Artcles

ሠላም ሲጠፋ መመለሻ መንገዱ ይርቃል

By Admin

February 02, 2018

ሠላም ሲጠፋ መመለሻ መንገዱ ይርቃል ኢብሳ ነመራ ሰላም ለሰው ልጆች ሁሉ የመኖር ዋስትና ነው። ሰላም በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ተግባር ውስጥ ከምንተነፍሰው አየር ያልተናነሰ ዋጋ አለው። በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው የሃገሪቱ አካባቢ ሰላምና መረጋጋት ይታያል። ወትሮ ቦግ እልም ይል የነበረው በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ያጋጥም የነበረ ተቃውሞና ሁከት ተረጋግቷል። የደቡብ ኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፤ የትግራይ፤ የአፋር፤ የኢትዮጵያ ሱማሌ፤ የቤኒሻንጉል ጉምዝ፤ የጋምቤላና ሃራሪ ክልሎች እንደወትሮው ሁሉ ሰላምና መረጋጋታቸው እንደቀጠለ ነው። ሰሞኑን የሁከትና ግጭት ዜና የተሰማው ከወደ አማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ፣ ቆቦና መርሳ ከተሞች ነው። የተቀረው የአማራ አካባቢ ሰለም ነው። በአጠቃላይ ሃገሪቱ አማን ነች ማለት ይቻላል። ሁከትና ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎችም ቢሆን ግጭቱ ትኩረት ያደረገው በከተሞች ላይ ነበር። አርሶ አደሩ ከተሞች ሲታመሱ ገበያ አልቆም እያለ ከመቸገሩ ያለፈ የሁከትና የግጭት ተሳትፎ አልነበረውም። የሰሞኑን የሰሜን ወሎን ግጭት ጨምሮ እያንዳንዱ ግጭትና ሁከት ለንብረት መውደምና ለዜጎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኖ ቆይቷል። በመሆኑም የዜጎች ተጠቃሚነትና የሃገሪቱ እድገት የውድመቱን ያህል ወደኋላ እየተጎተተ ይገኛል። በዚህም ዜጎች የእለት እንጀራ ከሚያገኙበትና ቤተሰብ ከሚያስተዳድሩበት ስራ ውጭ ይሆናሉ። የመንግስት አገልግሎትና የማህበራዊ አገልግሎቶችም ይስተጓጎላሉ። ህዝብ የፍትህና የልማት ተጠቃሚነቱ ካልተረጋገጠ ለተቃውሞ መውጣቱ ተገቢ ነው። ይሁን እንጂ የመንግስት የአፈጻጸም ችግር ህዝብ ላይ የፈጠረው መከፋት ወደ ቁጣ ተቀይሮ በተለያዩ አቅጣጫዎች አፈትልኳል። ይህ ቁጣ ደግሞ ህዝብን ሊጎዳ የሚችል ውጤት አስከትሏል። በዚህም የኢኮኖሚያዊና የማህበራዊ ልማት፣ የስራ እድል ጥያቄ ያነሱ ወጣቶች ከጥያቄያቸውና ፍላጎታቸው በተቃራኒ ተንቀሳቅሰዋል። እናም ለበርካታ ወገኖቻቸው የስራ እድል የፈጠሩ ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን አውድመዋል። እናቶች የሚገላገሉበትን፣ ህጻናት የሚታከሙባቸውን የጤና ተቋማት፣ የውሃና መሰል መሰረተ ልማቶችን አውድመዋል። ከዚህ ያለፈ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ጥቁር ነጥብ ጥሎ የሚያልፍ አስከፊ ሁኔታም አጋጥሞናል። በተደጋጋሚ ሲገለጽ እንደቆየው፣ ከ2008 መግቢያ ጀምረው ሲያጋጥሙ የነበሩ የነዚህ ተቃውሞዎች መነሻ የመንግስት የአፈጻጸም ችግር መሆኑ እሙን ነው። በሃገሪቱ ዜጎች ከመንግስት ተቋማት ተገቢ አገልግሎት ማግኘት አይቻልም ብለው ተስፋ እንዲቆርጡ እስከማድረግ የዘለቀ የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ነበሩ። ከአነስተኛ እስከ ትላልቆቹ የሃገሪቱ ከተሞች ከወጣቶች ቁጥር እድገት ጋር የሚመጣጠን የስራ እድል መፍጠርም አልተቻለም። ከተሞች በውስጣቸው ያደጉና ከገጠር የፈለሱ የተለያየ የትምህርትና የሞያ ደረጃ ያላቸው ስራ አጥ ወጣቶች መናኸሪያዎች ለመሆንም በቅተዋል። በከተሞች ዙሪያ የሚኖሩ አርሶ አደሮች በልማት ምክንያት የኑሯቸው መሰረት ከሆነው ይዞታቸው ሲፈናቀሉ ዘላቂ ህይወታቸውን ታሳቢ ያደረገ ካሳ አይከፈላቸውም። ፍርድ ቤቶች ፍትህ የሚገኝባቸው ሳይሆኑ የፍርድ ውሳኔ የሚሸጥባቸው መደብሮች መስለው ነበር። ይህ ደግሞ ፍትህን ለሚፈልግ ማንኛውም ዜጋ ያማል፣ ያስከፋል፣ ያስቆጣል። እርግጥ ነው መንግስት እነዚህን ህዝቡን ያማረሩ ችግሮችን ተገንዝቦ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ወስኖ ነበር። ይሁን እንጂ መንግስት የመልካም አሰተዳደር ችግሮችን ለማቃለል፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማዳከም ህዝባዊ ንቅናቄ አውጆ ገና አንድ እርምጃ ሳይራመድ፣ ችግሩ ተብላልቶ ነበርና ድንገት ገንፍሎ በተለያዩ የሃገሪቱ ከተሞች በተለይም በኦሮሚያ አደባባዮች አፍራሽ ተግባራት የተቃውሞ መገለጫዎች ሆነው ታይተዋል። ከዚያ በኋላ በተለይ በአማራና በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎችም የተለያዩ ለኳሽ ምክንያቶችን መነሻ በማድረግ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል። ህዝብ ላይ የተፈጠሩ ተገቢ ቅሬታዎች ወደ አውዳሚ ሁከትነትና የእርስ በርስ ግጭትነት መቀየራቸው የህዝቡ ፍላጎት አይደለም። በሰከነ ሁኔታ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ውድመቱንና ግጭቱን አይደግፈውም። አውዳሚ ሁከትና ግጭት የሚፈጠረው የቁጣ ስሜት በምክንያት ልጓም አልመራ ሲል ነው። በተለይ በግል ማመዛዘን በማይቻልበት ቡድናዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ውስጥ ስሜት ለምክንያት ልጓም በማይበገርበት አኳኋን ይበረታል። ይሄኔ ለምክንያት የማይበገረውን ሸምጣጭ ስሜት በመነካካት ለተለየ ዓላማ መጠቀም ቀላል ይሆናል። መሸምጠጥ የጀመረ ስሜት ጠላትህ ነው ብለው ያመላከቱትን ሁሉ ነው የሚጨፈልቀው። ወገንና ጠላቱን፣ የሚወስዳቸው እርምጃዎች ነገ በራሱና በሃገሩ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ወዘተ እየመዘነ የሚመራበት ምክንያታዊነቱ ይሰንፋል። በዚህ ሁኔታ በቀጥታ የጥቃት በትር መሰንዘር የማይችል የሃገርና የህዝብ ጠላት በትር የሚሰነዝርበት ቀኝ እጅ ያገኛል። ሃገር በራሷ ልጆች እንድትመታ ያደርጋል። ይህ በሃገራችን በተጨባጭ ታይቷል። አሁንም ከዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳልወጣን የሚያመለክቱ እውነታዎች አሉ። ለምሳሌ፣ ከዚህ ቀደምም በተለያየ አጋጣሚ ተሞክሮ ግቡን ሳይመታ የከሸፈ፣ አሁንም እየተሞከረ ያለውን የብሄር ግጭት የመፍጠር ቅስቀሳ ለዚህ አስረጂነት ማንሳት ይቻላል። በደረሰበት በደል የከፋውንና ተቆጥቶ የተነሳን ህዝብ፣ ጠላቱ አብሮት የሚኖረው የሌላኛው ብሄር ተወላጅ እንደሆነ አስመስሎ በመቀስቀስ የብሄር ግጭት ለመፍጠር ሙከራ ሲደረግ ቆይቷል። በአኙዋክና በኑዌር፣ በአማራና በኦሮሞ፣ በአማራና በትግራይ፣ በኦሮሞና በኢትዮጵያ ሱማሌ፣ በጉራጌና በጌዲኦ ወዘተ መካከል ግጭቶች ለመፍጠር የተደረገውን ሙከራ ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል። ይህ ሙከራ በተወሰነ ደረጃ ተሳክቷል። ብዙዎች በእርስ በርስ ግጭት ህይወታቸውን አጥተዋል፣ ከኑሯቸው ተፈናቅለዋል፣ ንብረታቸውን አጥተዋል። ሰሞኑን በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ከተሞች የምንመለከተው በትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ቅስቀሳና ጥቃት የዚሁ አካል ነው። ጥቃቱን የሚፈጽሙት ቡድኖች ይህን የሚያደርጉት የትግራይ ተወላጆች በአካባቢያችን ከሌላው በተለየ ተጠቃሚ ሆነዋል ብለው እንዲያምኑ ስለተደረጉ ነው። በኦሮሚያ ውስጥ አማሮች ላይ ጥቃት ሲሰነዘርም ይሄው ነው ሲደረግ የነበረው። 2009 መግቢያ ላይ ዲላ ላይ መጤ በተባሉ ዜጎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ተመሳሳይ መነሻ ነበረው። እርግጥ ነው የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ጥቂት ጥገኞች በተለይ የህወሃት አባላት የመንግስት ስልጣን ማግኘት በቻሉበት አዲስ አበባ ያልተገባ ጥቅም አግኝተዋል። የሃገር ልጅነት በፈጠረው መተማመን በጥቅም ተሳስረው በኮንትሮባንድ ንግድ የበለጸጉ አሉ። ይህም ቢሆን ግን በተለይ በትግራይ ተወላጆች ዘንድ ብቻ የታየ አይደለም። የየትኛውም ብሄር አባላት የሆኑ ጥገኞች ውስጥ ታይቷል። ሰበታ ላይ በመንደር ተቧድነው የቶሌ ልጆች፣ የወለጋ ልጆች . . . እየተባቡ የአርሶ አደሩን መሬት የቸበቸቡት ጥገኛ የኦሮሞ ልጆች መሆናቸውን አስታውሱ። በመሰረቱ አሁን በኢትዮጵያ ባለው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው በሚያስተዳድሩበት ሁኔታ፣ አንድ ብሄር ሌላውን ሊጨቁን ወይም በሌሎች መስዋዕትነት ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም። ጥገኛ ግለሰቦች ግን የማይገባቸውን ጥቅም የሚያገኙበት ሁኔታ አለ። እነዚህ ጥገኞች ደግሞ ከየትኛውም ብሄር ሊሆኑ ይችላሉ። እናም ተጠቃሚነት ያሳጣችሁ የዚህኛው ብሄር ተወላጅ ነው በሚል የሚካሄድ የጥላቻ ቅስቀሳ መድረሻው የእርስ በርስ ግጭት በመፍጠር ሃገሪቱን ማፍረስ ነው። በተለይ ትግራይና ህወሃት ላይ አተኩሮ የሚነዛ የጥላቻና የጥቃት ቅስቀሳ፣ ኢትዮጵያን ማተራመስ የእድሜ ልክ ስራው አድርጎ ከተነሳው በአንድ ግለሰብ ከሚመራው የኤርትራ መንግስት የተሳሳተ ስሌት የመነጨ ሴራ መሆኑን የሚያመለክቱ አስረጂዎች አሉ። በአንድ ሰው የሚመራው የኤርትራ መንግስት፣ ህወሃትን እጅግ አግዝፎ ነው የሚመለከተው። ህወሃት ኢትዮጵያ ውስጥ በተጋነነ ግምት አራት ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ የሚገመተውን የትግራይ ክልል እንደሚያስተዳድርና የሃገሪቱ ትልቁ የስልጣን አካል የሆነው 547 መቀመጫዎች ያሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ 38 መቀመጫዎች ብቻ ያሉት ፓርቲ መሆኑን የሚያውቅ አይመስልም። በአንድ ሰው የሚመራው የኤርትራ መንግስት ህወሃት ከተመታ ኢትዮጵያን ማፍረስ ቀላል ነው ወይም ሌሎቹን ተቆጣጥሮ መንዳት ይቻላል የሚል እጅግ የተሳሳተ ግምት አለው። እናም የኤርትራ መንግስት፣ ካስጠለላቸው የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ነን ባይ ቡድኖች ጋር በመተባበር የሚነዛው ትግራይና ህውሃት ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ቅስቀሳና የጥቃት ዘመቻ ከዚህ የተሳሳተ ስሌት የመነጨ ኢትዮጵያን የማፍረስ ዓላማ ያለው ነው። እርግጥ ከሃያ ዓመት በፊት የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ሲዋቀር፣ በተቻለ መጠን የሃገሪቱን የብሄር ስብጥር ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ለማድረግ ቢሞከርም፣ በተግባር የተፈተነ ሃገርን የመከላከል ብቃት ያለው ሰራዊት ለመገንባት ሲባል በትግል ውስጥ የዳበረ ብቃት የነበራቸው የትግራይ ተወላጆች ቁጥር በዛ ብሎ የታየበት ሁኔታ መኖሩ አይካድም። ይህ ምናልባት እስካሁንም በከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ውስጥ የትግራይ ተወላጆች ጎላ ብለው የታዩበትን ሁኔታ ፈጥሯል። ይህ ግን የሃገሪቱን ደህንነት ማስከበር የሚችል በተግባር የተፈተነ ብቃት ያለው መከላከያ ሰራዊት መገንባትን ዓላማ ያደረገ እንጂ የአንድ ብሄር የበላይነትን የማስፈን ዓላማ ያለው አልነበረም። ይህም ቢሆን አሁን ተቀይሯል። ሰራዊቱ ከተዋቀረ በኋላ የተቀላቀሉትና አሁን እጅግ አብላጫውን የሰራዊቱን ክፍል የሚወክሉት የመስመር ወታደሮችም ይሁኑ መኮንኖች ቁጥር የሀገሪቱን የብሄሮችና ብሄረሰቦች ቁጥር መሰረት ያደረገ ነው። እንግዲህ ቀደም ሲል እንደተነሳው የኢትዮጵያ ህዝብ በመንግስት አፈጻጸም ችግርና በኪራይ ሰብሳቢነት የደረሰበትን በደል መቃወሙ ተገቢ ነው። ነገር ግን ተቃውሞ የሚያቀርብበት መንገድ ፍፁም ሰላማዊና ጤናማ በሆነ መንገድ ሊሆን ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ህዝብ የሚጠቀምባቸውን የልማትና የመንግስት አገልግሎት ተቋማት ማውደም ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም። የችግር ምንጭ አብሮን የሚኖር የሌላ ብሄር አባል የሆነ ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ተደርጎ የሚቀርበውም ቅስቀሳ፣ በእርስ በርስ ግጭት ሃገሪቱን የማፍረስ ዓላማ ያለው የጠላት ስልት መሆኑን ማሰብ ብልህነት ነው። ይህ ሌላውን ብሄር ተጠያቂ አድርጎ በማቅረብ የማጋጨት የጠላት ስልት አንድ ቦታ ከተሳካ በሌላም ቦታ፣ በሌሎች ብሄሮች መሃከል መቀጠሉ አይቀሬ ነው። ዓላማው ሃገሪቱን በእርስ በርስ ግጭት ማተራመስ ብቻ ስለሆነ ተጋጮቹን አይመርጥም። የተለያዩ ብሄሮች አብረው በሚኖሩበት ቦታ ሁሉ ይቀጥላል። በዚህም ሰላም ከሃገሪቱ ምድር እየራቀ፣ እየራቀ . . . ይሄዳል። ግጭት ቀጠናውን እያሰፋ ሰላም በራቀ ቁጥር ወደ ሰላም መመለስ እየከበደ ይመጣል። በሰላም እጦት ክፉኛ ከተጎዳን በኋላ ቆም ብለን ወደነበርንበት ለመመለስ ብንሞክር በቀላሉ የሚሳካ እንዳልሆነ ከወዲሁ እናስብ። ሰላም ሲጠፋ መመለሻ መንገዱን በብዙ እጥፍ እያራቀው እንደሚሄድ ተጓዥ ነው። ሶሪያውያን፣ ሊቢያውያን . . . አሁን ሰላማቸውን መመለስ ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ የሰላም መመለሻው መንገድ በብዙ እጥፍ ከመራቁም በላይ ፈርሷል፤ ተፈረካክሷል። መንገዱን መገንባት እንደማፍረሱ በአጭር ጊዜ የሚሳካና ቀላል አይደለም። እናም በግጭት ሰላማችንን አባረን ማጣፊያው እንዳያጥረን በስሜት የማይሰንፍ የምክንያት ልጓም ይኑረን።