Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሥርዓቱን ጠባቂው ዘመናዊ ሰራዊት

0 365

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሥርዓቱን ጠባቂው ዘመናዊ ሰራዊት

                                                       ቶሎሳ ኡርጌሳ

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ህገ መንግስቱንና ህገ መንግሰታዊ ስርዓቱን ከማንኛውም የውስጥና የውጭ ፀረ ሰላም ሃይሎችና አሸባሪዎች የመከላከል ህገ መንግስታዊ ተልዕኮን ያነገበ ሃይል ነው። ራሱም ቢሆን ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በፅናት የሚያከብር ዘመናዊ ሰራዊት ነው። ሰራዊቱ በህገ መንግስቱና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ቁርጠኛ አቋም ያለው ህዝባዊና ዘመናዊ ሃይል ነው።

እንደሚታወቀው የአንድ አገር ሰራዊት ዘመናዊነት አንዱ መገለጫ ባህሪ ሰራዊቱ በህገ መንግስቱና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የሚኖረው ቁርጠኛ አቋም ነው። ከዚህ አኳያ መከላከያ ሰራዊታችን ትናንትም ይሁን ዛሬ እንዲሁም ነገም ይሁን ከነገ በስቲያ ሀገርና ህዝብ የጣለበትን የስርዓቱ የመጨረሻ ምሽግ የመሆን ሚና በፍፁም ህዝባዊ ወገንተኝነት የተሰጠውን ተልዕኮ የሚያከናውን ነው።  

“የመከላከያ መርሆዎች” በሚለው የህገ መንግስቱ አንቀፅ 87 (5) ላይ በግልፅ እንደተደነገገው፤ መከላከያ ሰራዊቱ ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነፃ በሆነ አኳኋን ይፈፅማል። ይህም መከላከያ ሰራዊታችን በማንኛውም ጊዜ ለህገ መንግስቱ ተገዥ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ህገ መንግስቱ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከአምባገነኖች ጋር ታግለው በመስዋዕትነታቸው ያገኙት በመሆኑ የሰራዊቱ ተጠሪነት ለመላው የሀገራችን ህዝቦች እንጂ፣ ለተወሰኑ ፖለቲከኞች አሊያም የፖለቲካ ፓርቲዎች አይደለም። ሊሆንም አይችልም።

በአጭር ቋንቋ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ስራቸውን ሲያከናውኑ፣ ሰራዊቱ በፍፁም ጣልቃ አይገባም። እርሱ የሚያከናውነው በህገ መንግስቱ የተሰጠውን የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የማስከበር የውትድርና ሙያን ማከናወን ብቻ ነው። ርግጥ ከሉዓላዊነት ማስከበሩ ባሻገር፤ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለአደጋ የሚያጋልጡ ተግባሮች ጊዜ፤ በህገ መንግስቱ መሰረት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚሰጡትን ተግባሮች ያከናውናል። የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በህዝባዊ መንፈስ የታነፀ እንደመሆኑ መጠን፤ ለእነዚህ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎች ያለው እምነትና ቁርጠኝነት እጅግ የላቀ ነው። ይህም የአንድ ዘመናዊ ሰራዊት መገለጫ ነው። ሰራዊቱ የሚሰራው በእነዚህ ማዕቀፎች ውስጥ ሆኖ እንጂ ህገ መንግስቱን በመፃረር አለመሆኑን ወዳጅም ይሁን ጠላት ሊያውቀው የሚገባ ይመስለኛል።

ርግጥ መከላከያ ሰራዊታችን ዘመናዊና ህዝባዊ ነው። ዘመናዊ ሰራዊት ለሀገሪቱ ህገ መንግስት ታማኝና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በቁርጠኝነት ከማንኛውም አደጋ ለመጠበቅ ኃላፊነት የተሸከመ፣ በዘመናዊ መንገድ የተደራጀ፣ ለህግና ሥርዓት ተገዥ የሆነና ማንኛውንም ተግባራት በሀገሪቱ ህጐች፣ ደንቦች ና መመሪያዎች መሰረት የሚፈፅም ነው።

ዘመናዊ ሰራዊት ለህገ መንግስቱ ታማኝ የሚሆነው የህዝቡ የሉዓላዊ ሥልጣን መገለጫና የሀገሪቱ የበላይ ህግ የሆነውን ህገ- መንግሥት ሲያከብርና ሲያስከብር ነው። ይህንን ኃላፊነት የሚሸከም ኃይል በዋናነት ለህገ መንግስቱና ለህዝብ ሉዓላዊነት ታማኝና ተገዥ ሊሆን የግድ ይለዋል። ከዚህ አኳያ መከላከያ ሰራዊታችን በህገ መንግስቱ የተደነገጉ መርሆችን፣ መብቶችንና ግዴታዎች በሙሉ ልብ የተቀበለ ነው—ያለ አንዳች መሸራረፍ። ሰራዊቱ የሀገሪቱ ህጐች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መነሻቸው ህገ መንግስቱ መሆኑን ስለሚገነዘብና ተልዕኮውም የሚመነጨው ከዚሁ ህገ መንግስት መሆኑን ስለሚያውቅ ታማኝነቱ በፍፁም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም።

በህገ መንግስቱ ላይ እንደተደነገገው፤ ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት ባለሥልጣን፣ የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም የፖለቲካ ድርጅቶች ህገ መንግስቱን የማክበር ግዴታ ተጥሎባቸዋል። ሰራዊቱ ምንም እንኳን እስከ ህይወት መስዋዕትነት የሚደርስ ከማንኛውም ዜጋ ላቅ ያለ ሃላፊነትና ተግባር ያለበት ሃይል ቢሆንም፤ የሀገሪቱ ዜጋ እንደመሆኑ መጠን ህገ መንግሥታዊ ስርዓቱን አክብሮ የመጠበቅ ኃላፊነት የተጣለበት ሃይል ነው። እናም በማናቸውም ጊዜ ህገ መንግስቱን መነሻ አድርገው ለሚወጡ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ተገዥ ሆኖ የመንቀሳቀስ ኃላፊነትና ግዴታ ያለበት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

የዘመናዊ ሰራዊት ሌላው ባህሪ ለህግ የበላይነት ተገዥ የመሆን ጉዳይ ነው። የህግ የበላይነት በማናቸውም ጊዜና ቦታ ህግና ስርዓትን የማነገስና ተግባርንም በዚያው መጠን ማከናወን ነው። ሰራዊቱ በሚሰማራባቸው የግዳጅ ቀጣናዎች ሁሉ የህግ የበላይነትን አክብሮ የመስራት ባህሪን ያጎለበተ አካል ነው። ተልዕኮውን በህግ የሚወሰን፣ በቁርጠኝነትና በታማኝነት ተግባራዊ የሚያደርግ እንዲሁም በአፈፃፀም ወቅት ከግለሰቦች ፍላጐት የነፃ፣ ሁሉንም የህብረተሰብ አካል በህጉ መሰረት በእኩል ዓይን የሚመለከት ብሎም ከማናቸውም አድልኦዎና ልዩነት  በፀዳ ሁኔታ ህግና ስርዓትን ተመርኩዞ ተግባሩን በህዝባዊነት መንፈስ የሚወጣ ኃይል ነው።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት “ዘመናዊ ነው” ሲባል እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ ለማለት ብቻ ሲባል የሚሰነዘር አባባል አይደለም። መገለጫዎቹ አያሌ መሆናቸውን መገንዘብ ያሻል። ምክንያቱም ሁሉም የሰራዊት አባላት ለአንድ ዓላማና ተልዕኮ የተሰለፉና የአስተሳሰብ አንድነት ያላቸው በመሆናቸው ነው።

እነዚህ የዓላማና የአስተሳሰብ አንድነት፤ ሰራዊቱ በሀገርም ውስጥ ይሁን በውጭ የሚሰጡትን ተልዕኮዎች በአግባቡና በላቀ ውጤት ለመፈፀም ያስቻሉት ናቸው። ምክንያቱም ግልፅ ነው—ሰራዊቱ እስካሁን ድረስ የሚነባበት አግባብ በህገ መንግስቱና ህገ መንግስቱን መነሻ አድርገው በሚወጡ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ ያለው እምነት እጅግ በመዳበሩ የተነሳ የጋራ አስተሳሰብ ስለፈጠረ ነው። እናም በሰራዊቱ መካከል ንፋስ እንኳን ማሾለክ የማይችል የዓላማና የአስተሳሰብ ፍፁማዊ አንድነት መኖሩን ማወቅና ተልዕኮውንም እንደ አንድ ሰው መወጣት የሚችል ጠንካራ ኃይል መሆኑን መገንዘብ ከተሳሳተ ድምዳሜ የሚያድን ይመስለኛል። በተለይም ፅንፈኛው ሃይል ‘ሰራዊቱ እንዲህ ሆነ…ምንትስ’ እያለ የሚወራውን የበሬ ወለደ ትረካ የውሸቶች ሁሉ ውሸት መሆን እንዲያውቅ ያደርገዋል ብዬ አምናለሁ።

ምንም እንኳን ፅንፈኛው ሃይል በአንድ አገር ውስጥ የዓላማና የአመለካከት አንድነት ያለው ዘመናዊ ሰራዊትን መገንባት የሚጠይቀውን የጋራ መንፈስ ለመገንዘብ የማይፈቅድ ቢሆንም ቅሉ፤ እንዲህ ዓይነቱ የአንድ ሰው ዓይነት ቁመና ያለው የጋራ አንድነት በዘፈቀደ የሚፈጠር አለመሆኑን ማወቅ ያለበት ይመስለኛል። በአጭር ጊዜ ውስጥ የማይገነባ መሆኑም እንዲሁ። ሰራዊቱ በ1988 ዓ.ም በአዋጅ ሲቋቋም ጀምሮ በተቋሙ ውስጥ በተከታታይነት ሲሰራ የመጣ ውጤታማ የሰራዊት ግንባታ ተግባር ነው ማለት ይቻላል።

ይህም ገና ከጅምሩ ሰራዊቱ ህገ መንግስቱን መነሻ ያደረጉ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች እንዲኖሩት ተደርጓል። እነዚህ ህጋዊ ሰነዶችም ከጊዜና ከሁኔታዎች ጋር እየታዩ ግንዛቤ እየተፈጠሩባቸው የመጡ ናቸው። በመሆኑም ሠራዊቱ ለአንድ ዓላማ በአንድ አስተሳሰብ እንዲታነፅ ማድረግ ተችሏል። በእኔ እምነት ይህን ከባድ ስራ ለተወጡትና ሰራዊቱን በአንድ እስትንፋስ ተልዕኮውን የሚወጣበት ቁመና ለፈጠሩት በየደረጃው የሚገኘው የሰራዊቱ አመራር አድናቆት ሊቸረው የሚገባ ይመስለኛል። በተለይ በአሁኑ ወቅት የሚገኘው የተቋሙ ስትራቴጂካዊ አመራር የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ ነው ብዬ አምናለሁ።

በተለይ መከላከያ ሚኒስቴር እንደ ተቋም በዘመናዊ ሰራዊት ግንባታ ስራው ውስጥ ሰራዊቱ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ሲጠብቅ፤ የራሱ የሆኑ እሴቶችን ተላብሶ እንዲንቀሳቀስ መደረጉ ግዳጁን በአንድ ሰው እስትንፋስ እንዲወጣ ያስቻሉት መሆናቸው አያጠያይቅም። እነዚህ እሴቶቹ በተልዕኮው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ወቅት ሳይሸራረፉ የሚተገበሩ ናቸው። የእሴቶቹ ማጠንጠኛዎች ህገ መንግስቱ፣ ህገ መንግስቱን ተርኩዘው የወጡ ሀገራዊና ተቋማዊ ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች እንዲሁም የህብረተሰቡ እሴቶችና ታሪካዊ ሂደቶች… ወዘተ. ናቸው።

ርግጥ የዚህ ፅሑፍ አንባቢ “እሴቶቹ ምንድናቸው?” የሚል ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል። ጥያቄው ተገቢነት ያለው ነው። በደማቅ ሁኔታ የካቲት 7 ቀን 2010 ዓ.ም ለስድስተኛ ጊዜ ከተከበረው የሰራዊቱ ቀን እንደተገነዘብኩት፤ እሴቶቹ ‘ከራስ በፊት ለህዝብና ለሀገር፣ ምንግዜም የተሟላ ስብዕና፣ ያልተሸራረፈ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ፣ በማንኛውም ግዳጅ/ሁኔታ የላቀ ውጤት’ የተሰኙ ናቸው። እነዚህን እሴቶች እያንዳንዱ የሰራዊት አባል የሚመራባቸው ብቻ ሳይሆኑ በፅናት የሚተገብራቸውም ጭምር ናቸው።

ይህም ሰራዊቱ ራሱን ለህዝብና ለሀገር ሲል የሚሰዋ፣ በሁሉም ዘውጎች በተሟላ ዲሲፕሊን የታነፀ ስብዕናን የተላበሰ፣ ከህገ መንግስቱና የህገ መንገስቱ ባለቤቶች ከሆኑት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በስተቀር ለማንም የማይወግን ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ያለው፣ በተሰማራባቸው ማናቸውም ተልዕኮዎች በአነስተኛ ኪሳራ የላቀ ውጤትን በማስመዝገብ የህዝብንና የሀገርን ሃብት በቁጠባ አብቃቅቶ የሚጠቀም ህዝባዊና ዘመናዊ ሃይል መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። በዚህ ቁመናው በሀገራችንና ለሰላም ማስከበር በተሰማራባቸው አካባቢዎች ባሉ ህዝቦች ሁሉ ውዴታንና አመኔታን ያተረፈ ሃይል ነው። በእንዲህ ዓይነት ብቃት የታነፀ ጀግና ሰራዊት በየትኛውም ጊዜና ሁኔታ ህዝብን ተፃርሮ የቆመበት ወቅት የለም። ከላይ ከተጠቀስኳቸው የሰራዊቱ አጠቃላይ ስብዕና በመነሳት እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የሚኖር አይመስለኝም—ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመጣል ሲሉ ሰራዊቱን በማይመጥነው ስያሜው ከህብረተሰቡ ጋር ለማጋጨት የቀን ቅዥት ከሚያልሙ አንዳንድ ፅንፈኞች በስተቀር።

ሆኖም እነዚህ ሃይሎች ይህ ሰራዊት ታማኝነቱ ለህገ መንግስቱና ለህገ መንግስታዊ ሥርዓቱ ዘብ የሚቆም መሆኑን ሊያውቁ ይገባል እላለሁ። ሥርዓቱን የሚጠብቀው ይህ ዘመናዊ ሰራዊት በአሉባልታ የሚፈታ አይደለም። ህዝቡም የሰራዊቱን ማንነት ስለሚያውቅ ልክ እንደ ትናንቱ ዛሬም ይሁን ነገ ከጎኑ ነው። ዘመናዊው ሰራዊት ተልዕኮውን የሚወጣው ህዝቡን ደጀን አድርጎ በመሆኑ ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ማንም ሊደፍረው አይችልም። የሥርዓቱ ባለቤቶች የሆኑት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እስካሉ ድረስ ሥርዓቱ ሊናድ አይችልም። ታዲያ ይህን እውነታ ወዳጅም ይሁን ጠላት ቢገነዘበው እሰየው ነው ባይ ነኝ።   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy