Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ርምጃ አንድ

0 267

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ርምጃ አንድ

ብ. ነጋሽ

መብትና ነጻነቱን ያወቀና የኖረበት እንዲሁም ዴሞክራሲንና ልማትን የቀመሰ ህዝብ ከቶም ወደ ኋላ አይመለስም። እነዚህን በእጁ የገቡ እሴቶች አያስነካም። አለማስነካት ብቻ አይደለም፤ ሁሌም ተጨማሪ ይፈልጋል። ፍጹም ዴሞክራሲን፣ በማያቋርጥ የለውጥ ሂደት ላይ ያለንና በተሻለ ህይወት የሚገለጽ ልማትን ይጠይቃል። እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰን ህዝብ መጨቆን አይቻልም። እንኳን ጨቋኝ መንግስት ቀርፋፋ መንግስትም እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰን ህዝብን አይመጥንም። በማያቋርጥ ለውጥ ላይ ያለውን የህዝብን የዴሞክራሲና የልማት ጥያቄ መመለስ የሚችል ንቁና ፈጣን መንግስት ነው የሚመጥነው። መንግስቱ ከተንቀራፈፈበት ህዝቡ ውክልናውን ማንሳቱ አይቀሬ ይሆናል።

አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ መብትና ነጻነቱን የራሱ አድርጓል። በዴሞክራሲ ውስጥ አልፏል። ልማትን ቀምሷል። እነዚህን አያስነካም። ካሁን በኋላ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሚኖሩበት መሬት ላይ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር – በተወካዮቻቻው የመተዳደር፣ በቋንቋቸው የመስራት፣ ባህላቸውን የማሳደግ፣ ታሪካቸውን የመንከባከብ፣ በፌደራል መንግስት ውስጥ ውክልና የማገኘት መብትና ነጻነታቸውን አያስነኩም።

ይህ ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ተጨማሪ ልማትና ዴሞክራሲ የሚፈልገበት ደረጃ ላይ ነው። የመንገድ፣ የኤሌትሪክ፣ የቴሌኮሚዩኒኬሽን ወዘተ መሰረተ ልማት ይፈልጋል። ስራ አጥነትን ተሸክሞ መዝለቅ አይፈልግም። የተሟላ የጤናና የትምህርት አገልግሎት ይሻል። በአጠቃላይ አምጣ! የሚል ህዝብ ተፈጥሯል።

ታዲያ፣ የኢፌዴሪ መንግስት፣ የየክልሉን መንግስታት ጨምሮ ባለፉት ሃያ ዓመታት በሃገሪቱ ታሪክ ያልነበረ ዴሞክራሲን ማስፈንና ልማትን ማምጣት መቻላቸው እውነት ቢሆንም፣ የህዝቡን የፍላጎት እድገት ተከተለው እርካታ መፍጠር ላይ ግን መንቀራፈፍ ታይቶባቸዋል። አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ትምህርት ቤትና የጤና ተቋም ሳይኖረው መኖር አይፈቅድም። አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲኖረው፣ ሁለተኛ ደረጃ ይፈልጋል፤ ሁለተኛ ደረጃ ሲኖረው ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ይፈልጋል። ጤና ጣቢያ ሲኖረው ሆስፒታል ይጠይቃል። የጠጠር መንገድ ሲኖረው መንገዱ አስፋልት እንዲሆንለት ይፈልጋል። የኤሌትሪክ ሃይል ሲያገኝ፣ ከመብራት አልፎ ከፍተኛ ጉልበት ያለው ሃይል እንዲኖረው ይፈልጋል። የቴሌፎን አገልግሎት ሲያገኝ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት ይጠይቃል። የልማት ፍላጎቱ አይቋረጥም። የዚህ አይነት ህዝብ የተፈጠረው በኢፌዴሪ መንግስትና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ቢሆኑም፣ ራሳቸው በፈጠሩት የህዝብ ፍላጎት እድገት ፍጥነት ልክ  መጓዝ ግን አልቻሉም።

የህዝቡን የማያቋርጥ የልማት ፍላጎት ማሟላት የሚያስችል አመራር መስጠት ካለመቻል በተጨማሪ ኪራይ ሰብሳቢነት ገብቷቸው ከህዝብ ጋር የተፋጠጡበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። በሁለት ዓመት ይጠናቀቃል ተብለው የሚጀመሩ የመሰረተ ላምት ግንባታዎች፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልማት ፕሮጀክቶች በሁለተኛው ዓመት ላይ የተመደበላቸውን ባጀት ቅርጥፈው  ጨርሰው በጅምር የሚቀሩበት ሁኔታ የተለመደ እየሆነ ሆኗል። ተገንብተው የተጠናቀቁ ፕሮጀከቶች በተጠናቀቁ ማግስት ፈራረሰው አገልግሎት መስጠት የማይችሉበት ሁኔታን መመልከት የተለመደ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን የመልካም አስተዳደሩና የፍትህ እጦቱ፣ የመሬት ወረራው፣ የተበዳይ አቤቱታ ሰሚ መጥፋቱት ወዘተ ህዝብ መንግስት ላይ አመኔታ እንዲያጣ አድርጓል።

ልማትና ዴሞክራሲ የቀመሰን ህዝብ በዚህ ሁኔታ ማስተዳደር ስለማይቻል፣ ህዝብ መንግስት ላይ ያለውን ቅሬታ በተቃውሞ አሳውቋል። መንግስትና ገዢው ፓርቲ አስቀድመውም ይህን አዝማሚያ አውቀውት ነበር። የችግሩ ምንጭ ውስጣዊ መሆኑን፣ ይህ ውስጣዊ ችግር ስርአቱንና ሃገሪቱን ለውጫዊ ጥቃት ማጋለጡ አይቀሬ መሆኑን ተረድተው የህዝብን ብሶት አዳምጠው ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።

በዚህ መሰረት በፌደራልና በክልል መንግስታ አዲስ ካቢኔ እንዲዋቀር ተደርጓል። የፖለቲካ ምህዳሩን ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ለማስፋት ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተለያዩ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም በስራ ላይ ያሉ አዋጆችን ለማስተካከል ድርድር ተጀምሯል። ይሁን እንጂ ቀድሞ የነበሩት ስር የሰደዱ የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና የመንግስት ችግሮች ላይ በየአካባቢው የተፈጠሩ የእርስ በርስ ግጭቶችና ሌሎች ውጪያዊ ሁኔታዎች ታክለው በታሰበው ልክ በተጨባጭ የሚታይ ለውጥ ማምጣት ያልተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ገዢው ፓርቲ አሁንም ለህዝብ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ራሱን ለማስተካከል ወስኖ ግምገማ አካሂዷል።

በቅርቡ የተካሄደውና በርካታ ውሳኔዎች የተላለፉበት የኢህአዴግ ስራ እስፈጻሚ ኮሚቴ ግምገማ የዚህ ማሳያ ነው። ግምገማው እንዳበቃ የኢህአዴግ አራት እህትማማች ድርጅቶች አመራሮች በጋራ የግምገማውን ሂደት፣ የደረሱበትን መግባባትና ውሳኔዎቻቸውን የተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል። ከተላለፉ ውሳኔዎች መሃከል ሃገራዊ መግባባት መፍጠርና ሃገራዊ አንድነትን መገንባት የሚያስችሉት በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ከእነዚህ መሃከል አንዱ በወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸውና በጥፋተኝነት የተፈረደባቸውን የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ሌሎች ግለሰቦች ክስ በማቋረጥና በይቅርታ ነጻ እንዲወጡ ማደረግ ነው። ይህ እርምጃ በወንጀል የተጠረጠሩትና በጥፋተኝነት የተፈረደባቸው ፖለቲከኞች የሚመሯቸው ፓርቲዎች ደጋፊዎች በመንግስትና በገዢው ፓርቲ ላይ ያደረባቸውን ጥርጣሬ የመግፈፍ አቅም አለው። ፓርቲዎቹ ከመንግስት ጋር በሚያደርጉት ውይይትና ድርድር የተሳትፎ አቅማቸውንም የሚያዳብርበት ሁኔታም አለ።

ይህ ደግሞ በተለያዩ አመለካካት ተከታይ ዜጎችና ቡድኖች መሃከል እንዲሁም በመንግስትና በህዝብ መሃከል መተማመንና ሃገራዊ መግበባት መፍጠር ያስችላል ተብሎ ይታመናል። በዚህ መሰረት የፌደራል መንግስት፤ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፤ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች በክስ ሂደት ላይ የነበሩና ፍርደኛ እስረኞችን ነጻ አሰናብተዋል። በፌደራል መንግስት በኩል እስካሁን የተለቀቁት በፍርድ ሂደት ላይ ያሉ ሲሆኑ፣ ፍርደኞቹ ህግ በሚፈቅደው መሰረት እየተጣራ እንደሚለቀቁ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታውቋል።

ይህ እርምጃ የመጀመሪያውና መንግስት ውሳኔዎቹን ተግባራዊ ለማደረግ ያለውን ቁርጠኘነት የሚያሳይ ነው። በቀጣይ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያሳለፋቸው ሌሎች ውሳኔዎችም ተግባራዊ ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከበርካቶቹ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔዎች መሃከል በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን ከሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶችና ከህዝቡ ጋር በመሆን ለማቃለል ያግዛሉ በሚል ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው ናቸው። በዚህ ውሳኔ መሰረት ምሁራንና የሲቪክ ማህበራት ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ተገቢ ሚናቸውን የሚጫወቱበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚያስችል እርምጃ ይወሰዳል።   

በተጨማሪም፤ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሃገራዊ አንድነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን ከህዝብና ከመንግሥት ጋር በመሆን ማከናወን እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባጸደቁት ህገመንግስት መሰረት ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት መንግስታዊ መዋቅር ካደራጁ 23 ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህ የዘመናት የህዝብ ትግል ውጤት የሆነ ታሪካዊ ድል ነው። ይሁን እንጂ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሃገራዊ አንድነታቸውን ማጠናከር የሚችሉበትን ተግባር ማከናወን ላይ ክፈተት ታይቷል። በዚህ ምክንያት ልዩነቶች እየሰፉ፣ ልዩነቶች በሰፋበት ልክ ሃገራዊ አንድነት እየላላ የመጣበት አዝማሚያ ታይቷል። ሃገራዊ አንድነትን የማጠናከር እርምጃ መውሰድ የሚያስችል አቅጣጫ ማስቀመጥ ያስፈለገው ለዚህ ነው። በዚህ ረገድ ጅምር ስራዎች ቢኖሩም በቀጣይነት አጥጋቢና ሁሉን አቀፍ በሆነ መልክ ይተገበራል ተብሎ ይጠበቃል።

በጽሁፉ መግቢያ ላይ እንደተመለከተው፣ የፌደራልም ሆነ ይክልል መንግስታት የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት የህዝቡን የልማት፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ፍላጎትና ጥያቄ ማርካት አልቻሉም። ይህ የሆነው መንግስታቱ ከህዝቡ ፍላጎት ጋር ጋር በፍጥነት እየተራመዱ የማያቋርጠውን ፍላጎቱን የማሟላት አቅም በማጣታቸው፣ የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ በማጣት ስልጣንን ለግል ኑሮ ማደላደያ በማድረጋቸውና በኪራይ ሰብሳቢነት ምክንያት ነው። የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በፌደራልም በክልልም ያለው ሲቪል ሰርቪስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የአገልጋይነት መንፈስ የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲረባረብ ማድረግ የሚያስችል ሁኔታን ለመፍጠር ቃል ገብቷል። ይህ እስካሁን ያለውን የህዝብ ቅሬታ በሙሉ በማቃለል ተስፋ የሚፈጥር፣ በመንግስትና በህዝብ መሃከል መተማመን  መገንባት የሚያስችል ርምጃ ነው።

በአጠቃላይ፤ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ካሳለፋቸው በርካታ ውሳኔዎች መሃከል የፖለቲካ አመራሮችን የመፈታቱ ተግባራዊ እየተደረገ ነው። ይህ ሌሎቹም ውሳኔዎች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ያመለክታል። ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎቹም የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ተግባራዊ ይሆናሉ ተብሎ የጠበቃል። ውሳኔዎቹን ተግባራዊ ማደረግ የምርጫ ጉዳይ አይደለም። ተግባራዊ አለማድረግ የህዝብን ቁጣና ተቃውሞ በማባባስ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ሂደትን በማደናቀፍ የሃገሪቱን ህልውናም አደጋ ላይ እስከመጣል ሊደርስ ይችላል። እናም እስረኞችን በመፍታት የተጀመረው ርምጃ በፍጥነትና ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጣ በሚችልበት ሁኔታ መቀጠል አለበት። እስረኞቹን የመፈታቱን ተግባር፣ ርምጃ አንድ እንበለው። ርምጃ ሁለት፣ ሶስት . . . ይቀሩናል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy