ሠላም በህዝብ ባለቤትነት ይመራል!!
አባ መላኩ
አዋጅ ቢወጣ ነጋሪት ቢጎሰም ምናልባት ጊዜያዊ መፍትሄ ሊያመጣ ይችል ካልሆነ በቀር ዘላቂ ሠላምን ከቶ እውን ማድረግ አይቻልም። ለኢትዮጵያችን ሠላም መረጋገጥ መሠረቱ ዜጋው ነው። በመሆኑም የአገራችን ሠላም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደነበረበት ቦታ እንዲመለስ ከተፈለገ መላው ህዝብ ለሠላም ያለውን ፅኑ ፍላጎት መሠረት አድርጎ መሰራት ይኖርበታል። በተለያዩ ወቅቶች ህዝቡ የየአካባቢውን ሠላም በመጠበቅ ረገድ ያሳየው ኃላፊነትን በተገቢው የመወጣት እንቅስቃሴ ሁሌም ሊጠቀስ የሚገባው ነው። ይህም ተግባር የሠላሙ ባለቤት ህዝቡ ራሱ ስለመሆኑ መልካም አስረጂ ነው።
የሠላምን ጥቅም ጠንቅቆ የሚረዳ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ህዝብ ከቶ የት አለ። ይህ ህዝብ ለሠላም እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል። ስለ ሠላም በተቀነቀነ ቁጥር ቀድሞ ከሥፍራው የሚገኘው ያለምክንያት አይደለም። የሠላሙ ባለቤት ሆኖ በመጀመሪያው ረድፍ ላይ የሚቆመውም ለዚሁ ነው።
ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ በኢትዮጵያ የተወሰኑ አካባቢዎች በውጭ ኃይሎችና በአገሪቱ የውስጥ ተላላኪዎቻቸው ቅንጅታዊ እኩይ ሴራ ግጭት ተፈጥሮ ነበር። በዚያን ወቅት ሁከቱን በቁጥጥር ሥር ማዋል እንዲቻልም በህገ መንግሥቱ መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ ነበር። ይህ አዋጅም በወቅቱ ሠላሙን ተነጥቆ ለነበረው ዜጋ በባለቤትነት ስሜት ድጋፍ ያለው ስለነበር ከፍተኛ ውጤት ማግኘት ተችሏል።
የአንድ አገር ሠላምና መረጋጋት ዋነኛ ባለቤቱ ሕዝቡ ነው፡፡ የአገሩም ባለቤት ሕዝብ ነው፡፡ ሠላምና መረጋጋት ለአገር ዕድገትና ልማት ያለው ድርሻም ከሁሉም የገዘፈ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደታየው ሠላምና መረጋጋት የሌላቸው የዓለም አገሮች ምን ያህል ለእልቂት፣ ለከፋ ትርምስና ቀውስ እንደበቁ በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ሁኔታ ማየት በቂ ይሆናል።
የሕዝብንና የአገርን ሠላም ለማወክና ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ አክራሪና ጽንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች በተለያዩ የውጭ ኃይሎች በመደገፍና በመታገዝ የጫሩት እሣት አገራትንና ሕዝቦቻቸውን ለእልቂትና ለውድመት ዳርጓቸዋል። በቅርብ ዓመታት በሊቢያ፣ በሶሪያ፣ በየመን እና በግብጽ የተከሰተውን ጥፋት መመልከት ተገቢ ይሆናል።
የውጭ ኃይሎች በአንድ አገር ውስጥ ትርምስና ሁከት እንዲፈጠር ሆን ብለው የዚያችን አገር ዜጎችና ተቃዋሚዎችን ከጎናቸው በማሰለፍና በገንዘብ በመግዛት ብጥብጥና ሁከት እንዲፈጠር፣ ሥርዓተ አልበኝነት እንዲሰፍን፣ ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ውጭ እንዲወጣ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት መግዛትና ማስተዳደር እንዲሳነው ለማድረግ ብዙ ሚሊዮኖች ዶላር በመመደብ የማተራመስ ተግባራቸውን ይከውናሉ፡፡
ሂደቱን በቅርብ በመቆጣጠር አስፈላጊና አመቺ ነው ብለው የሚያምኑበትን አዋጪ የሚሉትን አመጽና ሁከት እንዲቀሰቀስ ወይም እንዲገፉበት የሚያስችል ሥልትና ዘዴ ይቀይሳሉ፤ ይጠቀማሉ፡፡ ይህንን ዘዴያቸውን በበርካታ አገራት ላይ በሥራ ላይ በማዋል ተጠቅመውበታል፡፡ የተሳካላቸው በሌላም መልኩ የወደቁበት ሁኔታም ታይቷል፡፡
የውጭ ኃይሎቹ የአገር ውስጥ የዲያስፖራ ኃይሎችን በመጠቀም የሚያካሂዱት መጠነ ሰፊ ትግል ለአገሬው ሕዝብ ጥቅምና መብት በመቆርቆር አይደለም፡፡ ይልቁንም የራሳቸውን ሰፊ ጥቅም ለማስከበር ከዚያች አገር በዘረፋ ማግኘት ይገባናል ብለው ለሚያስቡት የተፈጥሮ ሀብት ምዝበራ ስኬት የሚያመቻቹ የአገሬውን ሰዎች በመመልመልና በገንዘብ ኃይል በመግዛት ሥምሪት በመስጠት፣ መሣሪያም በማስታጠቅና በማደራጀት የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር መሣሪያና ታማኝ አገልጋይ ይሆኑናል ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡
ህዝቡ ደግሞ በማንኛውም መስፈርት ሠላሙን ተፃርሮ ሊቆም አይችልም። በመሆኑም ለሠላሙ እውን መሆን አጥፊዎችን በማጋለጥ ለህግ እያቀረበ ይገኛል። ህዝቡ ለሠላሙ ምን ያህል ቀናዒ መሆኑን የሚያሳይ ተግባር ነው።
የትኛውም አገር ሠላም በህዝብ ፍላጎት እንጂ በሌላ አይጠበቅም። ስለ ሠላም በሚደረጉ ማናቸውም ክንዋኔዎች ውስጥ የህዝቡ ተሳትፎ ፋና ወጊ ነው። የአገራችንንና የህዝቦቿን ሠላምና መረጋጋት የማይሹ የውጭ ኃይሎችና የውስጥ ተላላኪዎቻቸው የፈፀሙት ፀረ ሠላም ድርጊት የት ድረስ እንደ ዘለቀ ከህዝቡ የተሰወረ እውነታ አይደለም። ህዝብ ሁሌም ከማንኛውም ተግባር በፊት ግራና ቀኝ የሚያይ፣ ህጋዊ አካሄዶችን በማጤንና አሉታዊና አዎንታዊ ጎኑን በመገንዘብ ሚዛናዊ ውሣኔ የመስጠት ባህል ያለው ነው።
ህዝቡ የወደፊት ዕጣ ፈንታው የሚወሰነው አገሪቱ በምትከተለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መሆኑን ስለሚያውቅ ሁሌም ሠላም ወዳድ ኃይሎች ጎን የሚቆም ነው። የሠላምን ጠቀሜታ ስለሚገነዘብም ከምንጊዜውም በላይ ሁሌም በየአካባቢው ለሠላሙ ዘብ እንደቆመ ነው።
ህዝቡ በየመንደሩ ላለው የሠላም ሁኔታ ዋነኛ መሠረት ነው። በዚያ አካባቢ የሚከሰት ማናቸውም የፀረ ሠላም ድርጊት መልሶ የሚጎዳው እርሱን በመሆኑ ለሠላሙ ይበልጥ መትጋት አለበት። እንዲህ ዓይነቱ ሠላምን የሚያጎሉ፣ ልማትን የሚያፋጥኑና ንትርክን የሚያስቀሩ መንገዶችን መከተል ባይቻል ኖሮ፤ የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን እውን ማድረግና ህዝቡም የተጀመረውን የፀረ ድህነት ዘመቻ አጠናክሮ መቀጠል በተሳነው ነበር። ከልማት ዕቅዱም በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ተፈላጊውን የዕድገት ራዕይ ሰንቆ ባልተጓዘም ነበር። አሁን እያለመ ላለውና ከመጀመሪያው ዕቅድ ጋር ተመጋጋቢ የሆነውን ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድንም ባላለመ ነበር።
በዚህ ደረጃ ላይ ሆኖ የተጀመረውን ዕድገት ለማስቀጠልና በዚያውም ልክ ዴሞክራሲው አገር በቀል ፍላጎትን መሠረት ባደረገ መልኩ እንዲጎለብት የተደረገው ጥረት፤ እንዳለ ሆኖ ይህ ህዝብ በአንዳንድ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ውስጥ ከመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ፅንፈኛ ኃይሎችና አገሪቱ እንድትለወጥ በማይሹ አንዳንድ ወገኖች አማካይነት የተከሰተውን ሁከት ለመቋቋም ህዝቡ በባለቤትነት ስሜት የከፈለው መስዋዕትነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ይህ የህዝቡ ስሜት የመነጨውም ከምንም ተነስቶ አይደለም፡፡ የሠላምን እሴት በምንም ሊለካው እንደማይችል ያለፉት ተጨባጭ ሂደቶች ስላስተማሩት እንጂ።
ከተግባር የበለጠ ትምህርት ቤት የለም። ይህ ህዝብ የሠላሙ ዘብ ሆኖ ቆሟል። ሁከቱን ለመቀልበስ በአገራችን የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ የህዝቡን ሠላምና ፀጥታ ለማረጋገጥና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል ሲባል በጎ ጥረቶች ተወስደዋል። የህዝቡ የነቃ ተሳትፎም በአገራችን ላይ ተደቅኖ የነበረው አደጋ እንዲቀለበስ ለማድረግ በተደረገው ርብርብ የህዝቡ ሚና ተዘርዝሮ አያልቅም።
ይህ ሠላም ወዳድ ህዝብ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሠላምን በማወክ ተግባር ላይ የተገኙ ወጣቶችን በመገሰፅ፣ ለሠላም እንዲሰሩና የሠላምን እሴት እንዲያውቁ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በቅርቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ባደረገው ግምገማ ሂደቱን ደረጃ በደረጃ ወደ መደበኛው የህግ ማስከበር የአሠራር ሥርዓት የሚያሸጋግር ለማድረግ የሚያስችል መመሪያ እንዲወጣ በማድረግ ረገድ ህዝቡ ያከናወናቸው የገዘፉ ተግባራት የህዝቡ መገለጫዎች ናቸው።
በአጠቃላይ ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ባለቤት በሆነች አገር ፣ ህዝቡን ከዳር እስከ ዳር የሚያንቀሳቅስ ልማታዊ መንግሥት እስካለና በዚሁ መሪ አካል አስተባባሪነት ብሎም በህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚዘወር ሠላም እስካለ ድረስ፤ ሰርቶ መለወጥና ማደግ እንደሚቻል ህዝቡ ጠንቅቆ ያውቃል። ለዚህም ነው ህዝቡ በየአካባቢው የሠላሙ ዋስና ጠበቃ ሆኖ እየሰራ የሚገኘው። ይህ አኩሪ ተግባሩም ወደፊት ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል።