአገራችንን መለወጥ የማይሹ ቡድኖች በሚያሴሩት ሽረባ  የተከሰተውን ሁከት ለመቋቋም ሕዝቡ በባለቤትነት ስሜት የከፈለው መስዋዕትነት በቀላሉ አይታይም። ይህ የሕዝቡ ስሜት የመነጨው የሠላም ዋጋ በምንም ሊለካ እንደማይችል ካለፉት ተጨባጭ ሂደቶች ስለተማረ ነው።

በእርግም ከተግባር የበለጠ ትምህርት ቤት የለም። ሕዝቡ የሠላሙ ዘብ ነው። ሁከቱን ለመቀልበስ በአገሪቱ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ የህዝቡን ሠላምና ፀጥታ ለማረጋገጥና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል ሲባል ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን ቆሞ ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል። ይህ አበረታች ውሣኔና ርምጃ ነው። በአገሪቱ ላይ ተደቅኖ የነበረው አደጋ እንዲቀለበስ ለማድረግ በተደረገው ርብርብ የህዝቡ ሚና ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።  

የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፉት 27 ዓመታት ያለፈባቸው የልማት ውጣ ውረዶች የሚቀራቸው ውስን ተጨባጭ ለውጥ ቢኖርም፤ ከትናንቱ በተሻለ ቁመና ላይ እንደሚገኙ ግን ግልጽ ነው።

ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ከተቀረፁ፣ ሕዝቡን ከዳር እስከ ዳር የሚያንቀሳቅስ ልማታዊ መንግሥት ካለና በዚሁ መሪ አካል አስተባባሪነት ብሎም በሕዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚዘወር ሠላም እስካለ ድረስ፤ ሰርቶ መለወጥና ማደግ እንደሚቻል ጠንቅቆ የሚያውቅ ሕዝብ ተፈጥሯል። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለሠላሙ መስፈን ድምጹን ከፍ አድርጎ ይዘምራል። በየአካባቢውም የሠላሙ ዋስና ጠበቃ ሆኖ ይንቀሳቀሳል። ይህ የነበረና ያለ አኩሪ ተግባሩ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy