Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰላምና መረጋጋት

0 675

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰላምና መረጋጋት

                                                               ይልቃል ፍርዱ

በሀገራችን በተለያዩ አካበቢዎች የተፈጠረውን የሰላምና መረጋጋት እጦት ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ በገሀድ እየታዩ ያሉትን ሕግና ስርአትን ያልተከተሉ ስርአተ አልበኛ  ሁኔታዎችን ለመክላት፤ የሕብረተሰቡን ሰላማዊ ሕይወት የመንግስትና የሕዝብ ንብረትን ከውድመት ለመታደግ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አስፈላጊ ሁኖ በመገኘቱ ታውጆአል፡፡

አሁን ባለንት ደረጃ መንግስት የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ በትጋት እየሰራ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል፡፡ ለውጥ ራሱን ችሎ ሂደትና ግዜን ይጠይቃል፡፡ መንግስት የሕዝብን ጥያቄዎች በተመለከተ እየሰጠ ያለው ምላሽ በእጅጉ የሚበረታታ ነው፡፡ይህንን ልንደግፈው ልናበረታታው ይገባል፡፡ ሚዛናዊ ሁኖ ማየትንም ይጠይቃል፡፡ ሁሉንም ነገር ብቻ መቃወም ምንም በጎ ነገር የለም ብሎ ማሰብ  በጭፍን ጥላቻ በስሜታዊነት መነዳት ለሀገርና ለሕዝብ አይበጅም፡፡

እስረኞች እንዲፈቱ የተደረገው ኢሕአዴግ ሰፊ ሀገራዊ ሰላምና መግባባት እንዲፈጠር በወሰነው ውሳኔ መሰረት የተደረገ ነው፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት የመድከም ወይም የሽንፈት ምልክት አይደለም፡፡ እንዲውም በተቃራኒው የአሸናፊነት ምልክት ነው፡፡ ሕዝብን የመስማት ሕዝብን የማዳመጥ ለሕዝብ ጥያቄዎች መልስ የመስጠት በፈተናዎችም መሀል በድል አድራጊነት የመወጣት ምልክት ነው፡፡

ወደወቅቱ ሁኔታ ስንመለስ የሕዝቡን ጥያቄ የበለጠ መመለስ የሚቻለው የተረጋጋ ሰላምና መረጋጋት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ተቃውሞን ሀገር በማንደድ የተገኘውን ሁሉ በማቃጠል መንገድ በመዝጋት ኢኮኖሚውን በማሽመድመድ የዜጎች ሕይወት ያለምንም ምክንያት እንዲያልፍ ሰላም እየጠፋ ዜጎች ወጥተው መግባት እየተሳናቸው በዚህ መልኩ ይቀጥል ማለት ሀገሪቱ የስርአተ አልበኞች መናሀሪያ እንድትሆን ብሎም ሕልውናዋ እንዲጠፋ መፍቀድ ነው፡፡ ይህ ደግሞ መቸም ተቀባይነት የሌለው ድርጊትና ተግባር ነው፡፡

በመጀመሪያ የተረጋጋ ሀገራዊ ሰላምና ደሕንነት መከበር መኖር አለበት፡፡ ማንኛውም ጥያቄ ሊስተናገድ የሚችለው በሀገር ሰላም መኖር ብቻ ነው፡፡ ለመቃወምም ሆነ ለመደገፍ የሀገር ሰላም ተጠብቆ ተከብሮ መዝለቅ አለበት፡፡ ንግዱና ሀገራዊ ኢኮኖሚው እንዲሞት እየተደረገ በዚህ መልኩ ትርምስና ሁከቱ እንዲቀጥል የሚፈቅድ ዜጋ የለም፡፡

በማያገባቸው የሀገራችን የውስጥ ጉዳይ እየገቡ ለመፈትፈት የሚከጅሉ ትላንት በሌላው አለም ከፈጸሙት ሀገራትን የማፈራራስና የማጥፋት ወንጀለኛ ድርጊታቸው ያልተማሩ የውጭ ኃይሎች ዛሬም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብተው ለማቡካት ደፋ ቀና እያሉ ነው፡፡ ትርምሱ እንዲቀጥል በማበረታታት ላይ ይገኛሉ፡፡

ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን በራሳቸው ለመምራት ለማስተዳደር ችግሮቻቸውን ተነጋግረው መፍታትና ሀገራቸውን ጠብቀው ማስቀጠል የሚችሉ በመሆናቸው አዛኝ ቅቤ አንጓቾች ከዚህ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ሕልማቸው ሊታቀቡ ይገባል፡፡ ምናልባትም ተረኛዋ ፈራሽ ሀገር ኢትዮጵያ ናት ብለው አስልተው ከሆነም ተሳስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ አትፈርስም፡፡ አትበተንም፡፡

እንነጋገር ካልን በአለም ድሀ ሀገራት በዲሞክራሲና በሰብአዊ መብት ስም የፈጸሙት ዘግናኝ ግፍና በደል በመላው አለም ሕዝብ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱን ችግር በራሱ የመፍታት አቅም አለው፡፡ ነጻ ሀገራዊ ታሪክ ያለን የተከበርን ሕዝቦች ነን፡፡ የማንም ተገዢ አይደለንም፡፡ በመጀመሪያ በራሳቸው ሀገር ስላለው ዲሞክራሲ ይጨነቁ፡፡

በተለመደው የቀለም አብዮት ሴራቸው ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ወይንም የራሳቸው ቡችላ የሆነ የሀገሪቱን ሀብት እንዳሻቸው ለመመዝበር የሚያስችላቸው አሽከር ለመፍጠር የሚያደርጉትን መክለፍልፍ ሊያቆሙ ይገባል፡፡ በሰው ሀገር የውስጥ ጉዳይ እየገቡ የሚፈተፍቱት ስራ ነው አለምን የማትወጣበት አዘቅት ውስጥ የከተታት፡፡ ዛሬም ትላንት ሀገራትን ካፈራረሱበት ወንጀለኛ ድርጊታቸው መማር አልቻሉም፡፡

በሀገሪቱ ላይ እየዘመቱ ያሉት ለእኛ ተጨንቀው አይደለም፡፡የውስጥ ችግር የሚፈታው በሀገሬው ሰው በዜጋው ነው፡፡ መሬት ይሸጥ ይለወጥ የሀገሪቱ ተቋማት ለአለም አቀፍ ከበርቴዎች ይሸጡ የሚለውን እምነታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የተመቸ ግዜ አገኘን ብለው ካልሆነ በስተቀር እንጂ ለኢትዮጵያና ለሕዝብዋ አስበው አይደለም፡፡ በዚህም ሀገሪቱን ለማራቆት ዜጎችዋንም የለየለት ባርነት ውስጥ ለመክተት እንቅልፍ አጥተው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሁከቱና ትርምሱ እንዲቀጥል ሀገሪቱ እንድትተረማመስ ብርቱ ምኞታቸው ነው፡፡ ግልጽ ጣልቃ ገብነታቸውን ሊቆሙት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያንም ስለሀገራቸው ሰላምና ክብር ሲሉ ጸንተው አንድነታቸውን ሊጠብቁ ይገባል፡፡

ትላንትም በኢትዮጵያ ላይ የፈጸሙትን ግፍና በደል የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንቅቆ ስለሚያውቀው ሕዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም የሀገሩን ሰላምና ጸጥታ ያስከብራል፡፡ እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱም ይጠይቃል፡፡የቀለም አብዮታቸው መቸም እንደማይሳካ ሊያውቁት ይገባል፡፡ ሊቢያን ሶርያን የመንን ኢራቅን ያወደሙ የእልቂት ተዋናዮች ይህን ቁማር በኢትዮጵያ ላይ እንዲጫወቱ የሚፈቅድ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ አሁን ባለው ሀገራዊ ሁኔታ ተገቢና ትክክል እርምጃ ነው፡፡ሀገርን ሕዝብን የመጠበቅ ከአደጋ የመታደግ የነበረው ሰላም የመመለስ መረጋጋትን የመፍጠር እርምጃ ነው፡፡ኢሕአዴግ አሁን በጀመረው ሰፊና ስርነቀል የሕዝብን ጥያቄዎች የመመለስ እርምጃ በእርግጠኝነት ሕዝብን የሚያረኩ ምላሾችን ያስገኛል፡፡ለኢትዮጵያ ሰላምና መፍትሔ የሚመጣው በኢትዮጵያውያን እንጂ በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት አይደለም፡፡

ለውጥ መምጣት ካለበት በሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ ምርጫ ብቻ ነው መሆን ያለበት፡፡በሁከት በትርምስ ሀገር በማፍረስና ሀገርን በማንደድ አይደለም፡፡ውሀ ሲወስድ አሳስቆ እንዲሉ ሌሎችም ሀገራት የጠፉት በዚህ አይነቱ ጀምሬ መነሻነት ነው፡፡ኢትዮጵያ ሰላሟና ሕልውናዋ አደጋ ላይ እንዲወድቅ የሚፈቅድ ዜጋ የለም፡፡የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ስራ የተጋረጡትን አደጋዎች የመቅረፍ የሕዝብን ስጋትና መረበሽ በማረጋጋት ሰላም የማስከበር ስራ ነው፡፡

ኢሕአዴግ ሰፊ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የገባውን ቃል በተግባር እያዋለው ይገኛል፡፡  ስርነቀል የሆኑ ለውጦችን ለማምጣት ተጨባጭ ምላሾችን እየሰጠ ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች በፍርድቤት ተፈርዶባቸው እንዲሁም ጉዳያቸው በፍርድቤት እየታየ የነበሩ በርካታ ግለሰቦች ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲፈቱ ተድርጎአል፡፡ይህ የተጀመረውን ብሔራዊ መግባባት ከዳር ለማድረስ በመንግስት በኩል የተወሰደው እርምጃ ትልቅ መሆኑን ያሳያል፡፡ የሕዝብን ጥያቄ በተጨባጭ የመለሰም ወሳኝ ተግባር ነው፡፡በዚህ ረገድ መንግስት ሊመሰገን ይገባዋል፡፡

መቼም የሚዛናዊነቱና የማመስገኑ ባሕል ባይኖረንም መልካሙን መልካም ብለን በጎደለው ደግሞ ለመሙላት መስራትና ማስተካከል የመንግስት ብቻ  ሳይሆን  የሁሉም  የጋራ ግዴታ ነው፡፡ጥላቻና የማያባራ ተቃውሞ ለብቻው መፍትሄ አያመጣም፡፡ተሳስቦ ተደማምጦ መስራቱ ነው ለሀገር የሚበጀው፡፡

በሕገመንግስቱ መሰረት አስቸኳይ ግዜ አዋጅ የሚደነግገው አንቀጽ 93 በንኡስ አንቀጽ 1 ሀ) ላይ የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገመንግስታዊ ስርአቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ስርአት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፤ ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ጤንንት አደጋ ላይ ሊጥል የሚጥል በሽታ ሲከሰት የፌደራሉ መንግስት የሚኒስትሮች ምክርቤት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የመደንገግ ስልጣን አለው ይላል፡፡

ሕገመንግስቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስቸኳይ ግዜ አዋጁ እንዲታወጅ ካደረገ በኃላ በተወካዮች ምክርቤት ቀርቦ እንዲጸድቅ ይደረጋል ይላል፡፡ በአንቀጽ 93 ንኡስ ቁጥር 2 ሀ መሰረት ምክርቤቱ በስራ ላይ ከሆነ በ48 ሰአታት መቅረብ አለበት፡፡ አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ሁለት ሶስተኛ ድምጽ ተቀባይነት ካላገኘ ወዲያውኑ ይሻራል፡፡ በአንቀጽ 93 ንኡስ አንቀጽ ለ መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በስራ ላይ ባልሆነበት ወቅት የሚታወጅ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት መቅረብ ያለበት አዋጁ በታወጀ በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ መሆኑ በግልጽ ተደንግጓል፡፡

በአንቀጽ 93 ንኡስ አንቀጽ 3 መሰረት በሚኒስትሮች ምክርቤት የተደነገገው የአስቸኳይ  ግዜ አዋጅ በምክርቤቱ ተቀባይነት ካገኘ በኃላ ሊቆይ የሚችለው እስከ ስድስት ወራት ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በሁለት ሶስተኛ ድምጽ አንድን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በየአራት ወሩ በተደጋጋሚ እንዲታደስ ሊያደርግ እንደሚችል በሕገ መንግስቱ ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

በአንቀጽ 93 ንኡስ አንቀጽ 6 ለ) መሰረት በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ወቅት የሚወሰዱት እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ ኢሰብአዊ አለመሆናቸውን መቆጣጠርና መከታተል እንዲሁም በንኡስ አንቀጽ 6 መ) መሰረት በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ እርምጃዎች ኢሰብአዊ ድርጊት የሚፈጽሙትን ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ የሚለው በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ስለዚህም ስጋት የሚፈጥር ምንም ሁኔታ የለውም፡፡

አሁን በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚታየው የሰላም መደፍረስ በዜጎች ላይ የሚደርስ የሕይወትና የንብረት ጉዳት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸው ሕዝብና መንግስትን ያሳሰበ በመሆኑ መንግስት የዜጎቹን ሕይወትና ንብረት ደሕንነታቸውን የመጠበቅ ግዴታውን የመወጣት ኃላፊነት ስላለበት ሁኔታውን በማረጋጋት ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለስ የሚቻለው በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ መሰረት ብቻ ነው፡፡

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ኮማንድፖስት የሚወስዳቸወ እርምጃዎች በግልጽ ተዘርዘረዋል፡፡ ወደ 18 የሚጠጉ ንኡስ አንቀጾች አላቸው፡፡ የአስቸኳይ ግዜ ኮማንድፖስቱ ሕገመንግስቱንና ሕገመንግስታዊ ስርአቱን ለማስከበር እና ከአደጋ ለመጠበቅ የሕዝብና የዜጎችን ሰላምና ጸጥታን ለማስጠበቅ አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን ማንኛውም ሁከት ብጥብጥ እና በሕዝቦች መካከል መጠራጠር እና መቃቃር የሚፈጥር ይፋዊ  ሆነ የድብቅ ቅስቀሳ ማድረግን፤ ጽሁፍ ማዘጋጀትን፤ማተም እና ማሰራጨትን፤ ትእይንት ማሳየትን፤ በምልክት መግለጽን ወይም መልእክትን በማንኛውም ሌላ መንገድ ለሕዝብ ይፋ ማድረግን ይከለክላል፡፡ ማንኛውም የመገናኛ ዘዴ እንዲዘጋ ወይም ደግሞ እንዲቋረጥ ሊደረግ እንደሚችል ተገልጾአል፡፡

የሕዝብ እና የዜጎች ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ ሲባል የአደባባይ ሰልፍና ማድረግን ፤መደራጀት፤በቡድን ሆኖ መንቀሳቀስን ይከለክላል፡፡ ዝርዝሩ በመመሪያው እንደሚወጣ ተገልጾአል፡፡ ሕገመንግስታዊ ስርአቱ ላይ የሚቃጡ ወንጀሎችን የጠነሰሰ፤የመራ፤ የተባበረ፤ የጣሰ ወይም ደግሞ በማንኛውም መንገድ በወንጀል ድርጊቱ የተሳተፈ ወይም ተሳትፎአል ተብሎ የሚጠረጠር ማንኛውም ሰው ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ስር ያደርጋል፡፡ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ በመደበኛው የሕግ መንገድ ተጠያቂ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑ በኮማንድ ፖስቱ ተገልጾአል፡፡

ወንጀል የተፈጸመባቸው ወይ ሊፈጸምባቸው የሚችሉ እቃዎችን ለመያዝ  ሲባል ማንኛወም ቤት፤ቦታ፤መጓጓዣ፤ ለመበርበርና እና እንዲሁም ማናቸውም ሰው ለማስቆም ማንነቱን ለመጠየቅ፤መፈተሸ ይቻላል፡፡ በብርበራ ወይም በፍተሻ የተያዙ እቃዎችን በማስረጃነት ለፍርድቤት መቅረባቸው እንደተጠበቀ ሁኖ ተጣርቶ ለባለመብቱ የሚመለስ መሆኑን የኮማንድ ፖስቱ መግለጫ ያስረዳል፡፡

ኮማንድ ፖስቱ የሰአት እላፊ ተፈጻሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ይወስናል፡፡ ለተወሰነ ግዜ አንድን መንገድ፤አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዲሁም ሰዎች ለግዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ፤ ወደተወሰነ ቦታ እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ይደረጋል የሚሉና ሌሎችንም ሰፊ ጉዳዮችን ያካተተ ነው፡፡ የሀገርን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር መረጋጋትን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ሁሉም ዜጋ ለጋራ ሀገሩ ሰላምና ሕልውና ሲል ተባብሮ መስራት ይጠበቅበታል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy